የአቶ ጃዋር መሐመድ ጽሑፍ ንድፈ ሐሳባዊ ቅንበባ (ክፍል ሦስት)

0
1 0
Read Time:28 Minute, 18 Second

ክፍል ሦስት)

በጌታሁን ሔራሞ

ከላይ በሠፈረው ዋና ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ ሚያዝያ 15 ቀን 2015 ዓ.ም. እና ሚያዝያ 29 ቀን 2015 ዓ.ም. በሪፖርተር ዕትሞች ክፍል አንድና ክፍል ሁለት መጣጥፎችን በተከታታይ ማስነበቤ ይታወሳል፡፡ ለንድፈ ሐሳባዊ ቅንበባው መነሻችን የነበረው ከኦሮሚኛው ወደ አማርኛ ሲተረጎም፣ ‹‹ያለንበት ሁኔታና ቀጣዩ የትግል ምዕራፍ›› በሚል ርዕስ በአቶ ጃዋር መሐመድ የተለቀቀው ጽሑፍ ነበር፡፡ በክፍል አንድና ሁለት በጽሑፉ ውስጥ ከተንፀባረቁት ንድፈ ሐሳቦች ውስጥ የ‹‹ኧርነስት ገልነርን›› ኢንዱስትሪ ወለድ ዘመናዊ ብሔርተኝነትን፣ የቤኔዲክት አንደርሰንን የኅትመት ካፒታሊዝም ወለድ ዘመናዊ ብሔርተኝነትንና የአንቶኒ ስሚዝን ኢቲኖሲምቦሊዝምን ለመዳሰስ ሞክረናል፡፡ በዛሬው ክፍል ሦስቴ ጽሑፌ በአቶ ጃዋር ጽሑፍ ውስጥ የተስተዋለውን የ‹‹ፕሪሞርዲያሊዝም›› ንድፈ ሐሳብ አዝማሚያዎችን ካነሳሁ በኋላ ወደ ማጠቃለያ ሐሳብ እሻገራለሁ፡፡

የፕሪሞርዲያሊዝም ንድፈ ሐሳብ

በአቶ ጃዋር ጽሑፍ ውስጥ በጣም ግልጽ በሆነ መልኩ ጥቅም ላይ ከዋሉ የብሔርተኝነት ንድፈ ሐሳቦች ውስጥ አንዱ የ‹‹ፕሪሞርዲያሊዝም›› ዕሳቤ ነው፡፡ ከብሔርና ከብሔርተኝነት ህላዌ አኳያ፣ በዚህኛው ፅንሰ ሐሳብና ቀድሞ በተነሱ ሌሎች ፅንሰ ሐሳቦች መካከል ያለው ልዩነት የትየለሌ ነው፡፡ ለምሳሌ ዘመናዊያኑ የብሔርተኝነት አጋፋሪዎች ማለትም ‹‹ገልነር›› እና ‹‹አንደርሰን›› የብሔር ማንነት ሰው ሲወለድ በተፈጥሮ የሚወረስ ሳይሆን፣ ከተወለደ በኋላ በታሪክና በማኅበራዊ ሥሪት (Social Construction) ውስጥ ተፀንሶና አድጎ የሚፈጠር ማንነት ነው ሲሉ፣ እንደ ስሚዝ ያሉ ኢቲኖሲምቦሊስቶች ደግሞ ለብሔር መፈጠር የግድ ተጨባጭ የሆነ ምክንያት (Objective Cause) ሳይሆን፣ የቡድኑን አባላት በበቂ ሁኔታ ማሳመን የሚችል አፈ ታሪክ (Myths) ካለ በቂ ነው ይላሉ፡፡ በሌላ አገላለጽ የ‹‹Common Ancestery›› ትርክት የግድ እውነት እንዲሆን አይጠበቅም፡፡ የአፈ ታሪኩ ጥንካሬ የሚፈተሸው ከእውነታ ጋር ተመሳክሮ ሳይሆን፣ የዘውጌ ቡድኖቹን ስሜትንና አዕምሮ ተቆጣጥሮ ከማሳመን ብቃቱ አንፃር ነው፡፡

ፕሪሞርዲያሊዝም ግን የዘውጌንም ይሁን የብሔር ማንነትን በቀጥታ የሚያገናኘው ከሰው ልጆች ተፈጥሯዊ ማንነት ጋር ነው፡፡ ለፕሪሞርዲያሊዝም ትንታኔ የአንበሳውን ድርሻ የሚጫወቱት የሳይንስ ዘርፎች፣ የባዮሎጂና የሶስዮ ባዮሎጂ ዲሲፒሊኖች ናቸው፡፡ የዘውጌን ማንነት በሶስዮ ባዮሎጂ ድጋፍ ትንተና ከሚሰጡ ምሁራን መካከል ደግሞ ቬን ዴን በርግ ተጠቃሽ ነው፡፡ በርግ በሶስዮ ባዮሎጂ መሥፈርት በአንድ የዘውጌ አባላት መካከል ያለው ግንኙነት በአንድ ቤተሰብ መካከል የሚኖር ግንኙነት ተቀጽላ (Kinship Extension) ነው ብሎ ያምናል፡፡ ስለዚህም የአንድ የዘውጌ አባል ለራሱ የዘውጌ ቡድን ቢያደላ ነገሩ ‹‹ዘመድ ከዘመዱ፣ አህያ ከአመዱ›› ነውና አትፍረዱበት ይለናል (Kin Selection/In Group Favourtism)፡፡ ከዚህም ባለፈ በርግ የዘውጌ ማንነት ብቻ ሳይሆን የአንድ ዘውግ አባላት ባህልም ሲወርድ ሲወራረድ የመጣው በዋናነት በ‹‹ዲኤንኤ›› ውቅርና በደም ትስስር ነው የሚል መከራከሪያም አለው፡፡ በደማችን ውስጥ ከትመው ባህልንና ሌሎች የባህሪይ እሴቶችን ፎቶ ኮፒ እያደረጉ፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚያስተላልፉ ‹‹Mirror Neurons›› በሰውነታችን ውስጥ አሉ ብሎም ያምናል፡፡ እንግዲህ እኛም አገር ከሩሲያዎች የገለበጥነው የዘውግ ማንነትን፣ በተለይም በአባት የዘውግ ግንድ መበየን የዚሁ የፕሪሞሪዲያል ዕሳቤ አንዱም ውጤት ነው፡፡ ለማንኛውም ቬን ዴን በርግ በንድፈ ሐሳቡ ዙሪያ ከጻፋቸው ወደ አሥር ከሚደርሱ መጻሕፍት ውስጥ ‹‹Race and Racism (1967), The Ethnic Phenomenon (1981), Race and Ethnicity: a Sociobiological Perspective (1978)››፣ ወዘተ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በአቶ ጃዋር ጽሑፍ ውስጥ ፕሪሞሪዲያል ዕሳቤ ስለመንፀባረቁ ማጤን ያን ያህል ከባድ አይደለም፡፡ ለምሳሌ በገጽ 8 ላይ በግልጽ ‹‹በደም የመተሳሰር›› ሥነ ልቦናን ሕዝቡ እንዲያዳብር ጥሪ ሲያስተላልፍ ይስተዋላል፡፡ ይህ እንግዲህ ፕሪሞርዲያሊስቶች በተደጋጋሚ ‹‹Common Ancestry, Blood Ties/Relationship›› በማለት የሚገልጹትን ፅንሰ ሐሳብ የሚወክል ነው፡፡ በዚሁ ገጽ ላይ አቶ ጃዋር የፕሪሞሪዲያሊዝም ቃና ያለውን ሌላም ሐሳብ አንፀባርቋል፣ ‹‹…ይህ ማለት አንድ ማኅበረሰብ ሊመጣ የሚችልበትን አደጋ ለመመከት የቡድኑን አባል በተናጠል በቀጥታ ሊቃጣበት የሚችልን አደጋ (Direct risk to members of the group) ለመቀልበስ በጋራ መመከት/መጋፈጥ ግድ ይላል››፡፡ ይህም ገለጻ በቀጥታ ከፕሪሞሪዲያል አስተሳሳብ ጋር የሚገናኝ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ለቬን ዴን በርግ ፕሪሞርዲያል ጥናቶች መነሻ የሆነለት በዋናነት የዳሪዊን የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ ነው፡፡ ዳርዊን ‹‹The Survival of the Fittest›› ንድፈ ሐሳቡ ውስጥ አንድ የእንስሳት ዝርያ በልዩነት የራሱን ዝርያ አባላትን ከተለያዩ ጥቃቶች ተከላክሎ ማስቀጠል የሚችልበትን ሥልት በተመለከተ በሰፊው ተንትኖ አስቀምጧል፡፡ አድልአዊነት በሠፈነበት ታክቲክና ስትራቴጂ የራስን ወገን ብቻ ከጥቃት የመከላከል ሥልት በሶስዮ ባዮሎጂስቶቹ ‹‹In Group Favoritism›› ወይም ‹‹Kinship Selection›› ተብሎ ይጠራል፡፡ በሌላ እንግሊዝኛ ደግሞ ‹‹Preference of kin over non-kin›› ተብሎም ሊገለጽ ይችላል፡፡

ስለ ‹‹In Group Favoritism›› ለማስረዳት፣ አቶ ጃዋር በጽሑፉ ውስጥ በሥልጣን ላይ ያሉ የኦሮሞ ብሔር አባላት ስህተት ቢፈጽሙ እንኳን አጋፍጠን ለባዕድ መስጠት የለብንም የሚል አንድምታን በሰነቀ ምሳሌ ያስረዳውን ከመጠቆም የሚሻል ማስረጃ የለም፡፡ ምሳሌው ይህን ይመስላል፡፡ ‹‹የባዕድንም የራስህንም አምባገነን በተመሳሳይ መንገድ ልትታገላቸው አትችልም፡፡ አንድ እንግዳ ከቤትህ በሬህን ቢሰርቅ መላው ቤተሰብህ አብሮህ ይፈልጋል፣ ይመልሳልም፡፡ ሆኖም ወንድምህ ቢሰርቅህስ? ማንም የራሱን ሥጋ ለመጉዳት እንደሌላው አይሯሯጥም፣ እኩል አይደለምና፡፡›› በአቶ ጃዋር ጽሑፍ ውስጥ የፕሪሞርዲያል ዕሳቤውን በመፈተሽ ሒደት ሌላ ማስረጃ ባይኖር እንኳን፣ ከላይ የተቀመጠው ምሳሌ ብቻውን በቂ ነው ባይ ነኝ፡፡ በነገራችን ላይ የ‹‹In Group Favoritism›› ጥናቶች ከሰው ልጆች ባለፈም በጉንዳኖች፣ በምስጦች፣ በንቦችና በሽኮኮዎች ላይ ተደርገዋል፡፡ በተለይም ሼርማን ፕ የተባለ ሳይንቲስት ሽከኮዎች ቡድናቸው ላይ የሚያነጣጥር አደጋ ከመከሰቱ በፊት ማስጠንቀቂያውን በልየታ (Exclusively) ለራሳቸው ዘር ብቻ የሚያስተላልፉበት ሚስጥራዊ ኮድ እንዳላቸው በ‹‹Nepotism and the Evolution of Alarm calls, 1977›› መጽሐፉ ግኝቱን አጋርቷል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሲንሳ ማሌሴቪክ የተባለ አየርላንዳዊ የሶሽኦሎጂ ፕሮፈሰር በ‹‹Sociology of Ethnicity፣ 2004›› መጽሐፉ በአንድ ቡድን ውስጥ ባሉ አባላት መከካል አንድነትና ትብብር ገቢራዊ እንደሚሆን፣ ነገር ግን ከባዕድ ቡድን ጋር ውስን ሀብትን ለመቀራመት ከሚደረግ ፉክክር የተነሳ ጥላቻ እንደሚሰፍን የሶስዮባዮሎጂስቶችን ሙግት በዋቢነት ጠቅሶ የጻፈው እንደዚህ በማለት ነበር፡፡

‹‹As claimed by sociobiologists, while there was a solidarity and co-operation within the groups they were largely hostile to other groups with whom they were in constant competition and conflict over scarce resources››.

በነገራችን ላይ በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚባል መልኩ የፕሪሞርዲያሊዝም የብሔርተኝነት ንድፈ ሐሳብ ለማኅበራዊ ሥሪት ዕሳቤ ሥፍራውን እየለቀቀ ወደ መክሰም ደረጃ ወርዷል፡፡ ለዚህም ውድቀቱ በዋናነት የሚጠቀሰው ከብዙ ሺሕ ዓመታት ወዲህ የሰው ልጆች እየተቀያየጡ የአንጡራ ዘውጌ ህላዌ ወደ ቅዠት መቀየሩ ነው፡፡ ምክንያቱም የሰው ልጆች በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀሱ (Migration) ዘውጌ ዘለል ጋብቻዎች (Cross Ethnic Intermarriages) ዕውን መሆናቸው አይቀሬ ነው፡፡ ታዲያ በዚህ ወቅት ፕሪሞርዲያሊስቶቹ በደም እንደሚተላለፍ የነገሩን የባህል ገጽታ ዕጣ ፈንታው ምን ሊሆን ነው? ከኦሮሞ ወንድ አያት፣ ከጉራጌ አባት፣ ከሱርማ ሴት አያት፣ ከአማራ እናት የተወለደ ልጅ ይዞ የሚወለደው የየትኛውን ዘውጌ ባዮሎጂያዊ ባህል ነው? በዘመናችን እንኳንስ አንጡራ የዘውጌ አባል ይቅርና አንጡራ የሰው ዘር (Race) ማግኘት በራሱ የሚታሰብ አይደለም፡፡ በአንድ ወቅት አሜሪካዊው የጎልፍ ስፖርት ንጉሥ ታይገር ውድስ በኦፕራ ሾው ፕሮግራም ቀርቦ ስለዘሩ ሲጠየቅ ጥቁር ነኝ ብሎ አልመለሰም፡፡ ይልቁንም ምላሹ፣ ‹‹…Cablinasian…ነኝ›› የሚል ነበር፡፡ ሲመነዘር የ‹‹Caucasian, Black (American), Indian, Asian›› ዘሮች ውሁድ መሆኑ ነው፡፡ እውነቱን ነው፣ የታይገር እናት የታይላንድ፣ የቻይናና የደች ዘር ሲኖርባት፣ አባቱ ደግሞ የአፍሪካ አሜሪካዊና የቻይና ውሁድ ዘር ነበረበት፡፡ ታዲያ የሰው ልጅ በዚህ ልክ በተቀያየጠበት እውነታ ውስጥ ፕሪሞርዲያሊስቶች እርግጠኛ ሆነው የሚደሰኩሩልን ስለየትኛው ‹‹…Common Ancestry…›› ነው?

ከላይ የጠቀስኩት የሶስዮሎጂ ፕሮፌሰር ሲንሳ ማሌሴቪክ የፕሪሞርዲያሊዝም ንድፈ ሐሳብ ቅቡልነት በዘመናችን መቀመቅ የወረደበት ሌላው ምክንያት ከሥነ ምግባር (Ethics) ጋር በተገናኘ ነው ይለናል፡፡ ለዚህ አስረጅነት ከላይ ከአቶ ጃዋር ጽሑፍ ውስጥ የጠቀስኩትን መጠቆም በቂ ሊሆን ይችላል፡፡ የአቶ ጃዋር፣ ‹‹ባዕድ ሲሰርቅ አሳድዶ መያዝ፣ ወንድም ሲሰርቅ ስህተቱን መሸፈን›› የሚለው መርሁ በየትኛውም የፍትሕና ሥነ ምግባር ልኬት የሚደገፍ አይደለም፡፡ ፕሪሞርዲያል አስተሳሰብ በዚህ ልክ ኢሚዛናዊ ለሆነ ውግንና አጋልጦ ይሰጣል፡፡ በአገሪቱ ፖለቲካም ቢሆን ፕሪሞርዲያሊዝም ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ በገሃድ ያልተጻፋ በገቢር ግን ዕውን የሆነ የብሔር ፖለቲካ ፖሊሲ (Ethnic Policy) ነው፡፡

በነገራችን ላይ በአገራችን ዜጎች ለአያሌ ዓመታት ከኖሩባቸው ቀዬዎቻቸው የደም ትስስራቸው ተፈትሾ፣ በገዛ አገራቸው ‹‹መጤ›› ተብለው የተሰደዱበት ምክንያትም ቢሆን በቀጥታ የሚቆራኘው ከመሬት ባለቤትነት ጋር ነው፡፡ ታዲያ ከአያት ቅድመ አያት ሲተላለፍ ለመጣ ርስት በብቸኝነት የባለቤትነትን ጥያቄ አንስቶ ሌሎችን ማፈናቀል ዓይነተኛ የፕሪሞርዲያል አስተሳሰብ ምልክት ነው፡፡ ይህ ርስት ተኮር ፕሪሞርዲያል የማፈናቀል ዕርምጃ ከወለጋ በተጨማሪ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልም እ.ኤ.አ. በ2013 ተፈጻሚ ስለመሆኑ ኢትዮጵያዊው የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ሰሚር ዩሱፍ (ዶ/ር) እ.ኤ.አ. በ2019 ‹‹Drivers of Ethnic Conflict in Contemporary Ethiopia›› በሚል ርዕስ በተሰናዳ ጥናታዊ ጽሑፋቸው ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ በወቅቱ የአማራ ገበሬዎችን ከክልሉ እንዲፈናቀሉ ያደረጋቸው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመሬት ባለቤትነት የምስክር ወረቀት እንዲሰጣቸው መጠየቃቸው ነበር፡፡ ይህ ጥያቄ የክልሉን ባለሥልጣናት ስላስቆስጣቸው በገበሬዎቹ ላይ የተወሰደው ዕርምጃ ምን እንደሆነ ሰሚር (ዶ/ር) በጥናታዊ ጽሑፋቸው የገለጹት ‹‹Citing land registration as a Stride towards land ownership, regional authorities displaced Amhara peasants in 2013›› በማለት ነበር፡፡ በክልሉ ሌሎች ብሔሮች በብዛት እንደሚኖሩ ቢታወቅም፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሕገ መንግሥት አንቀጽ 2 የክልሉ ባለቤቶች በማለት በዝርዝር ያስቀመጠው የበርካታ፣ ጉሙዝ፣ ሽናሻ፣ ማኦ እና ኮሞ ብሔር ብሔረሰቦችን ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ፕሪሞርዲያሊዝም በአገሪቱም ሆነ በክልል ሕገ መንግሥቶች ውስጥ እንደ ልቡ የሚንፈላሰስበት ሌላ አገር በዓለም አቀፍ ደረጃ ይኖር እንደሆነ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡

እንግዲህ በአቶ ጀዋር ጽሑፍ ይዘት ላይ ብዙ ብለናል፣ የተነሱትን ሐሳቦች ሰብሰብ አድርገን ወደ ማጠቃለያው ማዝገም ግድ ሊሆን ነው፡፡ የማጠቃለያ ሐሳቤን እንደሚከተለው ተራ በተራ ላንሳ፡፡

1). የአቶ ጃዋር ጽሑፍ ይዘት በዚህ ልክ ትኩረት ለምን ተሰጠው?

ምናልባት አቶ ጃዋር ለዚያውም ስማቸውን ሳይጠቅስ የእነ ኧርነስት ገልነርን ሐሳብ በጥቂት ዓረፍተ ነገሮች ውስጥ በመጠቀሙ ርዕሰ ጉዳዩ በዚህ ልክ ለምን ትኩረት ተሰጠው? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ ነገሩ ‹‹ሆድ ያባውን ብቅል ያወጣዋል›› ሆኖብኝ እንጂ፣ አቶ ጃዋር በተለይም ለኧርነስት ገልነር ዕሳቤ ስስ ልብ እንዳለው የሚገልጡልኝ ብዙ ምክንያቶች ወትሮም ነበሩኝ፡፡ በተለይም በአቶ ጃዋር ዙሪያ ላሉ ወጣቶች ኧርነስት ገልነር ማለት አቻ የማይገኝለት የብሔርተኝነት ጽንሰ ሐሳብ አባትና ፈር ቀዳጅ ተመራማሪ ነው፡፡ እስካሁን በብሔርተኝነት ጽንሰ ሐሳብ ላይ ከተሰጡ ገለጻዎች ውስጥ የኧርነስት ገልነርን የሚስተካከል እንደሌለ ወጣቶቹ በቪዲዮ ጭምር የለቀቋቸው መረጃዎች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ከተለቀቁ ቆይቷል፡፡ እንዲያውም በውጭው ዓለም የኧርነስት ገልነርን ንድፈ ሐሳብ የሚያካሂዱና የሚቃወሙ ካሉ እነሱ ገና ምራቅ ያልዋጡ ወጣት ተመራማሪዎች ናቸው እስከመባልም ተደርሷል፡፡ ነገር ግን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ይህ ድምዳሜ በሐሰተኛ መረጃ ላይ የተመሠረተ ማጠቃለያ ስለመሆኑ በእርግጠኝነት ማስመር እፈልጋለሁ፡፡ ማለትም የኧርነስት ገልነር ንድፈ ሐሳብ ተቃውሞ የገጠመው ከወጣቶች ብቻ አይደለም፡፡ በክፍል 1 ጽሑፌ እንደገለጽኩት ገልነር በጣት ከማይቆጠሩ በዕድሜ አንጋፋ ከሆኑ ወዳጆቹና ተማሪዎቹም ጭምር ሂስን አስተናግዷል፡፡ ለምሳሌ ‹‹Ernest Gellner’s Legacy and Social Theory Today,2022›› መጽሐፍ ውስጥ የተሳተፉ ምሁራን ዕድሜ ከ55 እስከ 85 የዘለቀ ነው፡፡ እንዲያው ለነገሩ እንጂ ወጣት ተመራማሪዎችም በገልነር ዕሳቤ ላይ ሂስ ሰንዝረው ከሆነ፣ ማጤን ያለብን የሂሳቸውን ይዘት እንጂ ዕድሜያቸውን መስሎ አይታየኝም፡፡

ለማንኛውም በገልነር ንድፈ ሐሳብ ዙሪያ ዛሬም በጥቂቱ ሦስት ነጥቦችን ላንሳ፡፡ ሲጀመር ኧርነስት ገልነር በብሔርተኝነት ንድፈ ሐሳብ ላይ ምንም ሥራ አልሠራም የሚል ሙግቱ የለኝም፡፡ የእኔ መከራከሪያ ጥናቱ አውሮፓ ተኮር በመሆኑ፣ ምንም ዓይነት የኢንዱስትሪ አብዮት ጭላንጭል ላልታየባቸው እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገሮች ፈጽሞ የሚመከር አይደለም የሚል ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ በክፍል አንድ ጽሑፌ እንዳስቀመጥኩት በኧርነስት ገልነር ንድፈ ሐሳብ ዙሪያ በተወሰነ ደረጃ ፅንሰ ሐሳባዊ ብዥታ ያየለ ይመስላል፡፡ ገልነር ያጠናቀረልን …የየትኛውም ብሔርተኝነት ዓላማ ግዛትንና ባህልን አንድ ማድረግ ነው… የሚል ዕሳቤን ነው፡፡ ይህ የብሔርተኝነቱ ፍላጎት እንጂ የገልነር ማጠቃለያ አይደለም፡፡ ለምሳሌ አንድ የእግር ኳስ ዳኛ፣ ‹‹የየትኛውም ተጋጣሚ ቡድን ዓላማ በጨዋታው አሸናፊ ሆኖ መገኘት ነው›› የሚል አስተያየት ቢሰጥ ፍላጎቱ የተጋጣሚዎቹ ቡድን እንጂ የዳኛው አይደለም፡፡ ገልነርም የየትኛውም ብሔርተኝነት ዓላማና ግቡ ወጥ ማኅበረሰብን መፍጠር ነው ማለቱ የኢንዱስትሪ አብዮት ባልተስተዋለባቸውም አገሮች ጭምር ወጥ የሆነ ማኅበረሰብ መፈጠር አለበት እያለን አይደለም (This is totally a misinterpretation of Gellner’s Nation-state congreuency Principle)፡፡ በእርግጥ በኢንዱስትሪ አብዮት ወደ ዘመናዊነት የገቡ አገሮች ወደ ወጥነት ሳይደርሱ ሲቀሩ ገልነርን ቅር ይለዋል፡፡ እናም ኧርነስት ገልነር ይህ የብሔርተኝነት የ‹‹አንድ ብሔር አንድ መንግሥት መርህ›› ህልም የሚሳካው በአውሮፓው የኢንዱስትሪ አብዮት ወቅት ነው ብሎ ያምናል፡፡ የኢንዱስትሪና የከተሜነት ባህሪይ አንድ ባህል የሚሻ እንደመሆኑ፣ የወቅቱን መሥፈርት ማሟላት ያቃታቸው ባህሎችና ቋንቋዎች (Low Cultures) ወቅቱን በሚመጥኑ ባህሎችና ቋንቋዎች (High Cultures) እየተዋጡ ይሄዱና የማታ ማታ ‹‹አንድ ባህል አንድ መንግሥት‹‹ ዕውን ይሆናል ይላል፡፡ እንግዲህ ገልነር የአውሮፓውን ብሔርተኝነት በየትኛውም መሥፈርት ከብሔር ትግል ወይም ጭቆና ጋር አገናኝቶ አልተነተነም፡፡ እሱ ያነሳው ብሔርተኝነት በዘመናዊነት ውሽንፍር ውስጥ በኢንዱስትሪና ከተሜነት ዕድገት ውስጥ የሚፈጠር እንደሆነ ነው፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ገልነር ዕድሉ ቀንቷቸው በዘመናዊነት ውስጥ ወጥ ባህል (Homogeneous Culture) መፍጠር የቻሉ አገሮች በጣም ስኬታማ ናቸው ይላል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን የብሔርተኝነት ገደብ አልባ የወጥነት ጥማት ጣራውን ይነካና በሌሎች ሁኔታዎች ውስጥ ያልተከሰተው የአንድ ባህል አንድ መንግሥት መርህ በጉልበት ማለትም በጄኖሳይድ፣ በስልቀጣና በማፈናቀል ዕውን ይሆናል ይላል፡፡ ስለዚህም የገልነር ምርጫው ምንድነው ቢባል በየትኛውም አገር ዘመናዊነት ዕውን ሆኖ ወጥነት እንዲፈጠር ነው፡፡ በማስገደድ ሳይሆን በኢንዱስትሪና በከተሜነት ማበብ ውስጥ በሚፈጠረው ማኅበረ ባህላዊ ውቅር ውስጥ ደግሞ አንድ የፖለቲካ ሥርዓት እንዲፈጠርም ይሻል፡፡ ገልነር ይህን በኢንዱስትሪ አብዮት አማካይነት የሚፈጠረውን ወጥነት የሚቃወሙ የዘውጌ ቡድኖች ሲያገጥሙት የ‹‹አንድ ባህል አንድ መንግሥት›› መርህን ስለሚያፋልሱበት ክስተቱን እንደ አሉታዊ አጋጣሚ (Anomaly) ይቆጥረዋል፡፡

የኧርነስት ገልነር የቅርብ ወዳጁ የሆነው ኖርዌጂያዊው አንትሮፖሎጂስት ቶማስ ኃይላንድ ኢሪክሰን ገልነር ከመሞቱ ከሁለት ዓመታት ቀደም ብሎ ምንም ዓይነት የኢንዱስትሪ አብዮት ባልታየበት በአማዞንና በሌሎች አገሮች እየተስተዋሉ ያሉ የብሔርተኝነት ንቅናቄዎችን በራሱ ኢንዱስትሪ ወለድ የብሔርተኝነት መነጽር አይቷቸው ምላሹን እንዲሰጥ በጠየቀው ጊዜ፣ ገልነር ትካሻውን እያንቀጠቀጠ ለጥያቄው ቀለል ያለ ምላሽ መስጠት አልችልም በማለት ጥያቄውን በቀጥታ ከመመለስ ታቀበ፡፡ በዚያው ቀን ሁለቱም በነበራቸው የአብሮነት ጊዜ ገልነር ኖርዌይ (የኢርክሰን አገር) ወጥና ጠንካራ ማኅበራዊ ትስስር ያላት አገር ነች… በማለት ለኢርክሰን ነገረው (ለንድፈ ሐሳቡ ትክክለኛነት ምሳሌ የምትሆን አገር መጥቀሱ ነው)፡፡ ነገርየው ‹‹ማን ያውራ የነበረ፣ ማን ያርዳ የቀበረ›› ነውና ገልነር ይህን በሚልበት ወቅት ኖርዌይ ውስጥ እንደ ሳሚ ብሔር ጭቆናን የሚጋፈጡ አናሳ ብሔሮች እንደነበሩ የአገሩ ተወላጅ የሆነው ኢሪክሰን አልጠፋውም፡፡ እንዲሁም ኖርዌይን በስደት የተቀላቀሉ ፓኪስታኖችና በኦስሎ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ከሌላ አውሮፓ አገሮች የመጡ ሕፃናት በራሳቸው ቋንቋ የመማር መብትን እንደተነፈጉ ገልነር መረጃው አልነበረውም፡፡ ብቻ ግን ገልነር ንድፈ ሐሳቡ ፉርሽ እንዳይሆንበት የኖርዌይን ወጥነት ለኖርዌይ አንትሮፖሎጂስቱ ሊያስረዳ ይታትራል፡፡ በነገራችን ላይ ገልነር ንድፈ ሐሳቡን ፉርሽ ከሚያደርጉበት ክስተቶች ጋር ጠበኛ ነው፡፡ ንድፈ ሐሳቡ ብዝኃ ብሔርነትን መሸከም የሚችልበት ጫንቃም አልነበረውም፡፡ ብቻ ሁሉም ብሔር እየተገነጠለም ቢሆን የእሱን ንድፈ ሐሳብ ትክክለኛነት እንዲያፀድቅለት በብርቱ ይፈልጋል፡፡ ለማንኛውም ከላይ በገልነርና በኢሪክሰን መካከል የተደረገውን ውይይት ያካፈልኳችሁ ከ‹‹Ernset gellner and Contemporary Social Thought 2007, PP 168›› መጽሐፍ ምዕራፍ 7 ነው፡፡ የምዕራፉ ርዕስ ‹‹Ernset gellner and the Muliticultural mess, by Thomas Hylland Eriksen›› ነው፡፡

ስለዚህም በእኔ ግምገማ የአቶ ጃዋር ጽሑፍ በለስ ቀንቶት፣ በፖለቲካ ሹማምንቶቹ ተቀባይነትን አግኝቶ ወደ ትግበራ ከተሻገረ፣ የሚፈጥረው አገራዊ የቀውስ መጠን (Risk factor) በቃላት የሚገለጽ አይደለም፡፡ እስካሁንም ቢሆን በተለይም በኦሮሚያ ክልል ከብሔር ስብጥር አኳያ ወጥ የሆነ ማኅበረሰብን (Ethnically Homogenous Society) የመፍጠር ፕሮጀክት ገቢራዊ ስለመሆኑ የሚጠቁሙ አንዳንድ ምልክቶች አሉ፡፡

በዋናነት የአቶ ጃዋርን ጽሑፍ አሥጊ የሚያደርገው ሌላው ምክንያት በፌዴራል መንግሥትና በክልል መንግሥት መካከል ግልጽ መስመር ያለ መሰመሩ ነው፡፡ አንዳንዴም ጽሑፉን በማንበብ ሒደት፣ አቶ ጃዋር እያነሳ ያለው ስለፌዴራል መንግሥት ይሁን ስለኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት መለየት እስኪያቅተን ግራ ሲያጋባን ነበር፡፡ ለምሳሌ ከጎረቤት አገሮች ጋር ግንኙነት መፍጠር አለብን ሲል እያነሳ ያለው ስለፌዴራል መንግሥት ሳይሆን ስለኦሮሚያ ክልል ነው፡፡ ለመሆኑ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ክልሎች በቀጥታ ከውጭ አገሮች ጋር ግንኙነት እንዲፈጥሩ የሚፈቅደው በየትኛው አንቀጽ ነው? እንዲሁም አቶ ጃዋር አሁን በማዕከላዊ መንግሥት ያሉ የኦሮሞ ባለሥልጣናት ለኦሮሞ ምንም አልፈየዱለትም የሚለውን ድምዳሜውን የሚያነፃፅረው የአፍሪካ አገሮች ከቅኝ ግዛት ነፃ ከወጡ በኋላ ከደረሰባቸው የአመራር ቀውስ ጋር ነው፡፡ በአጭሩ የክልልን ሁኔታ ሉዓላዊ ከሆነ አገሮች ሁኔታ ጋር ያነፃፅራል፡፡

እንዲሁም በተከታታይ እንደታዘብነው አቶ ጃዋር የኢትዮጵያን ፌዴራል መንግሥት ልክ እንደ ኦሮሞ መንግሥት የመቁጠር አዝማሚያን በግልጽ አንፀባርቋል፡፡ ለዚህም በዋቢነት በክፍል ጽሑፌ አቶ ጃዋር በገጽ 7 ላይ ያስቀመጠውን ሐሳብ ደግሜ ለማስቀመጥ እገደዳለሁ፡፡

‹‹…የአንድ ሕዝብ ትግል ዓላማ ለራሱ ጥቅም እንቅፋት የሚሆንን ሥርዓት ለራሱ በሚሆን መልክ መቀየር፣ ካልሆነ ደግሞ ነባሩን ሥርዓት ለራሱ በማፈራረስ ወይም በመገንጠል አዲስ ሥርዓት መገንባት ያስፈልጋል… አዲስ አገር እንመሥርት ወይስ ያለውን አገር ለእኛ በሚመቸን በኩል አዲስ ቅርፅ በመስጠት እንቀጥል በሚሉት ጉዳዮች መካከል ያለው ግጭት የተፈጠረበትም ምክንያት ለዚሁ ነው፡፡›› ገጽ 7፡፡

‹‹የኢትዮጵያ የፌዴራል ሥልጣን በእጃችን እንደገባ ለብሔረሰባችን ችግር መፍትሔው ባዕዳን ሳይሆኑ እኛው ራሳችን መሆናችንን በጥልቀት እንዳላሰላሰልነው ያሳያል… ለረዥም ዘመናት በባዕዳን በሚመራ አምባገነን ሥርዓት ሲሰቃይ የነበረ ጭቁን ሕዝብ በከፍተኛ መስዋዕትነት በከፈለው ትግል ወደ ሥልጣን ከወጣ ልጁ ብዙ ይጠብቃል፡፡ ነገር ግን አመራሩ ዕቅድና ስትራቴጂ ስላልነበረው ሕዝቡ የሚጠብቅበትን በፍጥነት ሊያሟላለት አልቻለም… በሥልጣን ላይ ያለው ባዕድ አይደለም፡፡ የኦሮሞን ሕዝብ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮች የመፍታት ፍላጎትና ብቃት ቢኖረው ኖሮ የወጣበትን ሕዝብ በማስደሰት ሥልጣንን ማጠናከር በቻለ ነበር፡፡›› ገጽ 31

ከላይ ከጠቀስኩትም በተጨማሪ በጽሑፉ ውስጥ አቶ ጃዋር ከክልላዊ መንግሥት ይልቅ ፌዴራላዊውን መንግሥት እንዴት መዘወር እንደሚቻል በተደጋጋሚ አንስቷል፡፡ እንደምናውቀው በፌዴራል ደረጃ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአጠቃላይ 547 የውክልና መቀመጫ ሲኖር፣ ከዚህም ውስጥ ጽሑፍኛ ሲሠላ ኦሮሚያ 32.5 ጽሑፍ፣ አማራ 25.2 ጽሑፍ፣ ደቡብ 19 ጽሑፍ፣ ትግራይ 6.9 ጽሑፍ፣ ሶማሌ 4.2 ጽሑፍ፣ አዲስ አበባ 4.2 ጽሑፍ፣ ሲዳማ 3.5 ጽሑፍ፣ ቤኒሻንጉል ጽሑፍ፣ ጉሙዝ 1.6 ጽሑፍ፣ አፋር 1.5 ጽሑፍ፣ ጋምቤላ 0.55 ጽሑፍ፣ ሐረር 0.04 ጽሑፍ፣ ድሬዳዋ 0.04 ጽሑፍ ይሆናል (ምንጭ ሪፖርተር ጋዜጣ ፌብሩዋሪ 21 2019)፡፡ እንግዲህ አቶ ጀዋር በጽሑፉ …የኢትዮጵያ የፌዴራል ሥልጣን በእጃችን ገብቷል፡፡ አሁን ሥልጣን ላይ ያለው ባዕድ አይደለም፡፡ ያለውን አገር ለእኛ በሚመቸን መልኩ እንቀርፃለን፣ ወዘተ. እያለ በግልጽ ሲያስቀምጥ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 68.5 ጽሑፍ መቀመጫ ያላቸውን ሌሎቹን ብሔር ብሔረሰቦች ከቁብ ሳይቆጥራቸው ቀርቶ ነው? በዩናይትድ ኪንግደም ፓርላማ እንግሊዝ ቶያላት መቀመጫ ከ80 ጽሑፍ በላይ ነው፡፡ በሩሲያ ደግሞ ሩሲኪዎቹ ከ70 ጽሑፍ በላይ መቀመጫ አላቸው፡፡ ሆኖም እነሱ እንኳን በጽሑፍ ደረጃ የአገሪቱ ሥልጣን ያለው በእጃችን ነው ብለው ሲደሰኩሩ አይስተዋሉም፡፡ ቢሉ እንኳን ከድርሻቸው አንፃር አባባሉ እውነትነት ሊኖረው ይችላል፡፡ አቶ ጃዋር ግን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 32.5 ጽሑፍ መቀመጫ ያለው ክልል 68.5 ጽሑፍ መቀመጫ ያላቸውን ሌሎች ክልሎችን በራሱ አምሳል የመቅረፅ አቅም እንዳለው አድርጎ ይነግረናል፡፡

ትንግርቱ አላለቀም፡፡ አቶ ጃዋር የፌዴራል መንግሥት ሥልጣን በኦሮሚያ ክልል እጅ ውስጥ እንደገባ ሳያመነታ በግልጽ ከነገረን በኋላ በተቃራኒው በገጽ 58 ላይ በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት ‹‹የኦሮሞ መንግሥት›› እያሉ መጥራትን ሲቃወም እንመለከታለን፡፡ እንዲያውም ‹‹በአገር ደረጃ የኦሮሞ መንግሥት›› ብሔረሰቦች ላይ መጫን የኦሮሞ ሕዝብ ትግል ሆኖ አያየውም፡፡ የኦሮሞ ምኞት በፌዴራል ደረጃ የኢትዮጵያ ሕዝቦች መንግሥት መመሥረት ነው›› የሚል ‹‹የውስጥ ማስታወሻ›› (Memo) የሚመስል መልዕክት ለብሔሩ ተወላጆች ያስተላልፋል፡፡ ጥያቄዬ ከላይ እንዳሠፈርኩት በጽሑፉ በሌሎች ገጾች… ሥልጣንን ከባዕድ ነጥቀናል፡፡ የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት ሥልጣን እጃችን ውስጥ ገብቷል፣ ወዘተ. እያሉ በመጻፍና ሥልጣን ላይ ያለውን ቡድን ‹‹የኦሮሞ መንግሥት›› ብሎ በመጥራት መካከል ያለው ልዩነት ምንድነው? በእኔ ግምገማ መጀመሪያ ላይ ያሠፈርኩት ለሁለተኛው ማብራሪያ መስሎ ይታየኛል፡፡

ከጽሑፉ ውስጥ ሌላም ጥያቄ የሚጭር ሐሳብ ላንሳ፡፡ አቶ ጃዋር በተወሰነ መልኩ አሁን በሥልጣን ላይ ያለውን የአሮሚያ ብልፅግና ፓርቲን ሲያሄስ ተመልክተነዋል፡፡ ያሄሰበት ምክንያት ግን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ቡድናዊ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በጽሑፉ በገጽ 31 ላይ በፌዴራል ደረጃ በሥልጣን ላይ ያለውን የኦሮሞን ቡድን የተቸው፣ ‹‹…ሕዝብ በከፍተኛ መስዋዕትነት በከፈለው ትግል ወደ ሥልጣን ከወጣ ልጁ ብዙ ይጠብቃል›› በሚል ክልላዊ ምክንያት ነው፡፡ በአጭር ቃል አቶ ጃዋር በፌዴራል ደረጃ በበላይነት ሥልጣኑን እንደጨበጠ የነገረን የኦሮሞ ቡድን ውግንናውን በሚፈለገው መጠንና ብቃት አልከወነውም የሚል ይመስላል፡፡ መቼም ይህ ትችት የሚመለከተው በአገሪቱ በከፍተኛ የአመራር ሥፍራ ያሉትን አመራሮችን እንጂ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ሆነ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ያሉትን ተመራጮችን እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ እነዚህ ባለሥልጣናት ሁሉንም የኢትዮጵያ ብሔሮችን በሚወክሉበት የሥልጣን መንበር ላይ ተቀምጠው በልዩነት ለወጡበት ብሔር እንዲወግኑ ጥሪን ማስተላለፍ ከሕግም ከሞራልም አንፃር ተገቢ ነው የሚል እምነቱ የለኝም፡፡

በአቶ ጃዋር ጽሑፍ ውስጥ የተስተዋሉ ንድፈ ሐሳቦች እንዴት ይቀንበቡ?

በጽሑፌ ከክፍል 1 እስከ 3 ለማጤን እንደሞከርነው አቶ ጃዋር የኦሮሞን የብሔር ትግል ውልደትና ሒደት ለመተረክ በጥቂቱ ወደ አራት ንድፈ ሐሳቦችን ጥቅም ላይ አውሏል፡፡ በማኅበራዊውም ሆነ በፖለቲካ ሳይንስ ዘርፍ አንድን ማኅበራዊ እውነታን ለመተንተን ከአንድ በላይ ንድፈ ሐሳቦችን ጥቅም ላይ ማዋል አዲስ ወይም ያልተለመደ የጥናት አካሄድ አይደለም፡፡ ከአንድ በላይ ንድፈ ሐሳቦችን ወደ አንድ ውሁድ ንድፈ ሐሳብ ቀይሮ ችግሮችን ለመፍታትም ሆነ ለመተንተን የመሞከር ጽንሰ ሐሳብ ንድፈ ሐሳባዊ ውህደት (Theoretical Synthesis) ተብሎ ይጠራል፡፡ ከዚሁ ጋር ተቀራራቢነት ያለው ጽንሰ ሐሳብ ደግሞ ትንተናዊ ቅይጣዊነት (Analytic Eclecticism) የሚባለው ሲሆን፣ ይህ የትንተና ዘዴ ከንድፈ ሐሳባዊ ውህደት የሚለይበት አንዱም መሥፈርት ተደማሪ ንድፈ ሐሳቦች ተደምስሰው ሌላ አዲስ ውሁድ ንድፈ ሐሳብን መፍጠር አለማስፈለጉ ነው፡፡

ታዲያ በየትኛውም ዘዴ ይሁን ከአንድ በላይ የሆኑ ንድፈ ሐሳቦች ለክስተት ትንተና ጥቅም ላይ በሚውሉበት ጊዜ ማሟላት የሚጠበቅባቸው ቅድመ ሁኔታዎች አሉ፡፡ ለአንድ ክስተት እርስ በእርስ የሚጣረሱትንም ንድፈ ሐሳቦች እንኳን ሳይቀሩ በአንድ ጽሑፍ ውስጥ በዘፈቀደ መጠቃቀሱ ግራ ያገባል፡፡ እናም ንድፈ ሐሳቦች ከመወሀዳቸው ወይም ከመቀየጣቸው በፊት ማሟላት የሚጠበቅባቸው አንዱም መሥፈርት የተገቢነት (Relevance) መሥፈርት ነው (The theories should first be tested for relevance.)፡፡ በመቀጠልም ይህን መሥፈርት ያሟሉ ንድፈ ሐሳቦች የሚያልፉበት ደረጃ አለ፡፡ ይኼውም ንድፈ ሐሳቦቹ ያላቸው የጋራና የልዩነት ነጥቦች (Points of Convergence and Divergence) ከተለዩ በኋላ የምስስሎሹን እሴቶች ማቀናበር ነው፡፡

እንግዲህ ከላይ በተቀመጡት መሥፈርቶች አቶ ጀዋር ከገልነራዊ ዘመናዊ ብሔርተኝነት እስከ ፕሪሞርዲያሊዝም ንድፈ ሐሳብ ድረስ የተጠቀማቸውን ንድፈ ሐሳቦች መፈተሽ ይቻላል፡፡ ስለዚህም በንድፈ ሐሳቦቹ ላይ ከሁሉም አስቀድመን የምናነሳው ጥያቄ የተገቢነት (Relevance) ነው፡፡ የተገቢነት መሥፈርቱን በምንፈትሽበት ወቅት ደግሞ የአንፃራዊ ብሔርተኝነት (Comparative Nationalism) ዲሲፒሊንን ጥቅም ላይ ማዋል ግድ ይላል፡፡ በክፍል አንድና ሁለት ጽሑፎቼ አቶ ጀዋር የኦሮሞን ብሔርተኝነት ውልደትና ሒደት ለመተንተን ከተጠቀማቸው ንድፈ ሐሳቦች ውስጥ በተለይም የኧርነስት ገልነር ኢንዱስትሪ ወለድ ብሔርተኝነትና የቤኔድክት አንደርሰን የኅትመት ካፒታሊዝም ወለድ ብሔርተኝነት በየትኛውም መሥፈርት የተገቢነትን መሥፈርት እንደማያሟሉ በስፋት ተመልክተን ነበር፡፡ በመቀጠልም አቶ ጃዋር በጽሑፉ ገጽ 8 ላይ፣ ‹‹በ19ኛው ክፍለ ዘመን በብዙ የአውሮፓ አገሮች የተወለዱ ብሔርተኝነቶች በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካዊና በማኅበረ ባህላዊ ለውጦች የተነሳ ማንበብና መጻፍን፣ ከተማንናና ፈጣን የቢሮክራሲ መስፋፋትን በማንበር እንዳደገ ይታወቃል፡፡›› በማለት፣ አውሮፓ ውስጥ በኢንዱስትሪ አብዮት ምክንያት የተወለዱትን ብሔርተኝነቶችን ከኦሮሞ ብሔርተኝነት ውልደት ጋር ለማነፃፀር መሞከሩ ተገቢነት እንደሌለውም አስምረን ነበር፡፡ ለኦሮሞ ብሔርተኝነት ውልደት ትንታኔ የገልነርንም ሆነ የአንደርሰንን ንድፈ ሐሳብ ለመጠቀም እ.ኤ.አ. በ1960ዎቹ በኦሮሚያ ምድር የኢንዱስትሪና የኅትመት አብዮት በስፋት ስለመከሰቱ በቂ ማስረጃ ሊሰጠን ይገባል፡፡ በአጭር ቃል ሁለቱም ንድፈ ሐሳቦች የኦሮሞን ብሔርተኝነት ውልደት ለየብቻቸውም ሆነ በጣምራ ለመተንተን ተገቢ አይደሉም፡፡

ስለዚህም አቶ ጃዋር የኦሮሞን ብሔርተኝነት ውልደትና ሒደት ለመተንተን ጥቅም ላይ ያዋላቸው አውሮፓ ተኮር (Eurocentric) ንድፈ ሐሳቦች በተናጠልም ሆነ በጣምራ ለመጠቀም ተገቢነታቸው አጠያያቂ ነው፡፡ እናም አቶ ጃዋርም ንድፈ ሐሳቦቹን የተጠቀማቸው ‹‹Theoritical synthesis››ንም ሆነ ‹‹Analytic Eclecticism››ን ሳይከውን እንደ ደሴት በየቦታቸው ከተቀመጡበት ብድግ እያደረጋቸው ነው፡፡

የኦሮሞ ብሔርተኝነት ውልደትንና ሒደትን ለመተንተን ተመራጭ የብሔርተኝነት ንድፈ ሐሳብ የትኛው ይሆን?

የብሔርተኝነት ዓይነቶች እንደ አገሩ ፖለቲካዊ፣ ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ሁኔታ ይለያያሉ፡፡ ስለዚህም በሌሎቹ የዓለማችን ክፍሎች የተከሰቱ ብሔርተኝነቶችን ከአንፃራዊ ብሔርተኝነት (Comparative Nationalism) ዲስፒሊን መርህ በተቃራኒ ለአገራችን ብሔርተኝነቶች አፈጣጣር እንደ ሞዴል ወስዶ መተንተን ፈጽሞ አይመከርም፡፡

ለኦሮሞ ብሔርተኝነት ውልደት ትንታኔ፣ የኢንዱስትሪ አብዮትን ተከትለው የተወለዱትን የምዕራብ አውሮፓዎቹን ዘመናዊ የብሔርተኝነት ንድፈ ሐሳቦችን መጠቀሙ ትክክል ካልሆነ፣ ለትንታኔው ጥቅም ላይ ማዋል ያለብን የትኛውን ንድፈ ሐሳብ ነው? ለሚለው ጥያቄ ምላሽ መሰጠት አለበት፡፡ በእኔ እምነት ለዚህ ጥያቄ ምላሹ በአቶ ጃዋር ጽሑፍ ውስጥ አለ ብዬ አምናለሁ፡፡ ለምሳሌ ገና ከመግቢያው ገጽ 4 ላይ አቶ ጃዋር የኦሮሞ ትግል ‹‹ብሔራዊ ትግል›› (National Struggle) እንደሆነ ይፋ አድርጓል፡፡ በታሪክ ውስጥ የጭቆና ቀንበር የተጫነበት ማኅበረሰብ የሚያደርገው ትግል ሁለት አቅጣጫዎችን ሊይዝ ይችላል፡፡ የመጀመርያው የመደብ ትግል (Class struggle) ሲሆን፣ ሁለተኛው የብሔር ጥያቄን ተከትሎ የሚከሰት የብሔር ትግል (National struggle) ነው፡፡ ሩሲያዊውና ማርክሲስቱ ዶቭ በር ቦሮቾቭ በሁለቱም የትግል ዓይነቶች መካከል ስላለው ቁርኝትና ልዩነት በተመለከተ፣ ‹‹The National Question and the Class Struggle›› በሚል ርዕስ ባዘጋጀው መጽሐፍ ውስጥ ሰፋ ያለ ትንታኔን መስጠቱ ይታወቃል፡፡ ለምሳሌ ብሔራዊ ትግል ሲባል ባለሁለት አቅጣጫ ነው፡፡ አንዱም የብሔር ጭቆናውን የሚጭነው ሥርዓት ሌሎቹን ለመዋጥ የሚያደርገው የማጥቃት ሚና ያለው ጭቆና (Offensive) ሲሆን፣ ሁለተኛው ተጨቋኞች ከጭቆናው ነፃ ለመውጣት የሚያደርጉት የመከላከል (Defensive) ትግል ነው፡፡ ሌኒን ከብሔር ጭቆና ነፃ ለመውጣት በሚደረግ ትንቅንቅ ውስጥ የሚፈጠረውን ብሔርተኝነት ‹‹Defensive Nationalism›› በማለት ይጠራዋል፡፡

እስኪ አቶ ጃዋር የኦሮሞ ብሔርተኝነት ትግል የብሔር ትግል ስለመሆኑ በጽሑፉ ውስጥ የሰጠንን ጥቆማዎች አብረን እናስስ፡፡ ለምሳሌ በገጽ 5 ላይ ‹‹አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ ከሁሉ አስቀድሞ የጋራ ጭቆናን ለማሸነፍ የጋራ መነቃቃትን ሊገነባ ይገባል…›› በማለት የጻፈው የብሔርተኝነቱ ምንጭ፣ ‹‹የጋራ ጭቆና›› እንደሆነ የሚጠቁም ነው፡፡ በዚያው ገጽ ደግሞ፣ ‹‹አንድ አምባገነን ጨቋኝ አገዛዝ ተሸናፊውን ሕዝብ በጉልበት ሲያስገብር፣ ሕዝቡ እንዳያምጽና ከጭቆና ቀንበር ነፃ እንዳይወጣ አገዛዙ በመጀመሪያ የሚያጠፋው የጋራ ማንነትን መሆኑ የታወቀ ሥልት ነው›› በማለት፣ አሁንም ስለብሔር ጭቆናው ህላዌ ጥቆማውን ይሰጠናል፡፡ ከሁሉም በላይ አቶ ጃዋር በገጽ 53 ላይ ብሔርተኝነት በሁለት መንገድ ይከሰታል ካለን በኋላ፣ የመጀመሪያው ‹‹የተበደለ አካል ከበደሉና ከግፉ ብዛት በንዴትና በእልህ ከተንቀሳቀሰ›› ሲሆን፣ ሁለተኛው፣ ‹‹ቀደም ብሎ የበላይነት የነበረው ቡድን የበላይነቱን አጣሁ ብሎ ሲያኮርፍ›› የሚፈጠር ብሔርተኝነት እንደሆነ ያሰምራል፡፡ እንግዲህ የመጀመሪያው የ‹‹Defensive Nationalism›› ማብራሪያ መሆኑ ነው፡፡

እንግዲህ አቶ ጃዋር በጽሑፉ ውስጥ የኦሮሞ ብሔርተኝነት የተወለደው የብሔር ጥያቄን ተከትሎ እንደሆነ በግልጽ በየአንቀጾቹ እየነገረን፣ በተቃራኒው ስለአፈጣጠሩ ለመተረክ ለምን ወደ ምዕራብ አውሮፓዎቹ ንድፈ ሐሳቦች እንደሚሄድ ግራ ያጋባል፡፡ በብሔር ትግል ሒደት የተፈጠረውን ብሔርተኝነት፣ በኢንዱስትሪ አብዮትና በኅትመት ካፒታሊዝም ከተፈጠሩ አውሮፓ ተኮር ብሔርተኝነቶች ጋር ማነፃፀር የሚቻለው በየትኛው አመክንዮ ነው? ኧርነስት ገልነር፣ ቤኔድክት አንደርሰንና አንቶኒ ስሚዝ ያነሱት የብሔርተኝነት አፈጣጠር፣ በቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረትና በዩጎዝላቪያ፣ በካናዳና በስፔን፣ በአፍሪካና በእስያ የብሔር ጥያቄን ተከትሎ ከተቀሰቀሱት ብሔርተኝነቶች ጋር የሚያገናኛቸው ምን የጋራ እሴት አላቸው? እንዲህ ዓይነቱን ንፅፅር ለመከወን ሌላው ይቅርና ኧርነስት ገልነር እራሱ አልደፈረም፡፡ እንዲያውም የእሱ ንድፈ ሐሳብ በምሥራቅ አውሮፓና በባልካን አገሮች የተቀሰቀሱትን ብሔርተኝነቶችን የማቀፍ አቅም እንደሌለው እ.ኤ.አ. በ1997 ‹‹Nationalism›› በሚል ርዕስ በታተመው መጽሐፉ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ በመጽሐፉ ውስጥ ኧርነስት ገልነር እሱ ያዋቀረው የብሔርተኝነት ንድፈ ሐሳብ በቀጥታ ከኢንዱስትሪ አብዮት ጋር እንደሚገናኝ ከገለጸ በኋላ፣ በባልካን አገሮች (ስሎቪኒያ፣ ክሮሽያ፣ ቦሲኒያ፣ ሄርዞጎቪኒያ፣ ሰርቢያ፣ ሞንቴኔግሮ፣ አልባኒያ፣ መቄዶኒያ፣ ግሪክ፣ ቡልጋሪያና ሮማኒያ) ውስጥ የነበረው የኢንዱስትሪ ዕድገት ኋላቀር በመሆኑ ንድፈ ሐሳቡ ለእነዚህ አገሮች እንደማይሠራ አስገንዝቧል፡፡ እንዲሁም የዘውግ ስብጥሩ ውስብስብ በሆነባቸው እንደ ምሥራቅ አውሮፓ ባሉ አገሮችም ንድፈ ሐሳቡ እንደማይሠራ እንደሚከተለው አስምሯል፣

‹‹Generally speaking, not merely Greek, but also the other Balkan naionslisms can be seen as constituting a major problem for the theory, given the backwardness of the Balkans by the standards of industrialism and modernity…in areas of great ethnic complexity such as eastern Europe , thre is no way of implementing the priniciples fairly. Demographic, historical geographic and other priniciples cut across each other.››

ከኧርነስት ገልነር ንድፈ ሐሳብ በተጨማሪ የቤኔድክት አንደርሰንና የአንቶኒ ስሚዝንም የብሔርተኝነት ንድፈ ሐሳብን ከኦሮሞ የብሔርተኝነት አፈጣጠር ጋር ማነፃፀርም ቢሆን ፈጽሞ የሚደገፍ አይደለም፡፡ ምክንያቱም በእነዚህም አጥኚዎች ንድፈ ሐሳቦች አወቃቀርም ውስጥ የዘመናዊነት ሚና አንበሳውን ድርሻ ይወስዳልና ነው፡፡ ይልቁን ከገልነር ከአንደርሰንና ከስሚዝ ንድፈ ሐሳቦች ይልቅ ለኦሮሞ ብሔርተኝነት ውልደት ትንታኔ ቀረቤታ ያላቸው የብርዩሊ፣ የማና፣ የጊዴንስና የቲሊ ንድፈ ሐሳቦች፣ እነዚህ አጥኚዎች ለብሔርተኝነት ውልደት በዋናነት እንደ ምክንያት የሚያስቀምጡት ፖለቲካዊ ንቅናቄዎችን ነው፡፡ ከምሥራቅ አውሮፓ ደግሞ የስታሊንና የሌኒን የብሔር ጥያቄ ንድፈ ሐሳብ ለኦሮሞ ብሔርተኝነት አፈጣጠር ትረካ ጥቅም ላይ መዋል ይችላል፡፡ በእኔ ምልከታ የኦሮሞ ብሔርተኝነት የብሔር ጭቆናን ተከትሎ በ‹‹Defensive Nationalism›› መርህ የተፈጠረ፣ በብሔር ልሒቃን አማካይነት ደግሞ በፕሪሞርዲያልና በኢንስትሩሜንታል ሥልት ተቃኝቶ ያደገና የተስፋፋ ብሔርተኝነት ነው፡፡ (የትግራይ ብሔርተኝነት የበለጠ የሚያመዝነው ወደ ኢንስትሩሜንታል ነው ማለት ይቻላል)፡፡

እዚህ ጋ አንድ እውነት ማስመር ግድ ይላል፡፡ በአንድ ወቅት በሆነ ምክንያት የተፈጠረ ብሔርተኝነት በሒደት የተለያዩ መልኮችን ሊይዝ አይችልም የሚል መከራከሪያ የለኝም፡፡ እስካሁን አጽንኦት ሰጥተን እያነሳን ያለነው ስለብሔርተኝነት ምንጭ (Origin) እንጂ፣ ስለሒደቱ (Process) አይደለም፡፡ የትኛውም ብሔርተኝነት ወቅታዊ ጥቅሙን እያሠላ በሒደት መልኩን እንደ እስስት ሊቀያይር ይችላል፡፡ ይህ በፒራግማቲዝም ላይ የተመሠረተው የብሔርተኝነት ባህርይ፣ በሶስዮሎጂው ዲሲፒሊን በአመክንዮአዊ ምርጫ ንድፈ ሐሳብ (Rational Choice Theory) ሥር የሚጠና ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል እ.ኤ.አ. ከ1991 በፊት ኮሶቮ ውስጥ የአልባኒያ ብሔር አባል ሆኖ መገኘት እንደ ክብር ይቆጠር ነበር፡፡ ምክንያቱም ከተጠቀሰው ዓመት በፊት አልባኒያዎች የኮሶቮን ፖለቲካውንና ስትራቴጂክ ተቋማትን በበላይነት ይመሩ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1991 በኋላ ግን ነገሮች ተቀያየሩ:: በአልባኒያዎች ተይዞ የነበረው ፖለቲካዊ የበላይነት ወደ ሰርቦቹ ዞረ፡፡ የፖለቲካ ሥልጣን የባለቤትነት ሚዛን ሲቀየር አልባኒያዊ መባል የበታችነት ምልክት ተደርጎ ተቆጠረ፡፡ ስለዚህም በቀጣዩ የምርጫ ወቅት አልባኒያዎቹ ድንገት ከመሬት ተነስተው ‹‹እኛ እኮ ግብፃውያን እንጂ አልባኒያውያን አይደለንም›› ብለው አረፉት፡፡ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ጥቅም ፍለጋ ወቅቱን እያሠሉ፣ እንደ እስስት የማንነት ቀለምን የመቀየሩን ሒደት የዘውጌ ማንነት አጥኚዎች ‹‹Identity switching›› በማለት ይጠሩታል (ምንጭ Sociology of ethnicity, Sinisa Malesevic, 2004)፡፡

በብሔርተኝነት ሒደት (Process) ውስጥ አዋጪና ውጤት ተኮር እስከሆነ ድረስ የብሔር ማንነት ብቻ ሳይሆን ትርክቱም ሊቀየር ይችላል፡፡ በዚህ ሒደት አመክንዮም ሆነ ነባራዊ እውነታ ሥፍራ ላይኖራቸው ይችላል፡፡ ለምሳሌ የገልነርን የብሔርተኝነት መርህን (One Culture- one Nation or Nation-sate congreuncy) በተለይም መገንጠልን በይደር የሚያቆዩ “Opportuistic secsseionists” በጣም ይወዷታል፡፡ እንዲሁም የገልነር… ወጥ የሆነ ባህል ያላቸው ብሔሮች (Homogeneous nations) ውጤታማ ናቸው የሚለው አባባሉ፣ ‹‹መጤ›› እና ‹‹ሠፋሪ›› ተብለው የሚፈረጁትን የማኅበረሰብ አካላትን ለማፈናቀል እንደ ጥሩ ማረጋገጫ ሊወሰድ ይችላል (This is to underline that the modern nationalistic theory of Gellner can purely serve the instrumentalist purpose against all odds and logic.)፡፡ ይህን ለመከወን ምናልባትም የፒራግመትክ ፍልስፍና መርህ ይጠቀስ ይሆናል፡፡ እኛ አገር ስሁት ግንዛቤ ከናኘባቸው አረዳዶች አንዱም ከፒራግማቲክ ፍልስፍና ጋር የተቆረኘ ነው፡፡ ፒራግማቲዝም በዘልማድ እንደሚባለው ‹‹የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው›› ዓይነት ፍልስፍና አይደለም፡፡ እኔ እስከገባኝ ፒራግማቲዝም ዱቄቱ የሚፈጭበት ወፍጮ ታሪክ ይጠና ይላል፡፡ የወፍጮ ቤቱ የደንበኞች ያለፈ ልምድና ታሪክም ከግምት ይግባ ይላል፡፡ ማለት የፈለኩት ፒራግማቲክ ውሳኔዎች በሚሰጡበት ወቅት መነሻ የሚሆኑት ልምድና (Experince) ታሪክ (History) ናቸው፡፡ ለምሳሌ አገርን ለራስ በሚመች መልኩ የመቅረፅ ሙከራ የአፄ ኃይለ ሥላሴ ሥርዓትን የቱን ያህል ስኬታማ አድርጓል? ትናንት የተቃወምነውን “Hegemony” ዛሬ ለመከወን ዳር ዳር ማለት ምን ያህል ርቀት ይወስደናል?

በአጭሩ ወጥነት (Homogenity) ተፈጥሯዊ አይደለም፡፡ ይልቁን ልዩነት (Diversity) ነው ተፈጥሯዊ፡፡ ከተፈጥሮ ጋር መላተም ደግሞ ውጤቱ ይታወቃል፡፡ የውይይትና የምክክር ዋናው ርዕስ መሆን ያለበት ልዩነትን እንዴት እናስተዳድረው? የሚለው እንጂ ልዩነትን እንዴት እናስወግደው? የሚለው መሆን የለበትም፡፡ ለምሳሌ አቶ ጃዋር በጽሑፉ ገጽ 45 ላይ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በኦሮሞ ጎሳዎች መካከል ያለውን ልዩነት ማስተዳደር ተገቢ እንደሆነ ‹‹የውስጥ ልዩነትን ማስተዳደር (Managing Diversity)›› በሚለው ርዕስ ሥር በስፋት አንስቷል፡፡ በኢትዮጵያ ደረጃ ዘውግ ተኮር የክልል አወቃቀር መተግበሩ ትክክል እንደሆነ ሲሞግት የነበረው አቶ ጃዋር በኦሮሚያ ውስጥ ግን ጂኦግራፊያዊው አከላለል ተፈጻሚ እንዲሆን ምክሩን ሲለግስ ይታያል፡፡ አቶ ጃዋር የወረዳዎች ስያሜ በጎሳዎች ስም መሰየም መከፋፈልን እንደሚያመጣ የሚገልጸው ‹‹ለምሳሌ እንደ ወረዳ ያሉ አስተዳደራዊ መዋቅሮች የተፈጠሩበትና በጎሳ ስም የተሰየሙበት መንገድ አለመግባባቶችን ያመጣል፡፡ ብዙ ጎሳዎች በአንድ ላይ ስለሚኖሩ ይህ የባለቤትነት ጉዳይ ሕዝቡን ይከፋፍላል፡፡›› በማለት ነው፡፡ አቶ ጃዋር በፌዴራል ደረጃ ወጥነት የሠፈነበት የሚመስለው የኦሮሞ ማኅበረሰብ፣ ወደ ክልል ሲወረድ ‹‹በጎሳ፣ በነገድና በሃይማኖት›› እንደሚለያይ ይነግረንና ማኅበራዊ ውህደቱ በኦሮሚያ ደረጃ መጠንከር እንዳለበት ያሳስባል፡፡ እንግዲህ ይህ ግንዛቤ ከላይ ልዩነት (Diversity) ተፈጥሯዊ ክስተት በመሆኑ ልናስተዳድረው እንጂ ልናስወግደው መሞከር የለብንም በማለት ያሠፈርኩትን ሐሳብ የሚያጠናክር ነው፡፡ ነገር ግን አቶ ጃዋር በክልል ደረጃ ለማስፈን የወጠነውን ልዩነትን የማስተዳደር ክህሎት በአገር አቀፍ ደረጃም እንዲተገበር በተመሳሳይ መልኩ ጥረት ቢያደርግ ምነኛ መልካም ነበር? በኦሮሚያ ጂኦግራፊያዊ አካባቢዎችን በጎሳ ስም መሰየም ከባለቤትነት አኳያ አለመግባባትን እንደሚፈጥር በነገረን መጠን፣ በአገር አቀፍ ደረጃም ጂኦግራፊዊ አካባቢዎችን በዘውጌ ስም ማካለል የባለቤትነትን ስሜት ፈጥሮ በአንድ አገር ዜጎች መካከል የ”ነባር” እና የ”መጤ” ትርክትና ክፍፍል ፈጥሮ ብዙዎችን ለግድያና ለመፈናቀል እንደሚዳርግ ቢያሳስበን ምን አለበት? በእኔ እምነት ላለፉት 32 ዓመታት ኢትዮጵያ የገጠማት ፖለቲካዊ ቀውስ ሌሎች ብዝኃ ብሔር አገሮች ከገጠማቸው ቀውስ ተለይቶ በፀጉረ ልውጥነት የሚፈረጅ አይደለም፡፡ ፀጉረ ልውጥ የሆነው ችግሮቻችንን ለመፍታት የሄድንበት መንገድ ነው፡፡ ከዛሬ 50 ዓመታት በፊት የተነሳውን የብሔር ጥያቄን ለመፍታት የሄድንበት መንገድ አያሌ የንዑስ ብሔርተኝነት ጥያቄዎችን (Ethnic Questions) ብቻ ሳይሆን በርካታ የጎሳና የነገድ ጥያቄዎችን አራብቶ አስረክቦናል፡፡ ሰሚር ዩሱፍ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት በትክክል እንዳስቀመጠው የብሔር ጥያቄው ከጥያቄነት ወደ ትንግርትነትና እንቆቅልሽ (Bizaree/Puzzle) ተሸጋግሯል፣ እውነቱን ነው፡፡ ቢያንስ ቀደም ሲል በአገር አቀፍ ደረጃ እንደጨቋኝ ብሔር ይቆጠር የነበረው አንድ ብሔር ብቻ ነበር፡፡ ዛሬ ላይ ግን ሁሉም “ብሔር” በየክልሉ ወደ ጨቋኝነት ተቀይሯል… ተጨቋኞቹ በየክልሉ በመጤነት የተፈረጁ የሌላ ብሔር አባላት መሆናቸው ነው፡፡ ሆኖም አሁንም ቢሆን ካለፈው ስህተታችን ለመማር ፈቃደኝነቱ ካለ የአገራችን ችግር መፍትሔ አልባ አይደለም፡፡ እንዲያውም በእኔ ብቻ ሳይሆን በብዙዎች ታዛቢዎችም ምልከታ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ቀውስ መሠረታዊ ችግር ያለው በአገሪቱ የብሔር ብዝኃነት አሊያም የኋላ ትርክት ላይ አይደለም፡፡ በጥናት ባይደገፍም በግምት ከ95 ጽሑፍ በላይ የአገሪቱ ችግር የሚያያዘው በብሔር ፖለቲካው ሊህቃን ዘንድ ልዩነትን ያለ አድልኦ በውይይት፣ በምክክርና በአካታችነት (A Kind of Consociational Democarcy Model) ለማስተዳደር ፖለቲካዊ ፈቃደኝነቱ (Poltical willingness) ካለመኖሩ ጋር ነው፡፡ ህንድ 2,000 ያህል ብሔሮችን በጉያዋ አቅፋ ከሌሎች የዓለም አገሮች የተሻለ የዴሞክራሲ ሞዴልን ያሠፈነችው በተዓምር አይደለም፡፡ በገዥና በተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ሊህቃን፣ የነባሩም ሆነ የመጪው ትውልድ እናት የሆነችውን ህንድ የምትባል አገርን በጋራ ለመገንባት ፖለቲካዊ ፈቃደኝነትን ስላሳዩ እንጂ!!

ሌሎች የኦሮሞ ታሪክ፣ ፖለቲካና ማኅበረሰብ ጥናት ምሁራን ስለኦሮሞ ብሔርተኝነት ውልደት ያስቀመጡት ትንታኔ ከአቶ ጃዋር ትንታኔ ጋር ሲነፃፀር ምን ይመስላል?

በኦሮሞ ብሔርተኝነት ታሪክ ዙሪያ የጻፉ አያሌ የብሔሩ ተወላጅና የውጭ አገር ምሁራን አሉ፡፡ ከብሔሩ ተወላጆች መካከል ፕሮፌሰር መሐመድ ሐሰን፣ ፕሮፈሰር መኩሪያ ቡልቻ፣ ፕሮፌሰር አሰፋ ጃለታ፣ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፣ ሲሳይ ኢብሳ ሌንጮ ለታና ሞቲ ቢያ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እስካሁን ባደረኩት ዳሰሳ የኦሮሞን ብሔርተኝነት ውልደትን በተመለከተ እንደ አቶ ጃዋር በቀጥታ ከገልነር፣ ከአንደርሰንና ከስሚዝ ጋር አቆራኝቶ የጻፈ ወይም የተነተነ የኦሮሞ ብሔር ምሁር አላጋጠመኝም፡፡ እንዲያውም የምሁራኑን የኦሮሞ ብሔርተኝነት ምልከታ በሁለት ጎራ ከፍሎ ማጤን ይችላል፡፡ ለምሳሌ እንደ ፕሮፌሰር አሰፋ ጃለታ፣ ሲሳይ ኢብሳና ፕሮፌሰር መኩሪያ ቡልቻ ያሉ ጸሐፍት የሚነግሩን ኢትዮጵያ የኦሮሚያ ቅኝ ገዥ አገር እንደሆነች ነው፡፡ በተለይም ፕሮፌሰር አሰፋ እ.ኤ.አ. በ2020 “The Oromo Movement and Imperial Politics” በሚል ርዕስ በጻፈው መጽሐፉ የኢትዮጵያን ቅኝ ገዥነት የገለጸው፣ “National Oromummaa reflects Oromo culture, history, knowledge, institutions, identity and ideology and opposes the main stream Ethiopianism. Ethiopianism as the main ideology of the Amhara-Tigrayan ethno-nations explains and justifies an ethno-naional hierarchy and Ethiopian Colonialism over the Oromo and other colonized nations in the Ethiopians Empire.” በማለት ነው፡፡ ለፕሮፌሰር አሰፋ አሁን በሥልጣን ላይ ያሉ የኦሮሞ ብሔር አባላት የቅኝ ገዥዋ ኢትዮጵያ ተባባሪዎች (Collaborators) ናቸው፡፡ በሁለተኛው ምድብ ያሉ የኦሮሞ ምሁራን የፕሮፌሰር አሰፋ ጃለታን የቅኝ ግዛት ትርክት አይጋሩም፡፡ ለምሳሌ በአንድ ወቅት ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና በ”አዲስ ነገር” ጋዜጣ በዚሁ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ጥያቄ በቀረባላቸው ጊዜ ምላሻቸው፣ ‹‹እንግዲህ ኢትዮጵያ የኦሮሞ ቅኝ ገዥ ነች ከተባለ፣ ኦሮሞ ኦሮሞን ቅኝ ገዝቶ ያውቃል ማለት ነው›› የሚል ዓይነት ነበር፡፡ እውነታቸውን ነው፡፡ ዛሬም ቢሆን ኢትዮጵያ የምር ቅኝ ገዥ ከሆነች በዓለም ታሪክ ‹‹ቅኝ ተገዥን›› የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጋ በመሾም በዓለም የመጀመሪያዋ አገር ልትሆን ነው ማለት ነው፡፡ በአሜሪካ የዴይተን ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር መሳይ ከበደም ለፕሮፌሰር አሰፋ ጃለታ ዓይነት አመለካከት እ.ኤ.ኤ በ1999 በታተመው መጽሐፋቸው ሰፋ ያለ ምላሽ መስጠታቸው ይታወሳል (Survival and Modernization, 1999, PP 10-54)፡፡ እንዲሁም ደራሲ ሀብታሙ አለባቸውም በ‹‹ታላቁ ተቃርኖ›› መጽሐፉ በተመሳሳይ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የኦሮሞ ምሁራን ባላቸው አቋም ላይ በስፋት ዝርዝሩን ጽፏል፡፡

ስለዚህም እንደ ፕሮፌሰር አሰፋ ጃለታ ያሉ ምሁራን የኦሮሞን ብሔርተኝነት ውልደት በቀጥታ የሚያገናኙት ከፀረ ቅኝ አገዛዝ ብሔርተኝነት (Anti-colonial nationalism) ጋር ነው፡፡ እንደ አቶ ጃዋር ከአውሮፓ ዓይነቱ ብሔርተኝነት ጋር አያይዘው ሲተነትኑ አይስተዋሉም፡፡ በአንፃሩ ሌሎች ምሁራን የኦሮሞን ብሔርተኝነት ትግል የሚያገናኙት የብሔር ጥያቄን ተከትሎ ከሚከሰት ከ‹‹Defensive Nationalism›› ጋር ነው (Being and Becoming Oromo, 1996)፡፡ ከይዘት አንፃር ትግሉ ጅምር ላይ የባህል ብሔርተኝነትን (Cultural Nationalism) ባህሪይ ተለብሶ በሒደት ወደ ፖለቲካዊ ብሔርተኝነት (Political Nationalism) ተቀይሯልም ይላሉ፡፡ ይህን ስንል በእግረ መንገድ የገልነርን ወይም የአንደርሰንን ስም አያነሱም ማለታችን አይደለም፡፡ በተለይም ገልነር እ.ኤ.አ. በ1983 ዓ.ም. መጽሐፉ ከኢትዮ ሶማሊያ ጦርነት ጋር አቆራኝቶ ስለወቅቱ የኦሮሞ የዘውጌ ቡድን የጠቀሰውን ፕሮፌሰር መሐመድ ሐሰንና ፕሮፌሰር አሰፋ ጃለታ አንስተዋል፡፡ እንዲያም ሆኖ አቶ ጃዋርም ሆነ ሌሎች የኦሮሞ ምሁራን የገልነርን ስም ለምን እንደሚያነሱት ግራ ይገባኛል፡፡ ምክንያቱም ገልነር (ልክ እንደ ሆብስዋም) የዘውጌ ፖለቲካ ንድፈ ሐሳቡን ፉርሽ ስለሚያደርግበት ‹‹አስቀያሚ›› (Ugly) እንደሆነ ይቆጥር እንደነበረ ወዳጁ ቤኔድክት አንደርሰን በ‹‹Theories of Nationalism, Umut Okirimil›› በሚል ርዕስ በተጻፋው መጽሐፍ ገጽ 116 ላይ ይፋ ማድረጉን በክፍለ አንድ ጽፌ ተመልክተን ነበር፡፡ ስለዚህም ከገልነር ይልቅ አንደርሰንና አንቶኒ ስሚዝን ቢጠቅሱት የተሻለ ነው የሚል አቋም አለኝ፡፡ እንዲያውም ገልነር በየትኛውም አገር ሊፈነዳ የሚችለውን የዘውጌ ብሔርተኝነት ንቅናቄን በተምሳሌነት የሚያነፃፅረው በገነት ውስጥ ካለች፣ ነገር ግን ማንም እንደይቀምሳት መለኮታዊ አዋጅ ከወጠባት ዕፀ በለስ ጋር ነው፡፡ ለዚህም ነው እነ ፕሮፌሰር መሐመድ ሐሰን እንኳን ሳይቀሩ ገልነር እ.ኤ.አ. በጻፈው መጽሐፉ የኦሮሞን የዘውግ ብሔርተኝነትን ንቅናቄን በዕፀ በለስ ‹‹Metahpor›› ተጠቅሞ በአሉታዊነት የጠቀሰውን እንደ አዎንታዊ ዕሳቤ ቆጥረው ሲጠቅሱት ግራ የሚገባን! ይልቁን አቶ ሌንጮ ለታ እ.ኤ.አ. በ1999 ‹‹The Horn of Africa as Common Homeland›› በሚል ርዕስ በጻፉት መጽሐፍ ገጽ 42 እና 43 ላይ በተለይ የገልነርን ‹‹nation-state cognreuncy›› መርህን በዋቢ መጻሕፍት አስደግፈው የሠሩት ሒሳዊ ሥራ እንዳስደመመኝ መደበቅ አልችልም፡፡ አንዱም የገረመኝ አቶ ሌንጮ ለትንትናቸው ገልነር እ.ኤ.አ. በ1983 ዓ.ም የጻፈውን “Nations and Nationalism” መጽሐፍ አለመጠቀማቸው ነው፡፡ አቶ ሌንጮ ገልነር የሌሎችን ሒስ ከግምት ካስገባ በኋላ እ.ኤ.አ. በ1997 የጻፈውን “Nationalism” መጽሐፍን መጠቀማቸው ሚዛናዊ ምልከታ እንዲኖራቸው አግዟቸዋል ብዬ አስባለሁ፡፡

የኤክስፐርት አስተያየት

ከክፍል አንድ እስከ ሦስት ያለውን ጽሑፍ ካጠናቀቅኩ በኋላ በብሔርተኝነት ንድፈ ሐሳብ በዓለም አቀፍ ደረጃ አንቱታን ካተረፉ ሳይንቲስቶች መካከል የሦስቱን አስተያየት ጠይቄ ነበር፡፡ የጥያቄዬ ዋና ማጠንጠኛ ከአንገብጋቢነቱ አንፃር ከኧርነስት ገልነር ዘመናዊ የብሔርተኝነት ንድፈ ሐሳብ ጋር የሚገናኝ ነበር፡፡ ሦስቱም ምላሻቸውን ሰጥተውኛል፡፡ ምላሽ ከመስጠትም አልፈው አስተያየታቸውን ለጽሑፌ እንድጠቀም ፈቅደውልኛል፡፡ የመጀመርያው አስተያየት ሰጪ በአየርላንድ የደብሊን ዩኒቨርሲቲ የሶስኦሎጂ ፕሮፌሰር የሆነው ሲንሳ ማሌሴቪክ ነበር (በጽሑፌ ውስጥ ተጠቅሷል)፡፡ ማሌሴቪክ በአሁኑ ወቅት በሚገርም ፍጥነት በጦርነት፣ በግጭት፣ በብሔርተኝነትና በዘውጌ ፅንሰ ሐሳብ ዙሪያ በሚደርጋቸው ጥናቶችና በጻፋቸው ዓይን ከፋች መጽሐፎቹ ዓለም አቀፍ ዕውቅናን እየተጎናፀፈ የመጣ ተመራማሪና ጸሐፊ ነው፡፡ ደግሞም ከገልነር ተማሪዎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ በጽሑፌ ይዘት ውስጥ ለኢትዮጵያ ሁኔታ የኧርነስት ገልነርን ዘመናዊ ንድፈ ሐሳብን መቃወሜን ከገለጽኩለት በኋላ የመለሰልኝ ምላሽ ይህን ይመስላል፡፡

‹‹Dear Getahun, thanks for sharing this experience from Ethiopia. I agree that using Gellner’s theory for the narrow political purpose is wrong. He (Gellner) was trying to understand what has happened in some historical contexts, mostly in Europe, without emplying that this is the only way to build nations .in fact, he often emphasizes that pursuing one nation one sate principle in Europe has led to ethnic cleansing and genocide…there are many different ways to build nations and Swiss example shows this too. In my Grounded Nationalism book I also articulate a differnt model.››

ቀጥሎም አስተያየት ጠይቄው ምላሹን ያልነፈገኝ ፕሮፌሰር ቶማስ ሃይላንድ ኢርክሰን ነው፡፡ የኖርዌይ ተወላጅ ሲሆን ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያለው አንትሮፖሎጂስት ነው ነበር (በጽሑፌ ውስጥ ተጠቅሷል)፡፡ ገልነር በሕይወት እያለ የቅርብ ወዳጁ ነበር፡፡ ምላሹ ይኸው፣ “Thank you very much indeed for your e-mail and not least for your complex and difficult question. I have always been intrigued by the complexities of Ethiopia, but my knowledge of the country is limited. Howevere, it is quite clear that it would be a travesty to impose a Gellnerian model of cultural homogeneity on Ethiopia-as indeed on most African countries…in my view, only some some kind of federal model would work for thses countries , where one ethnic group is not allowed to monopolise power…where there is enough in common to hold the state togethere. Probably, African nations should base their shared identity on the future, not the past. This was indeed the vision developed by people like Kwame Nikrumah during more optimistic time, just after independence.(In this too, Ethiopia is different of course, as it was never colonized by Europeans.) “

በመጨረሻም ምላሹን በአጭሩ የሰጠኝ ለብዝኃ ብሔር አገሮች ሕገ መንግሥትን በማዋቀር ዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ያለው የሕግና የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰር ነው፡፡ ቀደም ሲል በሩሲያ፣ በሩማኒያ፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በናጄሪያና በኬንያ ሕገ መንግሥት ሲነደፍ ከፍተኛ አማካሪ ሆኖ የተሳተፈ ፕሮፌሰር ነው፡፡ ለጊዜው ስሜ አይጠቀስ በማለቱ ፍላጎቱን አከብርለታለሁ፡፡ አጠር ያለው ምላሹ ግን ይህን ይመስላ፣

‹‹Dear Mr. Heramo, my reaction is that Ethiopia is too much ethnically mixed to create ethnically homogeneous states. All Gellner was saying is that ethnic nationalism would like, ideally, to do that.››

አመሠግናለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው wimget2023@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *