አቶ ሥዩም መስፍንን ጨምሮ ሦስት የሕወሓት ከፍተኛ አመራሮች መደምሰሳቸውን መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ
የመከላከያ ሠራዊት የኃይል ሥምሪት መምርያ ኃላፊ ብርጋዴር ጄኔራል ተስፋዬ አያሌው እንዳስታወቁት፣ አቶ ሥዩም መስፍንን ጨምሮ ሦስት የሕወሓት ከፍተኛ አመራሮችና አንድ የቀድሞ የመከላከያ ሠራዊት አባል እርምጃ ተወስዶባቸዋል፡፡
የመከላከያ ሠራዊቱ ባካሄደው ኦፕሬሽን ተገድለዋል የተባሉት ሦስት የሕወሓት ከፍተኛ አመራሮች አቶ ሥዩም መስፍን፣ አቶ ዓባይ ፀሐዬና አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ ናቸው።
አቶ ሥዩም መስፍን ቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩ፣ እንዲሁም ውጊያውን የመሩና ሠራዊቱ ከቦታ ቦታ እንዳይንቀሳቀስ ያዘዙ፣ በመጨረሻም በሠራዊቱ ላይ ውጊያ እንዲከፈት ትዕዛዝ የሰጡ መሆናቸውን ብርጋዴር ጄኔራል ተስፋዬ ገልጸዋል።
አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ የሕወሓት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር የነበሩ ናቸው። አቶ ዓባይ ፀሐዬ የሕወሓት ከፍተኛ የፖለቲካ አመራር የነበሩ ሲሆን፣ ከሕወሓት አመራሮች ውጪ የመከላከያ ሠራዊቱ አባል የነበሩና ከድተው በትግራይ ውጊያ ከክልሉ ልዩ ኃይል ጋር የተሠለፋ ናቸው የተባሉት ኮሎኔል ኪሮስ ሐጎስ ይገኙበታል።
በሌላ በኩል ወታደራዊና የክልል አመራሮች መሆናቸው የተገለጸ አምስት ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውም ተገልጿል።
እነዚህም ኮሎኔል ገብረ መስቀል ገብረ ኪዳን (ከመከላከያ የከዱ)፣ ኮሎኔል ፍሥሐ ብርሃኔ (ከመከላከያ የከዱ)፣ ኮሎኔል ዘረአ ብሩክ ታደሰ (ከመከላከያ የከዱ)፣ ኮማንደር ገብረ ኪዳን አስገዶም የልዩ ኃይል ክፍለ ጦር አዛዥ የነበሩና አቶ መብራህቶም ክንዴ ኃይሉ (የክልሉ ውኃ ሥራዎች ድርጅት የፋይናንስ ኃላፊ የነበሩ) ናቸው።
ብርጋዴር ጄኔራል ተስፋዬ ባስተላለፉት መልዕክት፣ አሁንም በየዋሻው የተደበቁ በሰላማዊ መንገድ እጅ እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል።
ምንጭ፡ https://www.ethiopianreporter.com/article/21014