ከ6 ሺህ በላይ የሳይበር ጥቃቶች በኢትዮጵያ ላይ ተቃጥተዋል – ዳይሬክተር ዶ/ር ሹመቴ
በ2014 በጀት ዓመት ከ6 ሺህ በላይ የሳይበር ጥቃቶች በኢትዮጵያ ላይ ተቃጥተዋል – ኢመደአ
አዲስ አበባ፡ ሐምሌ 23/2014 ዓ/ም፡ ባሳለፍነው 2014 በጀት ዓመት በኢትዮጵያ ላይ ከ6 ሺህ በላይ የሳይበር ጥቃቶች መሞከራቸውንና ከ97 በመቶ በላይ የሚሆኑትን መመከትና ማክሸፍ መቻሉን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሹመቴ ግዛው ገልጸዋል።
ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሹመቴ ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት (ኢቢሲ) ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለፁት፥ ጥቃቶቹ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀሩ ከ4 እጥፍ በላይ የተበራከቱና እጅግ አደገኛ የተባሉ ናቸው። ይሁን እንጂ ከ97 በመቶ በላይ የሚሆኑትን መመከትና ማክሸፍ መቻሉን ነው ዋና ዳይሬክተሩ የገለፁት።
ጥቃቶቹን በማክሸፍ ሂደት ከ75 በመቶ በላይ ሀገር በቀልና እሴት አከል መጤ ቴክኖሎጂን መጠቀማችን ትልቅ ሚና ነበረው ነው ያሉት ዶ/ር ሹመቴ።
በቀጣይም መሰል ጥቃቶችን ለመመከት የቴክኖሎጂ ውጤቶች ዕውቀትና ባለቤትነትን ማጎልበት ላይ እንደ ሀገር እየሰራን ነው ብለዋል።
የቢትኮይን ምናባዊ የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ስርዓትን በተመለከተም ዋና ዳይሬክተሩ ከፍተኛ የኃይል ፍጆታን የማስከተል እና ግብይትን ላልተፈለገ ዓላማ የማዋል ስጋት ቢኖረውም፤ ከቴክኖሎጂ መሸሽ የሚቻል ባለመሆኑ በአሰራር ስርዓቱ ላይ ጥናት እያደረግን ነው ብለዋል።
ምንጭ፡ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት
Source EBC