በጣሊያን ኤምባሲ ለከረሙት ሁለት የቀድሞ ባለሥልጣናት የተደረገው ይቅርታና አመክሮ የጫረው የሕጋዊነት ጥያቄ

0
0 0
Read Time:7 Minute, 46 Second


ዮሐንስ አንበርብር

Source: https://www.ethiopianreporter.com/index.php/article/20864


በኢትዮጵያም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ረዥም ጊዜ የፈጀ የፍርድ ሒደት የሚባለው፣ በእነ ሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም መዝገብ የተከሰሱ ተጠርጣሪዎች ፍርድ፣ 12 ዓመታት ከወሰደ በኋላ የተሰጠው የመጨረሻ ውሳኔ ነው።

በዚህ መዝገብ ክስ ከቀረበባቸው አጠቃላይ 55 ሰዎች ውስጥ 25 ያህሉ በሰብዓዊነት ላይ በተፈጸመ ወንጀል ጥፋተኛ ተብለው በሞት እንዲቀጡ ተወስኖባቸው ነበር።

የሞት ቅጣቱ ከተወሰነባቸው 25ቱ ተጠርጣሪዎች መካከል ሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያምና ሌሎች አራት ሰዎች በሌሉበት የተፈረደባቸው ሲሆን፣ አራቱ ፍርደኞችም በወቅቱ አማፂ የነበረው የኢሕአዴግ ጦር የትጥቅ ትግሉን አሸንፎ አዲስ አበባን በተቆጣጠረበት ወቅት አዲስ አበባ በሚገኘው የጣሊያን ኤምባሲ ጥገኝነት ጠይቀው ተጠልለው ነበር፡፡ ኤምባሲውም አሳልፎ ባለመስጠቱ የፍርድ ውሳኔው በሌሉበት እንደተላለፈባቸው ይታወሳል።

የሞት ቅጣቱ የተወሰነባቸውና በእስር ቤት ይገኙ የነበሩ 20 ሰዎች ውሳኔው ከተወሰነባቸው ከ20 ዓመታት በኋላ የሞት ቅጣቱ በይቅርታ ወደ ዕድሜ ልክ እስራት ተቀይሮላቸዋል። በኋላም በአመክሮ በሕግ መሠረት ከእስር ተፈተው ነፃነታቸውን አግኝተዋል።

በኢትዮጵያ የሞት ቅጣት ፍርድ በቀድሞ የደርግ ባለሥልጣናት ላይ ብቻ የተገደበ አልነበረም፣ በአሁኑ ወቅትም የሚወሰን የቅጣት ዓይነት ነው። ለአብነት ያህልም በኦሮሞና በጉምዝ ብሔረሰቦች ግጭት የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽመዋል በተባሉ ሰባት ግለሰቦች ላይ የሞት ቅጣት ተፈርዷል።

የቀድሞ የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ አመራር በነበሩ ግለሰቦች ላይም ተመሳሳይ የሞት ቅጣት ተወስኖ ነበር። ከእነዚህም መካከል የመን ሰንዓ አውሮፕላን ማረፊያ ተይዘው ለኢትዮጵያ ተላልፈው ተሰጥተዋል የተባሉት ፖለቲከኛው አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ አንዱ ናቸው።

የቀድሞ የደርግ ባለሥልጣናት በይቅርታና በአመክሮ ከእስር እንዲወጡ እንደተደረገው ሁሉ፣ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌም በተመሳሳይ ተፈርዶባቸው የነበረው የሞት ቅጣት በይቅርታ ወደ እስር ተቀይሮ በኋላም ከእስር መውጣታቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።

ከደርግ መንግሥት በኋላ በነበሩት ያለፉት 30 ዓመታት በሞት እንዲቀጡ የተፈረደባቸው በርካታ ግለሰቦች ሲኖሩ፣ እስካለፈው ሁለት ዓመት ድረስም 221 የሞት ቅጣት የተወሰነባቸው ግለሰቦች መኖራቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።

በኢትዮጵያ የሞት ቅጣት መወሰን የተለመደ ቢሆንም ባለፉት ሁለት ዓመታት ቅጣቱ ተግባራዊ የተደረጉት የቀድሞው የሕወሓት ጦር አባልና የአገር መከላከያ ሠራዊት የጦር አመራር የነበሩትን ሜጄር ጄኔራል ኃየሎም አርአያን፣ እንዲሁም የአገሪቱ የደኅንነት መሥሪያ ቤት ኃላፊ የነበሩትን አቶ ክንፈ ገብረ መድኅንን ገድለዋል ተብለው በተከሰሱ ሁለት ግንለሰቦች ላይ የተፈረዱት የሞት ቅጣቶች ናቸው።

የተቀሩት በይቅርታ ወደ ዕድሜ ልክ እስር ተቀይሮላቸውና አመክሮ አግኝተው ነፃ ሲሆኑ፣ ቀሪዎቹ ደግሞ አሁንም በእስር ላይ ይገኛሉ።

በዚህ ውስጥ ግን በተለየ አመክንዮ የተነሳ ከላይ የተገለጹትን ይቅርታና አመክሮ ሳያገኙ የቀሩ የሞት ቅጣት የተወሰነባቸው መኖራቸው አሌ አይባልም። የእነዚህ የሞት ፍርደኞች የተለየ አመክንዮም በእስር ላይ አለመሆናቸው ነው። እነዚህም በዚምባቡዌ በስደት ላይ የሚገኙት ሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያምና በአዲስ አበባ ጣሊያን ኤምባሲ የተጠለሉት የቀድሞ የደርግ ባለሥልጣናት ናቸው።

ይሁን እንጂ በጣሊያን ኤምባሲ ጥገኝነት ጠይቀው ከተጠለሉት ውስጥ፣ በሕይወት የሚገኙት የሞት ቅጣት የተፈረደባቸው ሁለት የቀድሞ የደርግ መንግሥት ባለሥልጣናት ጉዳይ ከሰሞኑ ዕልባት አግኝቷል።

ይህ የሆነበትም ሒደት በግለሰቦቹ ላይ የተወሰነው የሞት ቅጣት የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር ባደረጉት ይቅርታ አማካይነት ወደ ዕድሜ ልክ ተቀይሮላቸው፣ በኋላም በአመክሮ የሕግ ሥርዓት ነፃነታቸው እንዲመለስ ተወስኗል። ሒደቱ የተፈጸመበት መንገድ ግን የሕጋዊነት ጥያቄን ጭሮ የሕግ ባለሙያዎችን እያከራከረ ነው።

የተነሳው የሕጋዊነት ጥያቄም አንድ መሠረታዊ ጉዳይ ላይ የተንጠለጠለና ሁለት የክርክር ነጥቦችን የያዘ ነው። ይኸውም ሁለቱ የቀድሞ ባለሥልጣናት በእስር ቤት ሳይሆን በኤምባሲ የሚገኙ መሆናቸው መሠረታዊው ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ መሠረታዊ ጉዳይ የተነሳም ግለሰቦቹ ይቅርታ ማግኘት የሚችሉበት የሕግ አግባብ የለም፣ አመክሮ ማግኘት የሚችሉበት የአገሪቱ ሕግ ያበጀው ሥነ ሥርዓትም የለም የሚሉት የክርክሮቹ ባህሪያት ናቸው።

የይቅርታና የአመክሮ ምንነትና ጠቀሜታ

ይቅርታና አመክሮ ሁለት የተለያዩ ፋይዳ ያለቸው ለተፈረደባቸው እስረኞች ብቻ የሚሰጡ ዕድሎችን የሚያስቀምጡ የሕግ ሥነ ሥርዓቶች መሆናቸውን የሚገልጹ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ የሕግ ባለሙያዎች፣ ሰሞኑን በተቋሙ የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ላይ ትንታኔ ተሰጥተዋል።

በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የይቅርታ ቦርድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ዘለቀ ዳሎል ይቅርታ ማለት፣ ‹‹የቅጣት ፍርድ በሙሉ ወይም በከፊል ቀሪ እንዲሆን ወይም የቅጣት ፍርዱ አፈጻጸምና ዓይነት ቀለል ተደርጎ እንዲፈጸም ማድረግ ነው፤›› በሚል፣ የይቅርታ አሰጣጥና አፈጻጸም ሥነ ሥርዓትን ለመምራት በወጣው አዋጅ ቁጥር 840/2006 መተርጎሙን ይገልጻሉ።

የቅጣት ፍርድ ማለት ደግሞ በወንጀል ጉዳይ ዋና ቅጣትን፣ ተጨማሪ ቅጣትን ወይም የክልከላና የጥንቃቄ ዕርምጃን በተመለከተ በፍርድ ቤት የተሰጠ የመጨረሻ ውሳኔ እንደሆነ አዋጁን በመጥቀስ ያብራራሉ።

ይቅርታ በወንጀል ጉዳይ በፍርድ ቤት የመጨረሻ ውሳኔ የተወሰነ ዋና ቅጣት፣ ተጨማሪ ቅጣት ወይም፣ የጥንቃቄና ጥበቃ ዕርምጃ/ቅጣት በሙሉ ወይም በከፊል ነፃ ለማድረግ ይቅርታ የሚሰጠውም በይቅርታ ቦርድ አማካይነት በሚቀርብ የውሳኔ ሐሳብ መነሻ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 71/1 ለአገሪቱ ርዕስ ብሔር በተሰጠው ሥልጣን መሠረት በፕሬዚዳንት የሚወሰን እንደሆነ ገልጸው፣ በፍርድ ቤት በክርክር ላይ ያሉ ጉዳዮች ለይቅርታ የሚቀርቡበት የሕግ አግባብ እንደሌለም አክለዋል፡፡

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 28 ለተዘረዘሩ ወንጀሎች ማለትም የሰው ዘር ማጥፋት፣ ያለ ፍርድ የሞት ቅጣት ዕርምጃ የመፈጸም ወንጀል፣ በአስገዳጅ ሰውን መሰወር ወይም ኢሰብዓዊ የድብደባ ድርጊቶች በይቅርታ እንደማይታለፉ የሚገልጹት ኃላፊው፣ ይህ ቢሆንም በእነዚህ ወንጀሎች መነሻ የሞት ፍርድ ተፈርዶ ከሆነ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት የሞት ቅጣቱን ወደ ዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት መቀየር እንደሚችሉ በሕገ መንግሥቱ መደንገጉን ያስረዳሉ።

በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የንቃተ ሕግ፣ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት ምክትል ዳይሬክተር አቶ ጉደታ ቀንዓ በበኩላቸው፣ የአመክሮን ምንነትና የአፈጻጸም ሥነ ሥርዓት አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ አመክሮ በማረሚያ ቤት ለሚገኙ እስረኞች የእስር ቅናሽ የሚሰጥበት የሕግ ሥነ ሥርዓት እንደሆነ አስረድተዋል።

የፌዴራል ማረሚያ ቤት የታራሚዎች አመክሮ አሰጣጥ መመርያ ቁጥር 1/2009 አመክሮ አንድ ታራሚ መፀፀቱ፣ መታረሙ፣ ከተወሰነበት ቅጣት ውስጥ ሁለት ሦስተኛውን መፈጸሙ ሲረጋገጥ የሚደረግለት የአንድ- ሦስተኛ የእስራት ቅጣት ቅናሽ ነው በማለት ትርጓሜ እንደሚሰጠው ገልጸዋል።

‹‹ይህ አሠራር ታራሚው ከእስር ተለቆ ከኅብረተሰቡ ጋር እንዲቀላቀል ዕድል ይፈጥርለታል። እንዲሁም ታራሚው ከጥፋቱ ታርሞ የባህሪ ለውጥ እንዲያመጣ ለማበረታታት ይጠቅማል፡፡ በሌላ በኩል በአመክሮ ታራሚዎችን መፍታት በማረሚያ ቤቶች ያለውን መጨናነቅና ወጪን ለመቀነስም ያግዛል፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

በሱጡት ማብራሪያም በአመክሮ መፈታት ማለት የእስራት ቅጣት የተወሰነበት ሰው በማረሚያ ቤት ሆኖ ቅጣቱን በመፈጸም ላይ እያለ አመክሮ በሕግ የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎች ሲሟሉ፣ ለሕግ ታራሚ ወይም ፍርደኛ የእስራት ቅጣቱን ሳይጨርስ ቀድሞ የሚለቀቅበት አሠራር እንደሆነ፣ ከቅድመ ሁኔታዎቹ መካከልም የእስር ቅጣቱ ተፈጻሚ መሆን መጀመር አንዱ እንደሆነ ይገልጻሉ።

አያይዘውም አመክሮ ለታራሚዎች ወይም እስረኞች የሚሰጥ ቢሆንም፣ እስረኞቹ እንደ መብት የሚያገኙት እንዳልሆነ ይገልጻሉ። ‹‹ለአመክሮ የሚያበቁ ቅድመ ሁኔታዎችን መሟላት በአመክሮ ለመፈታት የሚያበቁ ቢሆንም፣ በአገራችን ልማደኛና ተደጋጋሚ ወንጀለኛና የሞት ፍርድ የተፈረደበት ሰው በአመክሮ የመፈታት ዕድል ተጠቃሚ እንደማይሆን በሕጉ ተደንግጓል፤›› ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

ሁለቱ የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ባለሙያዎች ከሰጡት ትንታኔ መረዳት የሚቻለው አንድ ቁም ነገር ይቅርታ ለማግኘትም ሆነ በአመክሮ ለመፈታት፣ በመጀመርያ በሕግ በተቋቋመ እስር ቤት ውስጥ የተፈረደውን እስር ተግባራዊ ማድረግ የሚገባ መሆኑ ነው።

ለሁለቱ የቀድሞ ባለሥልጣናት የተሰጠው ይቅርታና አመክሮ ሕጋዊነት

በጣሊያን ኤምባሲ የተጠሉሉት ሁለቱ የቀድሞ የደርግ ባለሥልጣናት ሌተና ጄኔራል አዲስ ተድላና ሌተና ኮሎኔል ብርሃኑ ባየህ የተፈረደባቸው የሞት ቅጣት ወደ ዕድሜ ልክ እስራት የተቀየረበትን ምክንያት፣ በኋላም በተሰጣቸው አመክሮ እስራቱ ቀሪ ተደርጎ ነፃ እንዲሆኑ ለፍርድ ቤት ጥያቄ የቀረበበትን አመክንዮ በተመለከተ በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የሙስናና የተደራጁ ወንጀል ጉዳዮች ዘርፍ ምክትል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ፍቃዱ ፀጋ ሐሙስ ታኅሳስ 15 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ አብራርተዋል።

በመሆኑም መንግሥት እነዚህን ሰዎች ከዚህ በላይ ነፃነታቸውን ገድቦ ማቆየቱ የፍትሕ ዓላማን ከማሳካት አንፃር የሚጨምረው ውጤት ባለመኖሩ፣ እንዲሁም ከፍርደኞቹ ዕድሜና ጤና አንፃር የሰብዓዊነት ዕይታን ከግምት በማስገባት በግለሰቦቹ ላይ ተወስኖ የነበረው የሞት ፍርድ ወደ ዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት እንዲቀየር ለኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት የይቅርታ ውሳኔ ሐሳብ ቀርቦ ይቅርታ መደረጉን ገልጸዋል።

ግለሰቦቹ እስካሁን በኤምባሲው ቅጥር ግቢ ውስጥ ነፃነታቸው ተገድቦ መቆየቱ አስተማሪነት ያለው መሆኑ ከግምት ገብቶ በአመክሮ እንዲለቀቁ፣ ጥያቄውን የፌደራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግና የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ጋር በጋራ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ማቅረባቸውን፣ ፍርድ ቤቱም የቀረበውን አቤቱታ ተቀብሎ ግለሰቦቹ በአመክሮ እንዲለቀቁ መወሰኑን ገልጸዋል።

ለፍርድ ቤቱ የቀረበውን የአመክሮ ጥያቄ የመረመሩት ሦስት ዳኞች ግለሰቦቹ ነፃ እንዲሆኑ ውሳኔ የሰጡት በአብላጫ ድምፅ መሆኑን የውሳኔ ግልባጩ ያሳያል። ዳኞቹ በልዩነት እንዲወስኑ ካደረጓቸው ምክንያቶች መካከልም መሠረታዊ የሆነው ጭብጥ፣ ግለሰቦቹ በሕግ በተቋቋመ እስር ቤት ውስጥ ሳይሆን በኤምባሲ ውስጥ የሚገኙ መሆናቸው ነው።

ይህንንም አስመልክቶ በአብላጫ ድምፅ ውሳኔ ያሳለፉት ሁለት ዳኞች (ወይም ችሎቱ) ግለሰቦቹ በፍርድ ቤት የተወሰነባቸውን ቅጣት ለመፈጸም ወደ ማረሚያ ቤት እንዳልገቡና በጣሊያን ኤምባሲ ለ30 ዓመት ተጠልለው እንደቆዩ፣ በዚህም ምክንያት በሕግ ማስፈጸም ወይም የማረምና የማነፅ ሥርዓት ውስጥ ያላለፉ መሆናቸውን እንደተረዱ አስገንዝበዋል።

በጣሊያን ኤምባሲ ቅጥር ግቢ ውስጥ መቆየት ማረሚያ ቤት መግባት እንዳልሆነም ከግንዛቤ ወስደዋል። ነገር ግን ደግሞ በጣሊያን ኤምባሲ ነፃነታቸው ተገድቦ፣ በቤተሰቦቻቸው የዕለት ተዕለት ድጋፍ መኖራቸውን በማገናዘብ በኤምባሲው ያደረጉት ቆይታ እንደ መደበኛ ማረሚያ ቤት ባይቆጠርም፣ በኤምባሲው ነፃነታቸው ተገድቦ ያደረጉት ቆይታ ከውጤት አንፃር ሲታይ ከመደበኛ ማረሚያ ቤት ጋር ተመሳሳይነት ያለው እስራት እንደሆነ ከግምት ወስደዋል።

እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲከሰት ፍርድ ቤቶች ነገሩን የሚመረምሩበት ዝርዝር የሕግ ሥርዓት ወይም በልምድ የዳበረ ተመሳሳይ የሆነ ጉዳይ ባለመኖሩ፣ ለሁለቱ ፍርደኞች አመክሮ እንዲሰጥ የቀረበውን ማመልከቻ ከሰብዓዊ መብቶች መሠረታዊ ዓላማ አንፃር ሰፋ አድርጎ መተርጎምን መምረጣቸውን ገልጸዋል።

በዚህም ከሁለቱ ግለሰቦች ጋር ተመሳሳይ ቅጣት የተጣለባቸው ሌሎች ይቅርታና አመክሮ ተደርጎላቸው መለቀቃቸውን፣ የሁለቱ ግለሰቦች ዕድሜ የገፋ መሆኑን፣ ፍትሕ ከማግኘት መብት፣ ከዓለም አቀፍ የኮሮና ወረርሽኝና ነፃነታቸው ተገድቦ ያሳለፉትን ጊዜ በበጎና በሰፊው ትርጉም በመመልከት በአመክሮ እንዲለቀቁ ውሳኔ መስጠታቸውን ገልጸዋል።

ችሎቱ በአብላጫ ድምፅ በሰጠው ብይን ላይ የልዩነት ውሳኔ የሰጡት ዳኛ አቶ ሳሙኤል ከበደ በመከራከሪያነት ካቀረቧቸው ነጥቦች መሠረታዊው ነጥብ፣ ግለሰቦቹ በማረሚያ ቤት የሚገኙ ባለመሆናቸው በአመክሮ ሊለቀቁ አይገባም የሚል ነው።

‹‹በጣሊያን ኤምባሲ መቆየታቸውም ሆነ መጠለላቸው አንድ የሕግ ታራሚ በማረሚያ ቤት በመሆኑ የሚያጣውን መብት ሊያሳጣ የሚችል አይደለም። እንዲሁም ማረሚያ ቤትንና በኤምባሲ የተጠለሉ ግለሰቦችን አንድ የሚያደርጋቸው ወይም ለማነፃፀር የሚያስችል ምንም ዓይነት የሕግ ፍልስፍናም ሆነ የሕግ መሠረት በእኔ እምነት የለውም፤›› ብለዋል።

እንዲሁም የይቅርታ አሰጣጥና አፈጻጸም ሥነ ሥርዓትን የሚደነግገው አዋጅ ቁጥር 840/2006 አንቀጽ 16 (ሠ) ላይ ለይቅርታ የሚቀርብ አቤቱታ ግለሰቡ የቅጣት ፍርዱን በመፈጸም ላይ የሚገኝበትን ማረሚያ ቤት ስም መጠቀስ እንዳለበት፣ ግለሰቡ በማረሚያ ቤት የቆየበትን ጊዜ መግለጽ የሚጠይቅ በመሆኑና ይቅርታው የተሰጠው ይህ ባልተሟላበት ሁኔታ ስለሆነ የሕግ ሒደቱ የተሟላ አለመሆኑን እንደሚያሳይ በመጥቀስ ልዩነታቸውን አስቀምጠዋል።

‹‹ፍርድ ቤቱ በግለሰቦቹ ላይ የሰጠው የቅጣት ውሳኔ ሳይፈጸም በጥገኝነት በኤምባሲ ተጠልሎ መኖርን በማረሚያ ቤት እንደ መቆየት አድርጎ መውሰድና የፍርድ ቤት ውሳኔን ወደ ጎን በመተው መወሰን፣ በእኔ እምነት የፍርድ ቤቶችን ነፃነት የሚጋፋ ነው። ግለሰቦቹ ቅጣታቸውን በማረሚያ ቤት ሳይፈጽሙ አመክሮ በማስላት እንዲፈቱ የሥራ ባልደረቦቼ መወሰናቸው የሕግ መሠረት የለውም በማለት ከእነሱ የአብላጫ ድምፅ ተለይቻለሁ፤›› ሲሉ አቶ ሳሙኤል በልዩነት ወስነዋል።

ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንድ የሰብዓዊ መብቶች የሕግ ባለሙያ ኢትዮጵያ የሞት ቅጣትን በሕጎቿ ያሠፈረችና ቅጣቱም በፍርድ ቤቶች የሚወሰን ቢሆንም፣ የሞት ቅጣትን ተፈጻሚ ባለማድረግ በአሠራር ደረጃ የሞት ፍርድን ከማይቀበሉ (De Facto Abolitionist of Death Penalty) ከሚባሉ አገሮች ተርታ ተመዳቢ ያደርጋታል ብለዋል።

በመሆኑም ከግለሰቦቹ ላይ የሞት ቅጣቱ ቀሪ እንዲሆን መደረጉ የሚደገፍ መሆኑን ገልጸዋል። ነገር ግን የሞት ቅጣቱን ቀሪ ለማድረግና ግለሰቦቹ በአመክሮ እንዲለቀቁ የተደረገበት የሕግ አግባብ፣ ሕጋዊ አሠራሩን ያልተከተለና በወደፊት የይቅርታና የአመክሮ አሰጣጥ የሕግ ሥነ ሥርዓት ላይ አሉታዊ አሻራ የሚያሳድር በመሆኑ እንደማይቀበሉት ገልጸዋል።

‹‹አሁን የተደረገውን ይቅርታና አመክሮ ለመስጠት ግለሰቦቹ ከኤምባሲ ወጥተው ለጥቂት ሳምንታት በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ በማድረግ፣ ቢያንስ አነስተኛውን የሕግ ሥነ ሥርዓት መፈጸም ይቻል ነበር፤›› ሲሉ የተሄደበትን የሕግ አግባብ ተችተዋል።

Source: https://www.ethiopianreporter.com/index.php/article/20864

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *