ዜና ዕረፍት
የዣንጥራር ገብረእግዚአብሔር ልጅ እና የእቴጌ መነን አስፋው የልጅ ልጅ፣ እንዲሁም የልዑል ራስ አሥራተ ካሳ ኃይሉ ባለቤት የነበሩት፣ ልዕልት ዙሪያሽወርቅ ገብረእግዚአብሔር፣ በዛሬው ዕለት መስከረም ፰ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም አርፈዋል።
ባለቤታቸው ልዑል ራስ አሥራተ ካሳ በዘውድ ሥርዓት ዘመን ኢትዮጵያን በታማኝነትና በሥርዓት በሥልጣናቸው ያገለገሉ፣ ሀገር ያስተዳደሩ፣ በፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ የኢትዮጵያን ሠራዊት ከመሩ ታላላቅ ልዑላን ባላባቶች መካከል የሆኑት የልዑል ራስ ካሳ ኃይሉ ልጅና ኤርትራን በእንደራሴነት ተልከው ያስተዳደሩ፣ በዘመኑ የዘውድ ምክር ቤት ሊቀ መንበር የነበሩ፣ እንዲሁም በደርግ ከተረሸኑት ስልሳዎቹ አንዱ የነበሩ ናቸው።
እርሳቸው ከሞቱባቸው በኋላ፣ ልዕልት ዙሪያሽወርቅ በደርግ አገዛዝ ለአስራ አራት አመት በእስር ቆይተው ከቀሩት ንጉሣዊ ቤተሰብ ጋር ተፈትተው በኋላም ሀገራቸውን ለቀውና ወደ ምዕራቡ ዓለም ተሰድደው ኖሩ። ከንጉሣዊ ቤተሰብ በመልካቸው፣ በሞገሳቸውና በመልካም ስብዕናቸው እጅግ የተወደዱና ደግ፣ ለሀገራቸው ታላቅ ፍቅር የነበራቸው ልዕልት ነበሩ።
ልዕልት ዙሪያሽወርቅ በአውሮፓ ንጉሣዊ ቤተሰቦች እጅግ የሚወደዱና የሚከበሩ፣ በታላቅ ስብዕናቸውና በሞገሳቸው ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን ተከብረው ያስከበሩ ሰው ነበሩ። እግዚአብሔር አምላክ የልዕልት ዙሪያሽወርቅ ገብረእግዚአብሔርን ነፍስ ከደጋገቹ አባቶቻችንና እናቶቻችን ዘንድ በዓፀደ ገነት በምሕረት ያኑርልን። አሜን።
ፎቶግራፍ: ልዕልት ዙሪያሽወርቅ ገብረእግዚአብሔርና ልዑል ራስ አሥራተ ካሳ