0 0
Read Time:2 Minute, 11 Second


አቶ መኮንን ሀብተወልድ በ1886 ዓ.ም. ሸዋ ውስጥ አድአ ቢሸፍቱ ቃጂማ በተባለ ሥፍራ ከአባታቸው ከአለቃ ሀብተወልድ ካብቴነህና ከወ/ሮ ያደግድጉ ፍልፍሉ ተወለዱ። አቶ መኰንን ሀብተወልድ በህዳር ወር 1967 ዓ.ም. ከ60 ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር የተገደሉት የፀሐፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድና የፍርድ ሚኒስትር የነበሩት የአቶ አካለወልድ ሀብተወልድ ታላቅ ወንድም ናቸው። አቶ መኰንን ሀብተወልድ በ1953 ዓ.ም. በተደረገው መፈንቅለ-መንግሥት ከመገደላቸው በፊት በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ካቢኔ ውስጥ ሶስት ወንድማማቾች እንደ ነበሩ መመልከት ይቻላል። አጋጣሚ ሆነና ሶስቱም ወንድማማቾች ተራ በተራ በወታደራዊ ኃይሉች ለመገደል በቅተዋል፡፡ በታህሣሥ ወር 1953 ዓ.ም. ታትሞ በወጣው “መነን” መፅሄት እንደተብራራው አቶ መኮንን ሀብተወልድ በሰባት አመታቸው ዝቋላ ገዳም የአማርኛ ትምህርት ጀምረው በ15 ዓመታቸው ዜማና ቅኔን አጠናቀው ጨረሱ። ከ1903 እስከ 1904 ዓ.ም. አፄ ምኒልክ ጤና አጥተው በእንጦጦ ማርያም ጠበል እንዲጠመቁ በተደረገ ጊዜ በፀሎት አንባቢነት ተመርጠው አገልግለዋል። በመሃሉም የፈረንሣይኛን ቋንቋ በግላቸው አጥንተዋል። በ1907 ዓ.ም. የጉምሩክ ፀሐፊ በመሆን የመንግሥት ሥራ ጀመሩ። ከዚያም በአሩሲ ጠ/ግዛት የእርሻ ሚኒስቴር ዋና ፀሐፊ ቆይተውም በአገር ግዛት ሚኒስቴር ዋና ፀሐፊ ሆኑ፡፡ በኋላም በእርሻና ሥራ ሚኒስቴር ዋና ዲያሬክተር ሆኑ፡፡ ከዚያም ተነስተው የንግድና ኢንዱስትሪ ሚ/ዋና ዲያሬክተር ሆነው ተሾሙ። ጠላት ኢትዮጵያን ለመውረር መሰናዳቱ እንደታወቀ በ1927 ዓ.ም. “የኢትዮጵያ ህዝብ የሀገር ፍቅር ማህበር” በሚል ማህበር አቋቋመው የስብከትና የቅስቀሳ (ፕሮፓጋንዳ) ሥራ በመሥራት ከፍ ያለ አገልግሉት አበረከቱ።

በማይጨው ዘመቻ ጊዜ የመንግሥቱ የፖለቲካና የፀጥታ ጠባቂ ኃላፊ ሆነው ሲሰሩ ቆዩ። ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረች ጊዜ ወደ ፈረንሣይ አገር ተሰደው በዚያም ማህበር አቋቁመው የዲፕሎማሲያዊ ትግሉን በገንዘብና በቅስቀሳ ሲያግዙ ቆዩ። ከነፃነት መልስ በ1934 ዓ.ም. የእርሻ ሚኒስቴር ሆኑ። በ1935 ዓ.ም. በያዙት ኃላፊነት ላይ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ሆኑ፡፡ በ1937 ዓም. የኢተዮጵያ የእርሻ ባንክ ፕሬዘዳንት ሆኑ፡፡ በ1941 ዓ.ም. የገንዘብ ሚኒስትርነትን ተሾሙ። በ1950 ዓ.ም. ራስ መስፍንን በመተካት የአገር ግዛት ሚኒስትር ሆኑ። በ1951 ዓ.ም. ተመልሰው የንግድና ኢንዱስትሪ የፕላኒግ ሚኒስትር ሆኑ። ከዚያም በቀር የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ ፕሬዘዳንትና የማስታወቂያ ሚኒስቴርም ተጠባባቂ ሚኒስትር ነበሩ። ታህሣሥ 7 ቀን 1953 ተይዘው በመፈንቅለ መንግሥት እድራጊዎች ተገደሉ፡፡



አቶ መኰንን የቀዳማዊ ኃይለሥላሴን መንግሥት በተለይም ከስደት መልስ በሁለት እግሩ ለማቆም እውቀታ ቸውን እና ጉልበታቸውን አስተባብረው ይሰሩ እንደነበር የንጉሠነገሥቱ አማካሪ የነበሩት ጆን ሐዛወይ ስፔንስር ሣይቀሩ በፃፉት መፅሃፍ የምሥክርነት ቃል አስፍረዋል፡፡ የአቶ መኮንን ሀብተወልድ ሞት እጅግ ብዙ እንደጕዳቸው ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ እራሣቸ ው የተናገሩበት አጋጣሚ ነበር። አቶ መኮንን በተገደሉበት ወቅት የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር የበላይ ጠባቂ ስለነበሩ የማህበሩ አባላት ወደ ንጉሠ-ነገሥቱ ቀርበው የማህበራቸው ጠባቂ ስለሞቱባቸው እሣቸው የበላይ ጠባቂ እንዲሆኗቸው ጠይቀው ነበር። ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ለተወካዮቹ መልስ ለመስጠት ጀመር ሲደርጉ እንባቸው ይተናነቃቸውና ምልስ ብለው ወደቢሯቸው ገብተው ከተረጋጉ በኋላ ዓይናቸውን እየጠረጉ ወደተሰበሰቡት ተመልሰው “አቶ መኩንን በሁሉም የሥራ መስክ እየገባ እኛ ልናደርገው የሚገባንን ሁሉ የሚያደርግልንና የሚፈፅምልን ታላቅ አገልጋያችን ነበር፡፡ አሁን የሱን ሸክም ለመሸከም ስለምንገደድ የናንተንም ማህበር በበላይነት ለመጠበቅ ፈቅደናል” ሲሉ ተናግረዋል። አቶ መኮንን ሌላው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴን መንግሥት ወቅታዊ መረጃ በመሥጠት ከፍተኛ ድጋፍ ያደርጉ እንደነበር ይነገራል። ለምሣሌ የ1953 ዓ.ም. መፈንቅለ መንግሥት እንደሚደረግ ለንጉሡ ተናግረው እንደነበር ከችግሩ መከሰት በኋላ ታውቆላቸዋል።

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *