አራት ሚኒስትሮች በኬክ ተሸኙ
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ፦
– የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ወ/ሮ ዳግማዊት ሞግስ፤
– የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ታከለ ኡማ፤
– የግብርና ሚኒስትር አቶ ኡመር ሁሴን፤
– የጠ/ሚኒስትር ፅ/ቤት ኃላፊ እና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ተፈሪ ፍቅሬን ዛሬ ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በተገኙበት መሸኛታቸውን በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገፁ ላይ አሳውቋል።
ፅ/ቤቱ ሚኒስትሮቹ / የምክር ቤቱ አባላት በ ” ክብር ተሸኙ ” እና ” ቀጣይ ጉዟቸው ስኬታማ እንዲሆንላቸው ይመኛል ” ከማለት የዘለለ ዝርዝር ጉዳይ አላብራራም።
የምክር ቤቱ አባላት ለምን ? በምን ምክንያት ? ወዴት ? እንደተሸኙ በዝርዝር ያልገለፀው የፅ/ቤቱ መረጃን በርካታ ትልልቅ ሚዲያዎች ቀጥታ በመውሰድ እየተቀባበሉት ይገኛሉ።
መረጃው በርካቶችንም ያወዛገበ ሲሆን የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ” ለምን እና ወዴት እንደተሸኙ ? ” የሚለውን መረጃውን ባሰራጨው የፅ/ቤቱ የማህበራዊ ትስስር ገፅ እና በሚዲያዎች ትስስር ገፅ ላይ በመግባት እየጠየቁ ነው።
ዛሬ ሽኝት ተደርጎላቸው ከተባሉት መካከል አቶ ኡመር ሁሴን ኦባ እና አቶ ተፈሪ ፍቅሬ ቡሳ በቅርቡ በፕሬዜዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በአምባሳደርነት መሾማቸውን ወደ ፕ/ት ፅ/ቤት የማህበራዊ ትስስር ገፅ ተመልሰን በመመልከት ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
ወ/ሮ ዳግማዊት እና ኢ/ር ታከለ ለሌላ ስልጣን ታጭተው ይሁን አይሁን የሚታወቅ ነገር የለም።