የድሬዳዋን ዘርፈ ብዙ ጥያቄዎች ለመመለስ ሪፈረንደም እንዲካሄድ አማራጭ ሐሳብ ቀረበ – ሪፖርተር

0
0 0
Read Time:2 Minute, 29 Secondየድሬዳዋ አስተዳደር ራሱን የቻለ ክልላዊ መንግሥት እንዲሆን ወይም ከሶማሌና ኦሮሚያ ክልሎች ወደ አንዱ እንዲጠቃለል ሪፈረንደም እንዲካሄድ ለፌዴራል መንግሥት ጥያቄ ቀረበ፡፡ ጥያቄው የድሬዳዋ አስተዳደር እያጋጠመው ካለው የበጀት እጥረት፣ ፍትሐዊ ያልሆነ የሀብት ክፍፍልና በዕድገት የመቀጨጭ ችግሮችን ለመቅረፍ የማይቻል ከሆነ፣ መፍትሔ ያስፈልጋል በሚል ለሁለቱ ምክር ቤቶች ቀርቧል፡፡

‹‹ድሬዳዋ በቻርተር በቀጥታ በፌዴራል መንግሥት ሥር መግባቷ በእጅጉ ጎድቷታል፡፡ ሌሎች ክልሎች ያመነጩትን ገቢ በቀመር ከፌዴራል መንግሥት ጋር ሲካፈሉ፣ ከድሬዳዋ የሚመነጨው ግብር ግን በቀጥታ ለፌዴራል መንግሥት ገቢ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ድሬዳዋ ከምታመነጨው ትልቅ ገቢ በፍትሐዊነት ተካፋይና ተጠቃሚ እንድትሆን የግድ የክልል ጥያቄ ጉዳይ መፍትሔ እንዲበጅለት እየተጠየቀ ነው›› ሲሉ የድሬዳዋው ተወካይ አቶ አብዱልጀዋድ መሐመድ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ድሬዳዋን በመወከል ሁለት የፓርላማ አባላት ያሉ ሲሆን አቶ አብዱልጀዋድ አንዱ ናቸው፡፡

ረቡዕ ጥር 3 ቀን 2015 ዓ.ም. የፌዴሬሽን ምክር ቤትና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጋራ ስብሰባ ባካሄዱበት ጊዜ ጥያቄው የቀረበ ሲሆን፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገርና የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ፣ ጉዳዩ በሌላ ጊዜ የሚታይ መሆኑን በመግለጽ፣ በዕለቱ በነበረው የንብረት ግብር ጉዳይ ላይ ብቻ እንዲተኮር ጠይቀዋል፡፡

ድሬዳዋ ከ1996 ዓ.ም. ጀምሮ በቻርተር በቀጥታ በፌዴራል መንግሥት ሥር የምትተዳደር ሲሆን፣ ይህም ከሶማሌና ኦሮሚያ ክልሎች የሚቀርበውን የይገባኛል ጥያቄ ለማለዘብ፣ ኢሕአዴግ ያመጣው የአስተዳደር አማራጭ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም የኦሮሚያና የሶማሌ ክልሎች ድሬዳዋን በየአራት ዓመቱ በመቀያየር በተራ ያስተዳድራሉ፡፡ ለድሬዳዋ የሚደርሰው የተወሰነ የድጎማ በጀትም በክልል መንግሥታቱ መልካም ፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ መሆኑን የድሬዳዋ ባለሥልጣናት ይገልጻሉ፡፡

በድርዳዋ ከሚገኙ ኃላፊነታቸው የተወሰነ ኩባንያዎች፣ ሁሉም የገቢ ግብርና ሌሎች የታክስ ዓይነቶች በቀጥታ ለፌዴራሉ መንግሥት ገቢ የሚሆኑ ሲሆን፣ የድሬዳዋ አስተዳደር በራሱ መሰብሰብ የሚችለው እጅግ አናሳ ግብ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ ከእነዚህ የግብር ምንጮች የድሬዳዋ አስተዳደር በአማካይ በዓመት የሚሰበስበው ከሁለት ቢሊዮን ብር በልጦ እንደማያውቅ ሪፖርተር ከድሬዳዋ ባለሥልጣናት ያገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ በሌላ በኩል በድሬዳዋ የሚገኙ የፌዴራል ገቢዎችና ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች፣ ከዚህ በብዙ እጥፍ የበለጠ ሰብስበው ለፌዴራል መንግሥት ገቢ እንደሚያደርጉ ተገልጿል፡፡ ድሬዳዋ በዓመት የሚደርሳት የድጎማ በጀትም ከ1.6 ቢሊዮን ብር በልጦ እንደማያውቅ መረጃው ያመለክታል፡፡

‹‹ድርዳዋ እጅግ ብዙ የገቢ ምንጮች አሏት፡፡ በዋናው የኢትዮ ጂቡቲ ንግድ መስመር ላይ በመሆኗ ብዙ ላኪዎችና አስመጪዎች አሉ፡፡ ብዙ የማምረቻ ድርጅቶች አሉ፡፡ አዲስ አበባ በራሱ ብድር መውሰድን ጨምሮ ብዙ የፋይናንስ አማራጭ አለው፡፡ የፌዴራል መንግሥት አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ድሬዳዋ ላይ ፈሰስ በማድረግ እንደ አዲስ አበባ እንድታድግም አላደረገም፡፡ የሚገኘው ገቢ በሙሉ ወደ ፌዴራል ይሄዳል፡፡ በቻርተር መተዳደር ከጀመረች ወዲህ ዕድገቷ ወደኋላ ተመልሷል፤›› ይላሉ አቶ አብዱልጀዋድ፡፡

በሌላ በኩል አስተዳደሩ ለድሬዳዋ ሕዝብ ሳይሆን በቅርበት ለሚገኙት የሶማሌ፣ ኦሮማያና ጂቡቲ ሕዝቦች፣ እንደ ጤና፣ ትምህርትና ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶችን እንደሚያቀርብ የክልሉ ባለሥልጣናት ይገልጻሉ፡፡ ነገር ግን አስተዳደሩ ያለው በጀት መሠረታዊ ፍላጎቶችን ለድሬዳዋ ሕዝብ ራሱ በምልዓት እንዲያቀርብ ማድረግ አለማስቻሉ ተገልጿል፡፡ ምንም እንኳን የክልልነት ጥያቄው እንዲፈታ በተደጋጋሚ ለመንግሥት ሲቀርብ መቆየቱ ቢገለጽም፣ ሕገ መንግሥቱ ካልተሻሻለ በቀር ሊፈታ እንደማይችል መንግሥት ሲገልጽ ቆይቷል፡፡

ይሁን እንጂ ጉዳዩ በቅንነት ከታየ ወደ መፍትሔ መሄድ እንደማይከብድ የድሬዳዋ ኃላፊዎች ይገልጻሉ፡፡ ጉዳዩ እየጀመረ ባለው አገራዊ ምክክር መድረክም ሊነሳ ይችላል ተብሎ ይታሰባል፡፡

‹‹የእኛ ኃላፊነት የድሬዳዋ ሕዝብን ጥያቄ ለመንግሥት ማቅረብ ነው፡፡ መፍትሔው ይኼ መሆን አለበት ብለን በራሳችን መወሰን አንችልም፡፡ ጥናት ተደርጎ መፍትሔው ድሬዳዋን ክልል ማድረግ ወይም ከሁለቱ የክልል መንግሥታት ወደ አንዱ ማጠቃለል ወይም ሌላ የመፍትሔ አቅጣጫ ሊቀመጥ ይችላል፡፡ ከዚያ ጉዳዩ ወደ ሕዝበ ውሳኔ አምርቶ በሕዝብ ምርጫ የመጨረሻው ውሳኔ ሊሰጥ ይችላል፡፡ የፖለቲካ ውሳኔም ሊያስፈልገው ይችላል›› ብለዋል አቶ አብዱጀዋድ፡፡ እነዚህ ጉዳዮች ገና በፌዴራል መንግሥት መታየት ያልጀመሩ ሲሆን፣ የድሬዳዋን ቻርተር የመከለስ ሥራ ግን እየተሠራ መሆኑ ታውቋል፡፡ 

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *