የምግብ ዋጋ ጣራ እየነካ ነው “
የምግብ ዋጋ ጣራ እየነካ ነው “
የዓለም አቀፉ ምግብ ፕሮግራም ኃላፊ ዴቪድ ባስሌይ የዩክሬን ጦርነት የምግብ ዋጋን እንደሚያንረውና ያላደጉ አገራትን ምጣኔ ሃብት ሊያደቅ እንደሚችል አስጠነቀቁ።
ዩክሬንና ሩሲያ የምግብ ምርቶችን በገፍ ከሚያመርቱ የዓለማችን አገራት መካከል ናቸው።
ኃላፊው እንደሚሉት ጦርነቱ አንዳንድ አገራትን ወደከፋ ረሃብ ሊገፋቸው ይችላል።
“ምድራችን ላይ ያለው የከፋ ሁኔታ ወደ ባሰ ሁኔታ አይሸጋገርም ብለን ተስፋ ብናደርግም እነሆ ይሄ ተፈጠረ” ብለዋል ኃላፊው።
ሩሲያና ዩክሬን በአንድ ወቅት የአውሮፓ የዳቦ ቅርጫት ይባሉ ነበር። የምድራችንን ሩብ የስንዴ ምርት አምራች አገራት ነበሩ።
በተጨማሪ ዓለማችን ግማሹን የሱፍ አበባና ከዚህ ሰብል የሚገኙት ዘይትና ሌሎች ምርቶችን የምታገኘው ከ2ቱ ሀገራት ነው።
ሩሲያ በነዳጇ ዩክሬን በበቆሎ ምርቷ የዓለማችን ትሩፋቶች ናቸው።
ዴቪድ ባስሌይ በዓለማችን የረሃብ ስጋት ተደቅኖባቸዋል የሚባሉ ሰዎች ቁጥር ከ80 ሚሊዮን ወደ 276 ሚሊዮን ማሻቀቡን ገልፀዋል። ይህ የሆነው የአየር ንብረት ለውጥና የኮሮና ወረርሽኝ ላይ ሩሲያ በዩክሬን ያወጀችው ጦርነት ሲታከልበት ነው ብለዋል።
ኃላፊው አንዳንድ አገራት አሁን ባጋጠመው ቀውስ ሳቢያ የከፋ አደጋ ፊታቸው ተደቅኗል ብለዋል። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ እኚህ አገራት ከፍተኛውን ጥራጥሬ የሚያስመጡት ከጥቁር ባሕር አካባቢ በመሆኑ ነው።
ባስሌይ ፤ “ሊባኖስ ለምሳሌ 50 በመቶ ጥራጥሬ የምታስመጣው ከዩክሬን ነው። የመን፣ ሶሪያ፣ ቱኒዚያ እና ሌሎች በርካታ አገራትን መጥራት እችላለሁ፤ ከዩክሬን በሚያስመጡት እህል ላይ ጥገኛ ናቸው” ያሉ ሲሆን “ነገር ግን አሁን የዳቦ ቅርጫት ከመሆን ወደ ዳቦ ጠባቂነት ስትለወጥ በጣም የሚያስገርም የእውነት መመሰቃቀል ነው” ብለዋል።