አቶ ክርሰቲያን ለ ጠ/ሚው ያቀረቡት ጥያቄ ምን ነበረ?
ዛሬ የካቲት 15 ቀን 2014 ዓ.ም እየተካሄደ ባለው 6ኛ ዙር ፓርላማ አንደኛ ዓመት የሥራ ዘመን በ3ኛ አስቸኳይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረብናቸው ጥያቄዎች፤
**
አመሰግናለሁ የተከበሩ አፈጉባዔ፤
አመሰግናለሁ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር
1) መንግስት በነአቶ ስብሃት ነጋ ላይ የመሠረተውን ክስ ያቋረጠው ከሕግ አግባብና ሕገ መንግሥቱን በሚጣረስ መልኩ ስለሆነ ማስተካከያ እንዲያደርግ እጠይቃለሁ፡፡ ማብራሪያዬን እንደሚከተለው አቀርባለሁ።
መንግሥት መጀመሪያ ዜናውን ሲነግረን በምሕረት ነው የተፈቱት ያለ ሲሆን እነስብሃት ነጋን የመሰለ ሰው በሰው ልጆች ላይ ግፍ ፈጽሟል፤ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽሟል፤ ተብሎ የጠረጠረውን ወይም የከሰሰውን ሰው በምሕረት መልቀቅ እንደማይችል ሲረዳ በፍትሕ ሚንሰትሩ በኩል ይቅርታም፥ ምሕረትም አይደለም፤ የክስ ማቋረጥ ውሳኔ ነው ብሎ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ ስለተከሳሾቹ የግል ሁኔታ መንግሥት ቀደም ብሎ ከገለጸው ጋር በሚጋጭ መልኩ ትክክለኛ የማይመስሉ ነገሮችን የነገረን ሲሆን፣ ዋናው ነገር እሱ ባለመሆኑ ወደ ቁምነገሩ እገባለሁ፡፡ መንግሥት የሰራውን፤ አገር ያወቀውን፥ ፀሐይ የሞቀውን ስህተት ለማረም እድል አለው፡፡ ይህንንም እድል ለመስጠት ነው ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩን የምጠይቀው፡፡ እነዚህ ሰዎች እኔ በምወክለው የአማራ ሕዝብ ላይ ተደራጅተው ያደረሱበትን ኅልቆ መሳፍርት የሌለውን ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳት እንዲሁም የኅሊና መጎሳቆል ለመዘርዘር ጊዜም ስለማይበቃኝ አላነሳውም፡፡ ይሁንና፤
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 28 ንዑስ አንቀጽ (1)፦
«ኢትዮጵያ ባጸደቀቻቸው ዓልም አቀፍ ስምምነቶች እና በሌሎች የኢትየጵያ ሕጎች በሰው ልጅ ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች ተብለው የተወሰኑትን ወንጀሎች፤ የሰው ዘር ማጥፋት፣ ያለፍርድ የሞት ቅጣት እርምጃ የመውሰድ፣ በአስገዳጅ ሰውን የመሰወር፣ ወይም ኢሰብዓዊ የድብደባ ድርጊቶችን በፈጸሙ ሰዎች ላይ ክስ ማቅረብ በይርጋ አይታገድም፡፡ በሕግ አውጪው ክፍልም ሆነ በማንኛም የመንግሥት አካ ውሳኔዎች በምሕረት ወይም በይቅርታ አይታለፍም»
በማለት ይደነግጋል፡፡
እንዲሁም በንዑስ አንቀጽ (2) ሥር፦
«ከዚህ በላይ የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) የተጠቀሱትን ወንጀሎች ፈጽሞ የሞት ቅጣት ለተፈረደባቸው ሰዎች ርዕሰ ብሔሩ የማት ቅጣቱነ ወደ ዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት ሊያሻሽለው ይችላል»
በማለት ይደነግጋል፡፡
እነዚህ ድንጋጌዎች የወንጀሉን ከባድነት ብቻ ሳይሆን ወንጀለኞችንም ለማስቀጣት መንግሥት ሊኖረው የሚገባውን ቁርጠኝነት የሚደነግጉ ናቸው፡፡
የክስ ማቋረጡ የሕግ ድጋፍ የሌለው ስለመሆኑ ጥቂት ምክንያቶችን ብቻ እዘረዝራለሁ፦
ሀ) ምናልባትም የተከበረው ምክር ቤት የሕገ-መንግሥቱን ድንጋጌ አንድምታውን ጭምር መረዳት እንዲችል የዚህን ድንጋጌ ልደት መቼት መግለጽ ያስፈልገኛል፡፡ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ሕገ-መንግሥት የተረቀቀው በሰው ልጆች ላይ ከባድ ግፍ ፈጽመዋል ተብለው የቀድሞ የደርግ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በእስር ላይ በነበሩበት ዘመን መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ በዚሁ አንቀጽ ላይ ውይይት ያደረጉት የሕገ-መንግሥት ኮሚሽን አባላት ዋና አሳሳቢ ነገራቸው እነዚህን ወንጀሎች የፈጸመ ሰው በማናቸውም መልኩ ከቅጣት እንዳያመልጥ ነው፡፡ ስለሆነም ወንጀሉን የፈጸመው ሰው ተግባሩን ከፈጸመ በኋላ ከቦታው ቢሰወርም በይርጋ አይታገድም፤ ማንም ባለሥልጣንም ምንም ሊያደርግለት አይችልም በማለት በግልጽ የሕግ-አውጪውንና አስፈጻሚውን ሥልጣን ገድበዋል፡፡ ተጠርጣሪው ወይም ተከሳሹ ጉዳዩ በፍርድ ሂደት ማለፉን ግዴታ በማድረጋቸው ነው ይህንን ድንጋጌ የደነገጉት፡፡ ሕገ-መንግሥቱ እሰከሚጸድቅ ድረስ የነባሩ ሥነ-ሥርዓት ሕግ ክስን ሰለማንሳት የሚደነግገው አንቀጽ 122(1) እና (2) በማዕከላዊ መንግሥት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁ 39/1985 ዓ.ም. አንቀጽ 24 ተሽሯል፡፡
ለ) በዚህ የሕገ-መንግሥቱ ድንጋጌ ላይ ውይይት በሚደረግበት ጊዜ በዋናነት ውይይት የተደረገው ርዕሰ ብሔሩ የሞት ፍርዱን ወደ እድሜ ልክ ጽኑ እስራት መለወጥ ሥልጣን ሊኖራቸው ይገባል ወይስ አይገባም በሚል ሆኖ ይህ አላግባብ በር እንዳይከፍት ብለው ከፍተኛ ተቃውሞ ያነሱት፣ የድንጋጌውንም ይዘት አሁን ያለውን መልክ እንዲይዝ ጠንክረው የተከራከሩት በወቅቱ አጠራር ከክልል አንድ የመጡ ወኪሎች ነበሩ፡፡
ይህን የመሰለውን የሕገ-መንግሥት ድንጋጌ የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁ. 943/2008 አንቀጽ 6(3)(ሀ) ድንጋጌ ሊሽረው እንደማይችል ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህ በሌለው ሥልጣን የፍትሕ ሚኒስቴር የደረሰበት የክስ ማቋረጥ ውሳኔ ሕገ-መንግሥቱን የሚጣረስ ስለሆነና ይህ ምክር ቤትም በአዋጅ ቁ. 943/2008 መሠረት ይህን የመሰለ ሥልጣን ለፍትሕ ሚኒስቴር የመስጠት ሕገ-መንግሥታዊ ሥልጣን ስሌለው የሰጠውን የክስ ማቋረጥ ውሳኔ በመሻር ክሱን እንዲቀጥል እንዲያደርግ እጠይቃለሁ፡፡
የተከበረው ምክር ቤት ያቀረብሁትን የኃቅ፣ የፍትኅና የሞራል ጥያቄ ሕጋዊነት መርምሮ፥ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩና ካቢኒያቸው ያሳለፉትን ውሳኔ በመሻር ጉዳዩ እንዲቀጥል እንዲያደርጉ እየጠየቅሁ፤ እኔ የምወክለው ታላቁ የአማራ ሕዝብ በዚህ ላይ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩን ማብራሪያ እንዲሰጡበት በጉጉት የሚጠበቅ ስለሆነ ክቡርነትዎ አስተያየት ቢሰጡበት?
2) በኢትዮጵያ መንግስትና አሸባሪው ትሕነግ መካከል ድርድር እየተካሄደ ሥለመሆኑ በተለያዩ ሚዲያዎች እየተገለፀ ነው፡፡
ሀ) ምን ያህል እውነት ነው?
ለ) እውነት ከሆነስ ማን ከማን ጋር ነው እየተደራደረ ያለው? በማን አደራዳሪነት?
ሐ) ትሕነግ በተከበረው ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀ ከመሆኑ አንፃር መንግስት የሚያደርገው ድርድር ሕጋዊነቱ እንዴት ይታያል?
መ) የድርድሩ ማኅበራዊ፣ ሕጋዊና ሞራላዊ ቅቡልነት የሚረጋገጠው ድርድሩ ግልጽና አሳታፊ ሲሆን ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ድርድሩ በኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይም ቀጥተኛ ተጎጂ በሆኑት የአፋርና አማራ ሕዝብ ዘንድ የሚያሣድረው ስሜት ተጢኗል ወይ?
3) አሸባሪው ትሕነግ በአገር ኀልውና እና አንድነት ላይ ያወጀውን ጦርነት ተከትሎ ዓይነተ ብዙ ውድመቶች ተከስተዋል፡፡ በተለይም በአፋርና አማራ ክልሎች እጅግ የከፉ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኀበራዊና ሥነ-ልቦናዊ ምስቅልቅሎች ተከስተዋል፡፡ አፋርና አማራ የጦር አውድማ እንጂ የአሸባሪው ትሕነግ ጦርነት ከኢትዮጵያና መላው ኢትዮጵያውያን ጋር መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይሁንና የደረሰውን ውድመት ለማካካስ እና መልሶ ለመገንባት በፌዴራል መንግስት በኩል የፀደቀው የድጎማ በጀት አንድ ተቋምን እንኳን በወጉ ጠጋግኖ ወደነበረበት መመለስ የሚያስችል አይደለም፡፡ ባለበጀት ክልሎችና የፌደራሉ መንግስት በልዩ ሁኔታ አገርን ለማዳን ሲሉ ከፍተኛ ቀውስ ያስተናገዱ ክልሎችን ለምን በበቂ ሁኔታ መደገፍ አልቻሉም?
4) አገራችን ከጎረቤት አገራት እና ከምዕራባዊያን ጋር ያላት ወቅታዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ምን ይመስላል? አገራዊ የደኀንነት አደጋው ባልተቀለበሰበትና በተለያዩ ምክንያቶች በቂ የወታደራዊ አመራሮች ባልተፈሩበት ሁኔታ ከፍተኛ የወታደራዊ መኮንኖችን በአምባሳደርነት መሾሙ ያለው ተገቢነት ላይ ማብራሪያ ቢሰጥ?
አመሰግናለሁ!