“..አጥራችንን ደህና አድርጎ ማጠር አስፈላጊ ነበር….!!!”

Sourced by Asrat keregne
ጠቅላይ ሚኒስትር ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ኃብተወልድ ፣ በአለም የፖለቲካ መድረክ ኢትዮጵያን በከፍተኛ ደረጃ ያስተዋወቁ ፣ ብሔራዊ ጥቅሟንና የግዛት ሉአላዊነቷን ያስጠበቁ ፣ ከነበሩን ትላልቅ ነፍሳት መሀከል አንዱ ነበሩ። ምሥጋና ላይ በአያሌው ቁጥብ መሆናቸው የሚነገርላቸው ፕሮፌሰር መስፍን ፣ መጨረሻ ባሳተሙት መጽሐፋቸው “…ከ 1960 ዓ.ም በሁዋላ ያለውን የኢትዮጵያ ታሪክ አቅጣጫ የለወጡ አንድ ጸሐፊ ትእዛዝ አክሊሉ ኃብተወልድ ናቸዉ።
አክሊሉ ኃብተወልድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ፣ ጸሐፌ ትእዛዝ ነበሩ። ከሁሉም በላይ በነጮች ዘረኛነት ዘመን ፣ የጥቁር ድምጽ በማይሰማበት ወቅት በተባበሩት መንግሥታት ጉባኤ የማይደፈሩትን ነጮች በሙግት እያሳፈሩ ቀልባቸውን ሲገፉ የነበሩ ሰዉ ናቸው…” በማለት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
በዚያን ሰሞን አሮጌ መጽሔቶች ሳገላብጥ “የመጨረሻው ኑዛዜ… !” በሚል ርዕስ እኚህ ታላቅ ሰው ለሀገራቸው የፈጸሙትን ታላቅ ገድል የሚያወሳ ጽሑፍ አገኘሁ። እሥር ላይ ሆነው ከመሞታቸው በፊት በማስታወሻ መልክ ያኖሩት አስገራሚ ታሪክ ነው።
አፋምቦን ከፈረንሳይ ፣ ጋምቤላን ከእንግሊዝ እጅ ፈልቅቀው ወደ ቀድሞ እናት ግዛታቸው ኢትዮጵያ የቀላቀሉበት የዲፕሎማሲያዊ ጥበብ በእጅጉ ያስደምማል።
“….ውጪ ጉዳይ እንደገባሁ ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ጋር ያላትን ወሰን በኢንተርናሽናል ውል መሠረት በትክክል መወሰን ዋና ጉዳይ አድርጌ ነበር ያየሁት ።….ትንሽ መንግሥት እንደመሆናችን መጠን የተከበብነው ያን ግዜ በነኛው በቅኝ ገዥዎች ስለሆነ ‘አጥራችንን ደህና አድርጎ ማጠር አስፈላጊ ነበር። ብዙ ግዜ ከአጼ ሚኒልክ ጋር የተደረገው ውል ግልጽ ያልሆነ ነበር። ኢትዮጵያ ከመወረሯ በፊት (1935) ካንድ ሀገር ጋር ብቻ ነበር ወሰናችን የተካለለው (ከእንግሊዝ ሶማሌ) በዚህ ምክንያት ነው ከጎረቤት ሀገራት ጋር በየጊዜው የድንበር ግጭት የነበረን…” በማለት ከባዱን የዲፕሎማሲያዊ ሥራ እንዴት እንደተያያዙት ጸሐፊ ትእዛዝ ያወሳሉ።
እስኪ ጋምቤላ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለስ (ከ 1954 — 1955 ዓ.ም) ያደረጉትን ትግል እንይ ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደገለጹት ኢትዮጵያ ዙሪያዋን በቀኝ ገዥዎች የተከበበች ብቸኛ ነጻ ሀገር ነበረች። እንዲህ እንዳሁኑ በዘርና በጎሳ ተከፋፍለን ፣ በጦርነት እርስ በእርስ ስንተላለቅ ፣ አጋጣሚውን በመጠቀም ቅኝ ገዢዎች በመስፋፋት ድንበራችንን ጥሰው በመግባት ብዙ ቦታዎችን ይዘውብን ነበር። በኃይል ከተያዙብን ሥፍራዎች አንዱ ጋምቤላ ነበር።
የኢትዮጵያና የሱዳን ድንበር የሚወሰነው በአጼ ምኒልክና በእንግሊዞች መካከል በተፈረመው ውል መሠረት ነበር። እዚህ ውል ላይ “…ጋምቤላ በእንግሊዞች እጅ ይቆያል ፣ ይኸውም እንግሊዝ ሱዳንን እስከያዘች ድረስ ነው ….”የሚል ነበረበት።
በ 1954 ዓ.ም ንጉሠ ነገሥት ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ እና ጸሐፊ ትእዛዝ አክሊሉ እንግሊዝን ይጎበኛሉ። አጋጣሚውን በመጠቀም ብልሁ አክሊሉ “..ሱዳን በቅርብ ግዜ ነጻ መሆኗ አይቀርም ፣ ስለዚህ በውሉ መሠረት አሁኑኑ ጋምቤላን ብታስረክቡን? ” ብለው የእንግሊዙን ጠቅላይ ሚኒስትር ኤደንን ይጠይቃሉ ኤደንም “..የሱዳን ነጻነት ገና ነው።
ቢያንስ ሁለትና ሦስት አመት ይወስዳል። በውሉ መሠረት ሱዳንን እስክንለቅ መጠበቅ አለባችሁ.. !”በማለት ኮስተር ብሎ ይመልሳል። "...ይሄማ አይሆንም! ሱዳን ነጻ መንግሥት እስክትሆን ጠብቀን በሁዋላ ከሱዳን ወንድሞቻችን ጋር ጋምቤላን አስረክቡን ብለን መጣላት አንፈልግም ስለዚህ አሁኑኑ ጋምቤላን አስረክቡን "በማለት አክሊሉ አጥብቀው ይጠይቃሉ። ከብዙ ክርክር በሁዋላ በአይበገሬው ኢትዮጵያዊ ጽናት አንድ ስምምነት ላይ ይደርሳሉ። ይህም "...ሱዳን ነጻ ከመውጣቷ ከሦስት ወር በፊት ጋምቤላን ለማስረከብ ሁለቱ መንግሥታት ተነጋግረው እንዲረካከቡ..."የሚል ነው።
ግን እንግሊዝ ውሉን ችላ ብላና ቃሏን አጥፋ ሦስት ወር ባልሞላ ግዜ ውስጥ ለሱዳን ነጻነቷን የምትመልስ መሆኗን በሬድዮ ታውጃለች። እንግሊዝ ጋምቤላን ሳታስረክብ ሱዳንን ለቃ መውጣቷ በኢትዮጵያና በሱዳን መሀከል ጦርነት መጫር ፈልጋ መሆኑን ለመረዳት አክሊሉ ግዜ አልወሰደባቸውም። ዜናውን እንደሰሙ በፍጥነት ማስታወሻ አዘጋጅተው በኢትዬጵያ የእንግሊዙን አምባሳደር ጠርተው ማስታወሻውን ይሰጡታል። የማስታወሻው ቃል "...በውሉ መሠረት ጋምቤላን እንግሊዞች የሚይዙት ሱዳን እስካለ ድረስ ነው። አሁን እንግሊዞች በድንገት ሱዳንን ስለሚለቁ ፣ በተስማማነው መሠረት ከሰኞ ጀምሮ (ከሁለት ቀን በሁዋላ) ኢትዮጵያ ጋምቤላን ትይዛለች ...!" የሚል ቆፍጠን ያለ መልእክት የያዘ ነበር። አምባሳደሩም ሀሳቡን ተቃውሞ መልእክቱን ግን ለሀገሩ መንግሥት እንደሚያስተላልፍ ተናገረ።
ወዲያው ለሱዳን የውስጥ አስተዳደር ባለስልጣናት በአቶ መለስ አምዶም (በወቅቱ የኢትዮጵያ አገናኝ ሁዋላም በግብጽ አምባሳደር በነበሩት) በኩል ቴሌግራም ይልካሉ።
“..ለነጻነታችሁ መልካም ምኞታችን ነው። ወደፊት እንደ ወንድማማቾች አብረን እንድንሠራ ጋምቤላ በቅኝ ገዢዎች በኃይል ተይዞብን ስለነበር ከሰኞ ጀምረን መያዛችን…. ወዳጅነታችንን የማይነካና የሱዳንም ቆንሲላ ማናቸውም ቤትና ንብረት ቢኖር ለግዜው መቆየት ይችላል… “የሚል ሀሳብ በመልእክቱ ተካቷል። አክሊሉ እንዳቀዱት ሰኞ እለት የኢትዮጵያ የፖሊስ ኃይል ጋምቤላ ገብቶ የኢትዮጵያን ባንዲራ ሰቀለ። አስተዳደሩንም ሙሉ በሙሉ ያለምንም ችግር ተቆጣጠረ። ሱዳኖች በወቅቱ በነጻነታቸው ተደስተው በጎ ምላሽ የሰጡ ቢሆንም.. ፣ ዘግይተው ሀሳባቸውን ለውጠዋል። ከሦስት ወር በሁዋላ በምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሚመራ ልዑክ ጋምቤላ ስላላቸው ንብረት ለመነጋገር አዲስ አበባ ይገባል። በስብሰባ ወቅት በቁጣ "..ለእንግሊዞች የፈቀዳችሁትን ጋምቤላን ለምን ለእኛ አፍሪካውያን ትነፍጉናላችሁ? ጋምቤላን መልሱልን.. !"በማለት ጠይቀዋል።
አክሊሉም “…እኛ ወደን የሰጠናቸው አይደለም! የእንግሊዝ ቀኝ ገዥዎች አፍሪካን ሲከፋፈሉ በኃይል የወሰዱብን ነው። አሁን ቅኝ ግዛት ሀገራት ነጻ ይውጡ ሲባል.. እንዴት እናንተ እንዲህ አይነት ጥያቄ ትጠይቃላችሁ? ! ይልቅ በሰላማዊና በወንድማማች መንፈስ የምትወስዱትን እቃ ዝርዝር ብንነጋገር ይሻላል። ወደዚህ የመጣችሁበትና የተስማማንበት ጉዳይ ይህ ነው!ከዚህ ውጪ በሌላ ጉዳይ ለመነጋገር የተስማማንበት ሥርአት አይፈቅድም.. !” አሏቸው። ሱዳኖችም ተቆጥተው ስብሰባውን ጥለው ወጡ። ጸሐፊ ትእዛዝ በማስታወሻቸው እንደሚዘክሩት "..በሌላ ጉዳይ ካልሆነ በቀር ከዚያን ግዜ አንስቶ የጋምቤላ ጉዳይ በሱዳኖች ተነስቶ አያውቅም.. !" ይሉናል።
“ክብር ኢትዮጵያን ከነ ነፃነቷ ላስረከቡን ጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን ይሁን🙏
