የአቶ ጃዋር መሐመድ ጽሑፍ ንድፈ ሐሳባዊ ቅንበባ (ክፍል አንድ)

0
1 0
Read Time:17 Minute, 44 Second


በጌታሁን ሔራሞ

በቅርቡ አቶ ጃዋር መሐመድ ወደ አማርኛው ሲተረጎም ‹‹ያለንበት ሁኔታና ቀጣዩ የትግል ምዕራፍ›› በሚል ርዕስ የተሰናዳ አንድ ረዘም ያለ መጣጥፍ መልቀቁ ይታወሳል፡፡ በእርግጥ ጽሑፉ በኦሮሚኛ ቋንቋ መቅረቡ የመልዕክቱ ታዳሚያንን ለመገመት ፍንጭ ይሰጣል፡፡ ቢሆንም ጸሐፊው ከይዘት አኳያ ከኦሮሚያ ክልል ባለፈ አገራዊና የሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችንም የወደፊት ዕጣ ፋንታን በተመለከተ በግልጽ በማንሳቱ ጽሑፉ ትኩረታችንን መሳቡ አልቀረም፡፡ የጽሑፉን የአማርኛ ትርጉም ተዓማኒነትን በተመለከተ ግን አስፈላጊው ማጣራት ሊደረግ ዘንድ ይገባ ነበር፡፡ እናም አቅም በፈቀደ ልክ ማጣራቱ ተግባራዊ ሆኗል፡፡ ሆኖም የትኛውም ጽሑፍ ወደ ሌላ ቋንቋ በሚተረጎምበት ወቅት ሊኖር የሚችል መጠነኛ የትርጉም ይዘት ክፍተት ሊኖር እንደሚችል ከወዲሁ በመገንዘብ በበቂ ማስረጃ እስከተደገፈ ድረስ፣ ማስተካከያውን ለመቀበል ዝግጁነቱ በጽሑፉ አዘጋጅ በኩል አለ፡፡ ከዚህ በመለስ እስካሁን በነበረው የማጣራት ሒደት በአቶ ጃዋር የኦሮሚኛ ጽሑፍና በአማርኛው ትርጉም መካከል ከይዘት አንፃር ይህ ነው የሚባል ልዩነት የለም ማለት ይቻላል፡፡ በትርጉሙ ዙሪያ የተባበሩኝ ወዳጆቼ በሙሉ ምሥጋናዬ ይድረሳቸው፡፡

  የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማ ከላይ የተጠቀሰውን የጸሐፊውን ጽሑፍ ከንድፈ ሐሳባዊ ቅንበባ (Theoretical Framing) አኳያ መፈተሽ ነው፡፡ ለመሆኑ የአንድን ጽሑፍ ንድፈ ሐሳባዊ ዳራውን የመፈተሽ ጠቀሜታው ምን ይሆን? ለዚህ ጥያቄ ምላሽ መንደርደርያ ይሆነን ዘንድ ጸሐፊው ወደ አማርኛ በተተረጎመው ጽሑፉ ገጽ 7 ላይ ያስቀመጠውን ሐሳብ አብረን እንመልከት፡፡ ‹‹የማንቃት ሥራዎችን ያሰረፅንበትን ሕዝብ የጋራ ባህል፣ ቋንቋ፣ ታሪክ፣ ዓርማና አገር በሕዝብ አዕምሮ ውስጥ ከፈጠርን በኋላ፣ የሚቀጥለው ምዕራፍ የሚሆነው በንድፈ ሐሳብ ደረጃ ያሰረፅናቸውን አስተምህሮዎችን ወደ ተግባር መሬት ላይ አውርዶ መሥራት ነው››፡፡

መልዕክቱ ግልጽ ነው፡፡ መሬት ላይ በተግባር ወርደው የምናያቸው ፖለቲካዊ ክንውኖች ከየትም የመጡ አይደሉም፡፡ መነሻ ላይ ንድፈ ሐሳባዊ አስተምህሮዎች የነበሩ ናቸው፡፡ አቶ ጃዋርም ሊያስገነዝበን የፈለገው ይህንኑ ነው፡፡ ለምሳሌ ላለፉት 30 ዓመታት ያህል በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዋር ውስጥ በገሃድ መሬት ላይ ወርደው ያጤንናቸው ፖለቲካዊ ሁነቶች ሥር ሲመዘዝ፣ በእነ ዋለልኝ መኮንን የሚመራው የወቅቱ የተማሪዎች ንቅናቄ አባላት ከያኔዋ ሶቪየት ኅብረት እንደወረደ የቀዱት የሌኒንና የስታሊን የብሔር ጥያቄ ንድፈ ሐሳብ መሆኑን መገንዘብ ያን ያህል ከባድ አይደለም፡፡

ከታሪክ ለመገንዘብ እንደሚቻለው እ.ኤ.አ. የ1990ዎቹ መባቻ ለሶቪየት ኅብረትና ለዩጎዝላቪያ የምጥ ወቅት ነበር፡፡ ምክንያቱም ሁለቱም አገሮች በታሪክ እንደ አገር የነበራቸው ዕውቅና ከእነ አካቴው ሊከስም የመጨረሻው ምዕራፍ ውስጥ የተገኙበት ወቅት ነበር፡፡ ታዲያ ለአገሮቹ መፈራረስና መክሰም በዋናነት ሰበቡ ምን ነበር? ብለን በአገሮቹ ዙሪያ ጥናት ሲያደርጉ የነበሩትን ምሁራንን ብንጠይቃቸው ምላሻቸው “ንድፈ ሐሳባዊ” ነው የሚል ስለመሆኑ እርግጠኛ ሆኖ ማስመር ይቻላል፡፡ ለምሳሌ አየርላንድ የሚገኘው የኩዊንስ ዩኒቨርሲቲ የብሔርተኝነትና የብሔር ግጭቶች አጥኚ የሆነው ኤፍሬም ኒሚኒ ለሶቪየት ኅብረት መፈራረስ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው ቀደም ሲል አገሪቱ ስትከተለው የነበረው የብሔር ጥያቄ (The National Question) ንድፈ ሐሳብ ነው ይለናል፡፡ እንደ እኛ አገር ብሔርተኛ ፖለቲከኞች “ችግሩ የአፈጻጸም ነው” የሚልበት ድፍረቱ የለውም፡፡ እንዲያውም ኤፍሬም ኒሚኒ (ዶ/ር) የእነ ሶቪየት መፈረካከስ ችግሩ ንድፈ ሐሳባዊ መሆኑን ለማስገንዘብ እ.ኤ.አ. በ1991፣ “Marxism and Nationalism: The Theoretical Origins of Political Crisis” በሚል ርዕስ መጽሐፍ አስጠርዞ አስነብቦናል፡፡ በተመሳሳይ በሌሎችም አገሮች ለተስተዋሉና ለሚስተዋሉ የፖለቲካዊ ቀውሶች መንስዔው ንድፈ ሐሳባዊ ሊሆን የሚችልበት አጋጣሚው ብዙ ነው፡፡ በእኔ እምነት በአገራችን የሚስተዋሉ አብዛኞቹ የፖለቲካ ትንታኔዎችና ሙግቶች ልክ እንደ “እግር ኳስን በሬዲዮ ተመልከቱ” መርሐ ግብር ሁነት ተኮር (Event Oriented) ብቻ ይመስላሉ፡፡ ለሁነቶቹ መነሻ የሆኑ ንድፈ ሐሳባዊ ሙግቶች በሁነቶቹ ልክ ርዕሰ ጉዳይ ሲሆኑ እምብዛም አንመለከትም፣ ትኩረታችን ከምንጩ ይልቅ ወንዙ ላይ ነው፡፡

እንግዲህ የአቶ ጃዋርንም ጽሑፍ ንድፈ ሐሳባዊ ዳራውን ለመቃኘት ተገቢነቱ (Relevance) የሚመነጨው ከላይ ካስቀመጥኩት እውነታ ነው፡፡ በእኔ ግምገማ የአቶ ጃዋርን ጽሑፍ ከይዘት አንፃር በአንድ ወጥ ንድፈ ሐሳብ ጥላ ሥር መቀንበብ የሚቻል ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ እስካሁን ባለኝ ግንዛቤ መነሻነትም በጽሑፉ ውስጥ በጥቂቱ ወደ አራት ዓይነት የብሔርተኝነት ንድፈ ሐሳቦች ተንፀባርቀዋል፡፡ በአራቱም የብሔርተኝነት ንድፈ ሐሳቦች መካከል ያለውን ተቃርኖንም ሆነ ቁርኝት በተመለከተ በይደር አቆይተን ንድፈ ሐሳቦቹን ተራ በተራ እንደሚከተለው ለመፈተሽ እንሞክራለን፡፡

 1. ዘመናዊ የብሔርተኝነት ንድፈ ሐሳብ

አቶ ጃዋር የኦሮሞን ብሔርተኝነት የትግል ሒደት ለማስረዳት በጽሑፉ የሁለት ጎምቱ ተመራማሪዎችን የዘመናዊ ብሔርተኝነት ንድፈ ሐሳብን ግልጽ በሆነ መልኩ ጥቅም ላይ አውሎታል፡፡ የመጀመርያው የኤርነስት ገልነር ንድፈ ሐሳብ ሲሆን ሁለተኛው የቤኔድክት አንደርሰን ነው፡፡ የሁለቱም ሳይንቲስቶች የብሔርተኝነት ንድፈ ሐሳቦች የሚመደቡት ከዘመናዊያኑ ጎራ ነው፡፡ ክፍል አንድ ጽሑፌ በኤርነስት ገልነር የብሔርተኝነት ንድፈ ሐሳብ ላይ ያተኩራል፡፡ ቀጣዩ ክፍል ሁለት ጽሑፌ ደግሞ በቤኔድክት አንደርሰንና በጽሑፉ ውስጥ በተንፀባረቁ በሌሎች ሦስት ንድፈ ሐሳቦች ዙሪያ ያተኩራል፡፡

 • የኤርነስት ገልነር ዘመናዊ የብሔርተኝነት ንድፈ ሐሳብ 

ጸሐፊው በገጽ 6 ላይ ያስቀመጠው ሐሳብ ይህን ይመስላል፣

“የብሔራዊ ትግሉ ዓላማ ሕዝቡንና ግዛቱን በመጠበቅ (Making The People And Its Territory Congruent) ከባዕድ ጭቆና ማላቀቅ በመሆኑ፣ በሕዝቡ ዙሪያ ከሚሠሩ ፕሮጀክቶች ተግባር ውስጥ አንዱ የእንደገና መገንባት (ማቋቋም) ሥራ በአዕምሮ ውስጥ በማስረፅ (Imagined Communities) በገቢርም መንቀሳቀስ እጅግ አስፈላጊ ነው››፡፡

የብሔርተኝነትን ጽንሰ ሐሳብ በተመለከተ መደበኛ የንባብ ልምድ ያለው የትኛውም አንባቢ፣ ጸሐፊው ከላይ ባሰፈረው ሐሳብ ውስጥ የኤርነስት ገልነርንና የቤኔድክት አንደርሰንን ሐሳብ ቃል በቃል መጠቀሙን ማጤን አያቅተውም ብዬ አስባለሁ፡፡ ከላይ ጠቀስ እንዳደረኩት ስለቤኔድክት አንደርሰን የብሔርተኝነት ንድፈ ሐሳብ በቀጣዩ ጽሑፌ እንመለከታለን፡፡ ለአሁኑ ግን የኤርነስት ገልነርን የብሔርተኝነት ንድፈ ሐሳብን ለመፈተሽ እንሞክራለን፡፡

በዜግነት ብሪትሽ-ቼካዊ የነበረው፣ ፈላስፋውና አንትሮፖሎጂስቱ ኤርነስት ገልነር (እ.ኤ.አ.1925 እስከ 1995) ዓለም አቀፍ ዕውቅናን የተጎናፀፈው ብሔርተኝነትን ከዘመናዊነት ጋር አቆራኝቶ በማጥናቱ ነው፡፡ በሕይወት ዘመኑ ከርዕሰ ጉዳዩ ጋር በተገናኘ አያሌ መጻሕፍት ለንባብ ማብቃቱ የሚታወቅ ቢሆንም፣ እ.ኤ.አ. በ1964 ዓ.ም. “Thought and Change”፣ እ.ኤ.አ. በ1983 “Nations and Nationalism” እና እ.ኤ.አ. በ1994 “Conditions of Liberty” የተሰኙ መጻሕፍት በወቅቱ የዘርፉን ምሁራን ትኩረት ከሳቡት ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ኤርነስት ገልነር ከዕውቀት አኳያ በይነ-ዲሲፕሊናዊ የሚባል ምሁር ሲሆን፣ በብሔርተኝነትና በዘመናዊነት መካከል ያለውን ቁርኝት በተመለከተ ያደረገው ጥናት ፈር ቀዳጅ የሚባል ዓይነት ነው፡፡ በዘመናዊ ብሔርተኝነት አፈጣጠር ዙሪያ የሚያደርጋቸው ጥናቶቹ ይዘትም በዋናነት የሚያተኩሩት በማኅበረ ባህላዊ (Socio-cultural) እሴቶች ላይ ነው፡፡

ኤርነስት ገልነር የሰው ልጅ ማኅበረሰባዊ ጉዞ ሦስት የዕድገት ደረጃዎችን ማለትም ቅድመ ግብርና፣ ግብርናና ኢንዱስትሪን እንዳስተናገደ ያነሳና ከነዚህ ከሦስቱም ደግሞ በዘመናዊነት ውስጥ ብቅ ያለው የኢንዱስትሪ ማኅበረሰብ ለብሔርተኝነት ምቹ ሁኔታዎችን በጉያው እንዳቀፈ ያስገነዝበናል፡፡ እንደሚታወቃው ዘመናዊነት ለኢንዱስትሪ፣ ለትምህርት፣ ለማኅበራዊ ዕድገት፣ ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ ወዘተ የሚሰጠው ትኩረት ወጥ (Homogeneous) የሆነ ማኅበረሰብን በመፍጠሩ ረገድ የበኩሉን አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ በዘመናዊ ማኅበረሰብ ውስጥ ከቴክኖሎጂውና ከሳይንሱ ዕድገት ጋር በእኩል ፍጥነት መመንደግ የሚችል ቋንቋና ባህል በሌሎች ቋንቋዎችና ባህሎች ላይ ተፅዕኖ እየፈጠረ በሒደትም ወጥና ተመሳሳይ ማኅበረሰብ ይፈጠራል፡፡ ይህም በዘመናዊነት እሴቶች አጋዥነት የተፈጠረውና በባህል፣ በቋንቋ፣ በሥነ ልቦና ተቀራራቢ ማንነትን የተላበሰ ማኅበረሰብ “ብሔር” ተብሎ ይጠራል፡፡ በሒደትም ይህ ብሔር ፖለቲካዊ መርህን ተላብሶ ወደ አገርነት ይቀየራል፡፡ ለተፈጠረው አገር የጋራ እሴቶች ስሜትንና ቀልብ ገብሮ መኖር ደግሞ ብሔርተኝነትን ይፈጥራል፡፡ በገልነር ዕይታ በዘመናዊነት ሰበብ የተፈጠረ ብሔር ሁሌም የራሱ መንግሥት ይኖረው ዘንድ ግድ ይላል፡፡ የብሔርተኝነት ዓላማና ግቡም ይኸው ነው፡፡ ለዚህም ነው ገልነር በ”Nations and Nationalism” መጽሐፉ ገና በገጽ 1 ላይ ብሔርተኝነት በፖለቲካ ካርታውና በብሔሩ መካከል ፍፁም ተመሳሳይነትን የሚሻ ፖለቲካዊ መርህ ነው የሚለው፡፡ “Nationalism is primarily a political principle, which holds that the political and the national unit should be congruent” እንግዲህ አቶ ጃዋርም በገጽ 6 ላይ “የብሔራዊ ትግሉ ዓላማ ሕዝቡንና ግዛቱን መጠበቅ” እንደሆነ ከጠቆመ በኋላ በቅንፍ ውስጥ “Making the People And its Territory Congruent” በማለት ያስቀመጠው ይህንኑ የገልነርን ዕሳቤ ነው፡፡ በተጨማሪ አቶ ጃዋር የኤርነስት ገልነርን ዘመናዊ የብሔርተኝነትን ዕሳቤን መርህ በግልጽ መዋሱን ማወቅ የምንችለው በገጽ 8 ላይ ነው፡፡

‹‹በ19ኛው ክፍለ ዘመን በብዙ የአውሮፓ አገሮች የተወለዱ ብሔርተኝነቶች በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካዊና በማኅበረ-ባህላዊ ለውጦች የተነሳ ማንበብና መጻፍን፣ ከተማንና ፈጣን የቢሮክራሲ መስፋፋትን በማንበር እንዳደጉ ይታወቃል፡፡›› አቶ ጃዋር የገልነርን ንድፈ ሐሳብ በጽሑፉ በግልጽ እስካስቀመጠ ድረስ የዕሳቤው ተከታይ እንደሆነ ከማመን የሚያግደን አመክንዮ የለም፡፡ በጽሑፉም ውስጥ ልክ እንደ ገልነር የአውሮፓውን የ19ኛውን ክፍለ ዘመን የዘመናዊነት ንቅናቄን ከኦሮሞ ብሔርተኝነት ጋር እያነፃፀረ ሊያስረዳን መሞከሩ ከገልነር ንድፈ ሐሳብ ጋር ያለውን ቁርኝት አመላካች ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፣ አቶ ጃዋር በክልል ደረጃ ብቻ ሳይሆን በአገር አቀፍ ደረጃም የወጥነትን ፕሮጀክት (Homogenization Project) የማስፈጸም ዕቅድ እንዳለው ፍርጥርጥ አድርጎ ሲነግረን ፍርኃት ብጤ ሳይወረን አልቀረም፡፡ ለምሳሌ በገጽ 7 ላይ አቶ ጃዋር እንደዚህ ይለናል፡፡

‹‹…የአንድ ሕዝብ ትግል ዓላማ ለራሱ ጥቅም እንቅፋት የሚሆንን ሥርዓት ለራሱ በሚሆን መልክ መቀየር፣ ካልሆነ ደግሞ ነባሩን ሥርዓት ለራሱ በማፈራረስ ወይም በመገንጠል አዲስ ሥርዓት መገንባት ያስፈልጋል… አዲስ አገር እንመሥርት ወይስ ያለውን አገር ለእኛ በሚመቸን በኩል አዲስ ቅርፅ በመስጠት እንቀጥል በሚሉት ጉዳዮች መካከል ያለው ግጭት የተፈጠረበትም ምክንያት ለዚሁ ነው››፡፡

እዚህ ጋ አቶ ጃዋር ስለኦሮሞ ብሔርተኝነት የትግል ሒደት ለማስረዳት የኤርነስት ገልነርን ዘመናዊ የብሔርተኝነት ንድፈ ሐሳብን ጥቅም ላይ ማዋሉ የቱን ያህል ተገቢ (Relevant) ነው የሚለውን ጥያቄ መጠየቅ ግድ ይላል፡፡ በእኔ ምልከታ ተገቢ ነው የሚል እምነቱ የለኝም፡፡ ምክንያቱም፣

ሀ. ከጥናቱ ዓውድ ጋር በተገናኘ

ገልነር የ19ኛውን ዘመን የኢንዱስትሪ አብዮትን መነሻ አድርጎ ያጠናው በዋናነት አውሮፓን ማዕከል አድርጎ ነው፡፡ በአጭር ቃል ጥናቱ አውሮፓ ተኮር (Euro-centeric) ነው፡፡ አውሮፓም ውስጥ ሆኖ ጥናቱ ይበልጥ ውጤታማ የመሆን ዕድል የሚኖረው አንድ ብሔር በአብላጫነት በሚኖርባቸው አገሮች ውስጥ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር የገልነር የብሔርተኝነት መርህ (One Culture-One State) ለብዝኃ ብሔር (Muti-national) አገሮችም ሆነ ለብዝኃ ባህል (Multi-cultural) አገሮች ፈፅሞ የሚመከር አይደለም፡፡ እንደ ኢትዮጵያ አያሌ ብሔሮች ለረዥም ዘመናት በአብሮነት ተሰባጥረው በሚኖሩባቸው አገሮች የገልነርን ንድፈ ሐሳብ ተግባራዊ ለማድረግ ተፍ ተፍ ማለት መዘዙ ብዙ ነው፡፡

ለምሳሌ አቶ ጃዋር በተደጋጋሚ አገርን “ለራስ በሚሆን መልክ መቀየር”… “ያለውን አገር ለእኛ በሚመቸን በኩል አዲስ ቅርፅ በመስጠት”… እያለ እንደ ዋዛ የሚያነሳቸው ፕሮግራሞች አሉት፡፡ በእርግጥ ገልነርም በኢንዱስትሪው አብዮት ውሽንፍር ውስጥ የዳበረ ባህል (High Culture) ያለው ብሔር ያልዳበረ ባህል ያላቸውን (Low Culture) አናሳ ብሔሮችን መሰልቀጡ (Assimilation) አይቀሬ ነው፡፡ ስለዚህም በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ የአናሳ ብሔሮች ዕጣ ፋንታ ሁለት ነው ይለናል፡፡ የመጀመርያው አቶ ጃዋር ቀደም ሲል እንዳስቀመጠው አብላጫው ብሔር በራሱ መልክ ለመቅረፅ በሚያደርገው የመሰልቀጥ ዕቅድ እጅ ሰጥቶ መቀጠል (ፈረንሣይ ውስጥ እንደሆነው) አሊያም ተገፍቶ ወጥቶ (Excluded Ethnicity) በመገንጠል የራስን አገር መመሥረት ነው፡፡

“Under the new social Regime, this condition becomes increasingly uncomfortable. Men then had two options, if they were to diminish such discomfort: they could change their own culture, or they could change the nature of the political unit” Earnest Gellner, Conditions of Liberty, PP 108” ይህም ብቻ አይደለም፣ እንደ እኛ ብዝኃ ብሔርነት በሰፈነበትና ብሔሮች ፖለቲካዊ የበላይነትን ለመቀዳጀት እርስ በርስ በሚፎካከሩባቸው አገሮች የገልነርን የብሔርተኝነት መርህ ማለትም አንድ ባህል አንድ መንግሥት (One Culutre-One State) ተግባራዊ ለማድረግ በሚወሰዱ ዕርምጃዎች ሊከሰቱ የሚችሉ ቀውሶችን ገልነር ሳይሸሽግ በ“Conditions of Liberty” መጽሐፉ ውስጥ አስቀምጧል፡፡ እንደ ገልነር ገለጻ ከሆነ ወጥ ያልሆነ ዥንጉርጉር የብሔሮችን ስብስብን ወደ ተመሳሳይነት ለማምጣት በተለይም አናሳ ብሔሮችን መሰልቀጥ፣ ማፈናቀል አሊያም መግደል (የዘር ፍጅት) ሊደርስባቸው ይችላል ይለናል፡፡

“If the eventual units were to be compact and reasonably homogeneous, more had to be done: many, many people had to be either assimilated, or expelled or killed.” Conditions of Liberty, 1964

ስለዚህም አቶ ጃዋር… አገሪቱን ለእኛ በምትመች ሁኔታ በመልካችን እንቀርፃታለን… ካለን፣ ቀረፃው ሊከወን የታሰበበትን ሥልት መጠየቅ ግድ ይላል፡፡ ከ80 ዘውጌዎች በላይ የሚኖሩባትን አገር በራስ ምሥል መቅረፁ ዕውን የሚሆነው ከላይ ገልነር እንዳስቀመጠው በመሰልቀጥ ነው? ወጥነትን (Homogenity) ለመፍጠር በሚደረግ ጥረት ውስጥ በእንቅፋትነት የተፈረጁትን፣ “መጤ” ወይም “ሰፋሪ” የሚል ታፔላ የተለጠፈባቸውን ዜጎች በማፈናቀል ነው? ወይስ በመግደል ነው? እንግዲህ አውሮፓ ውስጥ የኢንዱስትሪ አብዮት የፈጠረው ማኅበረ ባህላዊ ውቅርን መነሻ ተደርገው የተነደፉ ንድፈ ሐሳቦችን እንደወረዱ ወደ ኢትዮጵያ መኮረጅ ዳፋው ብዙ ዋጋ የሚያስከፍል መሆኑን መተንበይ አይከብድም፡፡ ቢያንስ አሁን ባለንበት ዘመን እነ ዋለልኝ ከ50 ዓመታት በፊት የፈጸሙትን የኩረጃ ስህተትን ዛሬም መድገም የለብንም፡፡ መግቢያዬ ላይ እንደጠቀስኩት ከዓውድ የተፋቱ ንድፈ ሐሳቦች ለፖለቲካዊ ቀውሶች ሰበብ የመሆን ዕድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡   

 ለ. ከዴሞክራታይዜሽን ጋር በተገናኘ

ሌላው እንደ ኢትዮጵያ አያሌ ብሔሮች ተሰባጥረው በሚኖሩበት አገር  የኤርነስት ገልነር “One Culture- One State” ወይም “Nation-State Congreuency” መርህ ለእኛ አገር ዓውድ ተገቢ የማይሆነው የዴሞክራታይዜሽን ፀር ስለሆነ ነው፡፡ በአጭር ቃል ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት በወጥነቱ (Homogenization) አፈጻጸም ወቅት መሪ ተዋናይ ለሆነው ለሰልቃጩ ብሔር መወገኑ አይቀሬ ነው፡፡ ለዚህም በዋቢነት የምጠቅሰው አቶ ጃዋር በገፅ 31 ላይ የሰነዘረውን ሐሳብ ነው

“የኢትዮጵያ የፌዴራል ሥልጣን በእጃችን እንደገባ ለብሔረሰባችን ችግር መፍትሔው ባዕዳን ሳይሆኑ እኛው ራሳችን መሆናችንን በጥልቀት እንዳላሰላሰልነው ያሳያል… ለረጅም ዘመናት በባዕዳን በሚመራ አምባገነን ሥርዓት ሲሰቃይ የነበረ ጭቁን ሕዝብ በከፍተኛ መስዋዕትነት በከፈለው ትግል ወደ ሥልጣን ከወጣ ልጁ ብዙ ይጠብቃል፣ ነገር ግን አመራሩ ዕቅድና ስትራቴጂ ስላልነበረው ሕዝቡ የሚጠብቅበትን በፍጥነት ሊያሟላለት አልቻለም… በሥልጣን ላይ ያለው ባዕድ አይደለም የኦሮሞን ሕዝብ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮች የመፍታት ፍላጎትና ብቃት ቢኖረው ኖሮ የወጣበትን ሕዝብ በማስደሰት ሥልጣንን ማጠናከር በቻለ ነበር፤›› በማለት ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የአንድ ብሔርን ችግር ለመፍታት ብቻ የተሰየመ እስኪመስል በግልጽ ውግንናውን ይጠቁማል፡፡ የአንድ ብሔር የፖለቲካ ልሂቃን ሥልጣን ላይ ያለው የፌዴራል መንግሥት የ80 ዘውጌዎች መንግሥት ነው ከማለት ይልቅ፣ “የእኔ መንግሥት ነው” ማለት ከጀመሩ ዴሞክራሲ ድምጥማጧ ጠፋ ማለት ነው፡፡

በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ የሶሺኦሎጂ ፕሮፌሰር የሆነውና በኤርነስት ገልነር የብሔርተኝነት መርህ ላይ የሰላ ሂስ በመሰንዘር የሚታወቀው ሮጀር ብሩባከር፣ በ”Nationalism Reframed: Nationhood and National Question in New Europe” መጽሐፉ ውስጥ የገልነርን ኔሽን ስቴት ዓይነት ፖሊሲን በሚተገብሩ አገሮች ያለው መንግሥት አፈጣጠር ከአብላጫው እንደመሆኑ ውግንናውም ለአብላጫው ብሔር እንደሚሆን በገጽ 3 ላይ ያስረዳል፡፡ እንደ ብሩባከር የገልነር የብሔርተኝነት ንድፈ ሐሳብ ሃያሲ የሆነው አሜሪካዊው የፖለቲካ ሳይንቲስት አልፍሬድ ስቲፓን “Arguing Comparative Politics” መጽሐፉ ምዕራፍ 9 (Transcending a Gellnerian Oxymorn) ላይ ቀደም ሲል የጠቀስኩትን የብሩባከርን ሐሳብ በመደገፍ እንደዚህ ይላል፡፡

 “For Rogers Brubaker, leaders who pursue nation-state policies assume that the state is of and for the dominant cultural nations…If there are two or more culturally conscious demoi in the polity, nation-building policies of and for the dominant nation would imply restricted citizenship, or at least unequal citizenship, for many of the long-standing minority residents in the state.”

እንግዲህ ብሩባከርም ሆነ ስቲፓን በአብላጫነት ትምክህት ሰበብ አንድን አገር በመልካቸው ለመቅረፅ የሚያቅዱ ብሔርተኞች የአገሩን መንግሥት ከራሳቸው የራሳቸው እንደሆነ አድርገው በምናባቸው እንደሚሥሉ አስምረውልናል፡፡ የሚገርመው አቶ ጃዋር ከዚህ ማጠቃለያ ጋር በጣም ተመሳሳይ የሆነ ዕሳቤን በጽሑፉ ማንፀባረቁ ነው፡፡ በእሱ ዕይታ አሁን ያለው የፌዴራል መንግሥት ከኦሮሞ ለኦሮሞ (of and for) ነው፡፡ በእርግጥ አቶ ጃዋር አልፎ አልፎም ቢሆን የግርጌ ማስታወሻ በሚመስል መልኩ በሁለተኛ ደረጃ ስለሌሎች ብሔሮች ዴሞክራሲያዊ መብት ያነሳል፡፡ ለእኔ ይህ ሚዛናዊ ለመምሰል የተሞከረ ባለ ድርብ ድምፅ ሃቲት (Double-Voiced Discourse) ነው፡፡ ለነገሩ ብዝኃ ብሔር በናኘበት አገር፣ ሥልጣንም በብሔር ፓርቲ አሳላጭነት በሚታፈስበት የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ፣ ከውግንና ነፃ የሆነ መንግሥትንም ሆነ መንግሥታዊ ተቋምን ማግኘት የሚታሰብ እንዳልሆነ የብሔርተኝነት ጽንሰ ሐሳብ ተመራማሪ ምሁራን ካስገነዘቡን ውሎ አድሯል፡፡ ለምሳሌ እንግሊዛዊ ፈላስፋና ፖለቲካል ኢኮኖሚስት ጆን ስቱዋርት ሚል በ”Utilitarianism, liberty, Considerations on Representaive Governmnet” መጽሐፉ ገጽ 396 ላይ ልዩ ልዩ ብሔሮችና ልዩ ልዩ ቋንቋዎች በሚነገርበት አገር ከውግንና የፀዱ ነፃ መንግሥታዊ ተቋማትን ማግኘት ህልም ነው ይለናል፡፡

“Free institutions are next to impossible in a country made up of different nationalities. Among a people without fellow-feelings, especially if they read and speak different languages, the united public opinion necessary to the working of representative institutions cannot exist…”

ሐ. ጽንሰ ሐሳባዊ ብዥታ

በእኔ አረዳድ የገልነርን ዕሳቤ ጥቅም ላይ በማዋሉ ሒደት ጽንሰ ሐሳባዊ ብዥታ (Lack of Conceptual Clarity) ያለ ይመስለኛል፡፡ ማለትም ሰውየው (ገልነር) የሚለውን የቱን ያህል ተረድተነዋል? ለምሳሌ በኤርነስት ገልነር “Nation-State Congreunecy” ጽንሰ ሐሳብ ውስጥ “ኔሽን” የሚለው ቃል የሚያመለክተው አንድን ንዑስ ብሔርን (ለምሳሌ የአማራን ወይም የኦሮሞን) አይደለም፡፡ ይልቁን ቃሉ የሚያመለክተው በታሪክ አጋጣሚ የዳበረ ባህልን (High Culture) የገነባ ንዑስ ብሔር በኢንዱስትሪ አብዮት አጋዥነት በሌሎች ብሔሮች ተፅዕኖ በማሳደሩ የሚፈጠር አገርን ነው፡፡ ስለዚህም በአንድ አገር ውስጥ ያለ አንድ ንዑስ ብሔር በገልነር “Nation-State Congreunecy” መርህ በመሰልቀጥና ወጥነትን በመፍጠር ሌሎችን በራሱ ምሳሌ ለመፍጠር ዕቅዱ ካለው ማሟላት ያለበት ቅድመ ሁኔታ አለ፡፡ ይህም ቅድመ ሁኔታ የኢንዱስትሪውን አብዮት ማሳለጥ የሚችል የዳበረ ባህል (High Culture) ባለቤትነት ነው፡፡ ለገልነር ናሽናሊዝም በዘመነ ኢንዱስትሪ አብዮት የዳበረው ባህል ባልዳበሩት ላይ በሚፈጥረው ተፅዕኖ የሚወለድ ክስተት ነው… “For Gellner, nationalism is the imposition of high culture on society replacing local, low cultures and most multiculturalism.” (Ernest Gellner,Mathew Cuff).

  እንግዲህ ከላይ በተብራራው የገልነር የብሔርተኝነት ንድፈ ሐሳብ መነሻነት ከዘለቅን ኢትዮጵያ ውስጥ በንፅፅር እንኳን ከወሰድን የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ የዳበረ ባህል፣ ቋንቋ፣ ሥነ ጽሑፍ፣ ታሪክ ወዘተ ባለቤት ሆኖ የ“Nation-State Congreunecy” መርህን ተግባራዊ የማድረግ ዕድሉ የነበረው የትኛው ብሔር ነበር? የዚህን ጥያቄ ምላሽ የሚሰጠን ገልነር ራሱ ነው፡፡ ኤርነስት ገልነር የኢንዱስትሪ አብዮት ባልተቀጣጠለባቸው እንደ አፍሪካ ባሉ አገሮች ታላላቅ ዓለም አቀፍ ሃይማኖቶች (ክርስትናና እስልምና) ወጥ ማኅበረሰብን በመፍጠሩ ሒደት የራሳቸውን ሚና እንደሚጫወቱ ግምቱን አስቀምጦ ነበር፡፡ በዚህም መሠረት ኢትዮጵያ ውስጥ የአማራው ብሔር ክርስትናን ከሌሎቹ የአገሪቱ ብሔሮች ቀድሞ በመቀበሉ በንፅፅር ሲታይ የ”High Culture” ባለቤት ሆኖ “Nation-state congreunecy” መርህን ለመተግበር መደላደሉን አመቻችቷል የሚለውን ሐሳብ በ”Nations and Nationalism” መጽሐፉ ገጽ 81 እና 82 ላይ አስቀምጧል (የእስልምናውን አንድ የማድረግ አቅም በተመለከተ በምሳሌነት የጠቀሰው ሶማሊያን ነው)፡፡ እንዲሁም ዋለልኝ መኮንንም በ1961 ዓ.ም. ባነበበው ጽሑፉ የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ አማራና በተወሰነ ደረጃ ደግሞ ተጋሩ በሌሎች የደቡብ ብሔሮች ላይ ጫና ከመፍጠር አንፃር የ”High Culutre” ባለቤት መሆናቸውን በግልጽ አስቀምጧል፡፡

የሚገርመው ገልነር የአማራና የሶማሊያ ብሔሮች ለ“Nation-State Congreunecy” ግንባታ እርሾ እንደሚሆኑ ቢተነብይም ትንቢቱ ሳይፈጸም ቀርቷል፡፡ ምክንያቱም ከታሪክ እንደተመለከትነው የአማራ ገዥው መደብ ልክ አንደ ፈረንሣይ አሃዳዊ መንግሥት ሌሎች ብሔሮችን ሙሉ በሙሉ የሚሰለቅጥበትን አጋጣሚ አላገኘም፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ፖለቲካዊ ግብዓቱ ነው፡፡ ማለትም ከ1960ዎቹ ጀምሮ በትግራይ፣ በኦሮሞና በሌሎች ብሔሮች የተቀጣጠለው የጭቆና ወለድ ብሔርተኝነት (ሌኒን “Defensive Nationalism” ብሎ የሚጠራው) ትግል የገልነርን ህልም ከንቱ አድርጎታል፡፡ የጎረቤታችን የሶማሊያ ሁኔታ ደግሞ ከማናችንም የተሰወረ አይደለም፣ በዚያ ሁሉ የብሔርና የሃይማኖት ወጥነት ውስጥ አንድ መሆን አቅቷት እስከ ዛሬም ምጥ ላይ ነች፡፡ በነገራችን ላይ ገልነር ለብሔርተኝነት መፈጠር የኢንዱስትሪ አብዮትን ብቻ ነው በዋናነት ያስቀመጠው፡፡ የኢንዱስትሪ አብዮት በሌለበት ፖለቲካው ከላይ እንደተመለከትነው “Defensive Nationalism”ን ሊፈጥር እንደሚችል ትኩረት ሰጥቶ አላጠናም፡፡ ከዚህም የተነሳ ገልነር ከብዙ አቅጣጫ ሂሶችን አስተናግዷል፡፡ ለዚህም ነው የገልነር የብሔርተኝነት መርህ ለኢንዱስትሪ አብዮት ብቻ ወግኖ ፖለቲካዊ ግብዓቶችን ያገለለ (Apolotical) እንደሆነ የሚነገረው፡፡ በነገራችን ላይ ኤርነስት ገልነር የተሰነዘሩበትን ሂሶች ተከትሎ የአቋም ለውጥ ካደረገባቸው ሐሳቦቹ ውስጥ አንዱ ይህ የኢትዮጵያና የሶማሊያ ምሳሌዎቹ ናቸው፡፡ ገልነር ይህን ምሳሌውን ሙሉ በሙሉ መተውን የነገረን ደግሞ ጆን ኤሃ ል በ”Ernest Gellner: An intellectual Biography, 2010” መጽሐፉ ገጽ 321 ላይ ነው፡፡ (Kindle Version)

የገልነርን “አንድ ባህል አንድ መንግሥት” (“One Culture-One State”) ዘመናዊ የብሔርተኝነት ትንታኔን በተመለከተ ጽንሰ ሐሳባዊ ብዥታ ተፈጥሯል ብዬ የምሰጋበት ሌላው ምክንያት ገልነር ለብሔርተኝነት ካለው አቋም ጋር የሚገናኝ ነው፡፡ ቀደም ሲል ለማስገንዘብ እንደሞከርኩት ገልነር በተለይም ብዝኃ ብሔርነት በሰፈነበት ማኅበረሰብ ወጥነትን ለማስፈን በሚወሰዱ ዕርምጃዎች ስልቀጣ፣ ማፈናቀልና ግድያ ሊፈጸም እንደሚችል በግልጽ አስቀምጧል፡፡ በዚህ ገለጻው ገልነር እያስገነዘበን ያለው በተጠቀስው ዓውድ ብሔርተኝነት አሉታዊ ክስተት (Negative Phenomenon) ሊሆን እንደሚችል ነው፡፡ በአንድ ወቅት የ”Imagined Communities” መጽሐፍ ደራሲና የገልነር ወዳጅ የሆነው ቤኔድክት አንደርሰን “ብሔርተኝነትን ትደግፋለህ ወይ ?” ተብሎ ለተጠየቀው ጥያቄ ምላሹ፣ ‹‹አዎን፡፡ በእርግጥ ብሔርተኝነት አስጠሊታ እንዳልሆነ በመጻፍ እኔ ብቸኛው ነኝ፣ ገልነርንና ሆብስዋምን ብትወስዳቸው ሁለቱም ለብሔርተኝነት ያላቸው ስሜት የጥላቻ ነው፣ እኔ ግን ብሔርተኝነት ማራኪ ርዕዮተ ዓለም መሆን ይችላል ብዬ አምናለሁ፤›› የሚል ነበር፡፡ ምንጭ (Theories of Nationalism, Umut Ozkirimli, 3rd edition, 2017፣ PP 116)

  ጥያቄዬ እንደምናውቀው አቶ ጃዋር የብሔርተኝነት ደጋፊ ነው፣ ብሔርተኝነትን እንደ አዎንታዊ ርዕዮት የሚያራምድ ብሔርተኛ ደግሞ አቋሙን ለመተንተን የሚጠቀመው ምናልባትም የእነ ቤኔድክት አንደርሰን ዓይነት ዕሳቤን ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህ በመለስ አቶ ጃዋር ብሔርተኝነት አናሳ ብሔሮችን ለስልቀጣ፣ ለመፈናቃልና ለግድያ ይዳርጋል እያለ በብሔርተኝነት ላይ ትችቱን የሚያዘንበውን የገልነርን ዕሳቤ ለመጠቀም መሞከሩ ግራ አጋቢ ነው፡፡ ይህ አካሄድ የካርል ማርክስን መጽሐፍ እየጠቀሱ የካፒታሊዝምን ርዕዮት ለመደገፍ እንደመሞከር ይቆጠራል፡፡    

 መ. በአሁኑ ወቅት በገልነር ንድፈ ሐሳብ ላይ እየተሰነዘሩ ያሉ ሂሶች መበራከት 

ሌላው በሌሎቹም አገሮች ዛሬ ላይ ስለብሔርና ብሔርተኝነት ጽንሰ ሐሳቦች ካለን ግንዛቤ አንፃር የኤርነስት ገልነር የብሔር ንድፈ ሐሳብ ቅቡልነት አጠያያቂ ነው፡፡ ለዚህም መንስዔው በ1990ዎቹ መባቻ ከኮሚኒዝም ርዕዮተ ዓለም መፍረስና ከቀዝቃዛው ጦርነት ማክተም በኋላ የገልነርን ንድፈ ሐሳብ የሚገዳደሩ አያሌ ጥናቶች መበራከታቸው ነው፡፡ በእርግጥ ገልነር ከዚህ ዓለም እ.ኤ.አ. በ1995 በሞት ከመለየቱም አስቀድሞም፣ የብሔርተኝነት መርሁ በተለይም ብዝኃ ብሔር ለሆኑ አገሮች እንደማይሠራ በመግለጽ የተቃወሙ ምሁራን ወዳጆቹ ነበሩ፡፡ ምንም እንኳን ገልነር በዘመኑ በብሔርተኝነት ጽንሰ ሐሳብ ዙሪያ ያበረከተው አስተዋጽኦ የሚናቅ ባይሆንም ዛሬ ግን እጅግ ለቁጥር የሚታክቱ ምሁራን የገልነርን ንድፈ ሐሳብ ሲጋሩ አይስተዋሉም፡፡

ለምሳሌ ገልነር የብሔር ወጥነት (Homogenization) የሚመነጨው ከኢንዱስትሪ አብዮት ብቻ እንደሆነ ያስቀመጠው ዕሳቤ አሁን ቅቡልነት የለውም፡፡ ለዚህም በዋቢነት በካታላንና በባስክ ብሔርተኝነት ጥናቶቹ ዕውቅናን ያተረፈው ዳንኤሌ ኮንቬርሲ (ፕሮፌሰር) “Homogenisation, Nationalism and War: Should We Still Read Ernest Gellner?” በሚለው ጥናቱ፣ የብሔር መፈጠር የኢንዱስትሪ አብዮት ባይኖርም ከወታደራዊ መስፋፋቶች (Millitary Expansion) ሊመነጭ እንደሚችል አስምሯል (በጥናቱ ሌሎች የብሔርተኝነት ምንጮችም ተጠቅሰዋል)፡፡ እንዲሁም የኖርዌይ ተወላጁና የአንትሮፖሎጂ ሳይንቲስት ቶማስ ሃይላንድ ኢሪክሰን እ.ኤ.አ. በ2007 ዓ.ም. በታተመው “Ernest Gellner and Contemporary Social Thought” መጽሐፍ ምዕራፍ 7 ላይ የገልነር አስተሳሰብ ለብዝኃ ብሔር አገሮች ፈጽሞ ሊሆን እንደማይችል “Ernest Gellner and the Multicultural Mess” ርዕስ ሥር በስፋት ተንትኗል፡፡ በገልነር የብሔርተኝነት መርህ ላይ የተጻፉ ሂሳዊ ጥናቶችን በሙሉ በዚህ ጽሑፍ ላይ ዘርዝሮ መዝለቅ ስለማይቻል በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ንባብ ለመከወን ፍላጎቱ ላላቸው አንባቢያን ቀጥሎ የተዘረዘሩትን መጽሐፍት በዋቢነት ላስቀምጥ፡፡

 1. እ.ኤ.አ. በ1998 ዓ.ም. በአሥር ምሁራን በጣምራ የተዘጋጀው “The State of the Nation Ernest Gellner and The Theory of nationalism”
 2. እ.ኤ.አ. በ2007 በ13 ምሁራን የተዘጋጀው “Ernest Gellner and Contemporary Social Thought”
 3. እ.ኤ.አ. በ2010 በ15 ምሁራን የተዘጋጀው “After the Nation፡ Critical Reflections on Nationalism and Post Nationalism”
 4. እ.ኤ.አ. በ2004 ፖል ለውረንስ የታተመው “Nationalism History and Theory”
 5. እ.ኤ.አ. በ2017 ዳሌ ጄ ስታ ተደርሶ የታተመው “Analysis of Ernest Gellner’s Nations and Nationalism”

6 , እ.ኤ.አ. በ2017 በኡመት ኦዚከሪመሊ ተደርሶ የታተመው “Theories of Nationalism”

ከላይ ከተጠቀሱት ምሁራን በተጨማሪ በብሔርተኝነት ጥናት አንቱታን ያተረፉ ሌሎች ምሁራንም የገልነርን የብሔርተኝነት ንድፈ ሐሳብ የሚያሄሱ ጠለቅ ያሉ ጥናቶችን አድርገዋል፡፡ ከነዚህም ውስጥ ጆን ኤ ሃል፣ ጆን ብርዩሊ፣ አልፍሬድ ስቲፓን፣ ብሬንዳን ኦሊሪ፣ አለን ቡኬነን፣ ሮጀር ብሩባከር፣ ኤፍሬም ኒሚኒ፣ ሲንሳ ማሌሴቪቺ፣ ቶም ናሪን ወዘተ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

የክፍል አንድ ጽሑፌን ከማጠቃለሌ በፊት “One Culture – One State” ወይም “Nation-State Congreuency” ተብሎ የሚታወቀው የብሔርተኝነት መርህ ንድፍ ፈጣሪው ኤርነስት ገልነር እንዳልሆነ መጠቆም አስፈላጊ መስሎ ይታየኛል፡፡ በ1960ዎቹ እና በ1980ዎቹ ኤርነስት ገልነር እስትንፋሱን እፍ ብሎበት ነፍስ እንዲዘራ ያደረገው ይህ ዕሳቤ ሥጋና አጥንቱ በሌሎች ቀደምት አሳቢያን የተዋቀረው ከመቶ ዓመታት በፊት ነበር፡፡ ለምሳሌ ያህል ቀጥሎ የተዘረዘሩት የዘርፉ ጎምቱ አጥኚዎች ከገልነርም ቀድመው የብሔርተኝነትን መርህ በቀጥታም በተዘዋዋሪ ቀምረውት ነበር፡፡

 1. ፈረንሣዊው አማኑኤል ሲስ እ.ኤ.አ. በ1789 (ከገልነር ጋር ሲነፃፀር ከ194 ዓመታት በፊት)፣
 2. እንግሊዛዊው ፈላስፋና ፖለቲካል ኢኮኖሚስት ጆን ስቱዋርት ሚል እ.ኤ.አ. በ1862 (ከገልነር ጋር ሲነፃፀር ከ121 ዓመታት በፊት)፣
 3. እንግሊዛዊው የታሪክ ተመራማሪ ሎርድ አክተን በ1862 (ከገልነር ጋር ሲነፃፀር ከ121 ዓመታት በፊት)፣
 4. አሜሪካዊው ፈላስፋ የብሔርተኝነት ተመራማሪ ሃንስ ኮሂን እ.ኤ.አ. በ1944 (ከገልነር ጋር ሲነፃፀር ከ39 ዓመታት በፊት)፡፡

በአገር ደረጃ ደግሞ አቶ ጃዋር ዛሬ ያነሳውን የገልነርን “Nation-State Congreuency”ን መርህ በብዝኃ ብሔርነት ከኢትዮጵያም በበለጠ የምትታወቀው ህንድ እ.ኤ.አ. በ1887 ሞክራ ሳይሳካላት እንደ ቀረ ህንዳዊው ፕሮፈሰር “Rajev Bhargava” በ”Multinational Federalism: Problems and Prospects, 2012” መጽሐፍ ውስጥ የገለጸው እንደዚህ በማለት ነው፣ “In roughly a century before India achieved independence from British colonial rule, four conceptions of nationalism developed in the subcontinent. The first, succinctly articulated by Gellner, manifested the idea that a community bounded by a single culture must have its own sate.”

ከላይ እንደተጠቀሰው ህንድ ከነፃነቷ በፊት ከሞከረቻቸው አራት ዓይነት ብሔርተኝነት ውስጥ የመጀመርያው ገልነር ከመቶ ዓመታት በኋላ በንድፈ ሐሳብ ደረጃ ካዋቀረው ጋር የሚመሳሰል ነበር፡፡ በዚህም መሠረት የህንዱ እምነት ብሔርተኞች ህንድን ለመቅረፅ የሞከሩት ለራሳቸው በሚመች መልኩ ነበር፡፡ ከዚህም የተነሳ በህንድ የሚኖሩ ህንዳዊያን የሙስሊምና የክርስትና እምነት ተከታዮች እንደ ሁለተኛ ዜጋ ይቆጠሩ እንደነበር ራጄቭ በመጽሐፉ ውስጥ ከትቧል፡፡ በሒደት ግን ይህ ሌሎችን የሚሰለቅጠው ገልነራዊ የሆነው ብሔርተኝነት የህንድን አንድነት አደጋ ላይ በመጣሉ ውድቅ ሊሆን ችሏል፡፡    

  በክፍል ሁለት ጽሑፌ በአቶ ጃዋር ጽሑፍ ውስጥ የተስተዋሉትን ሌሎች ንድፈ ሐሳባዊ አቅጣጫዎችን አብረን እንመለከታለን፡፡ እንዲሁም የኦሮሞ የብሔርተኝነት ትግል አፈጣጠርንና ታሪካዊ ሒደትን በተመለከተ የሌሎች የኦሮሞ ብሔር ምሁራን (ለምሳሌ የፕሮፈሰር አሰፋ ጃለታና የዶ/ር መሐመድ ሐሰን) ዕይታዎች ከአቶ ጃዋር ጽሑፍ ይዘት ጋር ሲነፃፀሩ ምን ይመስላሉ? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ እንሞክራለን፡፡ ለማንኛውም እስካሁን ባደረኩት ዳሰሳ እንደ አቶ ጃዋር በአንድ ጽሑፍ ውስጥ በአመዛኙ አራት እርስ በርስ የሚጣረሱ ንድፈ ሐሳቦችን (Incoherent Theories) ተጠቅሞ ስለኦሮሞ ብሔርተኝነት ለመተንተን የሞከረ አንድም የኦሮሞ ምሁር አላጋጠመኝም፡፡ ዝርዝሩ በቀጣዩ ክፍል ሁለት ጽሑፍ ይቀርባል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው ecotra2009@yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡፡           

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *