በኦሮሞ ብሔርተኞች የተወረሱት የዎላይታ ተወላጁ አቡነ ጴጥሮስ

0
0 0
Read Time:6 Minute, 44 Second

በኦሮሞ ብሔርተኞች የተወረሱት የዎላይታ ተወላጁ አቡነ ጴጥሮስ!

አቻምየለው ታምሩ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን በጠላትነት ፈርጆ ልጆቿን ሲያርድና ቅርሶቿን በማውደም ታሪኳን ሲያጠፋ የሚውለው የኦሮሞ ብሔርተኛነት የቤተክርስቲያኗ የበኩር ልጅና ፍሬ የሆኑትን አቡነ ጴጥሮስን ኦሮሞ ለማድረግ ያልፈጠረው ተረት፣ ያላቆመው የውሸት ሐውልትና ያላወጣው የሞጋሳ ስም የለም። ታሪክ እናውቃለን የሚሉ የኦሮሞ ብሔርተኞች ደግሞ በተለያየ ጊዜ ባወናከሯቸው ድሪቶዎች ሰማዕቱን አቡነ ጴጥሮስን ኦሮሞ ለማድረግ ያላወጡላቸው የኦሮምኛ ስም የለም። ከነዚህ የፈጠራ ስሞች መካከል በተደጋጋሚ ሲጠቀሱ የምናገኛቸው በዳሳ ለሜሳ፣ ጫላ መገርሳና መገርሳ በዳሣ የሚሉ የሀሰት ስሞች ናቸው። እነዚህ ስሞች አቡኑ ሰማዕት ከኾኑ ሰባና ሰማኒያ ዓመታት በኋላ በኦሮሞ ብሔርተኞች የተፈጠሩ እንጂ አዳቸውም አቡነ ጴጥሮስ በሕይዎት በኖሩበት ዘመን የነበሯቸው ስሞች አይደለም።

ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ እንደወሳነው የኦሮሞ ብሔርተኛነት እንቅስቃሴ ስለ እኩልነትና ዲሞክራሲ የሚደረግ ትግል ሳይሆን ሰማዩንም ምድሩንም «ኬኛ» የሚል የወረራና የመውረስ መንፈስ የተጠናወተው የዝቅተኝነት ፖለቲካ ነው። የኦሮሞ ብሔርተኞች ፖለቲካ የሌላውን መውረርና ኬኛ ማለት ስለሆነ የራሳቸው ያልኾነውን ለመውረር፣ ለመሰልቀጥና ኦሮማይዝ ለማድረግ ታሪክ፣ የቤተሰብ ጉዳይና የአለም እውነት አያስጨንቃቸውም። ለሕጻን እንኳ የማይወራ የጅል ፈጠራ ፈጥረን እንካ ብንለው ኦሮሞ ያምነናል ብለው ኦሮሞን ስለሚንቁትና ለመመርመር ፍቃደኛ ያልሆነ መንጋ ስላላቸው እውነት፣ ታሪክና እውቀት ሳያግዳቸው ሰውንም ይሁን ቤትን፤ ምድሩንም ይሁን ሰማዩን ለመውረስና ለመውረር አያመነቱም። ይህም በመሆኑም በእናታቸውም በአባታቸውም የዎላይታ ተወላጅ ለኾኑት ለአቡነ ጴጥሮስ ሰማዕት ከሆኑ ሰባና ሰማኒያ ዓመታት በኋላ የተለያዩ የፈጠራ ስሞችን አውጥተውና ባልነበራቸው የኦሮምኛ ስም ሐውልት ቀርጸው አሮሞ አድርገው ወርሰዋቸዋል።

የኦሮሞ ብሔርተኞች በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ላይ እየዘመቱ የቤተክርስቲያኗ ፍሬ የኾኑትን ሰማዕት ወርሰው ኦሮሞ ለማድረግ የሚኳትኑት የአቡነ ጴትሮስ የዘመን ተጋሪ የኾነ የኦሮሞ ተወላጅ የኢትዮጵያ አርበኛ አጥተው አይደለም። የኦሮሞ ብሔርተኞች ይኽን የሚያደርጉት ፖለቲካቸው የዝቅተኛነት ደዌ የተጠናወተው የመውረርና የመውረስ በሽታ ስለሆነ ትልቅ የተባለን ሰው ኦሮሞ ካላደረጉ ሰው ሆነው የሚቆሙ ስለማይመስላቸው ነው። በመንግሥትነት በተሰየመው ነውረኛ ቡድን በቆመው የአቡኑ ሐውልት ላይ ለሰማዕቱ የተሰጠው ያልነበራቸው የኦሮምኛ ስም ከየትኛው የታሪክ መዝገብ እንደተገኘ በቤተክርስቲያኗና በባለሞያ ለማስጠናት ሙዝ የመላጥ ያህል እንኳ ሙከራ አላደረገም፤ እንዲደረግም አይፈልግም። የማጣራት ሙከራ የማይደረገውም እውነቱ/ውጤቱ የኦሮሞ ብሔርተኞች የማይፈልጉት ሆኖ ስለሚገኝ ብቻ ነው። ቤተክርስቲያኗም ቅዱስ ብላ ለሰየመቻቸው ሰማዕቱ ፖለቲከኞች የፈጠራ ሐውልት ሲያቆሙ ለምን ብላ አልጠየቀችም።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሰማዕት አቡነ ጴጥሮስ የኦሮሞ ብሔርተኞች በፈጠራቸው እየተመኩ ሊነግሩን እንደሚሉን ማንነታቸው ኦሮሞ ሳይሆኑ የዎላይታ ተወላጅ ነበሩ። ይህንን የአቡነ ጴጥሮስ ማንነት የሚነግሩን አብሮ አደጋቸው፣ ስለ ሰማዕቱ የሕይዎት ታሪክ ሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ የነገሯቸውን የዐይን ምስክርነት የጻፉት የወላይታ ተወላጁ አቶ ዋና ዋጌሾ ናቸው።

“የደቡብ ኢትዮጵያ የትምህርት አባት” በመባል የሚታወቁት አቶ ዋና ዋጌሾ በተወለዱ በ108 ዓመታቸው ሐምሌ 25 ቀን 2011 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

አቶ ዋና “የዎላይታ ሕዝብ ታሪክ” እና “የታሪክ አብነት ከባለታሪኩ” በሚሉ አርዕስቶች መጽሐፍቶችን አሳትመዋል። ከዚህ ዓለም በሞት ከመለየታቸው ከ11 ዓመታት በፊት “የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጴጥሮስ አጭር የሕይወት ታሪክ” በሚል ርዕስ ጥቅምት 5 ቀን 2000 ዓ.ም. በጻፉት የሰማዕቱ ታሪክ የዐይን ምስክር ስለኾኑበት የአቡነ ጴጥሮስ ታሪክ ለትውልድ ትተውልን አልፈዋል።

አቶ ዋና በዚህ ጽሑፋቸው አቡነ ጴጥሮስን በግፍ በተገደሉበት ቀን ሳይቀር አግኝተው እንዳናገሯቸው፤ ማንነታቸውም የታሪክ ፀሐፊዎች በተዛባ ትርክት ምክንያት የሌላ ማንነት ለጥፈውባቸው እንደሚገልጿቸው ሳይሆን ወላይታ መሆናቸውን፤ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው በወላይትኛ ከአቡነ ጴጥሮስ ጋር ይነጋገሩ እንደነበርና ወላይታ ውስጥ የተወለዱበትን ሥፍራ ጭምር ከእሳቸው አንደበት መስማታቸውን ጽፈዋል።

ባጭሩ አቡነ ጴጥሮስ ከዎላይታ ወደ ሸዋ የመጡት የትግሬ ተወላጁን የወላይታውን ንጉሥ ካወ ጦናን ለማስገበር የዘመተው የማዕከላዊ መንግሥት ጦር አንድ ክፍል የሆነው የሰላሌ ገዢ የነበሩት የራስ ካሳ ዳርጌ ጦር ማርኮ ወደ ሰላሌ ስላመጣቸው ነበር። በወቅቱ ከአቡነ ጴጥሮስ ጋር ወደ ሰላሌ የመጡና እዚያው ሰፍረው የቀሩ በርካታ የዎላይታ ተወላጆችም ነበሩ። አቡኑ ግን ሰላሌ ውስጥ ያደጉትና የተማሩት ፍቼ በሚገኘው የራሳ ካሳ ግቢ ውስጥ ነበር።

አቶ ዋናም በጻፉት ማስታወሻቸው እንደነገሩን ራስ ካሳ ያዳደጓቸውን አቡነ ጴጥሮስን ይወዷቸው ስለነበር ሊድሯቸው ቢፈልጉም አቡኑ ግን ወደ ሃይማኖት በጣም ያዘነበሉ ሰው በመሆናቸው ፍቃደኛ ሊሆኑ አልቻሉም። ራስ ካሳ ይህንን የአቡነ ጴጥሮስን ፍቃደኛ አለመሆን ለወቅቱ አልጋ ወራሽ ለራስ ተፈሪም ጭምር ተነግረው ነበር። ሆኖም ግን አልጋ ወራሹ «ተወው ልመንኩስ ካለ አታስገድደው» ብለው ምላሽ መስጠታቸው ሊመነኩሱ ችለዋል። ቆይተውም ወደ ግብጽ ተልከው ጵጵስናቸውን ተቀብለዋል።

በወላይታ ወላጆች ልጆቻቸው በዐይን በሽታ እንዳይጠቁ «በቄ» በመባል የሚታወቀውን የባህል ምልክት ያደርጋሉ። በወላይታ ዘንድ «በቄ» የሚባለው በዐይን ግራና ቀኝ የሚደረገው ምልክት የመሀል አገር ሰው በተለምዶ የ«የወላይታ ስሙኒ» እያለ የሚጠራው ምልክት ነው። የወላይታ ተወላጁ አቡነ ጴጥሮስም እንደ ወላይታ ልጅነታቸው በቄ ወይም «የወላይታ ስሙኒ» በዐይናቸው ግራና ቀኝ የነበራቸው ሰው ነበሩ። ይህንን ታሪክ ያካፈሉኝ አባታቸው አቶ ዋና ዋጌሾ ስለ አቡነ ጴጥሮስ የጻፉትን የእጅ ጽሑፍ የሰጡኝ ልጃቸው ሲኾኑ ስለ አቡነ ጴጥሮስ ተክለ ሰውነት ያካፈሉኝ ታሪክ የነገሯቸው አባታችው እንደኾኑ ነግረውኛል።

የሰማዕቱ የአቡነ ጴጥሮስ እውነተኛ ታሪክ ባጭሩ ከላይ የቀረበው ነው። አቶ ዋና ዋጌሾ የአቡነ ጴጥሮስን ታሪክ አስመልክተው የጻፉት ሙሉ ታሪክና የዐይን ምስክር የኾኑበት የዘመን እውነት ደግሞ እንደወረደ እንደሚከተለው ቀርቧል።


የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጴጥሮስ አጭር የሕይወት ታሪክ
(በዋና ዋጌሾ)

በዎላይታ አውራጃ በኮይሻ ወረዳ በዋጪጋ መንደር ከዎላይታ ቤተሰብ የተወለዱ አቡነ ጴጥሮስ በአስከፊው ጦርነት ውስጥ ለምርኮ የበቁት ገና በልጅነት ዕድሜአቸው ነበረ፡፡ የሰላሌ አስተዳዳሪ የነበሩት የዎላይታ ዘመቻው ተካፋይ ልዑል ራስ ካሳ አቡኑን እንደ ምርኮኛ ሳይሆን እንደ ልጃቸው በመመልከት በእንክብካቤ እያስተማሩ አሳድገው የግምጃ ቤታቸው ኃላፊና ፀሐፊ አድርገው ሾምዋቸው፡፡ በሥራ ቅልጥፍናቸውና ፍፁም ታማኝነታቸው የረኩት ልዑል ራስ ካሳ ከአጠገባቸው እንዳይርቁ በጋብቻ ሊያስሩዋቸው ሲሞክሩ አቡኑ ፍላጎታቸው አለማዊ ሕይወት እንዳልሆነና ምኞታቸው ምንኩስና መሆኑን ይገልጹላቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት አፄ ምኒልክ በብሔርና በጎሣ ተለያይታ የነበረችውን ኢትዮጵያ አንድ የማትበገር ኃያል አገር ለማድረግ ካላቸው ጽኑ ፍላጎት በመነሳት እሺ ያለውን በስብከት እንቢ ያለውን በጦር ኃይል በማስገደድ አንድነትን ለመፍጠር በሚታትሩበት ወቅት በዎላይታ በኩል ያደረጉዋቸው ተደጋጋሚ ድፕሎማሲያዊ ጥረቶች ባለመሳካታቸው ወደ ኃይሉ አማራጭ አዘነበሉ።

በዚሁ የኃይል እርምጃቸው ጦርና የጦር መሪዎችን እያፈራረቁ አምስት ጊዜ ያካሄዱት የዘመቻ ሙከራዎች ባለመሳካታቸውና በስድስተኛው ጊዜ ከብዙ ሠራዊት ጋር የተላኩት የጦር ሚኒስትሩ ራስ መንገሻ አትክም ጭራሽ ለሽንፈት በመዳረጋቻዉ አፄ ምኒልክ ተበሳጭተው በ1887 ዓ.ም ራሳቸው ለመዝመት ክተት አውጀው ነጋሪት አስጎስመው ወደ ዎላይታ አመሩ፡፡

በወጣው የውጊያ ዕቅድ መሠረት ከተለያዩ ማዕዘናት ጦራቸውን አሰልፈው የንጉሡን ትዕዛዝ በተጠንቀቅ የሚጠባበቁት የራስ ወልደጊዮርጊስ፣ የደጃዝማች ገነሜ፣ የራስ ልዑልሰገድ፣ የደጃዝማች በሻህና የልዑል ራስ ካሳ ጦሮች በአንደኛው ግንባር ደግሞ ንጉሡ እራሳቸው ከሚመሩት ጦር ጋር በአንዴና በኅብረት ባካሄዱት ጦርነት ከሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች (ከአፄ ምኒልክና ከንጉሥ ጦና) ብዙ ሕይወትና ንብረት ጠፍቶ በአፄ ምኒልክ አሸናፊነት በንጉሥ ጦና ተሸናፊነት ጦርነቱ ተደመደመ፡፡ ከውጊያው በኋላ የሆነው በጻፍኩት ‹የዎላይታ ሕዝብ ታሪክ› መጽሐፍ በዝርዝር ተመልክቷል።

የዚህ ጽሑፍ ዓላማ የዎላይታን ጀግንነት ወይም በዘመናዊ መሳሪያና ትጥቅ የተዋጋውን የአፄ ምኒልክ ሠራዊት የውጊያ ጥበብ ለመዘከር ሳይሆን ውጊያውን ተክትሎ እንደ ዕድል በራስ ካሳ እጅ ስለለወደቁት እኔም በአካል ብፁእነታቸውን አግኝቼ ከአጫወቱኝ በመነሳት እየተንጋደደ ውሉን በመሳት ላይ ያለውን የብፁዕነታቸውን ማንነት ለወገኖቼ ለማሳወቅ ነው፡፡

አቡነ ጴጥሮስ ራሳቸው እንደነገሩኝ የተወለዱት በዎላይታ አውራጃ በኮይሻ ወረዳ በዋጪጋ መንደር ከዎላይታ ቤተሰብ ሲሆን በጦርነት ውስጥ ለምርኮ የበቁት ገና በልጅነት ዕድሜአቸው ነበር፡፡ በዚህ ዘመን የሰላሌ አስተዳዳሪ የነበሩትና የዎላይታ ዘመቻው ተካፋይ የሆኑት ልዑል ራስ ካሳ አቡኑን እንደ ምርኮኛ ሳይሆን እንደ ልጃቸው በመመልከት ከዎላይታ ጀምሮ እስከ ሰላሌ ድረስ በእንክብካቤ በማምጣት በግቢያቸው ውስጥ እያስተማሩ አሳድገው የግምጃ ቤታቸው ኃላፊና ፀሐፊ አድርገው ሾምዋቸው፡፡ በሥራ ቅልጥፍናቸውና ፍፁም ታማኝነታቸው የረኩት ልዑል ራስ ካሳ ከአጠገባቸው እንዳይርቁ በጋብቻ ሊያስሩዋቸው ሲሞክሩ አቡኑ ፍላጎታቸው አለማዊ ሕይወት እንዳልሆነና ምኞታቸው ምንኩስና መሆኑን ይገልጹላቸዋል፡፡

ይህ በጊዜው በራስ ካሳ ተቀባይነት ባለማግኘቱ አቡኑ ደጃዝማች ተፈሪ መኮንን እንዲያማልዱዋቸው ይማጸናሉ፡፡ በወቅቱ የባሶ ገዢ የነበሩት ደጃዝማች ተፈሪ መኮንን (በኋላ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ተብለው የኢትዮጵያ ንጉሥ) ልዑል ራስ ካሳን አስፈቅደውላቸው አቡኑ ለመመንኮስ በቁ፡፡ አቡኑ ከምንኩስናቸው በኋላ በደብረሊባኖስ ገዳም ከካህናቶች ጋር በትህትና ሲያገለግሉ ቆይተው የቤተክህነት ሹመት አግኝተው በትውልድ አገራቸው በዎላይታ የአቡነ ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን ሊቀመምህር ሆነው ለአመታት አገልግለዋል፡፡

ከዚያም በዝዋይ ደሴቶች አገልግለው ወደ ደብረሊባኖስ በመመለስ በእጬጌነት ሲያገለግሉ ሳሉ ታሪካቸውን ከመሠረቱ በሚያውቁ በግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ድጋፍ ሊቀ ጳጳስ ሆነው በተመረጡበት የሹመት መንበር ሊቀመጡ ችለዋል፡፡

የአቡነ ጴጥሮስን ታሪካዊ አመጣጥ ከታሪክ ያጠናው ማርሻል ግራዘያኒ ለመሰሪ ዓላማው ሊጠቀምባቸው አስቦ በዎላይታነታቸው በደል እንደደረሰባቸውና በማስደሰት ለኢጣሊያ መንግሥት ከሠሩ ከፍ ከፍ አድርጎ እንደሚሾማቸው ይነግራቸዋል፡፡ ሕዝቡ የጣሊያንን ገዥነት እንዲቀበል እንዲሰብኩላቸውም ይጠይቋቸዋል፡፡ አቡኑ በግላቸው ምንም በደል እንዳልደረሰባቸው ይልቁንም በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ በደል እየፈጸመ ያለው የኢጣሊያ መንግሥት በመሆኑ እንኳን ሕዝቡ መሬቷም እንዳትሸከማቸው ያወገዙ መሆናቸውን ይነግሯቸዋል፡፡ በዚሁ ውግዘታቸው ናላው የዞረው ግራዚያኒ እንዲረሸኑ ይወስናል፡፡

ብፁዕነታቸውም ለሀገራቸው መስዋዕት በመሆን በጠላት መትረየስ ያለ ርህራሄ ተረሸኑ፡፡ በታሪክ አጋጣሚ በአካባቢው ስለነበርኩ ይህንን መጥፎ ድርጊት በአይኔ ተመልክቻለሁ፡፡

ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ በግፍ ከተረሸኑ በኋላ በዱር በገደል የተሰማራው የኢትዮጲያ ጀግና አርበኛ ሁሉ ኃይላቸውን አጠናክረው ኢጣሊያኖችን መግቢያ መውጫ ከልክለው ሲያርበተብቱዋቸው ሳለ በእንግሊዝ የሚመራ የቃል ኪዳን ወታደሮች ቡድን ደርሶ በሕብረት ጣሊያኖችን ወግተው ሀገሪቷ ሙሉ ነፃነትዋን ከተጎናጸፈች በኋላ ለሀገራቸው መስዋዕት የሆኑ የክፉ ቀን ጀግች ልጆችዋን በማስታወስ ለምሳሌ ለአቡነ ጴጥሮስ ከተረሸኑበት ሥፍራ ትንሽ ከፍ ብሎ በማስታወቂያ ሚኒስቴር መ/ቤት አጠገብ ሐውልት አቁመውላቸዋል፡፡

ሐውልቱና የቆመበት አደባባይ በአሁኑ መልክ ታድሶና ተውቦ መመልከት በጣም ያስደስታል፡፡ ከዚህም አልፎ የአቡኑ ብቃታቸው ታምኖ በስማቸው ታቦት እንዲቀረጽ መወሰኑ ይበልጥ ያስደስታል፡፡ ከዚህ ሁሉ በጎ እንቅስቃሴ ጎን የአቡኑን ማንነት ለማጣመም ሆነ ተብሎ ወይም ካለማወቅ የሚናፈሱ የፈጠራ ታሪኮች ሐቁን በትክክል ለምናውቅና በሕይወት ላለን አዛውንቶች እጅጉን ያሳዝናል፡፡

ምርጥ ምርጡ ለመሐል ሀገርና ለሰሜን ብቻ ይሁን ካልተባለ በስተቀር በምንም መስፈርት የግለሰብ ማንነት በስሜት አይወሰንም፡፡ በዘመናዊው ሳይንስ ጭምር በቀላሉ ሊረጋገጥ የሚችል የቅርብ ጊዜ ክስተት ስለሆነ ጉዳዩ የሚመለከታቸው እኛን አዛውንቶችን እንዲያነጋግሩና የተዛባውን ታሪክ ትክክለኛውን ፈር እንዲያስዙ በቸሩ ፈጣሪና በቅዱሱ አቡኑ ስም እማፀናለሁ፡፡

ጥቅምት 5 ቀን 2000 ዓ.ም.

ዋና ዋጌሾ
ከምድረ ዎላይታ
__፟
ከታች የታተመው ፎቶ አቡነ ጴጥሮስ በኢየሩሳሌ አገር ሳሉ የተነሱት ፎቶ ነው።

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *