አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴን በመተካት በተመድ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ በመሆን ተሾሙ:
አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴን በመተካት በተመድ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ በመሆን ተሾሙ:
አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ በተመድ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ሆነው መሾማየውን የዲኘሎማሲ ምንጮችን ጠቅሶ አል ዐይን አማርኛ ዘግቧል።
በቅርቡ ዲፕሎማቶችን ወደ አዲስ አበባ በመጥራት ለአዲስና ነባር ተልዕኮዎች ስልጠና መሰጠቱ ይታወሳል፡፡
በቅርቡ በተለያዩ ሀገራት ተመድበው ሲሰሩ ለነበሩ አምባሳደሮች ምስጋና ከተደረገላቸው መካከል በተመድ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳዳር ታዬ አጽቀስላሴ፣ በፈረንሳይ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሔኖክ ተፈራና ሌሎችም ይገኙበታል።
ከቀናት በፊት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴዔታ ሀላፊነታቸው የተነሱትና በፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሆነው የተሾሙት አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ፣ አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴን ተክተው በተመድ የኢትዮጵያ ቋሚ መልክተኛ መሾማቸው ተገልጿል፡፡
አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ ከዚ በፊት በአፍሪካ ህብረት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ሆነው አገልግለዋል፡፡
ከሰሞኑ ከግብርና ሚኒስትርነታቸው የተነሱት ኡመር ሁሴን ደግሞ በተባበሩት አረብ ኢምሬት የኢትዮጵያ አምባሳደር ተደርገው ተሾመዋል፡፡
ላለፉት አመታት በተመድ የኢትዮጵያ ምክትል ቋሚ መልዕክተኛ የነበሩት አምባሳደር ማህሌት ሀይሉ በፈረንሳይ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ተሹመዋል።
አዲስ የተሸሙት አምባሳደሮችም በዛሬው ዕለት በፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ቃለ መሃላ ፈጽመው ወደ ስምሪት እንደሚገቡ ይጠበቃል፡፡
ይህ በእዲህ እንዳለ ዛሬ ከሰዓት ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊና ምክትላቸው አቶ ሰለሞን አረዳ ከፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ኃላፊነታቸው ይነሳሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡