#ቅዱስ ሲኖዶስም ሆነ መንግሥት ከማጋነን ይልቅ ማመዛዘን ይጠበቅበታል፤

0
0 0
Read Time:8 Minute, 28 Second

===»የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቃለ ምልልስ፤«===

#ቅዱስ ሲኖዶስም ሆነ መንግሥት ከማጋነን ይልቅ ማመዛዘን ይጠበቅበታል፤

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የተቃሟቸው መጠን ቢለያይም፤ ደርግንም ሆነ በጊዜው የነበሩትን ኤጴስ ቆጶስ አድርገው የሾሟቸውን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ፓትርያርክን ሳይቀር ተቃውመዋል፤ በሕወሀት ጊዜም አቡነ ጳውሎስን ከሚቃውሙ አባቶች መካከል አንዱ ነበሩ፤ አቡነ ማትያስ የተወለዱት ትግራይ ተንቤን ውስጥ ነው፤ ጊዜው መሽቶባቸው አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ሕልፈተ ሕይዎት በኋላ በሕወሀት ግፊት የተተኩ ስድስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ናቸው።

ትግራይ የትውልድ ሀገራቸው ይሁን እንጅ ያደጉት ጎንደር ነው። ማደግ ብቻ ሳይሆን መታወቂያቸው ላይ የትውልድ ቦታ ጎንደር ይል እንደ ነበር በቅርብ የሚውቋቸው አብሮ አደጎቻቸው ይመሠክራሉ፤ አቡነ ማትያስ ጎንደር ለማደጋቸው የማይለወጠው የአማርኛ አነጋገር ዘይቢያቸው እና ለዛቸው ግልጽ ምስከር ነው። ከአራተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ጋር ከጎንደር ጀምሮ እጅግ በጣም የወንድማማችነት ቀረቤታ ያለው የሕይዎት ገጠመኝ አላቸው።

ወደ አዲስ አበባ ከመጡ ጀምሮም ሁለቱም በአቡነ መልከጼዲቅ ቀዳማዊ ሊቀ ጳጳስ ተቀጥረው የመንበረ ጸባዖት ቅድሥት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በአንድ መንበር እየቀደሱ ፤ በአንድ ማዕድ እየቆረሱ ብዙ ጊዜያትን በወንድማማችነት አሳልፈዋል። በኋላም አቡነ መርቆሬዎስ የደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል አለቃ ሲሆኑ፤ አቡነ ማትያስ ደግሞ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት አቡነ ቀሲስ (የፓሮቶኮል ሹም) ሆነው አገልግለዋል።

ሁለቱም በአንድ ቀን በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንብሮተ ዕድ ኤጴስ ቆጶስነተ ተሹመዋል፤ አሁንም በእግዚአብሔር ፈቃድ ሁለቱም በአንድ የመንበረ ማርቆስን መንበር ተጋርተው የአንድ ዘመን የሐዋርያዊት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ፓትርያርካት ሆነው ይገኛሉ።

በሰው ዘንድ ብዙ ትርጉም ሊሰጠው የሚችል መሆኑ ቢታዎቅም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ይህ ይሆን ዘንድ ግድ ሆነ። የዐማራ እና የትግራይ ኅብረተሰብ ይህ የሆነበትን ምክንያት ሰዋውዊ ትርጉም ከመስጠት ይልቅ፤ መንፈሳዊ አስተምህሮቱን ተመልክቶ ይህን የዕርቅ መሠረት በማድረግ ያለፈውን ትቶ፤ የቀማ መልሶ የበደለ ክሶ ወደፊት ቅድመ ሕወሀት እንደነበረው ወንድማማች ሕዝብ ሆኖ እንዲቀጥል ማድረግ ይቻል ነበር። ግን በጥባጭ ሳለ ማን ጥሩ ይጠጣል ነውና ሕወሀት እያለ ዕርቅን ማሰብ ከንቱ ድካምና ምኞት ሆኖ ቀረ።

ሕወሀትን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከታገለው ይልቅ፤ ብዙ እራሱን የመሻሻያ ወርቃማ ጊዚያቶችን በከንቱ በማሳለፍ እራሱ በእራሱ ላይ የሚሠራው ስሕተት ይበልጥ ገዝፎ ጠልፎ እንደጣለውና ሥልጣኑን ባሳደጋቸው ግብረ በላዎቹ እንደተነጠቀ ግልጽ ነው።
ሕወሀት ሥልጣኑን ከተነጠቀ በኋላ ተተኪው ክፍል ከሕዝብ ጋር ለመገናኘት የተጠቀመበት አንዱና ዋናው ስልት በሕወሀት ምክንያት በሁለት ጎራ ወግኖ የነበረውን ቅዱስ ሲኖዶስ ወደ አንድነት መመለስ ነበር፤ ለዚህ ተግባር መሳካት የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀናነትና የመንፈስ ቅዱስ ወንደማቸውን አቡነ መርቆሬዎስን ያለምንም ቅሬታ በፓትርያርክነት ማዕረግ አክብሮ መቀበል ቅዱስ መንበሩን በማጋራት በወቅቱ እንደጉም ታይቶ ለጠፋው የኢትዮጵያ የሠላም ብልጭታና የለውጥ ገጽታ ትልቅ አስተውጽዖ ነበረው።

ሕወሀት የመሪነት መንበረ መንግሥቱን በእራሱ ድክመት ከማስረከቡም በላይ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የነበረውን የመንግሥት ሥልጣን ተጋሪነት ማለትም፤ የጠቅላይ ምንስትር አማካሪነት፣ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ፤ የኢንዱስትሪ ምንስትርነት፣ በልዩ ልዩ የመንግሥት ተቋማት የነበረውን ከፍተኛ ሥልጣን እና በውጭ ሀገራት የነበረውን የዲፕሎማቲክ ውክልና ድርሻ ሁሉ እርግፍ አድርጎ የበሬ ግንባር ከምታከለው ትግራይ ሄዶ ከተመ። ህወሀት የመጀመሪያው ስህተት ሳያንሰው አሁንም ሕጻን ልጅ ሊሳሳተው የማይችል ትልቅ ስህተትን በእራሱ ላይ ሠራ።
በዚህ ወቅት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስን ጠርቶ “እኛ እራሳችን ችለን ነጻ የትግራይ መንግሥት መሥርተናል፤ ዐቢይ አህመድን አውግዘው አክሱም ጽዮንን መንበረዎት አድርገው ይቀመጡ” በማለት ተሳስቶ ለማሳሳት በከፍተኛ ደረጃ ያስቸግራቸው ነበር።
ነገር ግን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ይህን ሰይጣናዊ ምክር ሳይቀበሉ በሰውና በእግዚአብሔር ፊት በመሐላ በአደራ የተቀበሉትን የኢትዮጵያዊ ኦርቶዶክሳዊ ተዋሕዶ ፓትርያርክነት አጽንተው ቆይተዋል። ይህም ፓትርያርኩ ሕወሀትን ያለመደገፋቸው ከአንድ አባት የሚጠበቅ መንፈሳዊ ጥንካሬ ሲሆን በሌላ አቅጣጫ ቅዱስነታቸው የሕወሀትን ምክር ሰምተው መንበራቸውን ለቀው ከሕወሀት ጋር ትግራይ ቢከትሙ ኖሮ በዚህ አረጋዊ የአባትነት ገጽታቸው ላይ አሁን ሊገጥማቸው የሚቸለው ከባድ ችግር መገመት አያዳግትም።

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በቅርብ እንደ ተረዳናቸው ቅንነት ያልተለየው መንፈሳዊ የክህነት አባት እንጅ፤ ልክ እንደ አቡነ ጳውሎስ ነገር የሚሰነጥቁ፣ አሽሙር የሚያንጸባርቁ፣ ኃይለ-ቃል የሚያጠራቅሙ ንግግር የሚያራዝሙ፤ በአብለጭላጭ እጅ መንሻና ስጦታ የሚታለሉ የመድረክ ሰው አይደሉም። አነጋገራቸው ከእድገታቸው ጋር የተዋሐደ ግልጽነት ያለው ቀጥተኛና የተመጠነ ነው። ከሸፍጥና ከተንኮል የፀዱ አባት ናቸው። ለቤተ ክርስቲያን ያላቸው ተቆርቋሪነት የላቀ መሆኑ ግልጽ ነው።

የቤተ ክርስቲያን ተቆርቋሪነት ባይኖራቸው ኖሮ፤ የሕወሀት ካድሬ ሆኖ በቤተ ክርስቲያንን ተጠግቶ የቤተ ክርስቲያን መዋዕለ ንዋይ ከሚዘርፈው እራሱን “ማኅበረ ቅዱሳን” ብሎ ከሚጠራው ኢመደበኛ ተቋም ጋር በግንባር አይጋፈጡም ነበር። “ማኅበረ ቅዱሳን የሚባለው ተቋም የተረገመ ነው፤ እንደ ረገምኩት እሞታላሁ” ያሉበት ምክንያት የቤተ ክርስቲያንን ገንዘብ እንደዘረፈ በተጨባጭ ሁኔታ ስለተረዱ ነው።

ቅዱስነታቸው የሕወሀት ደጋፊ ቢሆኑ ኖሮ ማኅበሩን መንግሥትን ተጠግቶ የቤተ ክርስቲያን ቀኝ ገዥ ነው እያሉ መቃወም አልነበረባቸውም ነበር። ዛሬም ማኅበሩ በየመንገዱ የሚታረደው የክርስቲያኖች ሕይዎት ሳያሳስበው መልኩን እንደ እስስት ለውጦ ቤተ ክርስቲያን ገንዘብ ዘረፋ እስከ መንግሥት ፓለቲካ አቀንቃኝነት “ርቱዓዊ ሐ” በሚል ቁንጽል ሐሳብ በቤተ ክርስቲያን ስም የሚጫዎተውን የፓለቲካ ቁማር ምን እንደሚመስል መረዳት ቀላል ስሌት ነው።

ጠቅላይ ምንስትር ዐቢይ በመንበረ መንግሥት ሥልጣን ላይ እየዋሉ እያደሩ ሲመጡ፤ ከሕዝብ የተጠበቀው ለውጥ በተፈለገው መንግድ አልመሩትም፤ ሕዝብ የተመኘው ሰላም በተነገረለት ተስፋ አልሠመረም፤ በየቀኑ የሚወራላት ኢትዮጵያ ለአፈር ገፊ፤ ለፍቶ አዳሪ እና ግብር ከፋይ ሕዝቦቿ ጋሃነብ እንጅ ገነት አልሆነችም፤ በሚያሳዝን ሁኔታ መራር እና አስከፊ ሞት እና ልቅሶ፤ መፈናቀልና መሳሰድ፤ የአቢያተ ክርስቲያናት መቃጠል የዕለት ተዕለት ዜና ነው።
ይህ ሁሉ ባልሰከነ አመራር ምክንያት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚደርሰው አሳዛኝ መከራ ሁሉ በቅዱስነታቸው ዘመነ ፕትርክና መፈጸሙ ከታሪክ ተወቃሽ ነጻ እንደ ማያደርጋቸው በአንጻሩም የሚሰጡት መግለጫና የሚያቀርቡት ምክረ ሐሳብና ጥያቄ ተሰሚነት በማጣቱ ምክንያት ችግሩ እያሳስባቸውና ግራ በመጋባታቸው የሕሊና ወቀሳ እንደ ደረሰባቸው ጭምር በአጽንዖት መገንዘብ ያስፈልጋል።

እርግጥ ነው፤ ሕወሀት በራሱ ድክመት በእራሱ ፈቃድ ያጣውን ሥልጣን በሁከት ለማደፍረስ የቀጥታም ሆነ የተዘዋዋሪ የግድያውና የማፈናቀሉ ችግር አካልና ተሳታፊ ቢሆንም፤ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት መሠረታዊ የአመራር ድክመት፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እና በተከታዮች ላይ ያነጣጠረ ሸፍጠኝነት ጎልቶ እንደሚታይበት መካድ አይቻልም። ቅዱስ ፓትርያርኩ በሚደርሱት ጥፋቶች ሁሉ የተሰማቸውን ሐዘን ከልቅሶ ጋር በታገዘ ቅሬታ በተደጋጋሚ መግለጫዎችን ሲሰጡ ቆይተዋል። ይህን ለመናገር አይኔን ግንባር ያርገው ብሎ መካድ አይቻልም።

ከዛም አልፎ ከጠቅላይ ምንስትር ዐቢይ ጋርም እንዴት መንግሥት ባለበት ሀገር በየቀኑ የሰው ልጅ ሕይዎት መጥፋት የንብረት ውድመት የአቢያተ ክርስቲያናት ቃጠሎ ይደርሳል በማለት ኃይለ ቃል እስከ መናገር ደርሰው እንደ ነበር፤ ፓትርያርኩ በመንግሥት በኩል ያላቸው ተስፋ ተሟጦ፤ ለሕዝበ ክርስቲያኑም “እኔ በፓትርያርክነት የተቀመጥኩት እናንተን ለመጠበቅ ነበር ነገር ግን ላድናችሁ አልቻልኩም አቅም አጣሁ” በማለት ልቅሷቸውን ለፈጣሪ አሰምተው፤ ከጠቅላይ ምንስትሩ ጋር ንግግር ያቆሙት ገና ሕወሀት ጦርነት ከማወጁ አስቀድሞ መሆኑ ተጨባጭ መረጃዎች አሉን።

ጠቅላይ ምንስትሩም ይህን ለመበቀል ይመስላል፤ በአንድ መንበር ያሉትን አባቶች ሁለቱንም መጋበዝ በሰከነ ሁኔታ በጋራ ለጋራ መመካከር ሲገባቸው፤ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን ብቻ ለይቶ ወደ ጠቅላይ ምንስትር ቢሮ መጋበዛቸውና ዜናውን ማሰራጨታቸው ጤነኛ ምክር የጎደለው ተግባር ከመሆኑም በተጨማሪ፤ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ጋር ቅራኔ ያላቸው መሆኑን አጉልቶ ከሚያሳይ በስተቀር ሌላ ትርጉም መስጠት አይቻልም ነበር።

በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ላይ መንግሥት ቅራኔው እያጠነከረ የመጣው በሱማሌና በሐረር አካባቢ በአንድ ቀን ከአሥር በላይ አቢያተ ከርስቲያናት በመቃጠላቸው ምክንያት፤ በተለይም በአዲስ አበባ የሚገኘው ሕዝበ ክርስቲያን በከፍተኛ ደረጃ በቁጣ በመነሳሳቱና ለሰላማዊ ሰልፍ መዘጋጀቱን ተከትሎ፤ ቅዱስ ፓትርያርኩ በመንግሥት በኩል ሰላማዊ ሰልፉን የሚያስቆም መግለጫ እንዲስጡ ሲጠየቁ፤ በፍጹም የምዕመናኑን ለቤተ ክርስቲያን ያለውን የባለቤትነት ድርሻ እና ለመንፈሳዊ እምነቱ ያለውን የተቆርቋሪነት ስሜት መግታት አልችልም በማለታቸው በመንግሥት በኩል ጥርስ የተነከሰባቸው መሆኑን መዘንጋት የለብንም።

የሕወሀት ከመሻሻል ይልቅ ግትርነት፤ ከትልቅነት ይልቅ ትንሽነትን፤ ከአንድነት ይልቅ ከፋፋይነትን፣ ከቅርብ ጎረቤቱ ይልቅ የሩቅ አሽከሩን በጠቅላላው ስልትና ምክር የጎደለው አናርኪነት ሂደቱ እራሱ ባሳደጋቸው ግብረ በላዎች የመንበረ መንግሥት ስልጣኑን ከመነጠቁም በላይ፤ የነበረውን የመንግሥት ተቋም ተጋሪነት በፈቃዱ ለቆ በሁሉም አቅጣጫ ጦርነትን ተመራጭ ማድረጉ፤ ጠላትነቱ ከሁሉም በላይ ያደረሰው ጉዳት በትግራይ ሕዝብ ላይ የከፋ መሆኑን እርግጥ ነው። በጥሬ ገንዘብ ብቻ ከሃምሳ ቢሎዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ሲያጠራቅም፤ በትግራይ ክልል ግን ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በጣሳ እየተሠፈረ በሚሰጠው የስንዴ ርዳታ ይኖር ነበር።
ሕወሀት ለትግራይ ሕዝብ ጠላት አበዛበት እንጅ የጠቀመው ነገር የለውም። ከዚህም አልፎ ያወጀው ጦርነት በቀዳሚነት የትግራይን ሕዝብ የጦርነቱ ገፈት ቀማሽ በማድረግ ሕይዎቱ እንዲጠፋ ንብረቱ እንዲባዝን አደረገው እንጅ ያገኘው ተስፋ የለውም። የትግራይ ሕዝብ አሁን በሕወሀት ምክንያት የደረሰበት በደል ከንግዲህ ሃምሳ ዓመት አይተካውም። ይህ እንኳን ለተወለደ ላልተወለደበትም ቢሆን ሐዘን ቢሆንም፤ በቀዳሚነት ተወቃሹ የሚሆነው እራሱ ሕወሀት መሆኑን መዘንጋት ባይኖርብንም ተረኛው መንግሥትም ያለው የአመራር አቅም ደካማነት የውሳኔ ሰጭነት ብቃት ማነስ ለችግሩ መባባስ ምክንያት መሆኑን መመስከር ግዴታ ነው።

በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ይህን ጦርነት ለማካካስም ሆነ የዓለም ኅብረተሰብን የተኩረት አቅጣጫ ለማስለወጥ በተመሳሳይ ሁኔታ በኦሮሚያ ክልል መንግሥት አስፈጻሚነት፤ በዐማራው ኅብረተሰብም ከቤተ መንግሥቱ ግንባር ከቡራዩ እስከ ወለጋ፤ ከሱሉልታ እስከ መተከል፤ ከሻሸ መኔ እስከ ከሚሴ፣ ከላፍቶ እስከ ሰሜን ሸዋ ደራ፣ አጣየ፣ ሸዋ ሮቢት፤ ድረስ በሰላማዊ ኗሪ ሕዝብ የደረሰው ግፍ በትግራይ ውስጥ ከደረሰው ጥፋት ጋር ተመሳሳይ ሚዛን ልንሰጠው ይገባል።

ህወሀት እራሱ በፈጠረው የጦርነት ዐውድ በትግራይ ሕዝብ መጎዳት በሰሜን ኤርትራን በደቡብ በሥልጣን ላይ ያለውን ተረኛ መንግሥትን አልፎም መከረኛውን ዐማራን እንደሚከስ ሁሉ፤ የዐማራ ሕዝብም በሰሜን የትግራይ ሚሊሻ በማይካድራ፤ በደቡብ የኦሮሞ ጠባብ ጽንፈኞች እና ሴረኛ የመንግሥት አካላት በመተባበር ባቀናው መሬቱ ላይ ገድለውታል ንብረቱን አቃጥለዋል፣ ዘርፈውታል አፈናቅለውታል።

በመሆኑም ቅዱስ ፓትርያርኩ እንደ ኢትዮጵያ ሕዝብ እና ኢትዮጵያዊ አባትነት የሁሉንም መገፋት ከመንግሥት አስተዳደር አመራር ድክመት አንጻር መተቸት፣ መውቀስ አልፎም ማውገዝ ሲቻል፤ በኦርሚያ ክልል የዐማራ እርጉዝ ሴት ከእነ ሕይዎቷ ሆዷ ተቀዶ የሞተ ጽንስ እንድትታቀፍ ስትገደድ፤ የትግራይ ወጣት ከሞተ በኋላ ገደል ውስጥ ሲጣል ልዩነቱን በአብላጫ ግንዛቤ መስጠት ትክክል አለመሆኑን መግለጽ ግዴታ ነው። የአንዱን ሞት ቀላል ፤ የአንዱን ሞት ከባድ የማድረግ የሞት ምርጫ ስሌት ቅዱስነታቸው በምን መንፈሳዊ መድሎት (ሚዛን) ለክተው ለማበላለጥ የተገደዱበት ሁኔታ ግልጽ አይደለም። የሞት ትንሽ ትልቅ የለውም፤ ሞት መራር ነውና ሁሉም እኩል መዝኖ እኩል ማዘን ይጠበቅ ነበር።

በመሠረቱ ጦርነት ቀላል አይደለም። ጦርነት የሕይዎትም የንብረትም ዋጋ ያስከፍላል። ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በቅርብ ያሉት አስተናጋጆቻቸው የቅርብ ዘመዶቻቸው እንደመሆናቸው መጠን፤ በየጊዜው የሚደርሳቸው ዜና ከአንድ አቅጣጫ ብቻ የጎላና የተጋነነ ይሆናል ተብሎ ይገመታል። በእርግጥም የተወለዱበት አካባቢ ቆላ ተንቤን ሕወሀት የመሸገበት በመሆኑ፤ ብዙ ጥቃት ደርሶ ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም፤ ጥቃቱ ሥጋ ዘመዶቻቸውንም ጭምር ሊያጠቃልል ይችላል። ምንም እንኳን መንፈሳዊ አባት ፓትርያርክ ቢሆኑም፤ ከሰው የተፈጠሩ ሰው መሆናቸውን ሳንዘነጋ፤ መወለድ ከልጓም የሚስብ ጠንካራ ኃይል ያለው መሆኑን መረዳት ግድ ይለናል።

ነገር ግን ፓትርያርክ (የብዙኃን አባት) ናቸውና ሁሉንም በእኩል ዓይን መመዘን እንደሚጠበቅ ቅድሚያ የሚሰጠው ቃል ኪዳን የተገባበት መንፈሳዊ ሥልጣንና አቋም መሆኑን ካለመዘንጋት ጋር በተጓዳኝ የቅዱስነታቸው ቀጥተኛ የአነጋገር ባህሪ፤ ሸፈጣዊነትና ሐኬተኝነት የተለየው የንግግር ስልተኛ መሆኑን ከግልጽነት ጋር ማነጻጸር ወይም ግምት ውስጥ ማስገባት ይገባል፤ ከግራም ከቀኝም የሚደርስባቸው ወከባ ጭምር ቅንነት ያልተለየው አስተያየት ጋር አቅንቶና አስፍቶ ማገናዝብ እና መመልከት እንጅ፤ ጉዳዩን ከወገንተኝነት አልፎም ከሕወሀት ደጋፊነት ጋር አጉልቶ በማየት አረጋዊዮን አባት፣ ማጨናነቅ፣ ማዋከብ፣ ማሳቀቅ ጠቀሜታ የለውም።

ቅዱስ ሲኖዶስ ይህን ጉዳይ ዳግም ስህተት ላለመሥራት እና በሐዘን ጥላ ሥር ለምትገኘው ቤተ ክርስቲያን ላይ እንደዚሁም መከራ በበዛበት ሕዝብ ላይ ተጨማሪ ሸክም ላለመፍጠር ጥንቃቄ በማድረግ ደረጃ ከባድ ኃላፊነት ይጠበቅበታል። በመንግሥት ሥልጣን ላይ ያልሰከነ አመራር ምክንያት በየቀኑ የሚሰማው አስከፊ የሞት ዜና መፈናቀል ከመጠን በላይ የሆነ የኑሮ ውድነት፤ ከዚህም ጋር በእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ ምረጡኝ አትምረጡኝ የሚለው መላ ቅጡ የጠፋው ውዥንብር፤ እንደዚሁም ኃላፊነት የጎደላቸው ጫንቃቸው የደነደነ፣ እምነታቸው የመነመነ መንፈሳዊነታቸው የተዳፈነ ወይፈን ሊቃነ ጳጳሳት የሥልጣን ፈላጊነት ሽኩቻ፤ በሁለንተናዊ መልኩ ለብራና እንደ ሚፋቅ የፍየል ሌጦ ተወጥሮ ለሚቃትተው ሕዝባችን እና ቁርጠኝነት በሌለው በአመራር እጦት የዓለም ሀገራት ሁሉ ጅራት ለሆነችው ኢትዮጵያ ተጨማሪ ከባድ ቀንበር እንዳይሆን ግዳዩን በሰከነ ሁኔታ መመልከት ተገቢ ነው።

ምክር የሚሠማ መንግሥት ካለ፤ ቅዱስ ፓትርያርኩ በተናገሩት የትግራይ ትግርኝ ደጋፊነት መስሎ በሚታይ ሐሳብ ከመደናገጥ እና ነገሮችን በማይጠቅም ትርጓሜ፣ ትንታኔ በመስጠት ግራ ከመጋባት ይልቅ፤ ከቅዱስ ሲኖዶስ ጋር በተረጋጋ መንፈስ በቅርብ በመመካከር ያልተካረረና ያልተጋነነ ማዕከላዊ አስታራቂ መግለጫ እንዲሰጥ በማድረግ፤ ቅዱስነታቸው መገለል እንዳይሰማቸው ሰላማዊ በሆነ መንገድ በቅርብ በማነጋገር ከማረጋጋት ውጪ፤ የተናገሩትን ነገር እንደ ኳስ እያጎኑ፣ እየመነዘሩ ማሳቀቅ ወይም ደግሞ እንደ ኢሳት በመሳሰሉ ልጓም በሌላቸው ቅጥረኛ የመገናኛ አውታሮች ወይም ጋጠወጥ ጀሌዎች ባልታረመ አንደበት ባልተገራ ቃላት መዝለፍና ማዘለፍ፤ መንፈሳዊ ሕይዎትን የሚጎዳ ቡድነኝነትንና መከፋፈልን ፈጥሮ ለተጨማሪ አደጋ እንዳያጋልጥ አስተዋይነት በተሞላው ጥበበብ እና አመራር ችግሩን ማርገብ ተገቢ ነው።

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *