ምርጫ ቦርድ የህወሓትን “ሕጋዊ ሰውነቴ ይመለስልኝ”ጥያቄ ውድቅ አደረገ
ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ህጋዊ ሰውነቱ እንዲመለስለት ያቀረበውን ጥያቄ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሳይቀበለው ቀረ።
ህወሓት በምርጫ አዋጁ 1162/2011 አንቀጽ 98/1/ /ረ/ ላይ የተደነገገውን በመተላለፍ ኃይልን መሰረት በአደረገ የአመጻ ተግባር ላይ ተሰማርቷል በሚል በቦርዱ መሰረዙ ይታወሳል።
የዚህ ውሳኔ ውጤትንም አስመልክቶ በአዋጅ 1162/2011 አንቀጽ 99/1/ ላይ ፓርቲው ከተሰረዘበት ቀን ጀምሮ መንቀሳቀስ እንደማይችል፤ የፓርቲውም ሃላፊዎች በፓርቲው ስም ምንም አይነት እንቅስቃሴ ማድረግ እንደማይችሉ መወሰኑ ይታወሳል።
ህወሓት ወቅታዊ ሁኔታዎችን በመጥቀስ ቦርዱ ውሳኔውን ሰርዞ ህጋዊ ሰውነቱን እንዲመልስለት ለምርጫ ቦርድ ጥያቄ ቢያቀርብም ፣ በርዱ ጥያቄውን ለመቀበል የሚያስችል የህግ መሠረት እንደሌለ በመጥቀስ ሳይቀበለው ቀርቷል።
በርዱ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ፤ “ምንም እንኳን በፓርቲው ደብደቤ እንደተገለጸው ፣ ለቦርዱ ውሳኔ ምክንያት የሆነው ኃይልን መሰረት ያደረገው የአመጻ ተግባር አሁን ባይኖርም እንደገና ህጋዊ ሰውነቱን ለፓርቲው ለመመለስ የሚያስችሉ ድንጋጌዎች በአዋጅ 1162/2011 ተደንግጎ አይገኝም፡፡ ስለዚሀ ቦርዱ የቀረበውን የህጋዊ ሰውነት ጥያቄ የማስለስ ጉዳይን በህግ የተደገፈ ሆኖ ባለማግኘቱ አልተቀበለውም” ብሏል።
በመሆኑም ፓርቲው ህጋዊ ሰውነት አግኝቶ ለመንቀሳቀስ የሚችለው በአዋጅ 1162/2011 አንቀጽ 66 እና ተከታዮቹ ድንጋጌዎች መሰረት በድጋሚ የምዝገባ ጥያቄ ሲያቀርብ እና ቦርዱ ህጉን መሰረት አድርጎ ሲፈቅድ መሆኑን በተጨማሪ ወስኗል፡፡
በመጨረሻም የፓርቲው አመራሮች እና ንብረትን በተለከተ የቀረበውን ጥያቄ በርዱ ፓርቲው ላይ የሰጠው የስረዛ ውሳኔ ውጤቶች በመሆናቸው እንደአዲስ የሚጠየቁ አለመሆንናቸውን በመጥቀስ ቦርዱ ውድቅ አድርጎታል።
Source: https://www.ethiopianreporter.com