በዝቅተኛ ኑሮ ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን በኮቪድ-19 ምክኒያት ለከፍተኛ ችግርና የማህበራዊ ቀውስ ተዳርገዋል።
የኮቪድ -19 ወረርሽኝና ወረርሽኙን ለመከላከል የተወሰዱ እርምጃዎች በዝቅተኛ ኑሮ ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ለከፍተኛ ችግርና የማህበራዊ ቀውስ መዳረጉን “የረሃብ ቅድመ ማስጠንቀቅ ግንኙነት መረብ” የተሰኘ የአሜሪካ መንግስታዊ የጥናት ተቋም ያወጣው ሪፖርት አመለከተ፡፡
ኮሮና ቫይረስ ባለፈው መጋቢት ወር በኢትዮጵያ መታየቱን ተከትሎ መንግስት የበሽታውን ወረርሽኝ ለመግታት የወሰዳቸው የእንቅስቃሴ ገደቦች በርካቶችን ለችግርና ለማህበራዊ ቀውስ ዳርጓል ብሏል የተቋሙ ጥናት፡፡
ለበርካቶች የቀን ገቢ ያስገኙ የነበሩ ሆቴሎች፣ የምሽት መዝናኛዎች፣ ት/ቤቶች ከስራ ውጪ መሆናቸው እንዲሁም በከተሞች ለአያሌዎች የስራ እድል የሚፈጥሩ የኮንስትራክሽን ስራዎች መቀዛቀዝ ብዙዎችን ለችግር መዳረጉንና የሚበሉት በማጣት ለረሃብ የተዳረጉም መኖራቸውን ጥናቱ ጠቁሟል፡፡
የእንቅስቃሴ ገደቦች መጣላቸው በገጠር የግብርና እንቅስቃሴና በገጠሩ ማህበረሰብ ኑሮ ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳረፉንም ሪፖርቱ ያትታል::
የንግድ ተቋማት የግብርና ግብአቶች በተፈለገው መጠን አለማቅረባቸው፣ አርሶ አደሩም ራሱን ከእንቅስቃሴ ማቀቡ የመኸርና የበልግ ግብርና ስራዎች የተፈለገውን ያህል እንዳይሆኑ አድርጓል ያለው ሪፖርቱ፤ ግጭቶችና የበረሃ አንበጣም በግብርና እንቅስቃሴው ላይ ተጽእኖ ማሳረፉን አመልክቷል፡፡
የድንበሮችን መዘጋትና የውስጥ እንቅስቃሴ ገደቦች በተለይ ከሚያዚያ እስከ ሰኔ ወደ ሱዳን በማቅናት በተለያዩ የግብርና የጉልበት ስራ ላይ ተሠማርተው ገቢ ያገኙ የነበሩ የትግራይና አማራ ክልል ወጣቶችንም በእጅጉ መጉዳቱና ማህበራዊ ቀውስ መፍጠሩን ሪፖርቱ ጠቁሟል::
በሀገር ውስጥም በአዋሽ ተፋሰስ ስር ይከናወኑ የነበሩ ሰፋፊ የመስኖ እርሻዎች ላይ የእንቅስቃሴ ገደቡ ተጽእኖ ማሳደሩንና በተጨማሪም በመተማ፣ ሁመራና በደቡብ ክልል በሚከናወኑ ሰፋፊ የግብርና ስራዎች ላይ ተጽእኖው የከፋ እንደነበር ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡ በዚህም በቀጣይ አመት ሀገሪቱ ለምርት እጥረት ልትጋለጥ እንደምትችልና ከወዲሁ በአንዳንድ የምግብ ሸቀጦች ላይ የዋጋ ጭማሪ መታየቱም የዚሁ ውጤት መሆኑን ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
በተጨማሪም በተለያዩ የአለም ሀገራት በኮቪድ 19 ምክንያት እንቅስቃሴዎች ለወራት መገደባቸውን ተከትሎ፣ ከውጭ ቤተሰቦቻቸው ገንዘብ ይላክላቸው የነበሩ የገጠርና ከተማ ነዋሪዎችም ለገቢ ማሽቆልቆል መዳረጋቸውን ሪፖርቱ ይገልፃል፡፡ መንግስትም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ማጣቱ ተጠቁሟል፡፡
ችግሩን ለመቋቋም መንግስት ከወዲሁ የተለየ ስልት ነድፎ በቀጣይ አመት እንዲንቀሳቀስ ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡