ዶክተር ልዑል አስፋወሰን አስራተ ካሳ፣ ዶክተር ጸጋዬ ደግነህ፣ አቶ ሺባባው በላይ እና አቶ ዮሃንስ ባይህ ተሸለሙ።

0
0 0
Read Time:4 Minute, 14 Second

በጀርመን የኢትዮጵያውያን ውይይት እና ትብብር መድረክ አራት ግለሰቦች ሸለመ

23.10.2022

በጀርመን የኢትዮጵያውያን ውይይት እና ትብብር መድረክ “ለሃገር በጎ እና የላቀ አስተዋጽዖ ላበረከቱ” አራት ግለሰቦች ትላንት ቅዳሜ የምስጋና እና የእውቅና ሽልማት አበርክቷል። ተሸላሚዎቹ ዶክተር ልዑል አስፋወሰን አስራተ ካሳ፣ ዶክተር ጸጋዬ ደግነህ፣ አቶ ሺባባው በላይ እና አቶ ዮሃንስ ባይህ ናቸው። 

በኢትዮጵያ ሰላም ልማት እና እድገትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ በጀርመን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በማስተባበር ላለፉት በርካታ ዓመታት መጠነ ሰፊ የእርዳታ እና ድጋፍ ተግባራትን ሲያከናውን የቆየው በጀርመን የኢትዮጵያውያን ውይይት እና ትብብር መድረክ ትላንት ቅዳሜ ደግሞ በዚሁ በጀርመን ነዋሪ ለሆኑ 4 ታላቅ የሃገር ባለ ውለታዎች የእውቅናና የምስጋና ሽልማት መርሃግብር አዘጋጅቶ ነበር።

ፍራንክፈርት ከተማ በሚገኘው የወጣቶች ማዕከል ሃውስ ዴር ዩጉንድ ከቀትር በኋላ በተከናወነው በዚሁ ሁለተኛ የሽልማት አሰጣጥ መርሃግብር ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ እና ወቅታዊ ሁኔታ እውነታውን በተለያዩ መድረኮች ባቋቋሟቸውና የቦርድ አመራር በሆኑባቸው ግብረ ሰናይ ድርጅቶች፣ በመጽሃፎቻቸው እና በመገናኛ ብዙሃን ለዓለም በማሳወቅ የበኩላቸውን ድርሻ በማበርከት ላይ የሚገኙት በጀርመን መንግሥት የአፍሪቃና የመካከለኛው ምስራቅ የፖለቲካ ተንታኝ እና አማካሪ ዶክተር ልዑል አስፋወሰን አስራተ ካሳ፣ ታዋቂው የምጣኔ ሃብት ተንታኝ ዶክተር ጸጋዬ ደግነህ የቀድሞው የኢትዮጵያ ዲፕሎማት አቶ ሺባባው በላይ እንዲሁም በኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲና በሌሎችም የዲያስፖራው የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች በአገሪቱ ለውጥ እንዲመጣ ከፍተኛ ትግል ማድረጋቸው የሚነገርላቸው አቶ ዮሃንስ ባይህ በመድረኩ የተዘጋጀላቸው የምስጋናና የዕውቅና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። የትብብር መድረኩ አመራር አባል አቶ የወንደሰን አናጋው “ይህ ዓይነቱ የእውቅና አሰጣጥ ዝግጅት እያንዳንዱ ዜጋ በተለይም ወጣቱ ትውልድ ለሃገሩ ጠንክሮ እንዲሰራ በእጅጉ ያነቃቃል” ሲሉ ገልጸውልናል።

Deutschland Frankfurt | Ethiopian Forum for Dialogue & Cooperation
በጀርመን የኢትዮጵያውያን ውይይት እና ትብብር መድረክ “ለሃገር በጎና የላቀ አስተዋጽዖ ላበረከቱ” አራት ግለሰቦች የምስጋናና እና የእውቅና ሽልማት አበርክቷል። የመድረኩ አመራሮች ተሸላሚዎቹ ዶክተር ልዑል አስፋው ወሰን አስራተ ካሳ፣ ዶክተር ጸጋዬ ደግነህ፣ አቶ ሽባባው በላይ እና አቶ ዮሐንስ ባየህ ናቸው። 

የንጉሰ ነገስት ቀዳማዊ ኃይለስላሴ የቅርብ አማካሪና ወዳጅ የነበሩ አያታቸው ልዑል ራስ ካሳ የኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ሕገ መንግስት ያረቀቁ መሆናቸው ይነገራል:: የቀድሞ የንጉሳዊውው ዘውድ አስተዳደር ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ልዑል ራስ አስራተ ካሳ ልጅ የሆኑት ዶክተር ሉዑል አስፋወሰን ወታደራዊው የደርግ አስተዳደር ቤቤተሰቦቻቸው ላይ ግድያና እስር መፈጸሙን ተከትሎ ወደ ጀርመን በስደት ካቀኑ በኋላ የፒ.ኤች.ዲ. ዲግሪያቸውን በኢትዮጵያ ታሪክ የትምህርት ዘርፍ ከፍራንክፈርቱ የዮሃን ቮልክጋንግ ጎተ ዩኒቨርሲቲ በማዕረግ ተቀብለዋል:: በጀርመኑ ቱቢንገን ዩኒቨርሲቲና በኬምብሪጁ ማግደሊን ኮሌጅም የሕግ የኢኮኖሚክስና የታሪክ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል:: ብዛት ያላቸው ትንተናዎቻቸው እና ጽሁፎቻቸው በጀርመን ዕለታዊ ጋዜጦች በታዋቂ መጽሔቶች የቴሌቪዥን እና እንደ ዶይቼ ቨለ ባሉ የራዲዮ ጣቢያዎች ጭምር ቀርበዋል:: እንደ ጎርጎሮዋዊው አቆጣጠር በ 1994 ዓ.ም ባቋቋሙት “ኦርቢስ ኤቲዮፒከስ” በሚል ስያሜ በመሰረቱት በኢትዮጵያ ባህል ታሪክና ጥንታዊ ቅርሶች ጥበቃ ላይ ያተኮረ ግብረሰናይ ድርጅታቸውና በአፍሪቃ አህጉር በተደጋጋሚ የሚከሰቱ የኃይማኖት ግጭቶችን ለመፍታት እንዲረዳ ባቋቋሙት “ፓክተም አፍሪካነም” በተሰኘው ድርጅታቸው እንዲሁም በሌሎችም መድረኮች የኢትዮጵያና የአፍሪቃውያን ችግሮች እንዲፈቱና የታፈኑ ድምጾች እንዲሰሙ ለዓለም አስተጋብተዋል:: በዚህም የሕይወት ዘመን የላቀ አስተዋጽዖ የፌደራል ጀርመን መንግሥት በተለያዩ ዘርፎች ወይም በጎ አድራጎት የላቀ አስተዋጽዖ ላበረከቱ ግለሰቦች የሚሰጠውን የክብር እውቅና ከኢኮኖሚና ልማት ትብብር ሚኒስቴር የዋልተር ሺል ሽልማት በተጨማሪም ከሎች ዓለማቀፍና  የጀርመን ተቋማት አያሌ የምስጋና ሽልማቶች ተበርክተውላቸዋል:: በዛሬው ዕለት ደግሞ የትብብር መድረኩ የዕውቅናና የምስጋና ሽልማት በመላው ኢትዮጵያውያን ስም ሰጥቷቸዋል:: ሽልማቱ ለእኛ እውቅና የሰጠ ብቻ ሳይሆን ብቻ በጎ ተግባር የሚከውኑ ኢትዮጵያውያንን በሞላ በተለይም ተግተው ለሃገራቸ እንዲሰሩ የሚያነቃቃ ነው ብለዋል” ዶክተር ልዑል አስፋ ወሰን::

የፌደራል ጀርመን መንግሥት በፖለቲካ በምጣኔ ሃብትና በባህል እንዲሁም በተለያዩ የእውቀት ዘርፎችና በበጎ አድራጎት መስክ የላቀ አስተዋጽዖ ላበረከቱ ግለሰቦች የሚሰጠውን “ፈርዲንስትክሮይትስ አም ባንደ” የተሰኘው የክብር ኒሻን ተሸላሚው ትውልደ ኢትዮጵያዊው የምጣኔ ኃብትና አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር ጸጋዬ ደግነህም ሌላው የትብብር መድረኩ የዕውቅናና ምስጋና ሽልማት ያበረከተላቸው ታዋቂ ባለሙያ ናቸው:: ዶክተር ጸጋዬ በጀርመኑ ፕሬዝዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር የተፈረመ የእውቅና የምስክር ወረቀትም ተቀብለዋል:: በአሁኑ ጊዜ በጀርመኑ ግዙፉ የመኪና አምራች ኩባንያ ሜርሰዲስ ቤንዝ ውስጥ በሰው ኃይል ዘርፍ በብዝሃነት ክፍል በኃላፊነት የሚሰሩት ባለሙያው በዶይቼ ቨለና በሌሎችም አያሌ መገናኛ ብዙሃን የኮረና ወረርሽኝ ከተከሰተ ጀምሮ ማህበረሰብን የሚያነቁ አስተማሪ መልዕክቶችን እና በዓለም የምጣኔ ኃብት ጉዳዮች ዙሪያ ሙያዊ ትንታኔዎችን ሲያቀርቡም ቆይተዋል:: ዛሬ የተበረከተላቸው ሽማት ሌሎች ኢትዮጵያውያንንም የሚያነቃ መሆኑን አውስተው እውቅናው የበለጠ ለስራ እንደሚያተጋቸው በመግለጽ አዘጋጆቹን አመስግነዋል::

Deutschland Frankfurt | Ethiopian Forum for Dialogue & Cooperation
ሽልማቱየተሰጣቸው ግለሰቦች ለአገራቸው ላቅ ያለ አስተዋጽዖ በማበርከታቸው የተመረጡ መሆናቸውን የመድረኩ አመራሮች ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። 

የባህዳር ፖሊቴክኒክ ኢኒስቲቲዩት ዲን የነበሩትና በቀድሞ ወታደራዊ አስተዳደር በምስራቅ አውሮጳ ሃገራት ዲፕሎማት በመሆን ያገለገሉት አቶ ሺባባው በላይም ሌላው ተሸላሚ ነበሩ:: ከከፍተኛ የትምህርት ኮሚሽን የረዳት ፕሮፌሰር ማዕረግ የተሰጣቸውና በተለያየ የሙያ ዘርፎች ለበርካታ ዓመታት ሃገራቸውን እና ሕዝባቸውን ያገለገሉት አቶ ሺባባው በቀድሞ የጎጃም ክፍለ ሃገር የቀይ መስቀል ማህበር ፕሬዝዳንትም ነበሩ:: ወታደራዊው አገዛዝ ከስልጣን ከተወገደ በኋላም በተቃውሞ ፖለቲካው እንቅስቃሴ የኢትዮጵያ መድኅን ፓርቲ ተቀዳሚ ም/ሊቀመንበር በመሆን አማራጭ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፕሮግራምን ለማስተዋወቅ ጥረት አድርገዋል::

የቀድሞ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ህብረት ፓርቲ አባል እና በዲያስፖራ የፖለቲካ የለውጥ ትግል የላቀ አስተዋጽዖ ማበርከታቸው የሚወሳው አቶ ዮሐንስ ባይህም በዛሬው የትብብሩ መርሃግብር ሌላው ሽልማት የተበረከተላቸው አንጋፋ ፖለቲከኛ ናቸው:: አቶ ዮሃንስ ኢትዮጵያ በነበሩበት ወቅት አዲስ አበባ በሚገኘው የውሃ ኃብት ልማት ባለስልጣን ከአስር ዓመት በላይ የአንድ መምሪያ በመሆን ያገለገሉ ሲሆን አብዮቱ ሲፈነዳና አዲስ የፖለቲካ ኃይል አሰላለፍ ሲፈጠርም በወቅቱ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ሕብረት /ኢዲዩ/ በሚባለው የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ የማስታወቂያ ክፍል ሃላፊ ሆነው በጉባኤ ተመርጠው ሰርተዋል:: እንደ ጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር በ 1982 ዓ.ም በስደት ወደ ጀርመን ከመጡ በኋላም በፕሮፌሰር አስራት ተመስርቶ ሰላማዊ የትግል እንቅስቃሴ በጀመረው መኢአድ እና በቅንጅት የፖለቲካ ድርጅቶችም ንቁ ተሳትፎ ማድረጋቸውን ግለ ታሪካቸው ያስረዳል::

በጀርመን የኢትዮጵያውያን ውይይት እና ትብብር መድረክ ባዘጋጀው የሽልማት አሰጣጥ መርሃ ግብር ላይ ማህበራዊ ሚድያ የህብረተሰቡን አስተሳሰብ በመቅረጽ ረገድ ስለሚኖረው ሚና ስለሚያስገኘው ፋይዳና ተግዳሮቶቹ በዶክተር ጸጋዬ “ዲጂታላይዜሽን እና የውቅረ ሃሳብ ለውጥ” በሚል ርዕስ የተዘጋጀ የዳሰሳ ጥናት ውይይት የተደረገበት ሲሆን ግጥሞች ወቅታዊ መልዕክቶች አዝናኝ ሙዚቃዎችና ሌሎችም ዝግጅቶች ቀርበዋል::

እንዳልካቸው ፈቃደ

ታምራት ዲንሳ

Source: DW

ፌስቡክ https: https://www.facebook.com/TheEthiopianTribune
ቴሌግራም https://t.me/TheEthiopianTribune
ዩቲዩብ https://youtube.com/c/TheEthiopianTribune
ቲዊተር https://twitter.com/EthTribune

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *