የጎንደሩ ሐኪም ወርቅነህ እሸቴ
በወለጋው አምባሳደር አማኑኤል አብርሃም አይን፣
A 19th Century Victorian Gentleman, and Ethiopian Nationalist – Dr Charles Martin
“ትውልዱ ከዚህ አውራጃ ነው ከዚያ ሳይሉ፣ ለበርካታ ኢትዮጵያውያን ይሰጡት የነበረው ርዳታና ድጋፍ እንዲሁም ያሳዩ የነበረው የእውነተኛ ኢትዮጵያዊነት አርአያነት እስከ ዘመኔ መጨረሻ በልቤ ውስጥ ይኖራል”
አዛዥ ወርቅነህ የተወለዱት በ1857 ዓ.ም ጎንደር አደባባይ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ነው፡፡ በ1860 ዓ.ም እንግሊዞች ከአጼ ቴዎድሮስ ጋር መቅደላ ላይ በተዋጉበት ጊዜ፣ ኮሎኔል ቻምበርሊን የተባለ የእንግሊዝ መኮንን የ3 አመቱን ልጅ ወርቅነህን ብቻቸውን በአምባው ላይ አግኝቶ ወደ ህንድ ወሰዳቸው፡፡ ኮሎኔሉ ብዙም ሳይቆይ በመሞቱ፣ ኮሎኔል ማርቲን የሚባል ጓደኛው ወርቅነህን ወስዶ በት/ት አሳደጋቸው፣ ክርስትና አስነስቶም ቻርልስ ማርቲን አላቸው፡፡
አዛዥ ወርቅነህን ለመጀመሪያ ጊዜ ያወቅኳቸው የተፈሪ መኮንን ት/ቤትን በአዳሪነት ስቀላቀል በ1918 ዓ.ም ነው፡፡ በአዲስ አበባ ስራ የማግኘት ተስፋ እንደሌለኝ ከተረዳሁ በኋላ፣ የቀድሞ ት/ቤቴ የተፈሪ መኮንን አስተዳዳሪ ለነበሩትና በጊዜው የሐረርጌ ጨርጨር አውራጃ አበጋዝ ሆነው ሲያገለግሉ ለነበሩት አዛዥ ወርቅነህ በደብዳቤ ስራ እንዲሰጡኝ ለመጠየቅ ወሰንኩ፡፡
ጓደኛዬ የቄስ ባድማ ልጅ ጳውሎስ ከአባቱ የቴምብር መግዣ ሲያመጣ፣ እኔ ደግሞ በ2ታችን ስም በእንግሊዝኛ ደብዳቤ በመጻፍ ለአዛዥ ወርቅነህ ላኩላቸው፡፡ አዛዥ ወርቅነህ በቀድሞ ተማሪዎቻቸው መንገላታት አዝነው ለሁለታችንም ስራ ሊሰጡን ወስነው፣ በጨርጨር የንግድ ሹም የነበሩት ልጅ ክፍሌ ዳዲ ሁለታችንንም ከአዲስ አበባ ይዘው እንዲመጡ አዘዟቸው፡፡
ይሁን እንጂ ጓደኛዬ ጳውሎስን መልእክተኛው አአ ከመድረሳቸው በፊት ራስ ኃይሉ ተ/ኃይማኖት ለት/ት ወደ ቤይሩት ስለላኩት፣ እኔ ጥቅምት 21 ቀን 1924 ዓ.ም ከአአ በባቡር ተሳፍሬ በማግስቱ አሰበ ተፈሪ ገባሁና ጥቅምት 23 ቀን 1924 ዓ.ም ከአዛዥ ወርቅነህ ጋር ተገናኘሁ፡፡
ከዚህ በኋላ አዛዥ ወርቅነህ ከቤታቸው ጀርባ አራት ክፍል ያሉት ት/ቤት በማሰራት እንዲሁም ዴስክ፣ ሰሌዳና ነጭ በሃ ድንጋይ/ጠመኔ ከአአ አምጥተው በማሟላት ህዳር 21 ቀን 1924 ዓ.ም ት/ቤቱ ተከፈተ፡፡ ተማሪዎች እየበዙ ሲመጡ ሌሎች 7 አስተማሪዎች ተቀጠሩ፡፡ ሐኪም ወርቅነህ የመማሪያ መጽሀፍት፣ ደብተር፣ ወረቀት፣ እርሳስ፣ ቀለምና ብእር እንዲገዛ ያቀረብኩትን ጥያቄ በመቀበል እነዚሁ እቃዎች በቀጥታ ከለንደን እንዲመጡ በደብዳቤ አዘዙ፣ ገንዘቡንም በለንደን ከነበራቸው የባንክ ሂሳብ እራሳቸው በግል በመክፈል የት/ሚኒስቴርን ቢሮክራሲ አስቀሩልኝ፡፡
በዚህ ሁኔታ ከአዛዥ ወርቅነህ ጋር እየኖርኩ በሳቸው ጸሃፊነት፣ በአስተማሪነትና በት/ቤት አስተዳዳሪነት ለ3 አመት ያህል ከሰራሁ በኋላ በ1927 ዓ.ም ወደ ውጭ አገር የሚያስኬድ እድል አገኘሁ፡፡ ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ለመውረር በምትዘጋጅበት ጊዜ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሐኪም ወርቅነህን በእንግሊዝ ባለሙሉ ስልጣን ሚኒስትር አድርገው ሾሟቸው፡፡ ብዙ ሰዎች በረዳትነት ይዘዋቸው እንዲሄዱ አዛዠ ወርቅነህን ቢጠይውቋቸውም፣ እሳቸው ግን የመረጥኩት ልጅ ስላለ አይሆንም ብለው መለሷቸው፡፡
ሰኔ 16 ቀን 1927 ዓ.ም በባቡር ተሳፍረን ወደ ጅቡቲ ሄድን፡፡ ከጅቡቲ በመርከብ በስዊስ ካናልና በፖርት ሳይድ አድርገን ሜዲትራንያንን እያቋረጥን እስከ ማርሴይ ወደብ ተጓዝን፡፡ በመጨረሻም በባቡር ከማርሴይ ወደ ፓሪስ፣ ከፓሪስ ወደ ሎንደን በመጓዝ ሰኔ 29 ቀን 1927 ኣ.ም ሎንዶን ከተማ ገባን፡፡ ሎንዶን ከመድረሳችን በፊትም ፓሪስ ላይ የኢትዮጵያውን ሚ/ር በጅሮንድ ተክለ ሐዋርያትን አገኘናቸው፡፡ እኔም ከ1927 -1931 ዓ.ም ድረስ በሎንዶን የኢትዮጵያ ሌጋሲዮን ጸሀፊ ሆኜ አገለገልኩ፡፡
ክቡር አዛዥ ወርቅነህ እሸቴ አገሬንና ወገኔን ለማገልገል እድል ካገኘሁበት ጊዜ ጀምሮ ለረጅም ዘመን ስራዬን እንደ ፋና እንድመራ የረዱኝ መሆኑን ይህንን ጽሁፍ ለሚነቡ ሁሉ ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡ ትውልዱ ከዚህ አውራጃ ነው ከዚያ እያሉ ሳይለያዩ ለበርካታ ኢትዮጵያውያን ይሰጡት የነበረው ርዳታና ድጋፍ እንዲሁም ያሳዩ የነበረውን የእውነተኛ ኢትዮጵያዊነት አርአያም እስከ ዘመኔ መጨረሻ በልቤ ውስጥ ይኖራል፡፡
የሕይወቴ ታሪክ፣ አማኑኤል አብርሃም፣ አአዩ ፕሬስ፣ ገጽ 11-23
የፎቶ መግለጫ፣ የመጀመሪያውን ፎቶግራፍ ሐኪም ወርቅነህ የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት በነበረችው ህንድ በ1865 ዓ.ም እንደተነሱ ይታመናል፡፡ 2ኛውን ፎቶ ሐኪም ወርቅነህ በእንግለዝ የኢትዮጵያ ሚ/ር በነበሩበት ጊዜ በ1928/1929 ዓ.ም በሎንዶን የተነሱት እንደሆነ ይታመናል፡፡
ተጨማሪ ማስታወሻ፣ ሐኪም ወርቅነህ ከ1875 ዓ.ም ጀምሮ ዘመናዊ የሕክምናና የሰርጀሪ ት/ት በመማር ከ135 አመት በፊት የእንግሊዝ ኮሎኒ በነበሩት በርማና ህንድ የእንግሊዝን መንግስት ያገለገሉ፣ ከአድዋ ጦርነት ማግስት ጀምሮ በውስጣቸው ሆኖ ያሸነፋቸውን የኢትዮጵያ ናፍቆት በመጨረሻ ከምኒልክ ጋር በመገናኘት እውን ያደረጉ፣ እስከ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ድረስ አገራቸውን ያገለገሉና እውነተኛ የአገር ፍቅር እንደነበራቸው ሌሎችም መስክረዋል፡፡
ከነዚህም አንዱ “Victorian Gentleman and Ethiopian Nationalist: The Life and Times of Hakim Wärqenäh, Dr Charles Martin” በሚል ርእስ በ Peter P. Garretson የተጻፈው በሀኪም ወርቅነህ የህይወት ታሪክ ላይ የሚያጠነጥነው መጽሀፍ እንደሆነ በመግለጽ የበለጠ ለማወቅ የሚፈልጉ ሁሉ ይህንኑ እንዲያነቡ አንዳንዶች መክረዋል፡፡