0 0
Read Time:10 Minute, 22 Second

ድንቁርና አንድ ጥቅም አለው፤ እንደ ታዬ አንደአ ደፋር ያደርጋል። ታዬ ደንደአ ታሪክ መጻፍ የኦነግ ተዋጊ እንደሆነው በድፍረት የሚገባበት ቀላል ነገር ይመስለዋል። ታሪክ የማሰብና የማስተዋል ችግር የተጫናቸው ሰዎች ተሸክመው ከሚዞሩት የፕሮፓጋንዳ ጉድፍ እያነሱ የሚያራግፉት ጭነት አይደለም። ስለ ታሪክ ለመጻፍና በታሪክ ዙሪያ ስርዓት የተላበሰ አስተያየት ለመስጠት መዘጋጀት ያስፈልጋል። መዘጋጀት ማለት ደግሞ በአብዛኛው ማንበብ ማለት ነው። በርግጥ አንድ ሰው «አነበበ» ማለት ታሪክ አወቀ ማለት አይደለም። አንድ ሰው «አነበበ» ማለት የተደረገውን ነገር ለማወቅ ሁኔታዎችን አመቻቸ ማለት ነው። ስለዚህ በታሪክ በተደረገ አንድ ጉዳይ ዙሪያ ለመፍረድ ለማሰብ ፈቃደኛ ባለመሆን ሲባል የሰሙትን ብቻ መድገም ሳይሆን አቀድሞው አንብቦ መዘጋጀት የግድ ይላል።

የኦነግን የፈጠራ ተረቶች ሲደግሙ መዋል ታሪክ ማወቅ የሚመስለው ታዬ ደንድአ የኤርትራን ፌደረሽን መፍረርስን በቁጥር አንድ ይቃወሙ የነበሩትን ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሊ ሃብተወልድን ድንቁርና በሚሰጠው ድፍረት እየተመራ እንዲህ ሲል ስለሳቸው አለማወቁን በአደባባይ አሳውቋል፤

“ኤርትራዊያን በከፊል ነፃነት ራሳቸዉን ማስተዳደራቸዉ ያልተዋጠለት ‘የጠቅላይ-አግላይ ፅንፈኛ አስተሳሰብ’ አቀንቃኞች ደግሞ ፌዴሬሽኑ ይፈርስ ዘንድ አፄ ኃይለስላሴ አባብሎ አሳምኗል! በ1954 ከኤርትራ ህዝብ ፍላጎት ውጭ ፌዴሬሽኑ ፈርሶ ኤርትራ ክፍለ ሀገር እንዲትሆን ሲወሰን 30 ዓመታትን የፈጀዉ ጦርነት ተጀምሯል! ከከባድ ሰበዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ በኋላ 1984 ላይ የኤርትራ ህዝብ በሪፍሬንደም ከኢትዮጵያ ተለይቷል! ለዚህ የሚጠየቅ አካል ካለ በነአክሊሉ ሀብተወልድ ይመራ የነበረዉ የጠቅላይ አግላይ ፅንፈኛ አስተሳሰብ አራማጅ ፊዉዳላዊ ጁንታ ይሆናል! ለአክሊሉ ሀብተወል ወንጀል ፕሬዝደንት ኢሳያስን መዉቀስ “የአብዬን እከክ ወደ እምዬ ልክክ” ተብሎ ሊጠራ ይችላል!”

በዚህ የታዬ ደንደአ አላዋቂነት የወለደው ድፍረት ከኢሳያስ ጀምሮ እስከ ተራ ተዋጊ የነበሩ የሻዐብያ ሰዎች ራሳቸው ሳይገረሙ የሚቀሩ አይመስለኝም። የፌዴረሽኑን መፍረስ ለኤርትራ “የነጻነት” እንቅስቃሴ መጀመር እንደ ሰበብ የሚቆጥሩ የሻዕብያ ተዋጊዎች ሁሉ አክሊሉ ሃብተወልድን የሚያነሱት ፌዴረሽኑ እንዲፈርስ ይፈልጉ እንዳልነበር እንጂ ፌዴረሽኑን በማፍረስ አይደለም።

ዋና ዋና የጀብሀና የሻዕብያ ተዋጊ የነበሩ ሰዎች የጻፉትን ሁሉ አንብቤያለሁ። የጀብሀ ተዋጊዮች ከነበሩት ሰዎች ብጀምር ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን ከተዋሀደች በኋላ የኤርትራ ዋና አስተዳዳሪ የነበሩት የተድላ ባይሩ ልጅና አሁንም ድረስ በሕይዎት ያለው የጀብሀ መሪ ኅሩይ ተድላ ባይሩ “ERITREA AND ETHIOPIA: A Front Row Look at Issues of Conflict and the Potential for a Peaceful Resolution” በሚል ያዘጋጀውን፤ የጀብሀ ተጋይ የሆነው ፕሮፌሰር ተስፋ ጽዮን መድኃኔ “Eritrea: Dynamics of a National Question” እና “Eritrea and Neighbours in the “New World Order”: Geopolitics, Democracy and Islamic Fundamentalism” በሚል የጻፋቸውን መጽሐፍት አንብቤያለሁ።

የሻዕብያ ታጋዮች ከጻፏቸው ደግሞ ከኢሳያስ በፊት የሻዕብያ መሪ የነበረው ኦስማን ሳለህ ሳቤ “The History of Eritrea” በሚል የደረተውን፤ የኢሳያስ አማካሪ የነበረውና የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የሆነውን “የኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት ቻርተር” ተብዮውን ደንብ ያረቀቀው ፕሮፌሰር በረከት ሀብተ ሥላሴ “The Crown and The Pen, Emperor Haile Selassie”, “Wounded Nation: How a Once Promising Eritrea Was Betrayed and Its Future Compromised”, “The Making of the Eritrean Constitution: The Dialectic of Process and Substance”, እና “Deliverance: A Tale of Colliding Passions and the Muse of Forgiveness, A Historical Novel” በሚል የጻፋቸውን፤ ዶክተር ስዩም ሀረጎት “The Bureaucratic Empire: Serving Emperor Haile Selassie” በሚል ያሰናዳውን፤ ሌላኛው የሻዕብያ ተዋጊ መዝገቡ ገብረ አምላክ “Amde’s Choice: The Route To Freedom” በሚል የጻፈውን፤ አሁንም ድረስ ኤርትራ ውስጥ በሚንስቴርነት ተሹሞ የሚገኘው የደርግ አባልና የሻዕብያ ተዋጊ የነበረው ሻምበል ሚካኤል ገብረ ንጉሥ በቅርቡ “ Downfall of an Emperor: Haile Silassie of Ethiopia and the Derge’s Creeping Coup” በሚል የጻፈውን አንብቤያለሁ።

ቀደም ሲል ከጠቀስኳቸው የጀብሀና የሻዕብያ ውጭ የሆኑት እንደ ፕሮፈሰር ተከስተ ነጋሽ አይነት ምሁራን “Eritrea and Ethiopia: The Federal Experience”፣ “Brothers at war : making sense of the Eritrean-Ethiopian war” ወዘተ በሚል የጻፉትንም አንብቤያለሁ።

እነዚህን ለአብነት ያህል የጠቀስኳቸው የጀብሀ፣ የሻዕብያና በሁለቱም ጎራ የሌሉብት የኤርትራ ተወላጆች ሁሉ ፌዴሬሽኑ መፍረሱን አስመልክቶ ስለ ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሃብተወልድ የጻፉት ነገር ሁሉ ተመሳሳይ ነው። በስም የተጠቀሙት የሻዕብያ የጀብሀ አመራሮች ሁሉ ስለ አክሊሉ ሃብተወልድ የጻፉት የፌዴሬሽኑን መፍረስ ይቃወሙ እንደነበር ነው።

እንግዲህ! ታዬ ደንድአ አክሊሉ ሃብተወልድን “ጁንታ” አድርጎ ፌዴሬሽኑን በማፍረስ የሚከሳቸው ተመዝግቦ የምናገኘው ታሪክ ብቻ ሳይሆን ተዋጉ ሁኖ የተቀላቀለውን ኦነግን ያሰለጠኑትና ያስታጠቁት የጀብሀና ሻዕብያ ሰዎች ሳይቀሩ አክሊሉ ሃብተወልድ የፌዴሬሽኑን መፍረስ ይቃወሙ እንደነበር የጻፉትን ተቃርኖ ነው።

የሆነው ሆኖ እውነት አክሊሉ ሃብተወልድ የኤርትራ ፌዴሬሽን እንዲፈርስ አድርገዋልን? እስቲ ዶሴው ይውጣና ይመርመር!

ስለኤርትራ ፌዴሬሽ መፍረስ ለማወቅ ስንመረምር የምናገኘው ቀዳሚው የታሪክ ምንጭ ፌዴሬሽኑን ያፈረሱትና ከመፍረሱ በፊት ለሰባት ዓመታት ያህል የኤርትራ ፌዴራላዊ አስተዳደር ዋና አስተዳዳሪ የነበሩትን ኤርትራዊውን ቢትወደድ አስፍሐ ወልደ ሚካኤል ነው። ስለፌድሬሽኑ መፍረስና ይህንን ተከትሎ ሲነዛ አለኖረው ፕሮፓጋንዳ አይደለም የብል[ጽ]ግናው ቃለ አቀባይ ታዬ ደንደአ የሻዕብያው አምበል ኢሳያስ አፈወርቂም ራሱ ከቢትወደድ አስፍሐ ወልደ ሚካኤል በላይ ሊያውቅና ምስክር ሊሆን አይችልም።

ስለዚህ ስለኤርትራ ፌዴሬሽን መፍረስና መፍረሱን ተከትሎ ስለሆነው ነገር ፌዴሬሽኑን ካፈረሱትና የኤርትራ ፌዴራላዊ አስተዳደር ዋና አስተዳዳሪ ከነበሩት ከኤርትራዊው ከቢትወደድ አስፍሐ ወልደ ሚካኤል የተሻለ ቀዳሚ የታሪክ ምንጭ ሊኖር አይችልም። ቢትወደድ አስፍሐ የኤርትራ ፌዴሬሽን ሲፈርስ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እና ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሃብተ ወልድ ስለነበራቸው ሚና የቀዳሚ ምንጭ የታሪክ ምስክርነታቸውን የሰጡት በቪዲዮና በጽሑፍ ነው። ቢትወደድ አስፍሐ ወልደ ሚካኤል ስለ ኤርትራ ታሪክና ስለፌዴረሽኑ መፍረስ የዐይን ምስክር ሆነው ያዩትን ታሪክ በተዋበ አማርኛ በመተረክ ከአርባ ሰዓታት በላይ ቪዲዮ ቀድተው ለትውልድ ትተውልን አልፈዋል። ቢትወደድ በቪዲዮ ቀድተው ለትውልድ የተውትን የ45 ሰዓታት የታሪክ ምስክርነት በክምችት ላይበራሪያችን ውስጥ ይገኛል። እንደ አሁኑ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ቢትወደድ አስፍሐ በልዩ ልዩ ጊዳዮች የሰጡትን የታሪክ ምስክርነት ወደፊት ለተከታዮቻችን እየቆነጠርን እናቀርባለን።

ለዛሬ የማቀርበው የቢትወደድ ምስክርነት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ፌዴሬሽኑ እንዲፈርስ አድርገዋል ስለሚባለው የፈጠራ ክስ በድምጽ የሰጡትን ምስክርነትና ታዬ ደንደአ በድንቁርው እየተመካ በአክሊሉ ሃብተወልድ ሃብተ ወልድ ላይ ያቀረበውን የጥላቻ ከስ በሚመለከት በጽሑፍ የምናገኘውን የቢትወደድ አስፍሐ ምስክርነት ነው።

ስለዚህ «ማን ያውራ የነበረ፤ ማን ያርዳ የቀበረ» ነውና ብሂሉ የኤርትራን ፌድሬሽን በማፍረስ ረገድ ተጠያቂው ማን እንደሆነ ባለጉዳዩና የኤርትራ ፌድሬሽን ሲፈርስ የኤርትራ አስተዳደር እንደራሴ ወይንም ገዢ የነበሩት ቢትወደድ አስፍሐ ወልደ ሚካኤል እውነቱን ከታት በታተመው የቪዲዮ ምስክርነታቸው ይነግሩናል። ቢትወደድ አስፍሐ ወልደ ሚካኤል እንደሚነግሩን የኤርትራ ፌድሬሽን ፈርሶ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር እንድትቀላቀል የተወሰነው ሐሙስ ኅዳር 6, 1955 ዓ.ም. ሲሆን ይህም ውሳኔ የኤርትራ ምክር ቤት 62 አባላት፤ ሙስሊም ክርስቲያን በሚል ሳይለያዩ ያለ አንድ ተቃውሞ ባደረጉት ምርጫ መሰረት ነው።

ከታች በታተመው የቢትወደድ አስፍሀ ወልደ ሚካኤል የቪዲዮ ንግግር ላይ እንደሚደመጠው ፌድሬሽኑ እንዲፈርስ ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ጫና ተደርጎባቸው እንደሆነ ተጠይቀው ቢትወደድ ሲመልሱ «ውሸት፣ ሀሰት፣ ሀሰት. . . ፌድሬሽኑ እንዲፈርስ ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ጫና ቢኖር ኖር መጀመሪያ የምሸፍተው እኔ ነበርሁ፤» ሲሉ የኤርትራ ፌድሬሽን የፈረሰው «ከኢትዮጵያ ጋር በአንድነት መሆን በሚያስገኝው የኤርትራ ጥቅም ላይ ብቻ በመመስረት ኤርትራ ከኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ መዋሀዷ ይጠቅማል? ወይንም አይጠቅምም? በሚል ኤርትራውያን ወደው ያደረጉት ነጻ ውሳኔ» እንደሆነ በአንደበታቸው ይናገራሉ።

ቢትወደድ ቀጠል አድርገውም አጼ ኃይለ ሥላሴ የፌድሬሽኑን መፍረስ ፈጽሞ የማይናፍቁት እንደነበሩ በግንባር ቀደምትነት የሚያቁትንና የወቅቱን እውነት ለዛ ባለውን አንደበታቸው ይነግሩናል!

እንግዲህ! በደተጋጋሚ እንዳልነው ዘመኑ የማይዋሽበት ነውና የኤርትራ ፌድሬሽን መፍረሱ የኤርትራውያን የራሳቸው ሙሉና ነጻ ፈቃድ ሆኖ የተፈጸመ እንጂ የግራ ፖለቲከኞች ሲያስተጋቡ እንደኖሩት የኢትዮጵያ ጣልቃ ገብነት ውጤት አለመሆኑን በክምችት ክፍላችን ሙሉ ንግግራቸው የሚገኘው ኢትዮጵያዊ እንደሆኑ እ.ኤ.አ. በ1997 ዓ.ም. በመዲናችን በአዲስ አበባ ከዚህ አለም የተለዩት የቀድሞው የኤርትራ አስተዳደር እንደራሴ ቢትወደድ አስፍሐ ወልደ ሚካኤል ሀቁን ፍንትው አድርገው ይነግሩናል።

ስለዚህ የብል[ጽ]ናው አስኳድ ታዬ ደንደአ የኤርትራን ፌድሬሽን መፍረስ አስለመክቶ የተናገሩትን የተለመደ ውሸት ከዋናው ምስክር ከቢትወደድ አስፍሐ ወልደ ሚካኤል በላይ ለጉዳዩ ቅርበት ያለው እውነተኛ ምስክር ሊኖር አይችልምና ይህን ጽሑፍ የሚያነብ ሁሉ ሲደጋገም የኖረውን የተለመደ ውሸት ከታች የታተመውን የቢትወደድ አስፍሐ ወልደ ሚካኤልን ምስከነት በማዳመጥ እውነቱን ከፈረሱ አፍ ማወቅ አለበት።

ታዬ ደንደአ ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሃብተወልድን በፌዴሬሽኑ አፍራሽነት ስለከሰሰበት ጉዳይ ደግሞ ቢትወደድ አስፍሐ ወልደ ሚካኤል የኤርትራን ፌድሬሽ በሚፈርስበት ወቅት ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ የነበራቸውን ሚና በሚመለከት የሰጡትን ምስክርነት አምባሳደር ዘውሬ ረታ በጻፉት «የኤርትራ ጉዳይ» መጽሐድ ውስጥ እናገኘዋለን።

ቢትወደድ በዚህ ምስክርነታቸው “ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሃብተ ወልድ በፌዴሬሽኑ መፍረስ ጉዳይ ምን አስተያየት ነበራቸው? ተብለው ሲጠየቁ የሚከተለውን መልስ ሰጥተዋል [ይህን የቢትወደድ መልስ ከታት በታተመው “የኤርትራ ጉዳይ” መጽሐፍ ከገጽ 495 – 496 ያለውን ይመለከቷል]”

“ጸሐፌ ትእዛዝ አክሊሉ የኤርትራ ፌዴሬሽን መፍረስ የለበትም ብለው ሲሞግቱ የቆዩ ናቸው። ነገር ግን እኛ አንድነቶች አሸንፈን የሕዝቡን ፍላጎት ስንፈጸም፣ እሳቸው ተቃዋሚነታቸውን በመቀጠላቸው አዝኜባቸው እኖር ነበር። ያዘንኩትም ለኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ መመለስ በዓለም ማኅበር በብርቱ የተዋጉና ብዙ የሚያኮራ ሥራ የፈጸሙ ሲሆኑ፣ በመላው የኤርትራ ሕዝብ እንደራሴዎች ሙሉ ድምጽ ፌዴሬሽኑን ሰርዘን አንድነቱን ስናዋህድ ለዲፕሎማሱ እንኳ ብለው የደስታን ተካፋይ ባለመሆናቸው ነው። ፌዴሬሽኑ በፈረሰበት ዕለት ልዕልቶቹም ጭምር “. . . አስፍሐ እንኳን ድካምህ ፍሬ ሰጠ። እንኳን ሁላችንንም ደስ አለን. . .” የሚል የደስታ መግለጫ ሲያጎርፉልኝ ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አንዲት ቃል አልደረሰኝም። በዚህ ወቅት ቅር ብሎኝ ለዤኔራል ዐቢይ ሳጫውታቸው የሰጡኝን አስተያየት ምን ጊዜም አልረሳውም። “. . . ቢትወደድ! አሉኝ. . . አባክዎ ጸሐፌ ትእዛዝን አይቀየሟቸው። እኔ ባለፈው አነጋግሬያቸዋለሁ። እሳቸው የፌዴሬሽኑ መፍረስ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ብዙ ጣጣ ያስከትላል። የውጭ ጠላት ያጠቃናል ብለው ያምናሉ። እርስዎና እኔ ደግሞ የኢትዮጵያ አንድነት ሲጠነክር በውስጣችን ሠላም ለመመስረት፣ ከውጭ የሚመጣብንን ጠላት ለመመከት ያስችለናል እንላለን። በጸሐፌ ትዕዛዝና በእኛ መካከል ያለው ልዩነት መጨረሻው እውነቱ የማን እንደሆነ ጊዜና ታሪክ ወደፊት ይገልጠዋል። አሁን ሁላችንም በየዕምነታችን መቆም ነው እንጂ ቅያሜ አያስፈልግም.. . .” አሉኝ። የዤኔራል ዐቢይ አስተያየት በጣም ነካኝ። የፍርድ ሚኒስትር ተብዬ ከሁለት ወር በኋላ አዲስ አበባ ስሄድ፣ በልቤ ይዤው የነበረውን ቅሬታዬን ለጸሐፌ ትእዛዝ አክሊሉ አልገለጥኩላቸውም። በተገናኘን ጊዜ ሰላምታ ከመለዋወጥ በስተቀር ስለ ፌዴሬሽኑ አፈራረስ፣ አሁን ስለአለው ሁኔታ፣ ወደፊትም ምን እንደሚሻል አሳቸውም ሳይጠይቁኝ እኔም ሳልናገር እንደዚሁ ቀረ።”

ከዚህ በተጨማሪ ቢትወደድ አስፍሐ ወልደ ሚካኤል ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሃብተወልድ የፌዴሬሽኑን መፍረስ መቃወም ብቻ ሳይሆን ከመፍረሱ በፊት አንዳንድ ሕግ እንዲሻሻል እንኳን ሲጠይቁ ምክንያት እየፈጠሩ ሲያግዱ እንደኖሩ ጭምርም ይወቅሷቿዋል። ይህንን የቢትወደድ አስፍሐ ወልደ ሚካኤል ምስክርነት መንበብ የሚሻ ከታች የለጠፍሁትን “የኤርትራ ጉዳይ” መጽሐፍ ገጽ 476 ይመልከት!

እንግዲህ! የፌዴሬሽኑን መፍረስ ብቻ ሳይሆን የፌሬሽኑ ሕግ እንዳይሻሻል ይቃወሙ የነበሩትን ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሃብተወልድን ነው የብል[ጽ]ግናው ታዬ ደንደአ በተካነበት ኦነጋዊ የፈጠራ ክስ የማምረት ድፍረት እየተመራ የፌዴሬሽኑን መፍረስ ይቃወሙት የነበሩትን ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉን በፌዴራሲዮኑ አፍራሽነት እየከሰሰ ጁንታ ሊያደርጋቸው የሚቃጣው። በእውነቱ ጁንታው በአለም መድረክ ተሟግተው፤ የምስራቁንም የምዕራቡንም ካምፕ በልዩ ብቃታቸው በማሸነፍ ኤርትራን ወደ እናት አገሯ ኢትዮጵያ የመለሱትና አለምን ያስደመመ አስደናቂ የአርበኛነት ተጋድሎ ያደረጉት ታላቁ የኢትዮጵያ አገልጋይ ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሃብተወልድ ሳይሆኑ ስልጣንን በኃይልን ለመቆጣጠርና አገር ለመገንጠል የተቋቋመውን ኦነግ የሚባለውን አሸባሪ ድርጅት በአባልነት የተቀላቀለውና ተዋጊው የነበረው ታዬ ደንደአ ራሱ ነው።

እዚህ ላይ አንባቢ የኤርትራ ተገንጣዮች “የነጻነት” እንቅስቃሴ የጀመሩት ፌድሬሽኑ በመፍረሱ እንዳልሆነ ሲነገር የኖረውንም ተረት እንደገና ማጤን አለበት። ጀብሀ የተመሰረተው ፌዴሬሽኑ ከመፍረሱ ከአመታት በፊት ነው። በሌላ አነጋገር የጀብሀ ወይም ኤርትራ ነጻ አውጭ ግንባር [ELF] ተገንጣዮች ኤርትራን «ነጻ ለማውጣት» በረሀ የወረዱት ኤርትራ በፌድሬሽን ትተዳደር በነበረበት ወቅትና የኤርትራ ፌድሬሽን ከመፍረሱ ከአመታት በፊት ነው። ከጀብሀ መመስረት በፊት የኤርትራ ነጻነት ንቅናቄ [Eritrean Liberation Movement] የሚል ተገንጣይ ድርጅት ኤርትራን ለመገንጠል ሱዳን ውስጥ ተቋቁሞ ነበር። ልብ በሉ የኤርትራ ነጻነት ንቅናቄ [Eritrean Liberation Movement] በሚል ራሱን ይጠራ የነበረው ተገንጣይ ድርጅት የተቋቋመው የኤርትራ ፌዴሬሽን ከመፍረሱ በፊት ከተቋቋመው ከጀብሀ አስቀድሞ በፌዴሬሽን ትተዳደርበት በነበረበት ወቅት ነው። እውነቱ ይህን ከሆነ ከነዚህ ድርጅቶች መመስረት ከአመታት በኋላ የፈረሰው የኤርትራ ፌዴሬሽን በኤርትራ የነጻነት እንቅስቃሴ እንዲጀመር ምክንያት የሚሆነው በነ ታዬ ደንደአ አስተሳሰብ ብቻ ነው።

እንዴውም ቢትወደድ አስፍሐ እንደሚሉት የኤርትራ እንደራሴዎች ምክርት ቤት ፌዴሬሽኑን ለማፍረስ ሙሉ በሙሉ ከወሰነባቸው ምክንያቶች አንዱ በአረብ አገራት እየተደለሉ ጫካ የገቡት እነ ጀብሀና የኤርትራ ነጻነት ንቅናቄ [Eritrean Liberation Movement] ፌዴሬሽኑን ተጠቅመው ኤርትራን በመገንጠል አረባዊት የሆነች አገር ለመፍጠር በመነሳታቸው ነበር። [ዝርዝር ታሪኩ ከታች ከታተመው “የኤርትራ ጉዳይ” መጽሐፍ ገጾች መካከል ከገጽ 492- 494 ያለው ታሪክ ያነቧል]

ከፍ ብዬ ጀብሀ የተመሰረተው ፌዴሬሽኑ ከመስፈሩ በፊት ነው ብያለሁ። ሻዕብያ የወጣው ከጀብሀ ነው። ከጀብሀ በፊት የተቋቋመው የኤርትራ ነጻነት ንቅናቄ [Eritrean Liberation Movement] የሚባለ ድርጅት በ1962 ዓ.ም. ከጀብሀ ጋር ስለተዋሀደ በኤርትራ ተገንጣይነታቸው የሚታወቁት ጀብሀና ሻዕብያ ናቸው። ይህ ማለት ከኤርትራ ፌዴሬሽን መፍረስ በኋላ የተፈጠረ አዲስ የኤርትራ ተገንጣይ ድርጅት የለም ማለት ነው። ይህ ማለት ለኤርትራ ፌዴሬሽኑ መፍረስ ምክንያቱ በአረብ አገራት የሚደገፉት ተገንጣዮች መፈጠር እንጂ ከፌዴሬሽኑ መፍረስ በኋላ የተፈጠረ አዲስ የኤርትራ ተገንጣይ ድርጅት ስለሌለ የፌዴሬሽኑ መፍረስ ለተገጣይ ድርጅት መፈጠር መንስኤ ሊሆን አይችልም ማለት ነው።

ከዚህ በተጨማሪ የፌዴሬሽኑ መፍረስ የኤርትራውያንን ንቅናቄ ቀስቅሶት እንደሆነ በሚል ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የሻዕብያ መሪ ለነበረው ለኦስማን ሳለህ ሳቤ እ.ኤ.አ. በ1972 ዓ.ም. “የምትዋጉት ፌዴራሲዮኑ ፈረሰ ብላችሁ ከሆነ ፌዴሬሽኑ ይመለስላችሁና በሰላም ግቡ” የሚል መልዕክት ልከውበት ነበር። ይህንን የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን መልዕክት በወቅቱ የመን ለነበረው ለሻዕብያው መሪ ለኦስማን ሳለህ ሳቤ ያደረሱት በወቅቱ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ ተጠሪ አምባሰደር የነበሩትና አሁንም ድረስ በሕይዎት የሚገኙት የኤርትራ ተወላጁ አምባሳደር ዮሐንስ ጽጌ ናቸው። ኦስማን ሳለህ ሳቤ ግን ንጉሠ ነገሥቱ ያቀረቡለትን ጥሪ ሳይቀበለው ቀረ። ይህን ታሪክ የሚነግሩን ለሰባት ወራት የደርግ አባል የነበሩትና ከዚያ በኋላ ደርግ ከድተው ሻዕብያን የተቀላቀሉት፤ ባሁኑ ወቅት አስመራ ውስጥ የኢሳያስ ባለሥልጣን የሆኑት ሻምበል ሚካኤል ገብረ ንጉሥ ኃይሌ ከሁለት ዓመታት በፊት “Downfall of an Emperor: Haile Silassie of Ethiopia and the Derge’s Creeping Coup” በሚል ባሳተሙት መጽሐፍ ገጽ 284 ላይ ነው። ኦስማን ሳለህ ሳቤ “የምትዋጉት ፌዴራሲዮኑ ፈረሰ ብላችሁ ከሆነ ፌዴሬሽኑ ይመለስላችሁና በሰላም ግቡ” የሚለውን የንጉሡን ጥሪ አለመቀበሉ የሚያሳየው ሻዕብያም ሆነ ኦስማን ሳለህ ሳቤ ትግል የጀመሩት አገር ለመመስረት እንጂ ፌዴሬሽኑ ፈረሰብን ብለው ስላልነበረ ነው። በመሆኑም ኤርትራን «ነጻ የማውጣቱ» እንቅስቃሴ መጀመር ከኤርትራ ፌድሬሽን መፍረስ ጋር የሚያገናኘው አንዳች ነገር እንደሌለው ነው።

እንዴውም የፌዴሬሽኑ መፍረስ ለኤርትራውያን በፌዴሬሽኑ ሕገ መንግሥት ያልነበራቸውን መብት አጎናጽፏቸዋል። የተባበሩት መንግሥታት ደርጅት ኤርትራን ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን ሲያስተሳስር ለኤርትራ የሰጠው ሕገ መንግሥት ግማሽ የኅብረተሰብ ክፍል የሆኑትን የኤርትራ ሴቶችን ሙሉ በሙሉ ከፖለቲካና አስተዳደር ሕይዎት ያገለለ ነበር። በፌዴሬሽኑ ሕገ መንግሥት መሰረት አንድ ሰው በኤርትራ አስተዳደር ለምርጫ የሚወዳደረው ወንድ ከሆነ ብቻ ነው። ይህንን የሚጠራጠር ቢኖር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኤርትራን በፌዴሬሽን ከኢትዮጵያ ጋር ካስተሳሰረ በኋላ ለኤርትራ ፌዴራል አስተዳደር የሰጠውን ሕገ መንግሥት አንቀጽ 20 ይመልከት። በመሆኑም የኤርትራ ሴቶች በምርጫ መወዳደርና በፖለቲካ ውስጥ ተሳትፎ ማድረግ የጀመሩት ፌዴሬሽኑ ፈርሶ ኤርትራ በንጉሠ ነገሥቱ ዘውዳዊ ሕገ መንግሥት ስር መተዳደር ስትጀምር ነው።

ታሪኩ ሲገለጽ፣ ዶሴው ሲወጣ የምናገኘው እውነት ከላይ የቀረበውን ይመስላል።

በተረፈ ሳይመረምሩ፣ ያሳጣሩና ሳያረጋግጡ ሀሳብ የሌለበት የፈጠራ ወሬ ለሚደግሙ ኦነጋውያን «ወሬ ሲነግሩህ ሀሳብ ጨምርበት» የሚለውን የአያቶቻችን ጥልቅ ምክር በመለገስ ልሰናበት!


ከታች የታተሙት፤

1ኛ. ቢትወደድ አስፍሐ ወልደ ሚካኤል የኤርትራን ፌዴሬሽ የፈረሰው በኤትራውያን ፍላጎት ብቻ እንደሆነ፤ ፌዴራሲዮኑ እንዲፈርስ በንጉሡ ቢገደዱ ኖሮ ከሁሉ በፊት ጫካ የሚገቡት እሳቸው እንደሆኑ የተናጋሩበትና ንጉሠ ነገሥቱ ፌዴሬሽኑ እንዲፈርስ የማይፈልጉ እንደነበሩ የሰጡት የቪዲዮ ምስክርነት እና

  1. ቢትወደድ አስፍሐ ወልደ ሚካኤል ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሃብተወልድ የኤርትራን ፌዴሬሽን መፍረስ ይቃወሙ እንደነበር፤ በዚህም ተቀይመዋቸው እንደሚኖሩ የሰጡትን የጽሑፍ ምስክርነት የሚያሳዩ ከአምባሳደር ዘውዴ ረታ የኤርትራ ጉዳይ መጽሐፍ የተወሰዱ ገጾች ናቸው።
Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *