የንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት የብር ለውጡ የአንድ ወር የጊዜ ገደብ እንዲበጅለት ጠየቁ

0
0 0
Read Time:2 Minute, 24 Second
የንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት የብር ለውጡ የአንድ ወር የጊዜ ገደብ እንዲበጅለት ጠየቁ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አዲሱን የብር ኖት ከብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ጋር ሆነው ሲያስተዋውቁ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አዲሱን የብር ኖት ከብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ጋር ሆነው ሲያስተዋውቁ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ አዲስ የታተሙት ብሮች ወደ ገበያ ገብተው አሮጌዎቹ ብሮች ሙሉ ለሙሉ የሚተኩበት የጊዜ ገደብ፣ ከሦስት ወራት ወደ አንድ ወር እንዲያጥር ጠየቁ፡፡ 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አዲስ የ200 የብር ኖት ማምጣቱንና የ100፣ የ50 እና የአሥር ብር ኖቶች ላይም ቅያሪ ማድረጉን ይፋ ባደረገበት መድረክ ሰኞ መስከረም 4 ቀን 2013 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስተያየታቸውን የሰነዘሩት አቶ አቤ፣ የሦስት ወራት የጊዜ ገደብ የተቀመጠለት የመቀየሪያ ጊዜ ረዥም ስለሆነ አንድ ወር ብቻ በቂ ነው ብለዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ ከ100 ሺሕ ብር በላይ ያለባቸው የተቀመጠው የአንድ ወር የመቀየሪያ ጊዜ ቢበዛ በሁለት ሳምንት፣ ከተቻለም በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ መቀየር እንዲቻል ጊዜው ቢያጥር ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ 

በተጨማሪም በጥሬ ገንዘብ ከአሥር ሺሕ ብር በላይ ይዞ ወደ ባንክ ለመቀየር የሚመጣ ማንኛውም  ሰው የባንክ አካውንት መክፈት እንዳለበት የተላለፈው ውሳኔ፣ ከአምስት ሺሕ ብር ጀምሮ ይዞ በሚመጣ ሰው ላይ ተግባራዊ እንዲደረግ ሲሉም ጠይቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተነሱትን ጥያቄዎች አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ፣ ይኼ የጊዜ ገደብ የተቀመጠው ባንኮች ሥራ ስለሚበዛባቸውና በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ቀይረው ያገባዱ ሲባል ሊከብዳቸው ይችላል በሚል ዕሳቤ ነው ብለዋል፡፡ በዚህም መሠረት ሦስት ወራት እንዲሆን እንደተወሰነ በማስታወቅ፣ ባንኮቹ እንችላለን ካሉ ግን በአንድ ወር ውስጥ እንዲጨርሱ ከብሔራዊ ባንክ ጋር ውይይት እንዲደረግ አሳስበዋል፡፡ 

የብር ለውጡን ለማድረግ ዋናው ምክንያት ከሁለት ዓመታት ወዲህ በአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለመለወጥ እየተሞከረ ያለውን የኢኮኖሚ ስብራት መጠገን እንደሆነ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከለውጡ በኋላ በተደረገ ዳሰሳ ኢኮኖሚው ከፍተኛ የሆነ የማክሮ ኢኮኖሚ ማዛባት እንዳለበት በመረጋገጡ ቁልቁል ሲሄድ የነበረውን ኢኮኖሚ  ማስቆም ዋናው ዓላማ ነው ብለዋል፡፡ 

የብር ኖቶቹን መቀየር አስፈላጊነት አክለው ያስረዱት የብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ኖቶቹን መቀየር ያስፈለገባቸው በርካታ ምክንያቶች እንዳሉት ተናግረዋል፡፡ የመጀመርያው ምክንያት በርካታ ገንዘብ ከባንክ ውጪ በመኖሩ ሕገወጥ ተግባራት፣ ሙስናና ኮንትሮባንድ ስለተስፋፉ ያንን ለመከላከል ነው ብለዋል፡፡  ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ባንኩና ውጪ ያለ ገንዘብ ሲበራከት የጥሬ ገንዘብ እጥረት ስለሚያጋጥማቸው ያንን ለመከላከል  ታስቦ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ 

ሌላው ምክንያት ደግሞ የገንዘቦቹን የደኅንነት መጠበቂያ ማሻሻያ ሲሆን፣ ከአሁን ቀደም በእነዚህ የደኅንነት ጠበቂያዎች ላይ ጉልህ ማሻሻያ ባለመደረጉ ለሐሰተኛ ህትመትና ሥርጭት ተጋላጭ ሆነዋል ሲሉም አስረድተዋል፡፡ 

ለገቢ አሰባሰብ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ያለው ጥቅም ሌላው የተገለጸ ምክንያት ሲሆን፣ ሰዎች ያላቸው የገንዘብ መጠን በባንክ ሲዘዋወር ምን ያህል ሀብት እንዳላቸውና ምን ያህል ታክስ መሰብሰብ እንዳለበት ለማወቅ ይቻላል ብለዋል፡፡ 

ከዚህ በተጨማሪም አሁን የተደረገው ቅያሪ የ200 ብር ኖት በማስተዋወቁ ትልልቅ ገንዘቦችን ማተም የኅትመት ወጪ ለመቀነስ እንደሚረዳ ገልጸው፣ የጥሬ ገንዘብ  ዝውውር ለመቀነስ ያግዛል ሲሉም አክለዋል፡፡ 

አሁን የታተመው የገንዘብ መጠን 262 ቢሊዮን ብር መሆኑን፣ የታተመው ኖት ደግሞ በቁጥር 2.9 ቢሊዮን እንደሆነ ይናገር (ዶ/ር) ለሪፖርተር ተናግረው፣ ለብር ኅትመቱ 3.7 ቢሊዮን ብር ወጪ መደረጉንም ገልጸዋል፡፡ 

ይኼ የብር ለውጥ ፕሮጀክት ኤክስ (X) ተብሎ በሚስጥር ሲሠራበት መቆየቱን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የኮሚቴውን አባላት አመሥግነዋል፡፡

This article is republished from ethiopianreporter under a Creative Commons license. Read the original article.

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *