በ ኢትዮዽያ ውስጥ የሚገኙ 32 ባንኮች አጠቃላይ የሀብት መጠን ከአራት ትሪሊዮን ብር በላይ ደርሷል።

በሒሳብ ዓመቱ አጋማሽ የሁሉም ባንኮች የተቀማጭ ገንዘብ መጠን 2.9 ትሪሊዮን ብር መድረሱ ተመላከተ
በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ዘርፍ እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ ባንኮች በዘንድሮው የሒሳብ ዓማት አጋማሽ በአብዛኞቹ ቁልፍ የባንክ ሥራ መመዘኛዎች ዕድገት እያሳዩ መሆናቸው ተመላከተ። የአገሪቱ ባንኮችን የ2017 ግማሽ የሒሳብ ዓመት አፈጻጸም እንደሚያሳየው፣ በገበያ ውስጥ የሚገኙ 32 ባንኮች አጠቃላይ የሀብት መጠን ከአራት ትሪሊዮን ብር በላይ ነው፡፡
ባንኮች ከደረሱበት አጠቃላይ የሀብት መጠን ውስጥ ብልጫ ያለውን ድርሻ የያዘው መንግሥታዊው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲሆን፣ የባንኩ አጠቃላይ የሀብት መጠን በ2017 ሒሳብ ዓመት አጋማሽ ላይ 1.97 ትሪሊዮን ብር መሆኑን ከመረጃው ለመረዳት ተችሏል። ቀሪው ደግሞ የግል ባንኮችና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ድርሻ ነው፡፡
በተቀማጭ ገንዘብ አሰባሰብ ረገድም የአገሪቱ ባንኮች የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ከ23 በመቶ በላይ ዕድገት አሳይቷል፡፡ በሒሳብ ዓመቱ ግማሽ ላይ የሁሉም ባንኮች አጠቃላይ ተቀማጭ የገንዘብ (ከወለድ ነፃን ጨምሮ) ከ2.9 ትሪሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡ ከዚህ ውስጥ በኢንዱስትሪው ከፍተኛውን የተቀማጭ ገንዘብ በማሰባሰብ ቀዳሚውን ድርሻ የያዘው መንግሥታዊው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲሆን ከግል ባንኮች ደግሞ አዋሽ ባንክ በቀዳሚነት ተቀምጧል፡፡ በ2017 የሒሳብ ዓመት በግማሽ ዓመት አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘቡ መጠን 1.42 ትሪሊዮን ብር ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ በመደበኛው የባንክ አገልግሎት ያሰባሰበው ተቀማጭ ገንዘብ መጠን 1.21 ትሪሊዮን ብር ነው፡፡ ቀሪው 152.5 ሚሊዮን ብር ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ያሰባሰበው መሆኑን የባንኩ መረጃ ያመለክታል፡፡
ከግል ባንኮች ደግሞ ከፍተኛ መጠን ያለው ተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ የቻለው አዋሽ ባንክ ሲሆን፣ እስከ ሒሳብ ዓመቱ አጋማሽ ድረስ ያሰባሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ከ253 ቢሊዮን ብር በላይ ነው፡፡ ከግል ባንኮች ሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው አቢሲኒያ ባንክ ሲሆን፣ የባንኩ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ከ220 ቢሊዮን ብር በላይ መሆኑን መረጃው ያመለክታል፡፡ ዳሸን ባንክም ከፍተኛ የተቀማጭ ገንዘብ በማሰባሰብ የሚጠቀስ ሲሆን በግማሽ ዓመቱ መጨረሻ ላይ የደረሰበት የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ከ166.7 ቢሊዮን ብር በላይ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
ከፍተኛ ተቀማጭ ገንዘብ ካሰባሰቡት የግል ባንኮች መካከል በቀጣይነት የተቀመጠው የኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ ሲሆን፣ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ከ130 ቢሊዮን ብር ማሰባሰብ ችሏል።
ከላይ የተጠቀሱት አራቱ የግል ባንኮች በተጨማሪ ሌሎች ስምንት የግል ባንኮች እያንዳንዳቸው የተቀማጭ ገንዘብ መጠናቸውን ከ40 ቢሊዮን ብር በላይ ማድረስ እንደቻሉ መረጃው ያመለክታል። ከስምንቱ ባንኮች ውስጥ ኅብረት ባንክ በግማሽ ዓመቱ መጨረሻ ላይ የደረሰበት የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ከ80.6 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ቀሪዎቹ ሰባት ባንኮች ደግሞ ኦሮሚያ ባንክ 63.9 ቢሊዮን ብር፣ ዓባይ 61.7 ቢሊዮን ብር፣ ወጋገን ከ58.15 ቢሊዮን ብር በላይ፣ ዘመን ባንክ 52.72 ቢሊዮን ብር፣ ንብ ባንክ ከ48.9 ቢሊዮን ብር በላይ፣ ቡና ባንክ ከ46.7 ቢሊዮን ብር በላይ፣ አንበሳ ባንክ ከ40 ቢሊዮን ብር በላይ የተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ ችለዋል፡፡
ሁሉም ባንኮች እስከ ግማሽ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ የሰጡት የተከማቸ የብድር መጠን (ቦንድን ጨምሮ) ከ2.8 ትሪሊዮን ብር በላይ የደረሰ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 1.32 ትሪሊዮን ብሩ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ድርሻ መሆኑ ተጠቀሟል።
በኢንዱስትሪው ውስጥ አሁንም ዕድገት እየታየበት የመጣው የባንክ ደንበኞች ቁጥር ነው፡፡ እስከ ግማሽ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ በሁሉም ባንኮች የተቀማጭ ሒሳብ የከፈቱት ደንበኞች ቁጥር ከ172 ሚሊዮን በላይ መድረሱ ተመላክቷል፡፡ በዚህም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብልጫ ያለውን ድርሻ የያዘ ሲሆን በግማሽ ዓመቱ መጨረሻ ላይ አጠቃላይ የደንበኞቹን ቁጥር 41.38 ሚሊዮን ማድረስ ችሏል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከደረሰበት 41.38 ሚሊዮን ደንበኞች ውስጥ 34.57 ሚሊዮን የሚደርሱት የመደበኛው የባንክ አገልግሎት ደንበኞች ሲሆኑ ቀሪዎቹ 6.81 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚዎች የከፈቱት አካውንት መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
የግል ባንኮችም የደንበኞቻቸው ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እየጨመሩ ሲሆን የደንበኞቻቸውን ቁጥር ከአንድ ሚሊዮን በላይ ማድረስ የቻሉ ባንኮች ቁጥር 14 መድረሱን መቻሉን ለማወቅ ተችሏል፡፡ እስከ ግማሽ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ 14ቱን ባንኮች የደንበኞቻቸውን ቁጥር ከ1.12 ሚሊዮን እስከ 14.2 ሚሊዮን በላይ ማድረስ የቻሉ ናቸው፡፡ በኢንዱስትሪው ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቀጥሎ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ደንበኞች የያዘው የኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ በ2017 የሒሳብ ዓመት ግማሽ ዓመት መጨረሻ ላይ አጠቃላይ የደንበኞችን ቁጥር 14.2 ሚሊዮን ማድረስ ችሏል፡፡ ይህም ከግል ባንኮች ከፍተኛ ቁጥር ያለው ደንበኞችን በመያዝ ለተከታታይ ዓመታት ቆይቷል፡፡
ዘንድሮ ለየት ባለ ሁኔታ ባንኮች የውጭ ምንዛሪ ግኝታቸውን ከፍ ያደረጉበት ዓመት እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡ በሒሳብ ዓመቱ በግማሽ ዓመት ውስጥ የግል ባንኮች ከ3.3 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ያስመዘገቡ ሲሆን በዚህ የውጭ ምንዛሪ ግኝትም በኢንዱስትሪው የቆዩ ትልልቅ ባንኮች ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ስለመቻላቸው ተመልክቷል፡፡
በግማሽ ዓመቱ ከግል ባንኮች ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሪ ግኝት ያስመዘገበው አዋሽ ባንክ ሲሆን በግማሽ ዓመት ውስጥ ብቻ ከ390.1 ሚሊዮን ዶላር አግኝቷል፡፡ ዳሸን ባንክ 548 ሚሊዮን ዶላር፣ አቢሲኒያ ባንክ 317 ሚሊዮን ዶላር ዘመን ባንክ 270 ሚሊዮን ዶላር በማስመዝገብ በተከታታይ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡
በግማሽ ዓመቱ የውጭ ምንዛሪ ግኝታቸውን ከ50 ሚሊዮን ዶላር በላይ ካደረሱት መካከል የኦሮሚያ የኅብረት ሥራ፣ ኦሮሚያ ባንክ፣ ወጋገን ባንክ፣ ኅብረት ባንክ፣ ዓባይ ባንክ፣ ብርሃን ባንክ፣ ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ ባንክ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ከኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ ቀጥሎ በርካታ የተቀማጭ ሒሳብ ደንበኞች የያዘው አቢሲኒያ ባንክ ሲሆን በግማሽ ዓመቱ መጨሻ የደንበኞቹ ቁጥር 13.92 ሚሊዮን መድረሱ ታውቋል፡፡ ቀጣዩን ደረጃ የያዘው አዋሽ ባንክ ሲሆን 13.3 ሚሊዮን ደንበኞችን መያዝ የቻለ ሲሆን በቅርቡ ከብድርና ቁጠባ ተቋማት ወደ ባንክ የተሸጋገረው ፀደይ ባንክም ከ14 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች እንዳሉት ሪፖርት አድርጓል፡፡ ፀደይ ባንክ የደንበኞቹ ቁጥር በዚህን ያህል ደረጃ ሊመዘገቡ የቻሉት በብድርና ቁጠባ ተቋም ሆኖ በሚሠራበት ወቅት ያሉትን ደንበኞች በሙሉ ወደዚህ በማዞሩ እንደሆነ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡
የደንበኞቻቸውን ቁጥር ከአራት ሚሊዮን በላይ በማድረስ ተጠቃሽ የሆኑት ባንኮች ኅብረት፣ ዓባይ፣ ወጋገን፣ ንብ፣ ቡና፣ ኦሮሚያና ዳሸን ባንክ ተጠቃሽ ሲሆኑ በተለይ ዳሸን ባንክ በግማሽ ዓመቱ መጨረሻ 7.34 ሚሊዮን ኦሮሚያ ባንክ ደግሞ 6.35 ሚሊዮን በማድረስ ይጠቀሳሉ፡፡
ከባንኮች የቅርንጫፎች ማስፋት ጋር በተያያዘ ግን ከዚህ ቀደም ይታይ የነበረው ያህል ዕድገት እያሳየ አፈጻጸም እየመዘገበ ስላለመሆኑ እየተነገረ ነው፡፡ በግማሽ ዓመቱ ባንኮች አዳዲስ ቅርንጫፎች የከፈቱና አጠቃላይ ባንኮች ያሏቸው የቅርንጫፎች ብዛት ከ12,200 በላይ የደረሰ ቢሆንም ይህ የቅርንጫፎች ቁጥር ዕድገት በቀደሙት ዓመታት ሲታይ በነበረው ልክ ዕድገት ያላሳየ ነው ተብሏል፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የባንክ ባለሙያ ለሪፖርተር እንደገለጹት ብዙ ባንኮች በተለይ ትልልቅ የሚባሉ ባንኮች የቅርንጫፍ ከፍታቸውን ገታ በማድረግ በዲጂታል የባንክ አገልግሎቶች ወደማስፋፋት መግባታቸው አንዱ ምክንያት ነው፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያሉ ደግሞ አንዳንድ ቅርንጫፎችን በማጠፍ እየሠሩ መሆኑንም የባንኮች የቅርንጫፎች ዕድገት አዝጋሚ ሆኖ እንዲታይ አድርጎታል ይላሉ፡፡ ወደፊትም ይህ ሁኔታ የሚቀጥል መሆኑንም ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡
የአገሪቱ ባንኮች በተናጠል እያሳዩ ያሉት ዕድገት የተለያየ ሆኖ መቀጠሉ እንዴት ይታያል ለሚለው ጥያቄ የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ አወት ተክኤ በሰጡት አስተያየት አፈጻጸማቸው አነስተኛ የሆኑ ባንኮች የተሻለ ዕድገት ለማስመዝገብ የተለያዩ አማራጮችን መጠቀም ይኖርባቸዋል፡፡
በተለይ ካፒታላቸው አነስተኛ የሆኑ ባንኮች ካፒታላቸውን ለማሳደግ በሌሎች አገሮች እንደሚደረገው አንዱ መፍትሔ ባለአክሲዮኖቻቸውን አሳምነው ካፒታላቸውን ከፍ ማድረግ ነው፡፡
ይህ ውሳኔ በሌሎች እንዳይዋጡ የሚያደርግ ሲሆን ከውጭ ባንኮች ጋር በጥምረት ለመሥራት ዕድል እንደሚፈጥርላቸው አክለዋል፡፡ ሌላው ዝቅተኛ አፈጻጸም አላቸው የሚባሉ ባንኮች በገበያው ለመቆየት እንደ አማራጭ ማየት የሚገባቸው ስፔሻላይዝድ የሆነ አገልግሎት የሚሰጥ ባንክ ማድረግ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ሁሉም የንግድ ባንኮች ተመሳሳይ ሥራ የሚሠሩ በመሆኑ ከዚህ ዓይነት አመለካከት ወጥተው ስፔሻላይዝድ የሆነ ባንክ ወደ መሆን ቢሸጋገሩ በገበያው መቆየት ብቻ ሳይሆን የተሻለ አትራፊ ሆነው የሚቀጥሉበት ዕድል እንዳለ አቶ አወት ያመለክታሉ፡፡
በባንኮች መካከል እየታየ ያለው ልዩነት ግን ለምን ተፈጠረ የሚለውን በደንብ ማየት የሚጠይቅ መሆኑን የገለጹት አቶ አወት የውስጥ ፖሊሲን በመፈተሽ ይህ ለምን ሆነ ለሚለው ጥያቄ መልስ በመስጠት የሚመለስ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አፈጻጸማቸው ዝቅ ማለት ግን ባንኮቹን ከኢንዱስትሪው ውስጥ እንዲቆዩ አያደርጋቸውም፡፡ አካሄዳቸውን እስካስተካከሉ ድረስ በውይይት የተሻለ ውጤት ሊያመጡ የሚችሉበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡ የውጭ ባንኮች በመግባታቸውም የሚጎዱበት ነገር ስለሌለ እስካሁን የመጡበትን መንገድ በመፈተሽ ወደፊት እንዴት ልናድግ እንችላለን የሚለው ላይ ሊሠሩ ይገባል ብለዋል፡፡
ይህ ካልሆነ ግን አነስ ያሉ ባንኮች በትልልቆቹ ሊዋጡበት የሚችሉበት ዕድል ሊኖር እንደሚችልም ጠቁመዋል፡፡
Source: ethiopianreporter.com