ድል አብሳሪዎቹ ጀግኖች ኢትዮጵያውያት

0

በእውቀቱ ስዩም ከአሜን ባሻገር መጽሐፉ “ሴቶች በዋሉበት” በሚል አርእስት ባሰፈረው ሃሳብ የሴቶችን በየዘመኑ ኹሉን አቀፍ አበርክቶ አብራርቷል።

img_1140
0 0
Read Time:2 Minute, 21 Second

በጋሻው አደመ

ኢትዮጵያ ልዕልናዋን፣ ክብሯን፣ ህልው ምግባሯን በጀግኖቿ ተጋድሎና በመስዋዕትነት ያጸናች ሀገር ናት።

ኢትዮጵያ ከታሪካዊ ጠላቶቿ መንጋጋ የወጣችባቸው የዘመን ሽራፊ አሻራዎች እንደሚነግሩን በየጊዜው ጊዜ የማይሽረው የታሪክ ጉልላት መሠራቱን ነው።

የድል ታሪኮቿ ኹሉ በ‘ዕድል’ የተገኙ ሳይኾኑ ኢትዮጵያዊነት ወኔንና ጀግነትን በታጠቁ ክንደ-ብርቱ ልጆቿ የተገኙ ስለመኾናቸው ታሪክ ምስክር ነው።

የጥቁር ሕዝቦች ኹሉ የነጻነት መስታዎት የዓድዋ ጦርነት የነጻነት ድል ታሪክ፣ እብሪተኛው ዚያድ ባሬ ድል የተደረገበት የካራማራው ጦርነት የድል ታሪክ የተገኘው በዕድል አልነበረም።

ፋሽስት ጣሊያን በ1888 ዓ.ም አድዋ ተራሮች ስር እርም በልታ ብትመለስም ከ40 ዓመታት በኋላ ግን እረመ-ቢስ ኾና የበቀል ስሌት ሰንዳ ለዳግም ወረራ መጣች። የሽንፈት ካባዋን ልታወልቅ፣ የበቀል በትሯን አነሳች። እኒያን የአድዋ ልጆች አደብ ልታስገዛ፣ ያችን የጥቁር ሕዝቦች ኹሉ ተምሳሌት ሀገር ልትረግጥ ወረራ ፈጸመች፤ በ1928 ዓ.ም።

ይኽ ድርጊቷም ቀድሞውንም በሀገራቸው ኅልውና ሰንፈው የማያውቁት ጀግኖችን ለሀገር ክብርና ልዕልና ተጋድሎ ቀሰቀሰ፤ የአርበኝነቱ ምዕራፍ ተጀመረ።

በዚያ የአርበኝነት ዘመን እነማን ነበሩ?

ጣሊያን በዳግም ወረራዋ ኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ስትከፍት የሀገርን ኅልውናና ልዕልና ለማስጠበቅ ወኔ የከዳው አልነበረም ማለት ይቻላል።

ስለ የኢትዮጵያውያን አርበኝነት ገድል ስናወሳ የሴት አርበኞችን ሚና ማስታወስ ተገቢ ነው።

በእውቀቱ ስዩም ከአሜን ባሻገር መጽሐፉ “ሴቶች በዋሉበት” በሚል አርእስት ባሰፈረው ሃሳብ የሴቶችን በየዘመኑ ኹሉን አቀፍ አበርክቶ አብራርቷል።

በእውቀቱ እንደሚለው የሴቶች የድል በረከት “ከጓዳ እስከ አውደ ግንባር” ሚዛኑ ከባድ ነው። ሴቶች በጦርነት ወቅት ምግብ ያቀርባሉ፣ ሃሳብ ያቀርባሉ፤ ወኔ ያስታጥቃሉ፤ ጥይት ያቀብላሉ፤ ታጥቀው ያዋጋሉ፤ ይዋጋሉ። በዚኽም ለሀገር ክብርና ልእልና በሚደረግ ተጋድሎ ያስቀመጡት አሻራ ታሪክ የሚዘነጋው አይደለም።

“…እናንተም ወዲህ ኑ እኛም
እንመጣለን
አረበረከቴ ላይ እንገናኝ፡፡ …

ምናባቱ ፋሽስት፣
ፋሽስት ምናባቱ፣
እንወጋዋለን በገዛ ብረቱ፤”

ይህ ግጥም ጀግኖችን የፈጠረ፣ የይቻላል ስነ-ልቦናን የገነባ፣ የጀግና ደንቡን ጥሪ ያስተጋባ፣ የቁርጥ ቀን አለኝታዎችን ያሰባሰበ፣ የጀግኖች አርበኞች ድምጽ በመኾን አገልግሏል።

በአርበኝነት ዘመኑ የተጋድሎ ታሪክ ሲወሳ ስማቸው ከፍ ብሎ የሚነሳ እልፍ ጀግኖች አሉ።

የጎጃሙን አባ ኮስትር በላይ ዘለቀን ስናነሳ – የሸዋዋን ቅምጥል ሸዋረገድ ገድሌን አንዘነጋም። የሸዋውን አይደፈሬ ራስ አበበ አረጋይን ስናወሳ – “አምሳለ- ጣይቱ” የሚባልላትን አርበኛዋን ልዕልት ከበደች ሥዩምን አንዘነጋም።

በሰሜን የማይጨው ግንባር ከዘመቱት ሴቶች መካከል ከአርሶ አደር ቤተሰብ እስከ ልዕልቶቱ ይገኙባቸዋል፡፡

“አፍሪካና ሁለተኛው የዓለም ጦርነት” በሚል ርዕስ በአሜሪካ ካምብሪጅ ፕሬስ በታተመ የጥናት መድበል ውስጥ ዶክተር ኀይሉ ሀብቱ ፋሽስቱን የተዋጉ የኢትዮጵያ ሀገር ወዳድ ጀግና ሴችን የቃኙበት ጥናት ተጠቃሽ ነው።

በዚህ ጥናታዊ ዳሰሳ ከተጠቀሱ ሴቶች መካከልም ወይዘሮ ዘነበች ወልደየስ ባለቤታቸውን ተከትለው የዘመቱት አርበኛ ከአርሶ አደር ቤተሰብ የተገኙ ናቸው ይሉናል።

ሌላዋ ዘማች ልዕልት ሮማንወርቅ ኃይለሥላሴ ከባለቤታቸው ከባሌው ገዢ ጋር አብረው ዘምተዋል።

ከባላቸውና ከልጃቸው ጋር የዘመቱት አርበኛዋ ወይዘሮ ልክየለሽ በያን በፋሺስት ጣሊያን ወረራ ጊዜ ባለቤታቸው ሰማዕትነትን ሲቀበሉ ያዩትንና እሳቸው የፈጸሙትን ጀብዱ ደግሞ ፀሐይ ብርሃነ ሥላሴ “ኖርዝኢስት አፍሪካን ስተዲስ” ባሳተመው መድብል ውስጥ “ሽምቅ ተዋጊ ሴቶች” በሚለው መጣጥፋቸው ገልጸውታል፡፡

አርበኝነት በየዘርፉ

ፋሽት ጣሊያን ባሕር ተሻግሮ ድምበር ጥሶ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ሲዳፈር ጀግና ሀገር ወዳድ ሁሉ ግምባር የዘመተው በየፊናው ነበር።

ከትጥቅ እስከ ስንቅ፣ ከሥነ-ልቦና ግንባታ እሰከ ሕክምና ሴቶችም ተሳትፈዋል።

ጦር ግንባር ድረስ በመሄድ ተዋጊው የሀገር ጀግና በቆሰለ ጊዜ ደሙን አጥበው፣ የተገኘውን የሀገር ባሕል መድኃኒት አድርገው፣ መግበውና ውኃ አጠጥተው ያድናሉ፡፡

በሕክምናው በኩል ወይዘሮ ስንዱ ገብሩ እና ወይዘሮ ጽጌ መንገሻ ተጠቃሽ መኾናቸውን ታሪክ ሰንዷል፡፡

ለዚኽም ‹‹ኢጣልያ በኢትዮጵያ – ከወልወል እስከ ጎንደር›› የተሰኘውን የተድላ ዘገየን መጽሐፍ ልብ ይሏል።

ክብር ለኢትዮጵያ አርበኞች!

()

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *