የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ወቅታዊ ጉዳይን አስመልክቶ የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይት በመካሄድ ላይ ነው
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ወቅታዊ ጉዳይን አስመልክቶ የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይት በመካሄድ ላይ ነው
ማክሰኞ ጥር 23 ቀን 2015 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ወቅታዊ ጉዳይን አስመልክቶ ዛሬ ጥር 23 ቀን 2015 የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይት በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት በማካሄድ ላይ ነው።
በውይይቱ ላይም አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኬያጅና የባህርዳር ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና በሰሜን አሜሪካ የኒዮርክና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳስ፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የየመምሪያ ኃላፊዎች፣ የድርጅት ሥራ አስኪያጆች፣ የሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎችና የየአኅጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች ተገኝተውበታል።
በውይይት መድረኩ በተከናወነው ኢ-ሕጋዊ የኤጵሲ ቆጶሳት ሹመት በተመለከተ ቅዱስ ሲኖዶስ የሰጠውን ውሳኔ እንዴት ማስፈጸም እንደሚቻል፣ የተጣሰው ኢ-ቀኖናዊ ቤተ ክርስቲያናዊ እና አስተዳደራዊ ጥሰት ከአገሪቱ ሕጎች አንፃር ሲታይ ምን እንደሚመስል፣ ቤተ ክርስቲያኗ ላይ ሊያስከትል የሚችለው አደጋ፣ በአጠቃላይ የተደረገው የቤተ ክርስቲያን የሃይማኖት፣ የቀኖናና የአስተዳደር ጥስትን በተመለከተ ከአለም ዓቀፍ አብያተ ክርስቲያናት ተሞክሮ አንጻር ምን ሊያስከትል እንደሚችል እንዲሁም፤ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ውሳኔ መሠረት ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ጀምሮ እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ድረስ ምን መደረግ እንዳለበት ውይይት እንደሚደረግ የኢኦተቤ መገናኛ ብዙሀን አገልግሎት ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።
የመድረኩ ተሳታፊዎችም ወደፊትም እንዲህ ዓይነት የቤተ ክርስቲያን ቀኖና ጥሰት እና ተመሳሳይ ድርጊት እንዳይፈጸም ምን መደረግ እንዳለበት በመወያየት የጋራ መግለጫ ያወጣሉ ተብሏል።
Source: EOTC TV