0 0
Read Time:2 Minute, 18 Second

ከ የኢትዮጵያ ዘውዳዊ ጉባኤ (ERC) የተሰጠ መግለጫ

ዕለተ ሃሙስ፣ መስከረም ፯ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም

በመተከል ዞን ከሰማኒያ በላይ ክርስቲያን አማራ/አገው ኢትዮጵያውያን ዘርንና እምነትን ኢላማ ባደረገ ጥቃት መገደላቸውን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ዘውዳዊ ጉባኤ መሪር ሐዘኑን ይገልጻል።

ኦሮሚያ በሚባለው ክልል መሰል የዘር ማጥፋት እና ፀረ ሃይማኖታዊ ጥቃቶች ሲፈጸሙ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማትን ጨምሮ ድርጊቱ ጄኖሳይዳዊ ተግባር መሆኑን በማሳወቅና ጠቅላይ ሚኒስትሩና የብልጽግና ፓርቲአቸው ጥቃቱን የሚፈጽሙን ኃይላት የመታገልና አገርንና ሕዝብን የመከላከል አንዳች ፍላጎት ያላቸው ከሆነ ጭፍጭፋ በሚፈጸምባቸው ቦታዎች ንጹሃንን ከገዳይ ኃይላት የሚከላከል ሠራዊት ማሰማራት እንዳለባቸው በተደጋጋሚ የተነገራቸው መሆኑ እሙን ነው። ነገር ግን በአዲስ አበባ ከተማ እና በተለያዩ ቦታዎች ለሕዝብ እይታ በሚተላለፉ መንግሥታዊ ትርኢቶች ታጥቆ የሚታየው ሠራዊት ንጹህ ዜጎችን የሚገድሉን አሸባሪ ኃይላት ታግሎና ንጹሃኑን ከጥቃት ተከላክሎ ሲያድናቸውና ሕግን ሲያስከብር ሕዝብ እያየ አይደለም። ሕዝብም ስለ ፍትሕ ወደ ፈጣሪው እየጮኸ ይገኛል። ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድና የብልጽግና ፓርቲአቸው ወንጀሉ በሚፈጸምባቸው ቦታዎች ሠራዊት በማሰማራት ዘርንና እምነትን ኢላማ አድርገው ጭፍጨፋ ከሚፈጽሙ አካላት ሕዝቡን መከላከልና ንጹሃን ዜጎችን መታደግ የማይፈልጉት ለምንድር ነው?

ሕዝብ ተስፋ የጣለበት አገዛዝ ባለበት ማንነትን እና እምነትን ኢላማ ያደረገ ጄኖሳይዳዊ ጥቃት መፈጸሙ ሕዝብ በአገዛዙ ላይ ተስፋ ቆርጦ የሞት ሽረት ትግል ውስጥ እንዲገባ እየገፋፋው ይገኛል። ጠቅላይ ሚኒስትሩና በሥልጣን ላይ የሚገኘው የብልጽግና ፓርቲአቸው በኢትዮጵያም ሆነ በውጩ ዓለም ያላቸውን ተቀባይነት የሚያጡም ብቻ ሳይሆን ሕዝብ በአሸባሪ ኃይላት ዘር እና ሃይማኖት ላይ ያነጣጠሩን ጥቃቶች እያስተናገደ ገዳዮቹን የማያስጥል፣ አልፎም ፊቱን በማዞርም ሆነ በተለያዩ መንገዶች የሚተባበራቸውን መንግሥት እንደ መንግሥት ተቀብሎ ለመቀጠል የሚያስችል ትዕግስትም ሆነ የሥነ ልቡና አቅም የማይኖረው መሆኑን ተገንዝበው፣ አስፈላጊ የሆኑን እርምጃዎች ሁሉ የመውሰድ ፍላጎትና ትኩረት የሌላቸው ከሆነ ትግላቸው ከሕዝቡ ጋር እንደሚሆንና ወደፊትም በዝምታቸውና በሥራቸው ከተጠያቂነት እንደማያመልጡ በፈሪሃ እግዚአብሔር ያስቡበት ዘንድ እናስጠነቅቃለን።

የአማራ ብልጽግና ተብሎ የሚጠራው የቀድሞው ብአዴንና አዴፓ ከሚያስተዳድረው ክልል ውጭ፣ በተለይ በኦሮሚያ እና በቤኒሻንጉል ክልሎች፣ ተበትኖ እና በጠባቂ አልባነት ስለሚኖረው አማራ/አገው ከሚያስተዳድሩት ክልል ውጭ በመሆኑ ብቻ ውክልና እንደሌላቸው በማመካኘትና ሕዝቡ በጠባቂ አልባነት በማንነቱና በእምነቱ ምክኒያት ችግር በተፈጠረ አጋጣሚ ሁሉ እየታደነ ባሰቃቂ ሁኔታ ሲገደል ማንነቱን በመካድ፣ በማዕከላዊ መንግሥትና በተጠቀሱት ክልሎች አመራሮች ላይ አስፈላጊውን ተጽእኖና ተገቢውን ግፊት ከማድረግ ይልቅ ወንጀሉ እንዲፈጸም የፈቀዱን አመራሮች በመተባበርና በመሸለም፣ ካባ አልብሶም በማክበር ሕዝቡን ክፉኛ አሳዝነውታል። የቀድሞው ብአዴንና አዴፓ የአማራ ብልጽግና አመራሮች በሥሙ የወከሉትን ሕዝብ በተጣለባቸው የሥልጣን ሃላፊነት ከዘር ማጥፋት ጥቃት መከላከልም ሆነ በማዕከላዊው መንግሥትና በተጠቀሱት ክልሎች አመራሮች ላይ አስፈላጊውን ተጽእኖ ከማድረግ ይልቅ በሥም የወከሉትን ሕዝብ ለአደጋ ተጋላጭ አድርገው የሚያስጠቁትን አካላት ለምን መተባበርን መርጠው ፊታቸውን ከሕዝቡ አዞሩ?

ይህን ሕዝብ በቁስሉ ላይ እንጨት መስደድ የሥልጣንን እድሜ ቢያሳጥር እንጅ አያረዝምምና የድርጊታቸውን ክፋት ተገንዝበውና ክፉኛ ተጸጽተው ለሕዝቡ ባይሆን ለራሳቸው ህልውና በፈሪሃ እግዚአብሔር ራሳቸውን አርመው ተገቢውን ሁሉ የሃላፊነታቸውን እርምጃ ይወስዱ ዘንድ እናስጠነቅቃለን።

ጊዜ የሚፈጅ ቢሆንም፣ ሐቀኛው ሕዝብ ለዘመናት የናፈቀውን ፍትሕ፣ ሰላምና እኩልነት በፈጣሪው እገዛ እና በፅኑ ትግል አምጦ የሚወልደው መሆኑ ለጥርጥር የሚውል አይደለም። የትኛውንም የሕዝብ አካል ሳይጎዱና ለይተው ሳይጠቅሙ ሕጋዊና ፍትሐዊ አስተዳደርን ማስፈን ላገርም ሆነ ለሕዝብ፣ እንዲሁም ለማንኛውም አይነት መንግሥት የህልውና መሰረታዊ ግብ ነው። የሕዝብን በሕይወት የመኖር መሰረታዊ መብት ማክበርና ማስከበር የማይፈልግ አገዛዝ ግን እድሜ ሊኖረው እንደማይችል እያሳሰብን በኢትዮጵያ አምላክ ፊት ለሚመለከታቸው ሁሉ ይህን መልዕክት አስተላልፈናል።

አግርር ፀሮ ታሕተ እገሪሁ

የኢትዮጵያ ዘውዳዊ ጉባኤ

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *