ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች፤ ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ በአፋጣኝ እንዲፈታ ጥሪ አቀረበ
የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይን በአፋጣኝ እንዲፈቱ ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ሲፒጄ (CPJ) ጥሪ አቀረበ። መቀመጫውን በአሜሪካ ኒውዮርክ ያደረገው የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ትላንት አርብ ባወጣው መግለጫ “በአገር ውስጥና በውጪ ያሉ የፕሬስ አባላትን ማዋከብ እንዲያቆሙ” ለኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ጥሪ አስተላልፏል።
“የአማራ ድምጽ” የተባለው በዩቲዩብ የሚተላለፍ የግል መገናኛ ብዙኃን መስራች እና አርታኢ የሆነው ጎበዜ፤ ሚያዝያ 28፤ 2015 በጅቡቲ በቁጥጥር ስር መዋሉን የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ይፋ እንዳደረጉ ሲፒጄ በመግለጫው ጠቅሷል። የጋዜጠኛው ጠበቃ አዲሱ አልማው፤ ጎበዜ ከጅቡቲ ለኢትዮጵያ መንግስት ተላልፎ መሰጠቱን እና በአዲስ አበባ በሚገኘው የፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ በእስር ላይ እንደሚገኝ ለሲፒጄ ተናግረዋል።
“የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይን ዝም ለማሰኘት እና ለመበቀል በድፍረት ድንበር ተሻግረዋል” ያሉት ከሰሃራ በረሃ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገራት የሲፒጄ ተወካይ ሙቶኪ ሙሞ፤ እስሩ “በስደት ደህንነት ፈልገው ከሀገራቸው በሄዱ ጋዜጠኞች ላይ ስጋት ይፈጥራል” ብለዋል። “ጎበዜ ያለመዘግየት ሊፈታ ይገባል” ያሉት የሲፒጄ ተወካይ የኢትዮጵያ እና የጅቡቲ ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር ስለዋለበት እና ተላልፎ ስለተሰጠበት ሁኔታ ማብራሪያ እንዲሰጡ ጠይቀዋል።