በትግራይ ክልል ለወደሙና ለተዘረፉ ድርጅቶች ባለሀብቶች መንግሥት መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠየቁ
ሲሳይ ሳህሉ
በትግራይ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ያሉ የማምረቻ ኢንዱስትሪዎች፣ መንግሥት በወሰደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ በደረሰባቸው የንብረት ውድመትና ዝርፊያ ተመልሰው ወደ ሥራ ለመግባት መንግሥት ሊያግዛቸው እንደሚገባ ባለሀብቶች ጠየቁ፡፡
ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በትግራይ ክልል ከሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪ ባለቤቶችና ኃላፊዎች ጋር ከሕግ ማስከበር ዘመቻው ጋር በተያያዘ ስለደረሰባቸው ጉዳትና በቀጣይ መደረግ ስላለባቸው ሥራዎች ዓርብ ታኅሳስ 18 ቀን 2013 ዓ.ም. በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ውይይት አድርጓል፡፡
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ፣ ድርጅቶቹ የደረሰባቸውን ጉዳት የሚመለከት ግብረ ኃይል አቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱን የገለጸ ሲሆን፣ በክልሉ ከሚገኙ 93 ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎችና ወደ 6,970 የሚደርሱ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ያሉበትን ሁኔታ እየገመገመ መሆኑን አስታውቋል፡፡
በውይይቱ በርካታ ድርጅቶች የተገኙ ሲሆን፣ በዋናነት የባንክ አገልግሎት አለመስጠት፣ የመንገዶች መዘጋት፣ የስልክና ኢንተርኔት አለመሥራት፣ የሠራተኞች የደኅንነት ሥጋት፣ በገቢዎችና ጉምሩክ አገልግሎት ምቹ ሁኔታ አለመፈጠር የመሳሰሉ ችግሮችን አንስተዋል፡፡
የሰማያት እምነ በረድ ፋብሪካ የገበያ ጥናት ባለሙያ የሆነችው ወ/ሮ ትዕግስት ፋንታሁን በውቅሮ ስለሚገኘውና ከ500 በላይ ሠራተኞችን በውስጡ ስለያዘው ድርጅት ስትናገር፣ በዘመቻው ወቅት በፋብሪካው ውስጥ የነበሩ ዘመናዊ ማሽነሪዎች ተቃጥለዋል፣ አንዳንዶቹም ተዘርፈዋል ብላለች፡፡ ወ/ሮ ትዕግስት አክላም ከአልባኒያና ከጣሊያን ያመጣናቸው ባለሙያዎች ለደኅንነታቸው ሠግተው ወደ አገራቸው ሄደዋል፣ ፋብሪካውን እንደገና እንመልሰው ብንል እንኳ ገንዘቡም የለንም፡፡ በአገር ውስጥ ባለሙያ ሊሠሩ የማይችሉ በርካታ ሥራዎችም እንዳሉም ተናግራለች፡፡
በመሆኑም መንግሥት የሚቻለውን ሁሉ አድርጎ ፋብሪካውን ወደ ሥራ ለመመለስ የሚያስችል ሥራ እንዲሠራ ጠይቃለች፡፡ ከ1000 በላይ ሠራተኞችን በውስጡ እንደያዘና በሕግ ማስከበር ዘመቻው ወቅት በፋብሪካው ይሠሩ የነበሩና ለደኅንነታቸው በመሥጋታቸው ከአገር መውጣት የፈለጉ የውጭ አገር ዜጎችን በድጋሚ አናገኛቸውም በሚል ሥጋት፣ በአዲስ አበባ አምጥቶ በድርጅቱ ወጪ እያኖሩ እንደሆነ የገለጹት የዳሸን ቆርቆሮና ሚስማር ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሚኪያስ ታደሰ ናቸው፡፡
እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ፣ በመቀሌ በሚገኘው ፋብሪካ የውጭ አገር ዜግነት ያላቸውን ሠራተኞች በሲኖትራክ መኪና ጭኖ ወደ አዲስ አበባ እንዳመጣቸውና አሁን ግን ተመልሰው ወደ ሥራ ለመግባት ሥጋት ላይ መሆናቸውን ገልጿል፡፡
ከሳባና የእርሻ ድርጅትና የኤጄጄ ወተት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ የተገኙትና የድርጅቱ ባለአክሲዮን የሆኑት አቶ አበራ ጣሰው ስለደረሰባቸው ጉዳት ሲናገሩ ከ500 በላይ የወተት ላሞችና ሌሎች ንብረቶችም ተዘርፈዋል፣ የተረፈውም ተቃጥሏል፡፡ በጣም አዝነናል ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
ድርጅቶቹ በአዲጉደምና በራያ እንደሚገኙ የገለጹት አቶ አበራ፣ በቀጣይ ወደ ሥራ ለመግባት ከፍተኛ የሆነ የመንግሥትን ዕርዳታ እንደሚሹና በአሁኑ ጊዜ የተዘጉ ባንኮች እንዲከፈቱና ያለ ሥራ ለተቀመጡ ሠራተኞች ደመወዝ ከፍለው እንዲያሰናብቱ ጠይቀዋል፡፡
በሌላ በኩል ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ ንብረቶች በዝርፊያና በቃጠሎ እንደወደመበት የገለጹት የሼባ ሌዘር የገበያና ቢዝነስ ልማት ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘርአብሩክ ገብረ ሚካኤል ናቸው፡፡
እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ ፋብሪካውን በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ ለመመለስ የሚያስችል ሁኔታ እንደሌላቸውና መንግሥት ማድረግ የሚቻለውን ሁሉ አድርጎ መመለስ ካልተቻለ ወደ 900 የሚጠጉ ሠራተኞችም ጭምር ከፋብሪካው ጋር አብረው ሥራ ሊያቆሙ እንደሚችሉ አስረድተዋል፡፡
‹‹መንግሥት የስም ማጥፋት ዘመቻ አድርጎብኛል፣ ከዓለም አቀፍ ገዥዎችና ከተለያዩ ተቋማት ጋር ያለኝን ግንኙነት አበላሽቶታል›› ያለው ደግሞ በመቀሌ የሚገኘው ቪሎሲቲ አፓራሌዝ የተባለው ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ነው፡፡
የፋብሪካው ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ህንዳዊ ባጃጅ ቲያ ደርጃን እንደተናገሩት፣ መንግሥት ከሕወሓት ጋር ግንኙነት አላቸው ያላቸውን 38 ድርጅቶች እንዳይንቀሳቀሱ በሚል ለሕዝብ ይፋ አድርጎ በነበረበት ወቅት፣ ፋብሪካቸው ከድርጅቶቹ ዝርዝር ያለምንም ጥፋትና በሌለ ግንኙነት አብሮ እንዳካተተባቸው አስረድተዋል፡፡
ይሁን እንጂ በቅርቡ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የካምፓኒው ስም ከዝርዝሩ መውጣቱን የገለጸ ሲሆን፣ ላደረገው ስህተት ግን ማብራሪያ እንዳልሰጠና ለተፈጠረው ስም ማጥፋት ምንም ዓይነት ማስተባበያ እንዳልሰጠ ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ዴኤታው አቶ ዮሐንስ ድንቃየሁ ለድርጅቶቹ ማብራሪያ ሲሰጡ፣ መንግሥት ለደረሰባቸው ጉዳት አስፈላጊ የሆነውን ሁሉ ትብብር ለማድረግ በየፋብሪካዎቹ እየተንቀሳቀሰ ጥናት እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡
በተጨማሪም ጉዳት ደረሰብን የሚሉ ድርጅቶች በአካል በመቅረብ ለሚኒስቴሩ ሪፖርት እንዲያደርጉና በቶሎ ወደ ሥራ ለመግባት እንደሚችሉ፣ ነገር ግን የፋይናንስ ችግር ያለባቸውና በአጭር ጊዜ ሊፈቱ የሚችሉ ችግሮች የገጧሟቸውን ድርጅቶች በማገዝ ወደ ሥራ ለማስገባት ሥራ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡
Source: Ethiopian Reporter