ያ ካፋው ሚካኤል የካቲት 12 የአዲስአበባ ነዋሪዎች በግፍ የተጨፈጨፉበት ቀን !

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በግፍ የተጨፈጨፉበት ቀን !
የካቲት 12 የጣልያኑ ማርሻል ሩዶልፍ ግራዚያኒ ላይ ለተደረገው የግድያ ሙከራ ጣልያን በአፀፋው የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን የጨፈጨፈችበት ቀን ነው፡፡
በወቅቱ እስከ 30,000 ሰዎች እንደሞቱ የተገመተ ሲሆን በጊዜው የከተማዋን ነዋሪዎች 20 ከመቶ ያህል ነው ተብሏል፡፡
የጣልያኑ የጦር መሪ ግራዚያኒ በቀድሞው ቤተመንግሥት በአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ” ለኢትዮጵያ ህዝብ ስጦታ እሰጣለሁ ” በሚል ዜጎቻችን ይሰበስባል።
በዝግጅቱ ላይ ኣብርሃም ደቦጭ ፣ ሞገስ ኣስግዶም ፣ ስምኦን ኣደፍርስ ፣ ስብሃት ጥሩነህ እና ሌሎች ወጣቶች ቦንብ ይዘው ወደ ስብሰባው ገቡ፡፡
በተለይ ኣብርሃም ደቦጭ እና ሞገስ ኣስግዶም በኤርትራ በነበሩበት ወቅት የጣሊያን መንግሥት በኤርትራ ሕዝብ ላይ ይፈጽም የነበረውን ግፍ ያውቁ ሥለነበር ከፍተኛ ቁጭት ነበረባቸው፡፡
ወጣቶቹ ወደ አዳራሹ እንደገቡ ግራዚያኒ ስለ ኢትዮጵያ ሕዝብ ፣ ስለ አርበኞች እና ስለ ንጉሡ በንቀት ይናገር ነበር፡፡
ወጣቶቹ በግራዚያኒ የንቀት ንግግር እና በስብሰባው ውስጥ በታደመው ተሰብሳቢ ተናደዱ፤ ወደ ግራዚያኒ ቀስ ብለው በመጠጋት ሰባት ቦንቦችን በተከታታይ ወረወሩ፡፡
ተሰብሳቢው የመጀመሪያው የቦንብ ፍንዳታ የደስታ ርችት መስሎት ስለነበር አልተደናገጠም፡፡
በ2ተኛው የቦንብ ፍንዳታ ግራዚያኒ ተመትቶ ብዙ ቦታ ላይ ቆሰለ፣ የጦር ኃይል አዛዥ የነበረውን አውራሊያ ሊአታ አይኑ ጠፋ፤ እግሩ ተቆረጠ፡፡ ሌሎች ሹማምንትም ሕይወታቸው አለፈ።
ይህን ተከትሎ ነው ግራዚያኒ #በአፀፋ_እርምጃ አ/አ ነዋሪዎችን በግፍ የጨፈጨፈው።
እለቱ ለ88 ጊዜ በአ/አ 6 ኪሎ በሚገኘው መታሰቢያ ሀውልት ተከብሯል።
ማጣቀሻ ፦ ኢትዮጵያና የጣልያን ጦርነት (ጳውሎስ ኞኞ)