“የጠላሽ…. ይጠላ….!!”
” የጠላሽ…. ይጠላ….!! “ ከአለባቸው ደሳለኝ አበሻ (ለንደን)
አፈሩን ያቅልለት ነፍሡን ይማረውና ድምፃዊ ጥላሁን ገሰሰ
“ የጠላሽ ይጠላ ብድሩ ይድረሰው
የጎዳሽ ይጎዳ ተፈጥሮ ትውቀሰው
በከንቱ የሚያማሽ ስምሽን የሚያነሳ
ክፉ በመሆኑ አለበት ወቀሳ … “
እያለ በምሬት እየጮህ ያንጎራጎረው እርግማን አሁን ድረስ በጆሮየ ውስጥ ያቃጭላል::
ጥላሁን ወዶ አልነበረም “የጠላሽ ይጠላ “ እያለ ለዘመናት የጮህው:: አሁንም የትግራይ ሕዝብ ወደ አምላኩ መጮህ አለበት::
እንደነ፣ ደብረፅዮን እንደ፣ ጌታቸው እረዳ፣ እንደ ጻድቃን ገብረ ትንሳይ፣ ወዘተ… የመሳሰሉ አረመኔ ሰይጣኖች በትግራይ ምድር ዳግም እንዳይፈጠሩ የትግራይ ሕዝብ እንደ ዕምነቱ ወደ ፈጣሪው ኤሎሔ ብሎ የጠላሽ ይጠላ በማለት መጮህ አለበት::
የአሸባሪው ትህነግ እኩይ ተግባር በትግራይ ሕዝብ ብቻ አላበቃም:: በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የመንፈስ ሽብር ፈጥሯል:: አንድ ለጋ የትግራይ ትውልድ/የትግራይ ወጣት እንዲቀጠፍ ምክንያት ሆኗል:: በውጤቱም አገር ያልተገባ መስዋእትነት ለመክፈል ተገዳለች ::
በአሸባሪው ትህነግ አጥፊ ቡድን የህዝቡ ላብና እውቀት የፈሰሰባቸውን የኢኮኖሚ ተቋሞች የዘመናዊ ስልጣኔ ምልክት የሆኑ ታሪካዊ ቦታዎች፤ ትምህርት ቤቶችና የጤና ጣቢያዎች ወድመዋል። የህዝብ መገልገያ ተቋማት ወድመዋል፤ተዘርፈዋል:: ትህነጎች በሀይማኖት ተቋማት ያልተገቡ ኢሞራላዊ ተግባራትን በመፈጸም ለህዝብ እምነት ያላቸውን ንቀት በአደባባይ ገልጸዋል።
በስልጣን በነበሩባቸው ዘመናት ለዘመናት በሰላም አብረው በመኖር የአንድ ቤተሰብ አካል የሆኑትን የአገሪቱን ሕዝቦች የሚለያይ፤ የአንድነት ገመዳቸውን የሚበጣጥስ ቋንቋና ዘርን መሰረት ያደረገ የፖለቲካ ስርአት በመፍጠር አገርን ለጥፋት መዳረጋቸው የቅርብ ግዜ ትውስታችን ነው።
ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ ደግሞ የትግራይን ሕዝብ የመንግስት ጠላት አድርገው በማቅረብ ቢያንስ ያለመተማመን እንዲፈጠር የመተሳሰብ የልብ ግንኙነት እንዳይኖር ጥላችን በመንዛት እጅ… እጅ ፣ በሚል ፕሮፖጋንዳ በሕዝብና በመንግስት መካከል ያለውን ግንኙነት በጠበንጃ አፈሙዝ ቀይረው ህዝቡን ለሞትና ለስደት ዳርገውታል: :
ትህነግ ትናንት ሆነ ዛሬ ለአገራችን የሰብአዊነት ስጋት የሆነ አሸባሪ ድርጅት ነው:: ላለፉት 27 አመታት ለእራሳቸው ፍላጎትና ጥቅም ሲሉ በስልጣን ላይ ስልጣን በሀብት ላይ ሀብት ሲሰበስቡ ለሆዳምነትና ሞራለቢስነታቸው ወሰንና ድንበር ያልነበራቸው. ስግብግብ የቀን ጅቦች እንደነበሩ ዛሬ መላው ዓለም በደንብ እያወቃቸው መጥቷል ::
ትናንት ስልጣን ይዘው በነበረበት ወቅት ትልቁ ችግራቸው ስልጣንና ዕውቀትን አቀናጅቶ የፖለቲካ ልዩነቶችን በማቻቻል ተባብሮ ለመስራት አለመቻላቸው፤ እራስን ብቻ ትክክል አድርጎ በመቁጠር ሌላውን ጠላት አድርገው መውሰዳቸው ነበር። በዚህ አጥፊ ባህሪያቸው የተነሳም ሕዝቡ አሽቀንጥሮ፣ በትረ መንግስታቸውን ቀምቶ ታሪክ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል::
በአገራችን በተቀጣጠለው. የመደመር ለውጥ ሁሉንም በይቅርታ ዘግተን በአገር ግንባታ ተሰልፈን የዲሞክራሲ ስርአትን በማነፅ ስለ ፍቅር ስለወንድማማችነት ስለአንድነት በመቆም ጠንካራ አገር እንፈጥራለን ብለን ስንነሳ ጭራሽ ይግረማችሁ ብለው የበቀል ጦርነት በማወጅ ሀያ ዓመት ቀበሮ ጉድጓድ ውስጥ ተኝተው የጠበቋቸውን የሰሜን ዕዝ የመከላከያ አባሎች በተኙበት የዛሬ ሁለት አመት በጥይት እረሸኗቸው:: እንደ ባእድ አያንገላቱም ክብርና ስብእናቸውን በማዋረድ ምርኮኛም አደረጓቸው። ይህንን የጭካኔ የክህደት ተግባር መቼም ቢሆን የማንረሰው እውነት ነው !
በጥይት የፈጇቸው ወታደሮች አስከሬናቸው እንኳን እንዳይቀበር ከልክለው እርቃናቸውን አደባባይ ጥለው በአስክሬናቸው ላይ ጨፍረዋል … በህይወት እያሉ ሲኖ ትራክ የነዱባቸውም ጥቂት አይደሉም:: ልብሳቸውን አስወልቀው እርቃነ ስጋቸውን በባዶ እግር ወደ ጎረቤት አገር ያሰደዷቸውም እነሱን ለመጠበቅ በሺዎች ኪሎ ሜትር አቋርጠው በዛው የተገኙ ለእነሱ ባለውለታና የአገሪቱም የቁርጥ ቀኝ ልጆች ናቸው:: ይህ አረመኔያዊ ጭካኔ “ታሪክና ትውልድ የማይረሳው የበደል ፍፃሜ “ ነው። ይህች ቀን የኢትዮጵያ ሰማዕታት ቀን ነች “ መቼም ቢሆን እናስባታለን “ ::
የኢትዮጵያ ክብር ጠባቂ ሰይፍ እና ጋሻ ሆነው ያለፉትን የሰሜን ዕዝ መከላከያ ሰራዊት አባሎችን በበኩሌ ባሰብኩ ቁጥር በደም ዋጋ የተገነባው መከላከያ ሰራዊታችን ውድ ሕይወቱን ለአገሩ በመስጠት እየከፈለ ያለውን መስዋዕትነት በምንም ቃላት ለመግለፅ እንደማልችል እረዳለሁ ::
በአንፃሩ ደግሞ አሸባሪው ትህነግ ዛሬም የትግራይን ሕዝብ የአጥፍቶ መጥፋት ትርኢቱ ተካፋይ አድርጎ ለማቅረብ የኢትዮጵያ መንግስት ለለውጥ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በትግራይ ሕዝብ እንደመጣበት አድርጎ በአጥፊና ዘረኛ ቅስቀሳ ወጣቱን የሽብር ድርጊቱ ተሳታፊና የእልቂቱ ሰለባ እያደረገው ይገኛል ::
ቡድኑ በእብሪትና በቀቢሰ ተስፋ በሕዝብ ላይ ሶስት ጊዜ ወረራ አካሄዷል:: ይህ አስቀያሚና ወራዳ ተግባር የወያኔ አንድ የተበላሸ የታሪክ ዘመን መባቻ ተደርጎ መመዝገቡ የብዙ. ኢትዮጵያውያን እናቶች እርግማን ይመስለኛል .::
የትግራይ ሕዝብ ግን እንደሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የአዲሱ ስርአት የለውጥ ራዕይ አጋር ለመሆን የተነሳ ሕዝብ ነበር :: ምንም እንኳን በአሸባሪው ትህነግ ካድሬዎች የጥላቻ መርዝ እንዲጨልጥ ተደረጎ በስቃይ፣ በጨለማ እና በጠኔ እየተገረፈ እንዲኖር የተገደደ መንፈሳዊና ሕሊናዊ ነፃነት ያጣ ህዝብ ቢሆንም ።
እንኳን እንደ ኢትዮጵያ አዲስ የእድገት ምእራፍ በጀመረች አገር ይቅርና ለማንኛውም ማህበረሰብ ቢሆን ጦርነት የሰላምና የልማት ጠንቅ በመሆኑ ማህበራዊ ሕይወትን ይረብሻል:: በሰላም ሰርቶ ለመኖር የሚፈልግን ሕብረተሰብ የማይነጋ መራራ ለሊት እንዲያሳልፍ የሚያደርግ ነው:: ጦርነት ውጤቱም ቢሆን የሚያስደስት ሳይሆን መድረሻ የሌለው ትርምስ ነው ::
ዛሬ አገራችንን ከአሸባሪው ትህነግ አገር የማፍረስ ተልእኮ ለመታደግ፤ የትግራይንም ህዝብ ከአሸባሪው ቡድን መንፈሳዊና ሕሊናዊ ባርነት ለመታደግ የምናካሒደውን ጦርነት ተገደን ገባንበት እንጂ ምርጫችን ምን ግዜም ሰላም ነበር ::
አሸባሪው ቡድን ግን እታገልልሀለሁ የሚለውን የትግራይን ህዝብ ጨምሮ ደም በማፍሰስ፣ ሕዝብን በማሰቃየት.፣ በማፈን፣ በመሰወር፣ በመጨፍጨፍና በመግደል የሚረካ በመሆኑ በአገርና በህዝብ ላይ ታሪክ ይቅር የማይለው ግፍ እየፈፀመ በአገራዊ ሰላማችንም ላይ ተግዳሮት ሆኖ ይገኛል::
ቡድኑ ደም በማፍሰስ የሚረካ አሸባሪ ቡድን መሆኑን በአፋርና በአማራ ሕዝብ ላይ የፈፀመውን ግፍ በማስረጃ ማቅረብ ይቻላል: : የንጹሀንን ደም፣ በማፍሰስ የሚረኩ ሰዎች ደግሞ ፍፁም ጤነኞች ናቸው ለማለት አይቻልም: :
ቡድኑ የሚያራምደውን የሽብር ጥቃት አቁሞ ያለፈውን እረስቶና ፍርዱን ለታሪክ አስረክቦ ትጥቁን በመፍታት በዘመናዊ ፖለቲካ በውይይትና በይቅርታ አምኖ አብሮ በሰላም ለመኖር በደልን ለመርሳት ቃል. እንዲገባ ላለፉት ሁለት አመታት ሲለመን ከርሟል::
ነገር ግን አንድን የጋራ ታሪክ የመሰረቱትን ሕዝቦች በፈጠራ ታሪክ ለመከፋፈልና የቅጥፈት ፕሮፖጋንዳ በማራገብ የአባቶቻችንን አኩሪ ታሪክ በመካድ ለትግራይ ሕዝብ የተቆረቆረ በመምሰል ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ከታሪካዊ ጠላቶቿ ጋር በማበር ጠመንጃ አንግቶ ምሽግ ቆፍሮ የኢትዮጵያን ሕዝብ ወግቷል ::
ይህም ሆኖ አሁንም በድጋሚ እጃችንን ለሰላም የዘረጋነው ሳንበደል ቀርተን ሳይሆን ሁሉም ነገር እንዳልነበረ ተቆጥሮ በሕዝቦች ላይ የተፈፀመው ግፍ ዶሴው ተዘግቶ ለዚህ ሁሉ ችግር ያበቁንን መሰረታዊ ጠንቆች ለትውልዱ ትምህርት በሚሰጥ መልኩ በሰላም ለመዝጋት ነበር ።
እነዚህ ጠንቆች ተመልሰው የማይመጡበትን ሁኔታ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ዘግተን ለሁሉም እኩል የሆነች የተረጋጋች ኢትዮጵያን ለማቆየት ስንልም ነበር ያለቅድመ ሁኔታ ለሰላም በሚደረግ ውይይት ዝግጁ ነኝ ሲል የኢትዮጵያን መንግስት አጨብጭበን የደገፍ ነው::
እነሱ ግን በሀያ አንደኛው ክፍለ ዘመን እየኖሩ አሁንም ከጫካው ፖለቲካቸው ጋር ነፍሳቸው ተጣብቆ የአልባኒያን ዲሪቶ ዲሞክራሲ እየጎተቱ ለተከበረው የትግራይ ሕዝብ ደንታ ሳይሰጣቸው የጀመሩትን የማተራመስና የማሸበር ተግባር ቀጥለውበታል::
ዛሬ እንኳን በአስራ አንደኛው ሰአት ለትግራይ ሕዝብ ቢያስቡ ኑሮ ደቡብ አፍሪካ የሚደረገውን የሰላም ንግግር በሸምጋዮች በኩል ተደራድረው ትጥቃቸውን ፈተው ለሰላም እጃቸውን ለመስጠት መስማማት ይጠበቅባቸው ነበር: : ቢያንስ ይህን ሁሉ ጥፋት ካጠፉ በኋላ ተፀፅተው አብሮ ለመኖር. በኢትዮጵያዊነት ለመተሳሰር በደልን ለመርሳትና የጋራ አገርን በጋራ ጠብቆ ለትውልድ ለማስተላለፍ ወዘተ..ቃል መግባትና የሕብረቱን ሽምግልና መቀበል ነበረባቸው: :
ነገር ግን ላለፉት ሀምሳ አመታት ቡድኑ የትግራይን ሕዝብ የአመፅ ትርምስ ባሕል ፈጥሮ ያአፈሰሰው ደምና እንባ አልበቃ ብሎት ትግራይን በራሷ ልጆች የገና ዳቦ እያደረጓት ይገኛል። ዛሬ በተግባር እንደምናየው ከላይም ከታችም በእሳት እንድትነድ አድርገዋታል። ግን አሁንም ድረስ ትግራይን የእርስ በእርስ ፍጅት መፀነሻ በማድረግ ጀርባዋ የተላላጠ እንዲሆን በማድረጋቸው ሲጸጽታቸው አይታይም::
ደቡብ አፍሪካ ላይ ለሰላም ውይይት ተቀምጠው አብይ ነጥቦች እያሉ የሚያስማሙባቸው ሀሳቦችም በልዩነት ላይ ብቻ ያለቅጥ አትኩረው ችግሮቹን ለመፍታት አለመፈለጋቸው ምን ያህል በጥፋትና በተስፋ መቁረጥ ውስጥ መዘፈቃቸውን አመላካች ነው። ስህተትን መቀበልና ማረም እንደ ነውር የሚቆጥሩት አሸባሪዎቹ ትህነጎች፣ የተሠጣቸውን የሰላም ዕድል ላለመጠቀም ለሰላም እጁን የዘረጋውን የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት አሻፈረኝ ብለው ስለ አጉል ግትር ፀባያቸው ተጨማሪ ዋጋ መክፈላቸው አይቀሬ ነው : :
የኢትዮጵያ ስጋት የሆነው አሸባሪው ትህነግ ሕገ መንግስቱን አክብሮ ትጥቁን ሲፈታ ብቻ መሆኑን የኢትዮጵያ መንግስት አቋሙን አስታውቋል። በትዕግስትና በብልሀት የሰላም ውይይቱ እንዲሳካ የአገራችንን ብሔራዊ ጥቅም በማይነካና በሉአላዊነታችንና በክብራችን እንደማንደራደር አስቀድሞ ይፋ በመድረጉ የኢትዮጵያን መንግስት ምስጋና ይገባዋል : :
አሸባሪው ትህነግ ግን ለጥፋት አላማ ግብ መምቻ የያዙትን አገር የማፈራስ ተልእኮ በሚተናነቃቸው ኢትዮጵያዊነት የታሪክ ፍርድ እንደሚቀበሉ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል:: የኢትዮጵያ አምላክም ይችን አገር ጥሎ አይጥላትምና ለኢትዮጵያ የደገሱላትን ጥፋት የሕዝብ እንባ እርግማን ሆኖ በምድራቸው በበደሉት ሕዝብ ፊት ላደረሱት በደል ዋጋ ይከፍላሉ :: ያን ግዜ ከትግራይ ሕዝብ ወንድሞቻችን ጋር በጋራ ሆነን የጠላሽ ይጠላ በማለት አብረን እንዘምራለን:: ለዛሬው በዚሁ አበቃሁ በሌላ ርዕስ እስከምንገናኝ ቸር እንሰንበት::
ከአለባቸው ደሳለኝ አበሻ (ለንደን)
Source: አዲስ ዘመን ሐሙስ ጥቅምት 24 ቀን 2015 ዓ.ም