አገር በመክዳት ወንጀል የተጠረጠሩት ሰባት ጄኔራል መኮንኖች ላይ 14 የምርመራ ቀናት ተፈቀደ

0
0 0
Read Time:1 Minute, 27 Second

የሬዲዮ መገናኛን በመጥለፍና ግንኙነት እንዳይኖር በማቋረጥ የሰሜን ዕዝ በሕገወጡ የሕወሓት ጦር ጉዳት እንዲደርስበት በማድረጋቸው፣ አገር በመክዳትና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል በመናድ ወንጀል ተጠርጥረው ፍርድ ቤት የቀረቡ የመከላከያ ሰባት ከፍተኛ መኮንኖች ላይ 14 የምርመራ ቀናት ተፈቀደ፡፡

የመከላከያ ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ የነበሩት ሜጀር ጄኔራል ገብረ መድኅን ፍቃዱ (ወዲ ነጮ)ን ጨምሮ ሰባት ከፍተኛ የመከላከያ መኮንኖች፣ በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት ኅዳር 3 ቀን 2013 ዓ.ም. ቀርበዋል፡፡

ምርመራውን እያካሄደ የሚገኘው የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን፣ ተጠርጣሪዎቹ ስለተጠረጠሩበት ጉዳይ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳው፣ ተጠርጣሪዎቹ የተጣለባቸውን ኃላፊነትና የገቡትን ቃል ኪዳን ወደ ጎን በመተው፣ አገርን በመክዳት፣ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ ተንቀሳቅሰዋል፡፡ መቀመጫውን በትግራይ ክልል ካደረገው የሕወሓት ሕገወጥ ቡድን (አመራር) ተልዕኮ በመቀበልና በአገሪቱ ባሉ የመከላከያ ሠራዊቶች ውስጥ ሌሎችን በማደራጀት፣ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. የአገር መከላከያ ሰሜን ዕዝ ሬዲዮ ግንኙነት እንዳይኖረው አቋርጠዋል፡፡ ይህንንም ድርጊት የፈጸሙት ሜጀር ጄኔራል ገብረ መድኅን ፍቃዱ (ወዲ ነጮ)፣ የመከላከያ ሠራዊት የምዕራብ ዕዝ አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ይርዳው ገብረ መድኅን፣ የደቡብ ዕዝ የሰው ሀብት ልማት አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ገብረ ሕይወት ሲስኖስ፣ የሰሜን ዕዝ መረጃ ዘርፍ ኃላፊ ብርጋዴር ጄኔራል ኢንስ ኢጃጆ አራሾ፣ ብርጋዴር ጄኔራል ፍስሃ ገብረ ሥላሴ፣ ኮሎኔል ደሳለኝ አበበና ኮሎኔል እያሱ ነጋሽ መሆናቸውንም መርማሪ ቡድኑ አስታውቋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ የመከላከያ ሠራዊቱ እርስ በርሱ እንዳይገናኝና እንዳይቀላቀል በማድረግ፣ በሰሜን ዕዝ ጦና ላይ የሞት፣ የአካል ጉዳትና ጦር መሣሪያ ዝርፊያ እንዲፈጸምበት ማድረጋቸውንም አስረድተዋል፡፡

በአገር ውስጥና በውጭ የሚቃጣን ጥቃት እንዳይከላከልና የሰሜን ዕዝ እንዲፈርስ በተቀናጀ ሁኔታ ከኦነግ ሸኔና ሌሎች የፀረ ሰላም ኃይሎች ጋር በመተባበር አብረው ሲሠሩ እንደነበርም መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ በተለያዩ ክልሎችም ሃይማኖትን ሽፋን አድርገው የብሔር ግጭት በማስነሳት አገርን ለመበተን ሲሠሩ እንደነበር መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ በማስረዳት፣ የወንጀሉን ክብደት ከግምት ውስጥ አስገብቶ በቀጣይ ለሚሠራው የምርመራ ሥራ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹም ድርጊቱን እንዳልፈጸሙ ለፍርድ ቤቱ በማስረዳት ተከራክረዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ መርማሪ ቡድኑ የጠየቀውን 14 ቀናት በመፍቀድ ለኅዳር 17 ቀን 2013 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *