ፀሐፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀ/ወልድ ከሃገረ ፈረንሳይ እንዲወጡ ታስቦ “ቶማስ ወልድ” በተሰኘ የሐሰተኛ ስም እና ዜግነታቸውን በኮሎምቢያ ተደርጎ ፓስፖርታቸው ስለመሰራቱ

0
0 0
Read Time:1 Minute, 49 Second

የአክሊሉ ሀብተወልድ ረጅሙ የዲፕሎማሲ ሥራ ፣ ብዙዎች እንደሚገምቱት ፣ የተጀመረው ከኢጣሊያ ወረራ በኋላ አይደለም፡፡ አክሊሉ ሀብተወልድ የዲፕሎማሲ ስራቸውን አሀዱ ብለው የጀመሩት በኢጣሊያ ወረራ ዋዜማ በ 1928 ዓ.ም ፓሪስ በሚገኘው የኢትዮጵያ ሌጋስዮን ውስጥ ነበር፡፡የተመደቡበትም ስራ የሌጋሲዮኑ የፕሬስ አታሼ እንዲሆኑ ነበር፡፡

በዚሁ ጊዜ ወጣቱ አክሊሉ ለኢትዮጵያ ነጻነት የሚታገሉ ሁለት ኮሚቴዎችን በፈረንሣይ አገር ያቋቋሙ ሲሆን ከዚህ ኮሚቴ ጋር በመተባባርም ‹‹ኑቬል ደ ኢትዮጲ›› ወይም (የኢትዮጵያ ዜና) የተባለ ጋዜጣ በፈረንሣይኛ በማዘጋጀት የኢትዮጵያን አቋም ለዓለም ለማስተዋወቅ ችለዋል፡፡

የአክሊሉ ስራ በኢትዮጵያ ሌጋሲዮን ብቻ ሳይገደብ ፤ በመንግሥታቱ ማህበር (League of Nations) ለሚሟገተው እና በፊታውራሪ ተክለሃዋርያት ለሚመራው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በጸሐፊነት ከፓሪስ ወደ ጄኔቭ እየተመላለሱ ያልተቆጠበ አገልግሎታቸውን አበርክተዋል፡፡

ከዚህም ሌላ ፋሽስቶች በኢትዮጵያ ላይ የሚፈጽሙትን የግፍ ወረራ በተለያዩ የጋዜጣ ጽሑፎቻቸው በማቅረብ የአገራቸውን ሁኔታ ለሠላም ወዳዱ የዓለም ማሕብረሰብ ሲያስተዋውቁ ቆይተዋል፡፡

ወጣቱ አክሊሉ ሀብተወልድ ከሚያዝያ ወር 1928 ዓ.ም ጀምሮ በፈረንሣይ የኢትዮጵያ ሌጋሲዮን አንደኛ ጸሐፊነት እንዲሁም ከመስከረም 1929 ዓ.ም ወዲህ ደግሞ ኤምባሲው ሥራውን እስካቆመበት ጊዜ ድረስ የሌጋሲዮኑ ጉዳይ ፈጻሚ በመሆን አኩሪ ግዴታቸው ተወጥተዋል፡፡

ናዚ ጀርመን የፈንሣይን ድንበርና የመከላከያ መስመር ጥሶ ወደ ፓሪስ ሲገሰግስ የፈረንሣይ መንግሥት ቦርዶ ወደ ተባለው ነጻ ግዛቱ ለመዘዋወር ተገደደ፡፡ አክሊሉም የኢትዮጵያ ሌጋሲዮንን ዘግተው የፈረንሣይን መንግሥት አዲሱ መቀመጫ ወደ ሆነው ቦርዶ በብስክሌት ተጓዙ፡፡ በቦርዶ ኢትዮጵያን በመወከል የጉዳይ ፈጻሚነታቸውን ተግባር በማከናወን ላይ እያሉ ናዚ ጀርመን ቦርዶን ለመያዝ እየተዋጋ መሆኑ ተሰማ፡፡

የናዚ ጀርመን ወራሪ ጦር እየተከታተለ መቆሚያ መቀመጫ ያሳጣቸው አክሊሉ ሀብተወልድ ወደ ሌላ አገር ለመሰደድ መዘጋጀት ነበረባቸው፡፡ ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በኃይል መያዟ በመላው አውሮፓ ስለታወቀ በእጃቸው ያለው የአገራቸው ፓስፖርት የተለመደውን አገልግሎት ሊሰጣቸው አልቻለም፡፡ ስለሆነም አክሊሉ የኢትዮጵያ ፓስፖርታቸውን በፈረንሣይ የአሜሪካ አምባሳደር ለነበረው ግለሰብ በአደራ ሰጥተው መላ ፍለጋ ተንቀሳቀሱ፡፡

አክሊሉ የገጠማቸውን ችግር ጠቅሰው ፤ ማርሴ (ፈረንሣይ) ይገኝ የነበረው የኮሎምቢያ ቆንስላ የኮሎምቢያ ሊሴ ፓሴ እንዲሰጣቸው አመለከቱ፡፡ ቆንስሉ ‹‹ቶማስ ወልድ›› በሚል ስም የተዘጋጀ የኮሎምቢያ የጉዞ ሰነድ (ሊሴ ፓሴ) አዘጋጅቶ ሰጣቸው፡፡ አክሊሉ አዲስ ስም ይዘው የፖርቱጋል ርዕሰ መዲና ወደሆነችው ወደ ሊዝበን ሹልክ አሉ፡፡ በአዲሱ መኖሪያ አገራቸው እንዳሉ የአሜሪካው አምባሳደር የኢትዮጵያ ፓስፖርታቸውን በፖስታ ላከላቸው፡፡

እንግዲህ ቶማስ ወልድ የተሰኘው ስም ፤ በአውሮፓ በ 2ኛው የዓለም ጦርነት ሰበብ የተነሳ በድንገት አገር አልባ የሆኑትን ወጣቱን የኢትዮጵያ ዲፕሎማት ከስቃይ እና ሞት የታደገ ስም ሆነ፡፡

አክሊሉን ካገር አገር ያሳደደው የጀርመን ናዚ ወራሪ ጦር በተራው የሚሳደድበት ቀን መጣ ፤ ኢትዮጵያን በግፍ የወረረው የፋሺስት ጦርም በተራው ሲንኮታኮት አክሊሉ ሀብተወልድ እውነተኛ ስማቸውን የያዘውን የኢትዮጵያ ፓስፖርት ተጠቅመው በ 1934 ዓ.ም ወደ ሀገራቸው ሊመለሱ ችለዋል፡፡

ታሪክን_ወደኋላ #TariknWedehuala

©️ ፀሀፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ

youtube.com/@tariknwedehuala11

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *