“ቅዱስ ሲኖዶስ ለአንገብጋቢ ጉዳዮች ቅድሚያ ሰጥቶ እንዲወያይ እንጠይቃለን”

0
1 0
Read Time:3 Minute, 44 Second

የጀርመንና አካባቢው ሀገረ ስብከት “ቅዱስ ሲኖዶስ ለአንገብጋቢ ጉዳዮች ቅድሚያ ሰጥቶ እንዲወያይ እንጠይቃለን” ሲል አሳሰበ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የጀርመንና አካባቢው ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ከነገ ግንቦት 2 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ የሚካሄደውን ርክበ ካህናትና የጳጳሳት ሹመት አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ቅዱስ ሲኖዶሱ ለአንገብጋቢ ጉዳዮች ቅድሚያ ሰጥቶ እንዲወያይበት አሳስቧል፡፡ የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
ግንቦት ፪ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም የሚጀመረው የዚህ ዓመት ርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ፤ አገራችን በብዙ ፖለቲካዊና ማኅበረሰባዊ ውስብስብ ችግሮች ስትሰቃይ በቆየችበትና አኹንም እየተሰቃየች ባለችበት ዓመት የሚከናወን በመኾኑ የኹላችንንም ትኩረት ስቧል። አገርን ኾና አገር ስታቀና የኖረች በመኾኗ፤ ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያንም የእነዚሁ ውስብስብ ችግሮች ግንባር ቀደም ተጠቂ መኾኗ በግልጽ የሚታወቅ ነው። እንደአገራችን ኹሉ ከኅሊና በላይ በኾኑ ችግሮች ስትታመስ የቆየችዋ፤ አኹንም ያለችዋ ቤተ ክርስቲያናችን ቀኖናዋን ጠብቃ ሲኖዶሷን ልታደርግ በዝግጅት ላይ ባለችበት በዚህ ሰዓት፤ በተለይ በመላው ዓለም ያሉ ልጆቿን ክፉኛ ያስጨነቀ አንድ ጉዳይ መኖሩ እየታየና እየተሰማ ነው።

ይኸውም ቅዱስ ሲኖዶስ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሕግና ሥርዐት በጣሰ፤የመላውን ኦርቶዶክሳውያን ካህናትና ምእመናንን ልብ በሰበረ፤ጦሱም የበርካቶችን ነፍስ በነጠቀ፣ ቤተሰብ በበተነ፣ በቤተ ክርስቲያኗ ታሪክ መጥፎ ጠባሳ ጥሎ ባለፈ መልኩ ጥር ፲፬ ቀን ፳፻፲፭ ዓ. ም. ተደረገ በተባለ ሢመት ኤጲስ ቆጶሳት ነን ብለው ብቅ ያሉ ሕገ ወጥ ግለሰቦችን በውጫዊ ጫና ተገድዶ እንዳይሾም የሚል ነው።

በተፈጸመው ሕገ ወጥ ድርጊት ከማንም በላይ በሐዘን የተመቱ፣ አዝነውም ከፊት በመቆም ልጆቻቸውን በማስተባበር ከፍተኛ ተጋድሎ ያደረጉ አባቶቻችን ይህንን ኹሉም የፈራውን ድርጊት በመፈጸም የቤተ ክርስቲያናቸውን ቁስል የበለጠ የሚያነቁሩ፤ ለራሳቸውም መጥፎ ታሪክ ጽፈው የሚያልፉ አይመስለንም። እኛ በጀርመንና አካባቢው የምንገኝ ማኅበረ ካህናትና ምእመናን አባቶቻችን ይህንን በቤተ ክርስቲያኗ ቀኖናዊና አስተዳደራዊ ቁመና ላይ ከፍተኛና የከፋ ምስቅልቅል የሚያስከትል ውሳኔ እንዳይወስኑ ተማጽኗችን ከፍተኛ ነው።

ስንማጸንም፤ በበርካታ ምክንያቶች ላይ ተመሥርተን ሲሆን በተለይም ከታች የተዘረዘሩት ዘጠኝ ውጫዊና ውስጣዊ ነባራዊና አንገብጋቢ ሁኔታዎች ባሉበት ኹኔታ የአባቶቻችን ስለ ሢመትና ሽልማት መነጋገርም ኾነ በተግባር መፈጸም ጊዜውን ያልዋጀ፤ አገርና ሕዝብ ለደረሰባቸውና ለተጋረጠባቸው አደጋ ቤተ ክርስቲያን ትኩረት እንዳልሰጠች የሚያስቆጥር ነው ብለን እናምናለን።

፩. በጥቂቶች የፖለቲካ ልዩነት ምክንያት በተነሣ የእርስ በርስ ጦርነት ከስምንት መቶ ሺ ያላነሱ ኢትዮጵያውያን (የሚልቁት ቤተ ክርስቲያኒቱ በጥምቀት ወልዳ ያሳደገቻቸው ኦርቶዶክሳውያን ናቸው) ረግፈው፤ በአግባቡ ክቡር አፅማቸው እንኳን ተሰብስቦ ግብአተ መሬት ያልተፈጸመበት፣ ብዙዎቹ የሙታኑ ቤተሰቦች በወጉ እንኳን ያልተረዱበትና እርማቸውን ያላወጡበት፤ በአጭሩ የኢትዮጵያውያን ደም በምድሪቱ ፈስሶ የሚጮኽበት ጊዜ በመኾኑ፤

፪. ኦርቶዶክሳዊ ማንነት የበለጠ ጎልቶ በሚታይበት አካባቢ የነበረውና ከፍተኛ ሰብአዊና ኢኮኖሚያዊ ድቀት አድርሶ ያለፈው ጦርነት አኹን ቆመ ቢባልም፤ የቆመበት መንገድ አገር እንደምትፈልገው ቤተ ክርስቲያንን ጨምሮ ሌሎች አገራዊ ተቋማት ያልተሳተፉበት፣ በሕዝቦች መካከል ፍፁም ይቅርታን ባሰፈነ መልኩ ሳይኾን፤ «ውረዱ ተወራረዱ» ብለው ወንድማማቾችን ወደ ጦርነት በከተቱ ውጫዊ አካላት ግፊትና አስገዳጅነት የተፈጸመ፤ ዝርዝሩም ይኹን ጥልቀቱ ጦርነቱን መርተው ወንድማማቾችን ባጫረሱ የውስጥም ይኹን የውጭ ፖለቲከኞች ኅሊና ውስጥ ብቻ የተቀመጠ እንደመኾኑ፤ ተመልሶ እንደማይመጣም እርግጠኛ ያልኾንበት ወቅት በመኾኑ፤

፫. ቤተ ክርስቲያን ጦርነቱ በተካኼደባቸው አካባቢዎች በሚገኙ ማኅበረ ካህናቷና ምእመናኗ እንዲኹም ቅዱሳት መካናቷና ቅርሶቿ ላይ ያደረሰውን ጉዳት አጥንታ ያልተረዳችበት ወቅት በመኾኑ፤
፬. የጦርነት ዜና ዛሬም ቢኾን በኹሉም የአገራችን ክፍል የሚታይበትና የሚሰማበት፤ ዜጎች እንደልብ ወጥተው የማይገቡበት ወቅት በመኾኑ፤

፭. በዘራቸውና እምነታቸው የተነሣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ምእመናን የታረዱበት፤አኹንም እየታረዱ ያሉበት ወቅት በመኾኑ፤

፮. ዘራቸው ተመዝዞ፤ እምነታቸው ተመርምሮ ከተወለዱበት፣ ካደጉበትና ሀብትና ንብረት አፍርተው ከሚኖሩበት ቀዬአቸው በግፍ ተፈናቅለው በልዩ ልዩ ቦታ በሚገኙ መጠለያዎች ረሃብና ጥም፣ ቁርና ሐሩር እየተፈራረቀባቸው የሚገኙ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የሚገኙበት ጊዜ በመኾኑ፤

ወደ ውስጣዊው ስንመጣም፤

፯. የሰሜኑ ጦርነት በቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደራዊ አንድነት ላይ ያመጣው ልዩነት ደብዳቤ ከመጻጻፍ ባለፈ አባቶች ቁጭ ብለው ተወያይተው ቢያንስ ፖለቲከኞቹ ያሳዩንን ያህል ሰላምና አንድነት አመጣን ያላሉበት ወቅት በመኾኑ፤

፰. የሃይማኖትና የፖለቲካ ዓላማን ባነገቡ ኃይሎች ድጋፍ ጥር ፲፬ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት በሶዶ ዳጡ ወረዳ አሮ በዐለ ወልድ ቤተ ክርስቲያን በድብቅ ሕገ ወጥ የኤጴስ ቆጶሳት ሹመት የፈጸሙም ይኹን ተፈጸመልን ያሉ ግለሰቦች ወደቤተ ክርስቲያን ተመለስን ያሉበት መንገድ ግልጽነት የጎደለው፣ ኹሉንም ግራ ያጋባ በመኾኑ፤ ተመለስን ያሉት ግለሰቦችም ዛሬም ቢኾን ሲያደርጉና ሲናገሩ የሚታየውና የሚሰማው አኹንም ከእኩይ ዓላማቸው ወደኋላ እንዳላሉ የሚያስረዳ በመኾኑ፤

፱. በቤተ ክርስቲያኗ አጠቃላይ አስተዳደር የሚታየው ክፍተት ቤተ ክርስቲያናችን እስካሁን ለደረሱባትና አሁንም ለሚደርሱት ጉዳቶች የተጫወተው ጉልኅ ሚና ስላለ፤ ይህንን ክፍተት ለመሙላት (ለመድፈን) ከኹሉ አስቀድሞ ወደውስጥ ተመልክቶ፤ ኹሉን ፈትሾ፤ የሚስተካከለውን አስተካክሎ መኼድ ስለሚገባ፤

በመኾኑም በእነዚህና በሌሎች በርካታ ምክንያቶች የተነሣ፤ ቅዱስ ሲኖዶስ በዚህ ወሳኝ ወቅት ችግሮችን በሚፈቱ ርእሰ ጉዳዮ ላይ ትኩረት ሰጥቶ በመወያየት ውሳኔ ማሳለፍ፤ ዕቅድ ማውጣትና ለተግባራዊነቱም የሚያስፈልገውን በጀት ከመመደብ ጋር ለሚመለከተው ኹሉ ትእዛዝ ማስተላለፍ ይገባዋል እንላለን። ያ ሳይኾን ቀርቶ፤ አባቶቻችን በዬትኛውም ኃይል ሊደረግባቸው ለሚችል ተጽእኖ እጅ ሰጥተው ሕገ ወጦችንም ይኹን ሌሎችን ለመሾም ውይይት ቢያደርጉና በተግባርም ቢፈጽሙ ቤተ ክርስቲያን አሁን ባላት ችግር ላይ ሌላ ተጨማሪ ችግር እንደ መጨመርና በቁስሏ ላይ ጨው እንደ መነስነስ ኾኖ ይሰማናል። አባቶቻችን ይህንን ቢፈጽሙ በታሪክ ተጠያቂ ይኾናሉ። ቤተ ክርስቲያን በቀጣይ ማድረግ ባለባት ተቋማዊም ይኹን አገራዊ አዎንታዊ እንቅስቃሴዎች ላይም ተጽእኖ እንደሚያሳድርም እናምናለን።

ስለዚህ እኛ በጀርመንና አካባቢው ሀገረ ስብከት የምንገኝ ካህናትና ምእመናን፤ ብፁዐን አባቶቻችን በጉባኤያቸው የካህናትን፣ የምእመናንንና በአጠቃላይም የሕዝብን የልብ ትርታ በማድመጥና አገራችንንና ሕዝቧን ወደቀቢፀ ተስፋ እያስገቡ ላሉ ጉዳዮች ቅድሚያ በመስጠት በመፍትሔአቸው ላይ ተወያይተው ውሳኔዎችን በማሳለፍ አባታዊ ኃላፊነታቸውን ይወጡ ዘንድ ከተማጽኖ ጋር በክብሮት እንጠይቃለን።

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *