ኑሮ የከበዳቸው የመንግሥት ሠራተኞች የምሳ ሰዓትን በቤተ እምነቶች እያሳለፉ መሆኑ ተነገረ
የቤትኪራይመክፈልያልቻሉተደብቀውቢሮውስጥያድራሉተብሏል
መንግሥት የሚከፍላቸው ወርኃዊ ደመወዝ አልበቃ ያላቸው የመንግሥት ሠራተኞች የምሳ ሰዓታቸውን ወደ ቤት እምነቶች በመሄድ፣ እንዲሁም ቤት ተከራይተው መኖር የማይችሉት ደግሞ ቢሮ ውስጥ ተደብቀው እንደሚያድሩ ተገለጸ፡፡
በ2010 ዓም ተሻሽሎ ወደ ሥራ ገበቶ የነበረው ባለ 106 አንቀጽ የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች አዋጅ፣ ከስድስት ዓመታት አገልግሎት በኋላ፣ በ160 አንቀጾች ተዋቅሮ በረቂቅ አዋጁ ላይ ውይይት እየተደረገበት ነው፡፡
ለመንግሥት መሥሪያ ቤት ኃላፊዎች የበዛ ሥልጣን የሚሰጥ፣ ለሠራተኞች ችግር ደግሞ መፍትሔ የማያመጣና ተቋማዊ አሠራርና አደረጃጀት ላይ ብቻ ያተኮረ ነው የሚል ትችት በረቂቅ አዋጁ ላይ ቀርቧል፡፡ የመንግሥት ሠራተኛውን ሕይወት የሚቀይር ሥራ እንጂ አዋጅ ማውጣት ብቻ አገርን አይቀይርም የሚሉ ድምፆችም ተሰምተዋል፡፡
ለመንግሥት ሠራተኞች የሚከፈለው ደመወዝ አነስተኛና ሊያኖር የማይችል ከመሆኑም በላይ፣ በበርካታ የኢትዮጵያ ክልሎች የሚገኙ የመንግሥት ተቋማት ደመወዝ መክፈል ተስኗቸው ሠራተኞች ለወራት ደመወዝ ሳይከፈላቸው መቆየታቸውን፣ እንዲሁም በአንዳንድ ክልሎች ደግሞ ከሚቀጥሉት ዓመታት በጀት ተበድረው ደመወዝ እየከፈሉ መሆናቸው በተደጋጋሚ ሲነገር ይደመጣል፡፡
በረቂቅ አዋጁ ላይ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፐብሊክ ሰርቪና ሰው ሀብት ልማት ቢሮ የሰው ሀብት ሥራ አመራር ድጋፍና ክትትል ቡድን መሪ አቶ አብርሃም ደግፌ በሰጡት አስተያየት፣ በከተማ አስተዳደሩ 70 ያህል የመንግሥት ተቋማት ላይ ክትትል እንደሚያደርጉና ሥልጠና እንደሚሰጡ ጠቅሰው የሠራተኛው ሕይወት እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡
በከተማ አስተዳድሩ አንድ ከፍተኛ የሚባል ባለሙያ ያልተጣራ ደመወዙ 9,056 ብር መሆኑን ጠቅሰው፣ ‹‹ከዚህ ግብር ተከፍሎበት በእጁ የሚደርሰውን ገንዘብ አስልታችሁ ድረሱበት፤›› ሲሉ ተሳታፊዎችን ጠይቀዋል፡፡ በዚህ ደመወዝ የቤት ኪራይ የከተማዋ ጫፍ እንኳ ቢኬድ 10,000 ብር መድረሱን፣ ነገር ግን ይህ ከፍተኛ ባለሙያ ሙሉ ደመወዙን ለቤት ኪራይ ላድርግ ቢል ገንዘቡ እንደማይበቃው አስረድተዋል፡፡
በዚህ ሁኔታ ላይ ያለ አንድ ሠራተኛ የተሻለ አገልግሎት መስጠት ይቻላል ወይ? ተፈጥሯዊ ሁኔታውስ በራሱ ይፈቅድለታል ወይ? ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ይህ ችግር ደመወዝ በመጨመርም ይፈታል ብለው እንደማያስቡ ገልጸው፣ በሌሎች አማራጮች እንዲጠቀም ቢደረግ ችግሩ ሊቀል ይችላል እንጂ 2,000 ብር ቢጨመር እንኳን ሕይወቱ ላይ ለውጥ እንደማያመጣ ተናግረዋል፡፡ ‹‹በዚህም የተነሳ ሠራተኞች አንዳንዴ ቢሮ መጥተው ያለቅሱብናል፣ ምሳ የምንበላበት የለም በማለት በግልጽ ይናገራሉ፤›› ብለዋል፡፡
ገንዘብ አልበቃቸው ያሉ የመንግሥት ሠራተኞች በምሳ ሰዓት ወደ ቤተ እምነቶች ሄደው እንደሚያሳልፉ አስረድተዋል፡፡ የመንግሥት ሠራተኛው ታማኝ ግብር ከፋይ ቢሆንም፣ ነገር ግን የሠራተኛውን ሕይወት የሚቀይር ነገር እስካልመጣ ድረስ በሚፈለገው ደረጃ አገልግሎት ሊሰጥ እንደማይችል ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን የሰው ሀብት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ሰሎሞን ይልማ፣ ‹‹የረቂቅ አዋጁን መዘጋጀት የሰማ የመንግሥት ሠራተኛ የደመወዝ ጭማሪ አለ የሚል አዝማሚያ እየሰማን ነው፤›› ብለዋል፡፡ የመንግሥት ሠራተኛው የረቂቅ አዋጁን ዝርዝር የማየትና የመስማት ፍላጎት እንደሌለው ጠቅሰው፣ ‹‹አዋጁ ቶሎ ተዘጋጅቶ ሠራተኛው የሚጠቀምበት አሠራር ካልተዘረጋ በቀጣይ ከሠራተኛው ጋር የምንጋፈጠው እኛው ነን፤›› ብለዋል፡፡ የመንግሥት ሠራተኛው ተስፋ መቁረጡንና ችግር ውስጥ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ሰሎሞን፣ ‹‹አሁን ስለአዋጁ ወይም ዝርዝር እንድናወራለት ፍላጎት የለውም?›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
አሁን ባለው የደመወዝ አከፋፈል ሠራተኛው ችግር ውስጥ ስለመሆኑ የሚናገሩት አቶ ሰለሞን፣ የደመወዝ መነሻ ከፍ ተደርጎ ሊስተካከል እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ለአንድ የፅዳት ሠራተኛ 1,624 ብር እንደሚከፈል፣ ነገር ግን የራሳቸው ተቋም በሚገኝበት ሕንፃ ላይ የፅዳት ሥራን ለሦስተኛ ወገን ሰጥተው የሚቀጥሩ ድርጅቶች ለፅዳት ሠራተኛ እስከ 5,000 ብር ይከፍላሉ ብለዋል፡፡ በጋዜጣ የፅዳት ሠራተኛ ለመቅጠር ማስታወቂያ ወጥቶ አንድ ሰው ብቻ ሊመዘገብ መምጣቱን አክለዋል፡፡
በአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን ውስጥ የሚሠሩና ደንብ የሚቆጣጠሩ ከ6,500 በላይ ኦፊሰሮች በወር 3,934 ብር እየተከፈላቸው ለአሥር ዓመታት በተመሳሳይ ደመወዝ እያገለገሉ መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ በዚህ የተነሳ መሄጃ እያጡ ቢሮ ምቹ ሁኔታ አለ በሚል እየተደበቁ የሚያድሩ አሉ ብለዋል፡፡ በመሆኑም የመንግሥት ሠራተኞች መነሻና መድረሻ ደመወዝ ሊስተካከል ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ዳይሬክተር አቶ ካሳየ አረጋ፣ ሠራተኞች በተደጋጋሚ እየለቀቁ ዓመቱን በሙሉ ቅጥር ሲፈጸሙ እንደሚውሉ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ነገር ግን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አገልግሎት ለመስጠት የተሻለ አደረጃጀትና ባለሙያ፣ ቢቻልም የሥራ አስፈጻሚው የመንግሥት አካል ውስጥ ያለውን ባለሙያ ሊገዳደሩና ሊጠይቁ የሚችሉ፣ ለቋሚ ኮሚቴዎች የተሻለ ድጋፍና ሙያ ያላቸው ሠራተኞች ቀጥረን ልንሠራ ይገባል፤›› ብለዋል፡፡
‹‹አልቻልንም ባለሙያም የለም፣ ጉዳዩ በደንብ መታየት አለበት፤›› ያሉት ዳይሬክተሩ፣ አዋጅ በወጣ ቁጥር ሠራተኛው ተስፋ የሚያደርግበት ድንጋጌ እየገባ ነገር ግን ለዓመታት ሳይተገበር ቆይቶ እንደገና እንዲሻሻል መምጣቱ በቅጡ ሊጤን ይገባል ብለዋል፡፡
የቤት ሠራተኛ ወርኃዊ ደመወዝ ከ2,500 ብር ላይ ባለፈበት በዚህ ጊዜ አንድ መንግሥት የፅዳት ሠራተኛ በ1,300 ብር መቅጠር የሰብዓዊ መብት ጥሰት አይሆንም ወይ ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ በመሆኑም አሁንም ወደፊት ታይቶ የሚባለው ነገር ቀርቶና ያለው ነባራዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ ገብቶ፣ ታች ያለው ሠራተኛ ዜጋ በመሆኑ ችግሩ ሊታይለት ይገባል ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
በፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕገ መንግሥት ትርጉምና የሕጎች ሕገ መንግሥታዊነት ዳይሬክተር አቶ ሙለዬ ወለላው፣ የመንግሥት ሠራተኛው ሀቀኛና ታማኝ ግብር ከፋይ ሆኖ እያለ ለተለያዩ ዓይነቶች የታክስ ግዴታዎች ተገዥ መደረጉን፣ ለአብነትም ሠራተኛውን እንዲጠቅም ተብሎ ለትራንስፖርትና ለቤት ኪራይ የሚከፈል ገንዘብ ጭምር ግብር እየተከፈለበት እየተበዘበዘ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስ ቢሮ የሰው ሀብት ክትትል ድጋፍና ኦዲት ዳይሬክተር አቶ መላኩ ተመስገን በሰጡት አስተያየት፣ አዋጆች እየወጡ ቁልፍ ጉዳዮች በመመርያ ይታያሉ እየተባሉ ነገር ግን መመርያ ሳይወጣና በውስጡ ያለው ድንጋጌ ሳይፈጸም ጊዜው ደርሶ እንደገና እንደሚሻሻል አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ተወዳዳሪ ባለመሆኑ ሠራተኞችን መሳብና ማቆየት እንደማይቻልና አንዳንዶችም ‹‹መሄጃ አጣን ብለው የተቀመጡ መሆናቸውን›› የተናገሩት አቶ መላኩ፣ እነዚህ ሠራተኞች እንዴት አገልግሎት ማሻሻል ይችላሉ? ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ (ዶ/ር) በሰጡት ምላሽ፣ በአዲስ አበባ ያለው ክፍያ የፌዴራል ተቋማት ከሚከፍሉት ይሻላል ብለዋል፡፡ ነገር ግን በሁለቱም የሚከፈለው ግን የኑሮ ሁኔታን ለመቋቋም የሚያስችል አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡
‹‹ብዙውን ጊዜ ትኩረት የሚሰጠው የመጨረሻ ውጤት ላይ እንጂ ደመወዝ እዚህ ደረጃ ድረስ እንዲወርድ ያደረገው ምንድነው የሚለው በሚገባ አይታይም፡፡ አሁን ኃላፊነት ላይ ያለን ሰዎች ነን ወይ በዚህ ጉዳይ ላይ መጠየቅ ያለብን?›› ሲሉ ተሳታፊዎችን ጠይቀዋል፡፡
ችግሩ የብዙ ነገሮች ድምር ውጤት እንደሆነ ጠቅሰው፣ በየአካባቢው ያለው ጦርነት ያስከተለው ችግር ሥራን መገደቡን አስረድተዋል፡፡ ‹‹የሚሰበሰበው ገንዘብ የት ነው ያለው? አገሪቱ የምታመርተው ምን ያህል ነው? የሚለው ጉዳይ በደንብ ሊታሰብበት ይገባል፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ስለዚህ መፍትሔው የመንግሥት ሠራተኛ ወደ ሥራ ይግባና አርሶ አደሩን ይደግፍ፣ የንግድ ማኅበረሰቡን ይደግፍ፣ ባለሀብቱን ይደግፍ፣ የገበሬ ምርት ይሰብሰብ፣ ገቢ ይሰብሰብ፡፡ ይህ ካልሆነ ገዥው ፓርቲ እንዴት ብሎ ነው የመንግሥት ሠራተኛ ደመወዝ የሚያስተካክለው?›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የሲቪል ሰርቪስ ፖሊሲና አዋጁ አጠቃላይ የአሠራር ሥርዓትን ቀይሮ ወደ ተሻለ ምርት እንግባ የሚል ነው ያሉት ኮሚሽነሩ፣ አሁንም ቢሆን ደመወዝ አይስተካክልም የሚል እምነት የለም ብለዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ነገረ ሌንጮ (ዶ/ር) የደመወዝ ጥያቄ በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ብቻ የሚመለስ እንዳልሆነ ገልጸው፣ ‹‹ይህ የሕዝብ ጥያቄ አንድ ቀን በሒደት ምላሽ እንደሚያገኝ ተስፋ እናደርጋለን፤›› ብለዋል