የረጅም ዘመን ባልንጀሮቹ ሼህ አላሙዲንና አቶ አብነት ገብረመስቀል በችሎት እየተሟገቱ ነው!!
የረጅም ዓመታት የቅርብ ጓደኛሞቹ ሼህ መሀመድ አላሙዲንና አቶ አብነት ገብረመስቀል በገንዘብ ድርሻ ይገባኛል በችሎት ተካሰው እየተሟገቱ ነው።
ሼህ መሀመድ አላሙዲን ናሽናል ኦይል ኢትዮጵያ ኃ/የተ/የግል ማህበር ውስጥ ባለድርሻ ናቸው። በዚህም ከኩባንያው የሚገባቸው ትርፍ በዛን ጊዜ ወዳጃቸው አቶ አብነት ገብረመስቀል በኩል በውክልና ሲከፈላቸው እንደነበር ኩባን ያው ክፍያ የፈፀመበትን ዝርዝር አቅርቧል።
ከ2004ዓ/ም እስከ 2013 ዓ/ም ማህበሩ ካተረፈው ትርፍ ላይ ለከሳሽ አላሙዲን ሁለት ቢሊየን ብር ያህል የትርፍ ተጋሪነት ድርሻ አለኝ ያሉ ሲሆን የተለያዩ ክፍያዎች ተቀናንሰው ስምንት መቶ ሀምሳ ሚሊየን ብር ገደማ እኔጋ ገቢ አልተደረገም የሚል አቤቱታ አቅርበዋል።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀጥተኛ ፍትሐ ብሄር ችሎት ልደታ ምድብ ጥር 24 ቀን 2014 ዓ/ም በሰጠው ብይን መሰረት የተሻሻለው የክስ ዝርዝር 852,462,650 (ስምንት መቶ አምሳ ሁለት ሚሊዩን አራት መቶ ስልሳ ሁለት ሺ ስድስት መቶ ሃምሳ ብር) የትርፍ ድርሻ ናሽናል ኦይል ኢትዩጵያ ኃ/የተ/የግል ማህበር በተለያዩ ግዜያት በውክልና ወደ ተከሳሽ አቶ አብነት ገብረመስቀል የባንክ ሂሳብ መተላለፉን ይገልፃል።
በቀጣይ ቀጠሮ የተሻሻለውን የሼህ መሀመድ አላሙዲንን ክስ ፍርድ ቤቱ በተለዋጭ ቀጠሮ በዝርዝር ይሰማል። አላሙዲን የክስ ጭብጥ ወደ አቶ አብነት በውክልና የተላለፈውን ገንዘብ ፍርድ ቤት እንዲያስከፍላቸው የሚጠይቅ ነው።
አቶ አብነትም ስለተከሰሱበት ከስምንት መቶ ሚሊየን ብር በላይ ውንጀላ ምላሻቸውን ያቀርባሉ።
ሼህ መሀመድ አላሙዲን በአሁኑ ወቅት በሳዑዲ ዓረቢያ የሚገኙ ሲሆን የችሎት ክርክራቸውን እያካሄዱ ያሉት ጠበቃ አቁመው ነው።
አላሙዲንና ወዳጆቻቸው በሀገሪቱ በርካታ የስራ ዕድል የፈጠሩ በርካታ ፕሮጀክቶችን በጋራ ሲያከናውኑ ከሶስት ዓስርት ዓመታት በላይ ቢቆዩም ባለፉት ሶስት ዓመታት በመካከላቸው በተከሰተ ውዝግብ ወደ ከረረ ውዝግብና አለመግባባት ተዘፍቀዋል።
Via ዋዜማ ራዲዮ