የኢዜማ ጥናት. . . አህያውን ፈርቶ ዳውላውን. .
ኢዜማ በአምስት ክፍለ ከተሞች የሚገኙ የተወስኑ ቦታዎች ላይ ብቻ ባካሄደው ጥናት ያገኘውን ውጤት ዛሬ ባሰራጭው ሪፖርት 213,900 ካሬ ሜትር ቦታ የመሬት ወረራና ከ95, 000 በላይ የኮንደምኒየም ቤቶች ለተረኞች መታደላቸውን አረጋግጧል።
ከዚህ በተጨማሪ ኦሮሚያ የሚባለው ክልል “የመንግሥት ሠራተኞች” ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ እና በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ ከተሞች ከተሰጣቸው ቦታ እና ኮንዶሚኒየም በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት ድጋሚ በአዲስ አበባ የጋራ መኖሪያ ቤቶች እየታደላቸው መሆኑን ኢዜማ በጥናቱ ገጽ 11 ላይ ነግሮናል።
ይህንንም በዝርዝር ባቀረበው ማስረጃ ሲያስረግጥ ኦሮሚያ ከሚባለው ክልላዊ መንግሥት ቢሮዎች አዲስ አበባ ሳር ቤት አካባቢ ከሚገኘው ጽሕፈት ቤት ሁሉም የተመዘገቡ የክልሉ ሠራተኞች በሰኔ 12 ቀን 2012 ዓ.ም በሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶች የድልደላ እጣ እንደወጣላቸው፤ የድልድል እጣ ለደረሳቸው ሰዎች ሰኔ 16 ቀን 2012 ዓ.ም ድልደል እንደተደረገላቸው፤ በዚህ ቀን ሁሉም ሠራተኞች የኮንዶሚኒየም ብሎክ ቁጥር እና የቤቱን ቁጥር በስማቸው ተረጋግጦ እንደተሰጣቸውና ኦሮምያ በሚባለው ክልል ጽሕፈት ቤት በኩል ኮሚቴ ተቋቁሞ ኮንዶሚኒየም ቤቶች በሚገኙባቸው ክፍለ ከተሞች በሚገኙ ወረዳዎች መታወቂያ የተሠራላቸው መሆኑን ለማወቅ መቻሉን ኢዜማ በጥናቱ አቅርቧል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በጥናቱ ገጽ 7 ላይ እንዳቀረበው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሕንጻዎች ውስጥ የተሠሩ የንግድ ቤቶች የልማት ተነሺ አርሶ አደሮች፣ ልጅ እና የልጅ ልጅ ተብለው በገፍ መታደላቸውንና በእግር ኳስ ደጋፊነት ስም ለተሰባሰቡ ማኅበራት መከፋፈላቸውን ተጨባጭ ባላቸው ማስረጃዎች ማረጋገጡን ነግሮናል። በሁለት ዓመት ውስጥ የተካሄደው ይህ መጠነ ሰፊ የሆነ የመሬት ወረራና “ሕገ ወጥ” የመኖሪያ ቤት ዕደላ በግልጽ የተደረገና በኢትዮጵያም በአዲስ አበባም ታይቶ በማይታወቅ መጠን እና ስፋት በግልጽ የተካሄደ መሆኑንም ኢዜማ አስታውቋል። ይህ ማለት በሁለት ዓመት ውስጥ በዚህ መጠን የተካሄደ የመሬት ወረራና የባለጊዜዎች የመኖሪያ ቤት እደላ በወያኔ የ27 ዓመታት የአገዛዝ ዘመን አልተካሄደም ማለት ነው።
ኢዜማ ጥናቱን ሲደመድም እንዳስታወቀው የአዲስ አበባ የመሬት ወረራና ሕገ ወጥ የመሬት እደላ የተካሄደው በክፍለ ከተማ እና በወረዳ ኃላፊዎች እና ፈፃሚዎች ሲሆን ኢፍትሐዊ ያላቸው ሕጎችን እና መመሪያዎችን በማውጣት እና ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ሕጎችን እና ደንቦችን በማሻሻል ለካቢኔው እና ለከንቲባው የተሰጠው ልዩ ሥልጣን (መመሪያ ቁጥር 1 እና 2/2011፣ ክፍል 2 አንቀጽ 12/2) ከንቲባውም ሆነ ካቢኔያቸው ቤቶችን እንደፈለጉ እንዲያድሉ ምክንያት ሆኗል ብሏል።
እዚህ ላይ አህያውን ፈርቶ ዳውላውን ያልሁበትን የኢዜማን ጥናት ጎደሎነት ላንሳ። ኢዜማ በጥናቱ ለመሬት ወረራውና ለሕገ ወጥ የመኖሪያ ቤት እደላው መንሳኤን ነው ብሎ ያቀረበው ምክንያት ከንቲባውና ካቢኔው ሕጎችን እና ደንቦችን እንዲያሻሽሉ የተሰጣቸውን ልዩ ሥልጣንና በተሰጣቸው ልዩ ሥልጣን ያወጧቸውን መመሪያ ቁጥር 1 እና 2/2011፣ ክፍል 2 አንቀጽ 12/2ን ነው። ሆኖም ግን ይህን ልዩ ስልጣን ለከንቲባውና ለካቢኔው የሰጠው ዐቢይ አሕመድ ነው። ዐቢይ አሕመድ ለካንቲባውና ለካቢኔው ይህን ልዩ ሥልጣን የሰጠው ወደ ስልጣን እንደመጣ አዲስ ደንብ አመንጭቶ ከንቲባ የሚሆን የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል ሳይታጣ ታከለ ኡማን ከአዲስ አበባ ምክር ቤት ውጭ አምጥቶ ለአዲስ አበባ ከንቲባ አድርጎ በሾመበት ወቅት ነው።
ይህ ማለት አዲስ ደንብ አውጥቶ የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል ያልነበረውን ታከለ ኡማን ከንቲባ ያደረገውና ደንቦችንና ሕጎችን እያሻሻለ መሬትና የመኖሪያ ቤት ለፈለጉት ሰው እንዲያድል ልዩ ሥልጣን የሰጠው ዐቢይ አሕመድ ነው። ይህ ማለት ኢዜማ በጥናቱ በፈተሻቸው በአምስት ክፍለ ከተሞች ውስጥ በሚገኙ የተወስኑ ቦታዎች ላይ ብቻ የተካሄደው 213,900 ካሬ ሜትር የመሬት ወረራ፣ ከ95, 000 በላይ መኖሪያ ቤቶች በሕገ ወጥ መንገድ ለባለጊዜዎቹ የታደሉትና በሺዎች ለሚቆጠሩ ኦሮምያ ክልል ለሚባለው ሰራተኞች የአዲስ አበቤ ቤቶች የታደሉት ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን እንደመጣ የአዲስ ስበባ ምክር ቤት አባል ያልነበረውን ታከለ ኡማ ከንቲባ ለማድረግ ባወጣው ሕግና ከንቲባውና ካቢኔው ሕግና መመሪያ እያወጡ መሬትና ቤት ለሚፈልጉት ሰው እንዲያድሉ በሰጣቸው ልዩ ሥልጣን አማካኝነት ነው።
ኢዜማ ግን በጥናቱ ለመሬት ወረራውና ለሕገ ወጥ የቤት እደላው ለከንቲባውና ለካቢኔው ልዩ ሥልጣን የሰጡ መመሪያዎችን ተጠያቂ አድርጎ ለከንቲባውና ለካቢኔው አዲስ ሕግ አውጥቶ ልዩ ሥልጣን የሰጣቸውን ዐቢይ አሕመድን ለመሬት ወረራውና ለሕገ ወጥ የቤቶች እደላው ተጠያቂ ሳያደርገው ቀርቷል። እንዲህ አይነቱን ድፍረት ማጣት ነበር በዓሉ ግርማ “ድፍረት ከሌላት ብዕር ባዶ ወረቀት ብዙ ይናገራል” ሲል የተቸው።
ባጭሩ አሕያውን ፈርቶ ዳውላውን እንዲሉ በዐቢይ አሕመድ የተመራውን የአዲስ አበባ ወረራና ዐቢይ አሕመድ ራሱ አዲስ ሕግ አውጥቶ በሰጠው ልዩ ሥልጣን የተካሄደውን የመሬት ወረራና ለባለጊዜዎች የተደረገውን የመኖሪያ ቤቶች እደላ ከዐቢይ አሕመድ አናት ወርዶ መልእክተኞቹ ላይ ማነጣጠር ሞያ አይደለም! በአዲስ አበባ ጉዳይ ዐቢይ አሕመድ ከሁሉም ጽንፈኛ የኦሮሞ ብሔርተኞች የበለጠ ወሮ በላ ነው። መልዕክተኛው ታከለ ኡማ አድርግ የተባለውን ከፈጸመ በኋላ ለዋለው ውለታ ማዕረግ ተጨምሮለት ወደ ሚኒስቴርነት ያደገው <<ፊንፊኔ የኦሮሚያ መሆኗ የማይዋጥለት ካለ መንገዱን ጨርቅ ያርግለት>> ሲል የተናገረውን ወዶለት አዲስ ሕግ አውጥቶ ምክትል ከንቲባ ያደረገውን የዐቢይ አሕመድን አጀንዳ በተካሳ ሁኔታ ካስፈጸመ በኋላ ነው። ያለ ዐቢይ አሕመድ ፍቃድ፣ ይሁንታና መሪነት አዲስ አበባም ይሁን በሌላው የኢትዮጵያ ክፍል የሚፈጸም አንድም የአፓርታይድ ተግባር የለም።
በነገራችን ላይ በአዲስ አበባ ሕዝብ ገንዘብ ተሰርተው ለባለጊዜዎቹ የታደሉት 95 ሺህ መኖሪያ ቤቶች፣ በልማት ስም የአዲስ አበቤ ቤት እየፈረሰ ለመሬት ባንክ ገቢ ተደረገ ተብሎ የተወረረው 213,900 ካሬ ሜትር ቦታና በሺዎች ለሚቆጠሩ ኦሮምያ ክልል ለሚባለው ሰራተኞች የታደሉት የአዲስ አበቤ ቤቶች የዐቢይ አሕመድ የአፓርታይድ አገዛዝ አዲስ አበባ ውስጥ እያካሄደው ያለው የዲሞግራፊ ለውጥና የዘር ማጥራት [Ethnic cleansing] መገለጫዎች[manifestations] ናቸው። በዓለም አቀፍ ሕግ ሰው በሚኖርበት ቀዬው የሰራውን ቤት ቀምቶ ከሌላ አካባቢ አምጥቶ በዘር ላይ የተመረኮዘ ሰፈራ ማካሄድ ዘር ማጥራት [Ethnic cleansing] ነው። በኢዜማ ጥናት እንዳየነው በአዲስ አበባ የተካሄደውም ይህ የዘር ማጥራት [Ethnic cleansing] ነው።
ከታች የታተመው የፕሮፌሰር ብርሃኑ ንግግር ዛሬ ኢዜማ በጥናቱ ያቀረበው የመሬት ወረራና ሕገ ወጥ የመኖሪያ ቤቶች እደላ ለባለጊዜዎች ያካሄዱትን እነ ዐቢይ አሕመድና ታከለ ኡማን አሻጋሪ ናቸው ሲሉ ያሞካሹበት ምስክርነት ነው። ለነ ዐቢይና ታከለ ይህንን የመሰለ ምስክርነት የሰጡት ፕሮፈሰር ብርሃኑ ነጋ ወይ ስለ ንግግራቸው የአዲስ አበባን ሕዝብ ተንበርክከው ይቅርታ ጠይቀው ይህን አይነት የአመራር ብቃት ማነስና አድርባይነት ይዘው በመሪነት መቀጠል ስለማይችሉ የኢዜማ አመራርነቱ አስረክበው ውልቅ ማለት አለባቸው አልያም በሊቀመንበርነት የሚመሩት ድርጅት ኢዜማ ያወጣውን በዐቢይ አሕመድ የተመራ የአዲስ አበባ የመሬት ወረራና ለባለጊዜዎች የተካሄደ የመኖሪያ ቤቶች እደላ ጥናት ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ማስተባበል ይኖርባቸዋል።