” የወይብላ ቅድስት ማርያምና ቅዱስ ሚካኤል የጥምቀት በዓል በተለመደው ቦታ ይከበራል ” – ብፁዕ አቡነ ሄኖክ
የወይብላ ቅድስት ማርያምና ቅዱስ ሚካኤል የጥምቀት በዓል በተለመደው ቦታ ይከበራል ” – ብፁዕ አቡነ ሄኖክ
ብፁዕ አቡነ ሄኖክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስና የተዋሕዶ ሚዲያ ማዕከል የበላይ ጠባቂ የቅዱስ ሲኖዶስ አባል የኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓልን አስመልክተው የ “እንኳን አደረሳችሁ” መልእክት አስተላልፈዋል።
በመልዕክታቸውም ፤ የጥምቀት በዓል በአደባባይ ሲከበር 1500 ዓመታትን አስቆጥሯል ብለዋል።
ብፁዕነታቸው፤ በአዲስ አበባ ደረጃ ከጃንሜዳ በተጨማሪ 83 የጥምቀተ ባሕረ ማክበሪያ ቦታዎች መኖራቸውን ገልጸው ጥር 10 ቀን ታቦታቱ ከመንበረ ክብራቸው ወደ ባሕረ ጥምቀቱ በመውረድ ቃና ዘገሊላን ጨምሮ ለ3 ቀናት በየባሕረ ጥምቀቱ እንደሚከበር ተናግረዋል።
በ2014 ዓ.ም የጥምቀት በዓል የወይብላ ማኅደረ መለኮት ቅድስት ማርያም እና ቅዱስ ሚካኤል ታቦታት ከኦሮሚያ ወደ አዲስ አበባ መጥቶ ከሌሎች ታቦታት ጋር አድሮ ሲመለስ ተፈጥሮ በነበረው ግጭት የሰው ሕይወት የመጥፋትና የአካል መጉደል አደጋ በዚህ ዓመት አይደገምም ብለዋል።
በዚህ ዓመት በአደባባይ የሚከበረውን የጥምቀት በዓል ሰላማዊ ለማድረግ ከኦሮሚያ ክልል የመንግሥት ባለሥልጣናትና ከአዲስ አበባ መስተዳድር ኃላፊዎች ጋር ስለበዓሉ አከባበር ሰፊ ሥራ መሠራቱን አውስተው የማኅደረ መለኮት ወይብላ ማርያም በዓልም በዚያው በተለመደው የማክበሪያ ቦታ እንደሚከበር ገልጸዋል።
ብፁዕነታቸው፤ መላው ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን በተለይ በልዩ ልዩ መልክ የተደራጁ የወጣት ማኅበራት ኅብረት፣ ለበዓሉ ድምቀት በሁለንተናዊ ሥራ እየተሳተፉ የሚገኙ ወጣቶችና የሰ/ት/ቤት አባላት ከጸጥታ አካላት ጋር በመናበብና በጋራ በመሥራት ” የክብረ በዓሉን መንፈሳዊ ድባብ እናስጠብቅ ” ሲሉ አሳስበዋል።
(የኢ/ኦ/ተ/ቤ ህዝብ ግንኙነት)