የምርጫ ቁሳቁሶችን ማጓጓዝ 274.5 ሚሊዮን ብር ይጠይቃል

0
0 0
Read Time:1 Minute, 54 Second

ብሩክ አብዱ
ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. በበርካታ የአገሪቱ ክፍሎች ለተደረገው የሕዝብ ተወካዮችና የክልል ምክር ቤቶች ምርጫ ቁሳቁሶችን ወደ ምርጫ ጣቢያና ከምርጫ ጣቢያ ወደ ማዕከል ለማጓጓዝ፣ 274,477,000 ብር እንደሚጠይቅ ሪፖርተር ያገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

ሪፖርተር የተመለከተው የቁሳቁስ ማንቀሳቀሻ ወጪዎች ዝርዝር እንደሚያሳየው፣ ይኼ ወጪ የተሰላው በ50 ሺሕ የምርጫ ጣቢያዎች ታሳቢነት ሲሆን፣ የትግራይ ክልልን ሳይጨምር ምርጫው ያልተከናወነባቸው 67 የሕዝብ ተወካዮችና 133 የክልል ምክር ቤቶች የምርጫ ክልሎች ይገኛሉ፡፡

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስቀድሞ በፀጥታና በድምፅ መስጫ ወረቀቶቸ ኅትመት ብልሽት ሳቢያ የተራዘሙ ሳይኖሩ በፊት ሊከፍታቸው ያቀዳቸውን 50 ሺሕ የምርጫ ጣቢያዎች ለመድረስ፣ ከማዕከል ወደ ምርጫ ክልል ለማጓጓዝ 40 ሚሊዮን ብር የሚጠይቅ ሲሆን፣ አምስት ሺሕ መኪኖች ለዚህ አገልግሎት ይውላሉ፡፡ የምርጫ ቁሳቁሶችን ከምርጫ ክልል ወደ ምርጫ ጣቢያዎች ለማድረስ፣ ለእያንዳንዱ የምርጫ ጣቢያ 1,000 ብር ወጪ ሆኖ 50 ሚሊዮን ብር ወጪ ይጠይቃል፡፡ በአውሮፕላን ቁሳቁሶችን አጓጉዞ አገር ውስጥ ባሉ መዳረሻዎች ለማድረስ 6.8 ሚሊዮን ብር ይጠይቃል፡፡ እነዚህ መዳረሻዎችም ድሬዳዋ፣ ቄለም ወለጋ፣ ጋምቤላ ክልልና፣ ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ናቸው፡፡

ምርጫው ተከናውኖ ሲያበቃ ቁሳቁሶችን ከምርጫ ክልል ወደ ማዕከል ለማጓጓዝ 16.9 ሚሊዮን ብር ወጪ የሚጠይቅ ሲሆን፣ ለዚህም ተግባር 250 ተሽከርካሪዎች ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡ ከ50,000 የምርጫ ጣያዎች ወደ ምርጫ ክልሎች የሚደረግ የቁሳቁሶች ዝውውር ለማድረግ ደግሞ፣ ለእያንዳዱ ጣቢያ 700 ብር የሚጠይቅ ሲሆን፣ በጠቅላላ 35 ሚሊዮን ብር ያስወጣል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በደቡብ አፍሪካ የታተሙ የምርጫ ቁሳቁሶችን ወደ አዲስ አበባ ለማጓጓዝ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትራንስፖርት አገልግሎት የሰጠ ሲሆን፣ ለዚህም ለአራት በረራዎች ለእያንዳንዳቸው 7,455,000 ብር ወጪ ተደርጎ በጠቅላላው 29.8 ሚሊዮን ብር ጠይቋል፡፡ በዱባይ የታተሙ የድምፅ መስጫ ወረቀቶችን ወደ አዲስ አበባ ለማጓጓዝ በጠቅላላው 95,850,000 ብር የጠየቀ ሲሆን፣ ለዚሁ ዓላማ ለተደረጉ ስድስት በረራዎች ለእያንዳንዳቸው 15,975,000 ብር ወጪ ተደርጓል፡፡

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ለማከናወን ዝግጅት በጀመረበት በ2012 ዓ.ም. የኮሮና ወረርሽኝ ከመከሰቱ አስቀድሞ ከመንግሥት 2.5 ቢሊዮን ብር የተመደበለት ሲሆን፣ ምርጫው በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ በአንድ ዓመት ሲራዘም ደግሞ ለተጨማሪ ወጪዎች በሚል ከመንግሥት 1.1 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት ጠይቆ ነበር፡፡ ይሁንና እስከ ዛሬ ይህ ገንዘብ አልተለቀቀም፡፡

ከዚህ ውጪ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) የኢትዮጵያን ዴሞክራሲ ለማጠናከር ምርጫን መደገፍ (Supporting Elections for Ethiopia’s Democratic Strengthening) በሚባለው ፕሮጀክቱ አማካይነት 40,004,000 ዶላር ድጋፍ አድርጓል፡፡ ይኼም ድጋፍ ከካናዳ፣ ከዴንማርክ፣ ከፊንላንድ፣ ከአየርላንድ፣ ከጃፓን፣ ከሉግዘምበርግ፣ ከኒውዚላንድ፣ ከኖርዌይ፣ ከስዊድን፣ እንዲሁም ከእንግሊዝ የዓለም አቀፍ ልማት መምርያ የተገኘ ነው፡፡

ቦርዱ ከተያዘለት በጀት ከፍተኛው ወጪ ከ225 ሺሕ በላይ ለሆኑ የምርጫ አስፈጻሚዎች የተከፈለ ክፍያ ሲሆን፣ ሌላው ከፍተኛ ድርሻ የወሰደው የምርጫ ተግባር የድምፅ መስጫና የሌሎች ወረቀቶች ኅትመት ነው፡፡

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *