አቶ እስክንድር ነጋ በመንግስት ጫና ሳቢያ በፓርቲያቸው በአመራርነትም ሆነ በአባልነት መስራት የማይችሉበት ደረጃ መድረሳቸውን ገለጡ
የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ፕ/ት አቶ እስክንድር ነጋ ፤ በመንግስት ጫና በአባልነትም ሆነ በአመራርነት መስራት የማልችሉበት ደረጃ ላይ መድረሳቸው አሳወቁ።
አቶ እስክንድር ሀምሌ 16/2014 ዓ/ም ካሉበት ቦታ ሆነው ፃፉት በተባለውና በፓርቲው የፌስቡክ ገፅ ላይ በተሰራጨ ደብዳቤ በመንግስት ጫና ሳቢያ በፓርቲያቸው በአመራርነትም ሆነ በአባልነት መስራት የማይችሉበት ድረጃ መድረሳቸውን ገልፀዋል።
” ኢትዮጵያ ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንድትሻገር ለዓመታት የበኩሌን አስተዋጽዖ ሳደርግ መቆየቴ ይታወሳል። ” ያሉት አቶ እስክንድር ” በአሁኑ ጊዜ ግን፣ ተረኛው ጨቋኝ መንግስት በባልደራስም ሆነ በሃገር አቀፍ ደረጃ በፈጠረው የለየለት አምባገነናዊ ጫና ሳቢያ፣ በአባልነት ሆነ በአመራርነት መስራት የማልችልበት ደረጃ ላይ ደርሻለሁ። ” ብለዋል።
በዚህም ” የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፣ አባላት፣ በየደረጃው ያሉ የፓርቲው አመራር አባላት፣ መላ አባላትና ደጋፊዎች፣ እንዲሁም መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ከፓርቲው ምክትል ፕሬዝደንት አቶ አምሃ ዳኘው ጋር ሙሉ ለሙሉ በመተባበር ስራቸው የተቃና እንዲሆን እንድትተባበሯቸው በትህትና እጠይቃለሁ። ” ብለዋል።
በእቅድ ላይ ያለው የባልደራስ ጠቅላላ ጉባኤ በተሳካ ዝግጅት እንዲከናወን ያላቸው ተስፋ የገለፁት አቶ እስክንድር ” ባልደራስ በሃገር አቀፍ ፓርቲነት አድጎ የማየት ተስፋችን ወደ ተግባር ተተርጉሞ ለማየት የፈጣሪ መልካም ፈቃድ ይሁን ” ሲሉ መልዕክታቸውን አጠቃለው።