የ2014 ዓ.ም ጾመ ፍልሰታ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ መልዕክት ከአገረ አሜሪካ

0
0 0
Read Time:3 Minute, 32 Second

የ2014 ዓ.ም ጾመ ፍልሰታ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት መልዕክት ከዋሽንግተን ዲሲ ሰሜን አሜሪካ።
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
በሀገር ውስጥም ሆነ በመላው ዓለም ዙርያ የምትገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናንና ምእመናት፣ እንዲሁም ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት በሙሉ እንኳን ለጾመ ፍልሰታ ለማርያም በሰላም አደረሳችሁ !!
“ወተዘከረ ሣህሎ ዘይቤሎሙ ለአበዊነ ለአብርሃም ወለዘርዑ እስከ ለዓለም፤ ለአባቶቻችን ለአብርሃምና ለዘሩ የነገራቸውን ይቅርታውን ለዘላለሙ አሰበ” (ሉቃ.፩፥፶፭ )
ማኅደረ መለኮት፣ ማኅደረ መንፈስ ቅዱስ የሆነች እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልታ እግዚአብሔርን ባመሰገነችበት ምስጋናዋ፣ ከላይ የተጠቀሰውን ይህንን ዐረፍተ ነገር መናገሯን በቅዱስ ወንጌል ተጽፎልናል፡፡
ቅድስት ድንግል ማርያም በዚህ ምስጋናዋ የገለፀችው ዓቢይ መልእክት የክብር አምላክ እግዚአብሔር የተናገረውን የማያስቀር አምላክ መሆኑን ነው፤ ኤልሻዳይ እግዚአብሔር የተስፋ አምላክ ነውና በየጊዜው ለፍጡራኑ የተስፋ ቃል ይሰጣል፣ ቃል ኪዳንም ይገባል፣ እግዚአብሔር በክዋኔው ዘላለማዊ እንደሆነ ሁሉ ቃል ኪዳኑም ዘላለማዊ እንደሆነ “ወተዘከረ ኪዳኖ ዘለዓለም፣ ማለትም ዘላለማዊ ቃል ኪዳኑን አሰበ” በማለት ቅዱስ መጽሐፍ ያስተምረናል፡፡ እግዚአብሔር መፍቀሬ ሰብእ ከሆነ አምላካዊ ጠባዩ በመነጨ ፍቅሩ ከመጀመሪያው ሰው ከአዳም ጀምሮ ለአበው ቃል ኪዳን እንደገባላቸው ተጽፎልናል፣ ይልቁኑም ለአብርሃም “በዘርእከ ይትባረኩ ኲሎሙ አሕዛበ ምድር ማለትም የምድር አሕዛብ ሁላቸው በዘርህ ይባረካሉ” ብሎ ለዓለም ሁሉ የሚሆን በረከትና ድኅነት ከእርሱ እንደሚገኝ ቃል ኪዳን ገብቶለታል፤ ቅድስት ድንግል ማርያም “ለአብርሃምና ለዘሩ የተናገረውን ቃል አሰበ” ብላ የገለፀችውም ይህንን ቃል ኪዳን ነው፤ ምክንያቱም የምድር አሕዛብ ሁሉ የሚባረኩበት ዘር ኢየሱስ ክርስቶስ በወቅቱ በማኅፀኗ እንዳለ ታውቃለችና ነው፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት
ከቅድስት ድንግል ማርያም ምስጋና የምንማረው ዓቢይ ትምህርት ሁሌም የእግዚአብሔርን ድንቅ ፍቅር በማስታወስ፣ በመናገርና በመመስከር ማመስገን፣ ማሰብና ማስታወስ እንደሚገባን ነው፡፡ እግዚአብሔርም ይህንን እንደሚወድ “ወተዘከሩ መንክሮ ዘገብረ፤ ያደረገውን ድንቅ ሥራ አስቡ” ብሎ ነግሮናል፡፡
እግዚአብሔር የተናገረውን የማያስቀር ታማኝ አምላክ ነውና ለአብርሃምና ለዘሩ የገባውን ቃል ኪዳን እነሆ ከዛሬ ሁለት ሺሕ ዐሥራ አምስት ዓመታት በፊት ቃል ኪዳኑን እንደተስፋ ቃሉ በተግባር ፈጽሞአል፤የምድር አሕዛብ ሁሉ የሚባረኩበት ወይም የሚድኑበት ዘር እርሱም መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የአብርሃም ዘር ከሆነች ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ የምድር አሕዛብ የሆነውን በሙሉ በደመ መስቀሉ ባርኮ አንጽቶና ቀድሶ አድኖአል፡፡ እግዚአብሔር የምድር አሕዛብ ሁሉ በምሕረትና በይቅርታ እንድንባረክበት የሰጠን ዘር አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ ሁላችንም መገንዘብና ማመን ይገባናል፣ ይህንን ማወቅ፣ ማስተዋልና ማመን ብፅዕና ማግኘትን ያስከትላል፡፡ ቅድስት ድንግል ማርያም “ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ነሽ ይሉኛል” ስትል የተናገረችው ቃለ ትንቢት የእግዚአብሔር ማደሪያ ቤተ መቅደስ መሆኗን ስለተረዳች ነው፡፡
እኛም እንደእሷ “አንትሙ ውእቱ ታቦቱ ለመንፈስ ቅዱስ ማለትም እናንተ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ናችሁ” ተብለናል፤ ቅድስት ድንግል ማርያም ማኅደረ መለኮት የሆነችው በሃይማኖት በትሕትና ነው፤ ከዚህ አንጻር እኛም በሃይማኖት ጥላ ሥር ሆነን በትሕትና በፍቅር በአንድነት የምንኖር ከሆነ የእግዚአብሔር ማደሪያ ለመሆናችን ሌላ ምስክር አያስፈልገንም፡፡ ምክንያቱም ጌታችን “ተፋቀሩ በበይናቲክሙ ወእምከመ ተፋቀርክሙ በበይናቲክሙ የአምረክሙ ዓለም በዝንቱ ከመ አርዳእየ አንትሙ፤ እርስ በርሳችሁ አብዝታችሁ ተፋቀሩ፤ እርስ በርሳችሁ ከተዋደዳችሁ ደቀመዛሙርቴ እንደሆናችሁ ዓለም በዚህ ያውቃል” ብሎ እንዳስተማረን ምስክሮቻችን ፍቅር አንድነትና ትሕትና ይሆናሉና ነው፡፡
የተወደዳችሁ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት
ከነገው ዕለት ጀምሮ የምንጾመው የጾመ ማርያም ዋና ዓላማ ጠብንና ጥላቻን ማሸነፍ የሚያስችል የይቅርታን የፍቅርንና የአንድነትን ኃይል በመለኮት ፈቃድ ለማጐልበት ነው፤ የተለየ የጾም፣ የጸሎት፣ የንሥሐ ጊዜ ወስኖ እግዚአብሔርን መለመንና ከእርሱ ጋር መገናኘት ከጥንት ጀምሮ የሃይማኖት መርሕ ነው፡፡ በዚህ መርሕ ተመርተው ሕዝባቸውንና ሀገራቸውን ከመከራና ከፈተና የታደጉ ቅዱሳን ብዙ ናቸው፡፡ የልቡናቸውን መልካም ምኞት ያገኙም እንደዚሁ ብዙ ናቸው፡፡
እኛም ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን በደነገገችው የቀኖና ድንጋጌ መሠረት የምንጾመው ጾመ ማርያም፣ ቅዱሳን ሐዋርያት ጌታችን የልቡናቸውን መሻት እንዲፈጽምላቸው የጾሙትና የለመኑትን ያገኙበት ኩነት መነሻ አድርገን እግዚአብሔር እንደነሱ የልቡናችንን መሻት እንዲፈጽምልን በማመንና ተስፋ በማድረግ ነው፤ ከዚህ አንጻር የቅድስት ድንግል ማርያም ነገረ ትንሣኤ ወፍልሰት በማሰብ ከእግዚአብሔር ጋር ለመገናኘት በብርቱ እንጥራለን፣ እንጾማለን፣ እንጸልያለን፣ በንሥሐም ወደ እርሱ እንቀርባለን፣ ቅዱስ ምሥጢረ ቊርባንንም እንቀበላለን፤ በዚህም ከእግዚአብሔር ጋር እንገናኛለን፡፡ ይህ ሲሆን እግዚአብሔር የልባችንን መሻት በብሩህ ገጽ ተቀብሎ ይፈጽምልናል፡፡ ሁላችንም እንደምንገነዘበው በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎት ፍጹም ሰላም ያላት ሀገር እንድትኖረው ነው፤ ይህ ትክክለኛ ፍላጎት ነው፡፡ ይሁንና ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ ሁሉም ነገር ስለማይሆን ፍጹም ሰላም በሀገር ሰፍኖ ሕዝባችን እግዚአብሔር በሰጠው ምድር በፍቅር፣ በአንድነት በነጻነትና በእኩልነት እንዲኖር ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ሁሉ በዚህ ወቅት የቅድስት ድንግል ማርያምን ጸሎትና ስእለት ተማኅፅኖና አስተበቊዖት አጋዥ አድርገን በልዩ ሱባዔ ወደ እግዚአብሔር በመቅረብ በንሥሐ፣ በጾም፣ በጸሎት፣ ነዳያንን በመርዳትና ቅዱስ ቊርባንን በመቀበል እሱን መማፀን ይኖርብናል፡፡
በመጨረሻም
በሀገራችን የተከሠቱት ያላስፈላጊ ግጭቶችን በድርድር ለመፍታት እየተሞከሩ ያሉ አንዳንድ የሰላምና የውይይት ድምፆች ተስፋ ሰጪ ስለሆኑ ሥር ሰደው፣ በተግባር ተተርጉመው፣ ለተጐዳው ሕዝባችን መጠገኛ ይሆኑ ዘንድ፣ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ሁሉ በዚህ ዙርያ በሱባዔው ወቅት ወደ እግዚአብሔር አቤት በማለትና ሂደቱን በመደገፍ የበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ፣ መንግሥትም ሆነ የዓለም አቀፉ ማኅበረ ሰብ በዚህ በጎ ሐሳብ እንዲገፉበትና ሕዝባችንንና ሀገራችንን ከጥፋት እንዲታደጉ አባታዊ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ጾሙን የሰላም የሥርየት የፍቅር የአንድነት ጾም ያድርግልን፡፡
ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን
አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ዋሽንግተን ዲሲ አሜሪካ ፡፡

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *