ባል እና ሚስት ከአንድ ወንዝ ይቀዳሉ ወይስ በተመሳሳይ ቀን ይወለዳሉ?

ተፃፈ በ ታዘብ አራጋው
የመድሃኒት ጥቂት ይበቃል እያለች፤
የምኒልክ እናት አንድ ወልዳ መከነች፡፡
የስልጣኔ ሸማኝ፣ የሃገር ባለውለታ፣ የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ አንጥረኛ፣ የማትደፈር ሃገር መስራች እንደሆኑ ይነገራል፡፡ ባለቤታቸው ደግሞ ለንጉሰ ነገስቱ ብቻ ሳይሆን ለሚወዱት ሕዝብ ጭምር ዘውድ፣ የአዲስ አበባ ቆርቋሪ፣ የሴት ባለመላ እና የጦር አጋፍሪም ጭምር ናቸው ይባላሉ፡፡በአራት ዓመታት ልዩነት ነሐሴ 12 ቀን 1836 እና ነሐሴ 12 ቀን 1832 ዓ.ም ሚስት እና ባል በቅደም ተከተል በኢትዮጵያ ምድር ስር ፈለቁ፡፡ የሚገርመው ግን ተመሳሳይ ቀን መወለዳቸው ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያዊያን ወግና ባህል ብዙም ባልተለመደ መልኩ ሚስት ባልን አራት ዓመታት አስከንድተው መብለጣቸው ነው፡፡ እቴጌ ጣይቱ እምየ ምኒልክን በአራት ዓመታት ይቀድሟቸዋል፤ ይችንም ዓለም ሲሰናበቱ የአራት ዓመታት ልዩነት አላቸው፡፡
የንጉስ ሳህለ ስላሴ ልጅ ከሆኑት አባታቸው ልዑል ኃይለ መለኮት እና ከእናታቸው ከወይዘሮ እጅግአየሁ ለማ ከደብረ ብርሃን ደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ አምስት ኪሎ ሜትር ገደማ ርቃ በምትገኘው የገጠር መንደር አንጎለላ ልዩ ስሟ እንቁላል ኮሶ መንደር ውስጥ ነሐሴ 12 ቀን 1836 ዓ.ም አንድ ህፃን ይህችን ምድር ተቀላቀለ፡፡ ይህ ህፃን የኋላ ኋላ በአካልና በአዕምሮ ጎልምሶ እና ነግሶ በሚመራው ሕዝብ ዘንድ ሞገስ ተችሮት የጥቁር አፍሪካውያን ሁሉ መከታ ይሆናል ብሎ ያሰበ ባይኖርም ስሙን ግን ምኒልክ ሲሉ አወጡለት፤ ዳግማዊ መሆኑን ሲያመሰጥሩ ነው፡፡
ህፃኑ ምኒልክ የመፃዒ መራሂ መንግስትነቱ መክሊት ይገለጥ ዘንድ ግን ከ12 ዓመታት በላይ መጠበቅ አላስፈለገውም፡፡ ህዳር 1 ቀን 1848 ዓ.ም ልክ በ12 ዓመታቸው የአባታቸው ኃይለ መለኮት የቀብር ስነ ስርዓት እንደተፈፀመ የአባታቸውን አልጋ በይፋ ተቀበሉ፡፡
ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ እቴጌ ጣይቱ ብጡል ደግሞ ትልቁ ራስ ጉግሳ የጎንደሯን ባላባት ወይዘሮ ማሪቱን አግብተው ወይዘሮ ሂሩትን፤ ወይዘሮ ሂሩት ከራስ ገብሬ እና ከወይዘሮ ሳህሊቱ የሚወለዱትን ደጃዝማች ኃይለ ማሪያምን አግብተው ደጃዝማች ብጡልን፣ ደጃዝማች መርሶንና ሌሎችንም ልጆች ይወልዳሉ፡፡ ደጃዝማች ብጡል ደግሞ የጎጃም ደብረ መዊዕ ባላባት የሆኑትን ወይዘሮ የውብዳርን አግብተው ነሐሴ 12 ቀን 1832 ዓ.ም ጎንደር ውስጥ በደብረ ታቦር ከተማ እቴጌይቱን ወለዱ፡፡
እቴጌ ጣይቱ የአባታቸው አያት በሆኑት በወይዘሮ ማሪቱ በኩል የአፄ ፋሲል ተወላጅ ከሆኑት ከአፄ ተክለ ጊዮርጊስ (ፍፃሜ መንግስት) የሚመዘዝ የዘር ሃረግ አላቸው፡፡ እናም እቴጌ ጣይቱ የዘር ሃረጋቸው ከጎንደር፣ ከጎጃም እና ከወሎ ይመዘዛል ማለት ነው፡፡ እቴጌ ጣይቱ በ13 ዓመታቸው አባታቸው በጦርነት ላይ በመሞታቸው ደብረ ታቦርን ለቅቀው ወደ እናታቸው አገር ወደ ጐጃም በመምጣት የእንጀራ አባታቸው በሚያስተዳድሩት እና ደብረ መዊዕ በሚገኘው ደብር ቀደም ሲል ጐንደር ውስጥ በማህደረ ማርያም ጀምረውት የነበሩትን ትምህርታቸውን እየተማሩ ተቀመጡ:: የኋላ ኋላ ወደ ደብረ መዊዕ ተመልስው ትምህርታቸውን አስቀጥለው እንደነበር ይነገራል፡፡
እቴጌ ጣይቱ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ በጥበብና በሕይወት ፍልስፍና የላቀ ችሎታ ባለቤት መሆናቸው እየታወቀ መጣ፡፡ ይህንን የጣይቱን ዝና ከሰሙ ልዑላን መካከል ወጣቱ ምኒልክ አንዱ ናቸው፡፡ ምኒልክ ስለ እቴጌ ጣይቱ ዝና የሰሙት አብረው ይኖሩ ከነበሩት አሉላና ወሌ ብጡል ከሚባሉት የእቴጌ ወንድሞች እንደሆነም ይነገራል፡፡ በወቅቱ የምኒልክ ሞግዚት የነበሩት ደጃዝማች ተሰማ ናደው ከሌሎች ቅርብ ሰዎቻቸው ጋር ተማክረው ጣይቱን እና ምኒልክን ለማጋባት ሙከራ አድርገው ነበር፤ ምንም እንኳን በወቅቱ በተለያዩ ችግሮች ጋብቻው ቢዘገይም፡፡
ዘመኑ በደረሰ ጊዜ ግን አፄ ምኒልክ እቴጌ ጣይቱን አገቡ፡፡ ንጉሥ ምኒልክ ሚያዚያ 25 ቀን 1875 ዓ.ም በአንኮበር መድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን ከእቴጌ ጣይቱ ብጡል ጋር በቁርባን ጋብቻቸውን ፈፀሙ፡፡ አምስት ዓመታት ቆይቶም ጥቅምት 27 ቀን 1882 ዓ. ም ጣይቱ ብጡል “እቴጌ” ተብለው ተሠየሙ፡፡ በዚህ ጊዜ ንጉሥ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ዘ ኢትዮጵያ” ከተባሉ ሶስተኛ ቀናቸው ነበር፡፡ አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ ዳግማዊ አጤ ምኒልክ በተሰኘው መፅሃፋቸው እቴጌ ጣይቱ ለዚህ ታላቅ ሥልጣን በበቁ ጊዜ የተፈጠረውን ስሜት ሲገልፁ “የሸዋ ቤተ መንግሥት ዓለሙ የዚህን ቀን ተጀመረ:: የሸዋ ቆሌ፣ የሸዋ ደስታ የዚህን ቀን ተጀመረ:: የሸዋ ቤተ መንግሥት ከጣይቱ በኋላ ውቃቢ ገባው፣ ግርማና ውበት ተጫነው፣ ጥላው ከበደ፣ የእውነተኛው አዱኛ፣ የእውነተኛው ደስታ ከጣይቱ ብጡል ጋር ገባ” ሲሉ ጽፈዋል፡፡
እቴጌ ጣይቱ አፄ ምኒልክን ካገቡ በኋላ ያልተሳተፉበት ምጣኔ ሃብታዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳይ አልነበረም፡፡ አፄ ምኒልክ አዳዲስ ሥልጣኔዎችን ለማስገባት ቁርጠኛ አቋም ይዘው በተንቀሳቀሱበት ጊዜ አጋራቸው እቴጌ ጣይቱ ነበሩ፡፡ በተለይም ዘመናዊ ትምህርት ቤት ሲያቋቁሙ፣ የባቡር ሃዲድ ሲዘረጉ፣ ውሃ በመዘውር እንዲቀዳ ሲያደርጉ፣ በቀጭኑ ሽቦ በስልክ ግንኙነት በተጀመረ ጊዜ፣ ተሽከርካሪዎች ወደ አገር ቤት በመጡ ጊዜ፣ የእህል ወፍጮ ሲተከልና ሌሎችም የቴክኖሎጂ ውጤቶች ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ አጋዣቸው የነበሩት ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ እቴጌ ጣይቱ ነበሩ፡፡ የእቴጌ ጣይቱን ስም ዘላለም ሲያስጠሩ ከሚኖሩ ተግባሮቻቸው መካከልም ግንባር ቀደሙ አዲስ አበባ ከተማን መቆርቆራቸውና መጠሪያ ስሟንም ለመሰየም መቻላቸው ነው፡፡ እቴጌ ጣይቱ የመጀመሪያው ዘመናዊ ሆቴል መስራች ናቸው፤ የባልትና ሙያን እና የሽመና ጥበብን ለቤተ መንግሥቱ በማስተዋወቅም ግንባር ቀደም ነበሩ፡፡
እቴጌ ጣይቱ በፖለቲካዊ ተግባራቸው ሲመዘኑም ሁሌም ሚዛን የሚደፋው ሥራቸው ጣሊያኖች በውጫሌ ውል ካሰፈሯቸው ነጥቦች በአንቀፅ 17 ስር የተቀመጠውን የጣሊያንኛ ትርጉም ኢትዮጵያን በሚጎዳ መልኩ ጥቅም ላይ ውሎ በተገኙ ጊዜ የያዙት የማያወላውል አቋም ነው፡፡ አንቶኔሊ የተባለው የጣሊያን ዲፕሎማት በቤተ መንግሥት ተጠርቶ ከአፄ ምኒልክ እና ከእቴጌ ጣይቱ ፊት ቀርቦ በውጫሌው ውል ከተካተቱት ነጥቦች መካከል በአንቀፅ 17 ሥር የሰፈረውን ትርጉም እንዲያስተካክል ሲጠየቅ የአገሩን መንግሥት ክብር የሚነካ ስለሚሆን ይህ እንደማይደረግ በግልፅ ተናገረ፡፡ በዚህ ጊዜ እቴጌ ያንተ ፍላጎት ኢትዮጵያ በሌላ መንግሥት ፊት የኢጣሊያ ጥገኛ መሆኗን ለማሳወቅ ነው፡፡ ነገር ግን ይህን የመሰለው የምኞት ሃሳብ አይሞከርም፡፡ እኔ ራሴ ሴት ነኝ ጦርነት አልፈልግም፤ ነገር ግን ይህን ውል ብሎ ከመቀበል ጦርነትን እመርጣለሁ” ሲሉ ተናገሩ፡፡
በኢትዮጵያ እና በጣሊያን መካከል እሰጥ አገባው ቀጥሎ ከቆየ በኋላ ጦርነቱ አይቀሬ ሆነና አፄ ምኒልክ “ምታ ነጋሪት፤ ክተት ሠራዊት” ብለው ወደ አድዋ ጦርነት ሲዘምቱ ኑሯቸውም ሆነ ህልፈታቸው ከባለቤታቸው ሊነጠል እንደማይችል የተገነዘቡት እቴጌ ጣይቱ በራሣቸው የሚመራ 3 ሺኅ እግረኛ ጦር እና 6 ሺኅ ፈረሰኛ አስከትለው ከባለቤታቸው ጎን ተሰልፈው ውጣ ውረድ የበዛበትን የጦርነት ጉዞ በድል አድራጊነት አጠናቀቁ፡፡
እቴጌ ጣይቱ በዚህ መልኩ አገራዊ ተልኳቸውን እየተወጡ እያሉ ባለቤታቸው አፄ ምኒልክ በጠና ታመሙና ከህዳር 1902 ዓ.ም ጀምሮ ከቤት ዋሉ፡፡ ታህሳስ 3 ቀን 1906 ዓ.ም በእለተ አርብ አረፉ፤ ሕዝቡ የምኒልክን ሞት ከሰማ ይረበሻል ተብሎ በሕይወት አሉ! እየተባለ እየተወራ እስከ ሰገሌ ዘመቻ ሁለት ዓመት ከ10 ወር ድረስ ሞታቸው ተደበቀ፡፡
በምኒልክ ሁኔታ ግራ የተጋባው ሕዝብም እንዲህ ሲል የንጉሱን ሁኔታ ይጠይቅ ነበር፡፡ ሕዝቡም አልጋ ወራሽ የሆኑበትን ጨምሮ
አርባ ስድስት ዓመት የገዛኸው ንጉስ፤
እንዳለህም ስጠኝ ከሌለህም ላልቅስ፡፡
”መኸሬን ከትቻለሁ፤ እንግዲህ እኔ እዚህ ምን አለኝ ጌታዬ! እኔም በተራዬ እከተልዎታለሁ”
የሚል ቃል ተናግረው ቤተ መንግስቱን ለቅቀው ወደ እንጦጦ አቀኑ፡፡ እቴጌ ጣይቱ ከጥር ወር 1910 ዓ.ም ጀምሮ እንደዋዛ የጀመራቸው ህመም ጠናባቸውና የካቲት 4 ቀን 1910 ዓ.ም ሌሊት በተወለዱ በ78 ዓመታቸው በአራት ዓመት የሚበልጧቸውን ባለቤታቸውን በሞትም አራት ዓመት አስቀድመዋቸው ይችን ዓለም ተሰናበቱ፡፡ የማረፋቸው ዜና እንደተሰማም በቤተ መንግሥቱ 25 ጊዜ መድፍ ተተኮሰ፡፡
መልካም ልደት ለንጉሱ እና ለንግስቲቱ!
ታዘብ አራጋው
Source:- https://www.facebook.com/share/p/16uP3zq91o/?mibextid=wwXIfr