ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴና የእንግሊዞች ሴራ።

ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴና ከእንግሊዞች ጋር በደቡብ ኢትዮጵያ ስለነበረው የድንበር ውዝግብ፣
የእንግሊዙ ወኪል ሻለቃ ግዊን የምኒልክን መታመም በመጠቀም ሁለቱ መንግስታት የተስማሙበትን መስመር በመከለስ የኬንያ አርብቶ አደሮችን ለመጥቀም ሞያሌ አካባቢ የነበረውን ድንበር ወደ ሰሜን ገፍቶ ከለለው፡፡ ይሁን እንጂ ይህንን የሜጆር ግዊንን የተናጠል ውሳኔ የኢትዮጵያ ሹማምንት አልተቀበሉትም፡፡
በተለይም የቀደዱማን የውሃ ጉርጓዶች በዘመኑ የኬንያ ቅኝ ገዢ ለሆነችው እንግሊዝ አሳልፎ መስጠት ከቶም የማይታሰብ መሆኑ ለእንግሊዞች ተነገራቸው፡፡ አዲሱ የእንግሊዝ አምባሳደር በፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ከሚመራው የሚኒስትሮች ም/ቤት ጋር ሐምሌ 21 ቀን 1902 ዓ.ም ባደረገው ቆይታ እንግሊዝ የኢትዮጵያን ግዛት ቆርሳ መውሰዷን ኢትዮጵያ በጭራሽ እንደማትቀበል ከመግለጽ አልፎ ግዊን ያስቀመጣቸው የድንበር ምልክቶች እንዲነሱ ጠየቀ፡፡ የሚ/ም/ቤት ህዳር 18 ቀን 1903 ዓ.ም ከእንግሊዙ አምባሳደር ጋር ባደረገው ሌላ ስብሰባም ኢትዮጵያ ከአቋማ ንቅንቅ እንደማትል ገለጸች፡፡
ይህንን ተከትሎ እንግሊዝ ከኢትዮጵያ የሚነሱ ሽፍቶች ስላስቸገሩኝ ድንበሩ ላይ ጦር አሰፍራለሁ ወደሚል ዛቻ ተሸጋገረች፡፡ በግንቦት ወር 1905 ዓ.ም ካፒቴን አይምለር የተባለ የእንግሊዝ መኮንን መገደሉን ተከትሎ ውዝግቡ የከረረ መልክ ያዘ፡፡ ይህንን አስታከውም እንግሊዞች የኢትዮጵያ መንግስት 300ሺ ማርትሬዛ ካሳ በመክፈል የግዊንን የድንበር መስመር እንዲቀበል ወተወቱ፡፡
የምኒልክና የፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ቋሚ ጥረት የቦረና ሕዝብ ኢትዮጵያ ውስጥ መጠቃለሉን ማረጋገጥ ነበር፡፡ ዴኒስ ሃኪ በእንግሊዝና በኢትዮጵያ መካከል የነበረውን የደቡብ ድንበር ውዝግብ በማስመልከት የነበረውን ተቃርኖ የገለጸው እንደሚከተለው ነበር፣
“ለምኒልክ የድንበር መሰረቱ ሕዝብ ነው፡፡ ስለሆነም የሕዝቡ የመሬት ክልል የትም ይሁን የት የኔ ዜጎች ናቸው የሚል እሳቤ ነበረው፡፡ በአንጻሩ የእንግሊዞች ጥረት የግጦሽ መሬትና ውሃ ያለበትንና በቀላሉ ሊከላከሉት የሚችሉትን ወሰን ማስከበር ነው፡፡ እነዚህን ተጻራሪ አስተሳሰቦች አንድ አስርት አመት የፈጀ ድርድር ሊፈቷቸው አልቻሉም፡፡”
እንግሊዚዞች ኢትዮጵያን ለመያዝ የነበራቸውን አላማ ለማሳካት በኬንያ በኩል አርብቶ አደሮችን ወደ ኢትዮጵያ በማስገባት በየጊዜው ግጭቶችን ሲቀሰቅሱ የነበረ ሲሆን ከነዚህ ግጭቶች ጋር በተያያዘም በደቡብ ኢትዮጵያ ጠረፍ ጠባቂዎች አንድ ታዋቂ የእንግሊዝ ኮሎኔል ተገደለ፡፡ የኮሎኔሉን ሞት ተከትሎም የእንግሊዝ መንግስት አንድ ልዑካን ወደ አጼ ምኒልክ ላከ፡፡
ልዑካኑ በኬንያ ድርቅ መግባቱን በመግለጽ ኢትዮጵያ ለምለም ስለሆነች ለወዳጅነት ሳርና ጅረቶች ያሉት ግዛት እንድትሰጣቸው፣ ለኮሎኔሉ ግድያ ካሳ እንዲከፈልና የኬንያ አርብቶ አደሮች ለግጦሽ ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ የሚፈጸምባቸው ዝርፊያ እንዲቆም በመጠየቅ የመጣበትን ምክንያት ለምኒልክ አስረዳ፡፡
አጼ ምኒልክም የመጣችሁበት ጉዳይ ገብቶናል፣ የሚበጀውን ሁሉ ሀብተ ጊዮርጊስ ያስታውቃችኋልና ወደ ሀብተ ጊዮርጊስ ሂዱ በማለት ልዑካኑን ወደ ፊታ/ሀብተ ጊዮርጊስ ላኩት፡፡ ፊታውራሪውም የእንግሊዝ ልዑካን ተቀብለው በማነጋገር ያቀረበውን ጥያቄ በሙሉ እንደሚቀበሉ ሲገልጹ መልእክተኛው ከደስታው ብዛት ቁጭ ብድግ እያለ ምስጋና አቀረበላቸው፡፡
ይሁን እንጂ ፊታ/ሀብተ ጊዮርጊስ ገለጻቸውን በመቀጠል እንግሊዝም በበኩሏ የሚከቱሉትን ለኢትዮጵያ መፈጸም የሚገባት መሆኑን ጠየቁ፣
- የኢትዮጵያን መሬት ቆርሰን እንድንሰጣችሁ ከፈለጋችሁ፣ እናንተም በበኩላችሁ የእንግሊዝን ምድር ኢንግላንድን አስረክቡን፣
- ለሞተው ኮሎኔል ካሳ እንድንከፍላችሁ ከፈለጋችሁ፣ እናንተም የአጼ ቴዎድሮስን ልጅ ልዑል አለማየሁን ገድላችኋልና ካሳ ክፈሉን፣
- የኢትዮጵያ አርብቶ አደሮች የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ወደሆነችው ኬንያ የገቡ እንደሆነ እናንተም ዝረፉ፣
ይህንን ከፈጸማችሁ መፍትሄው በጣም ቀላል ይሆናል በማለት ለእንግሊዙ ልዑክ ገለጹለት፡፡ ከዚህ በኋላ አዋቂ ነው የተባለው የፈረንጅ ልዑክ ምላሽ በማጣቱ ወደ አገሩ መመለስ ግድ ሆኖበታል፡፡
ሀብቴ አባ መላ፣ ከጦር ምርኮኝነት እስከ አገር መሪነት፣ ባህሩ ዘውዴ፣ ገጽ 125-130፣ 135-145
ማስታወሻ፣ ፊታ/ሀብተ ጊዮርጊስ የቦረና አስተዳዳሪ፣ የማዕከላዊው መንግስት የጦር ሚ/ርና እንደ ጠቅላይ ሚ/ር የሚኒስትሮች ም/ቤት ሰብሳቢ በመሆን ያገለገሉ ሲሆን ልክ እንደ ደጃዝማች ባልቻ አባ ነፍሶ ከጦር ምርኮኛነት ተነስተው በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን ከፍተኛው ባለስልጣን ለመሆን የበቁ የጦርና የፍርድ ብልሀት አዋቂ ነበሩ፡፡ በአስቸጋሪ ጉዳዮች በሚያቀርቧቸው የመፍትሄ ሀሳቦችና በሚሰጧቸው ውሳኔዎች ምክንያትም አባ መላ እየተባሉ ይጠሩ ነበር፡፡