ኢሰመኮ ወደ አዲስ አበባ በሚገቡ መንገደኞች ላይ ደረሰ የተባለውን በደል እያጣራሁ ነው አለ::

0
0 0
Read Time:3 Minute, 41 Second

በየኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከሰሞኑ ከአማራ ክልል በደብረ ብርሃን በኩል ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙ ተሳፋሪዎች ወደ ከተማዋ እንዳይገቡ በመታወቂያ ተለይተው እንደተከለከሉና እንግልት እንደተፈጸመባቸው የተገለጸውን የመብት ጥሰት እያጣራሁ ነው አለ፡፡

የኮሚሽኑ የሲቪልና ፖለቲካ መብቶች ኮሚሽነር አብዲ ጂብሪል (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በተጠቀሰው አካባቢ ተከስቷል የተባለውን የመብት ጥሰት የሚያጣራ ቡድን ወደ አካባቢው መላኩን ገልጸዋል፡፡

በቀጣይ የምርመራ ቡድኑ የተፈጠረውን ሁኔታ ተከታትሎ ካጣራ በኋላ የደረሰበትን መግለጫ እንደሚሰጥ አብራርተዋል፡፡

ካለፉት ጥቂት ሳምንታት ወዲህ ከአማራ ክልል በተለይም ከሰሜን ወሎና ደቡብ ወሎ አካባቢዎች በደብረ ብርሃን በኩል አልፈው ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙ ዜጎች፣ በፀጥታ አካላት አማካይነት መታወቂያቸው እየታየና እየተመረጠ፣ የአዲስ አበባ መታወቂያ ያልያዙትን ወደ መጡበት እንዲመለሱ እየተደረጉ መሆኑንና በደል ተፈጸመብን ያሉ ዜጎችን አነጋግሮ ሪፖርተር ዘገባ መሥራቱ ይታወሳል፡፡

በዜጎች ላይ የመብት ጥሰት ተፈጸመ የተበላውን ሁኔታ አስመልክቶ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ኃይለ ማርያም፣ የመንግሥት አካላት ሁኔታው ከፀጥታ ጉዳይ ጋር የተገናኘ መሆኑን ቢገልጹም፣ በማንኛውም ዓይነት መልኩ ዜጎች በአገራቸው ውስጥ ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ ነፃነታቸውን በዚህ ደረጃ በሚያውክ መልኩ የሚፈጸም ዕገዳ ሕገ መንግሥቱን የሚጥስ ነው ብለዋል፡፡

አክለውም ተፈጸመ የተባለው ተግባር የዜጎችን አገራቸው ውስጥ የመዘዋወርና የመንቀሳቀስ እንዲሁም ወደፈለጉት ቦታ የመሄድና የመኖር መብትና ነፃነት የሚጥስ አሠራር ከመሆኑም በላይ ከዚህ በዓለም አቀፍ ሕግ ኢትዮጵያ የፈረመቻቸውን ስምምነትም የሚጥስ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

አገሪቷ አሁን የገባችበትን የፀጥታ ችግር ግምት ውስጥ በማስገባት ከአገር ደኅንነት ጋር የተያያዘ ሥጋት መኖሩ ቢረጋገጥ እንኳ ሊደረግ የሚገባው ነገር ሥርዓት ባለው መልኩ የዜጎችን መብትና ነፃነት የጠበቀ የፍተሻ አሠራር ሊዘረጋ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ሽማግሌዎች፣ እናቶችና ሕፃናት ወደ መንግሥቱ መቀመጫና የአገሪቱ ዋና ከተማ ወደ ሆነችው አዲስ አበባ ለተለያዩ ዓላማዎች ዜጎች ለፍርድ ቤት ቀጠሮ፣ ለሕክምና፣ ለትምህርትና ሌላ ሥራ እንዲሁም ቤተሰብ ለመጠየቅ ሊንቀሳቀሱ የሚችሉ ሰዎችን አደጋ ላይ መጣልና ለእንግልት መዳረግ ከሕግ ውጪ የሚደረግ አሠራር መሆኑን አቶ ያሬድ አስረድተዋል፡፡

በተለይም መታወቂያ ብቻ እያዩ መመለስና ማንነትን መሠረት አድርጎ የተወሰኑትን ለይቶ ወደመጡበት መላክ ከመንግሥት በኩል ‹‹ከደኅንነት ሥጋት አንፃር ነው›› በሚል የቀረበውን ምክንያት ውድቅ ያደርገዋል ብለዋል፡፡

‹‹ከደሴ የሚመጡ ሕፃናት፣ አረጋውያንና እናቶች ለአገሪቱ በምን መልኩ ሥጋት ሊሆኑ ይችላል? ይህ ትልቅ የመብት ጥሰት በመሆኑ የመንግሥት አካላት በተለይ ደግሞ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ይህን ዕገታ እንዲያቆሙ እኛም በተለያየ መልኩ እየጎተጎትን ነው፤›› ብለዋል፡፡

ይህ ጉዳይ በሁለት መንገይ አደጋ እንዳለው የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ አንደኛው፣ ከሆነ አካባቢ ብቻ የሚመጡ ሰዎችን በመታወቂያ እየለዩ ለደኅንነት በሚል መመለስ አሠራሩ ትክክለኛ የሆነ አለመሆኑን የሚያሳይ ሲሆን፣ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ዜጎች በገዛ አገራቸው የባዳነትና የመገለል ስሜት እንዲሰማቸው ምክንያት ይሆናል፡፡ ያ ደግሞ ዜጎችን ወደ ሌላ አላስፈላጊ የሆነ ግጭትና የፖለቲካ ቅራኔ እንደሚፈጥር አስረድተዋል፡፡

በተመሳሳይ አገሪቱ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች እየተከሰተ ያለውን ግጭት ፈርቶ አንድ ሰው አዲስ አበባ ቢመጣ መብቱ አይደለም ወይ? ባለበት አካባቢ የመንግሥት አካላት ጥበቃ አድርገውለት ሕይወቱን ካልታደጉለት ወደ ዋና ከተማ መጥቶ ሕይወቴን ልታደግ ቢል የአንድ ኢትዮጵያዊ መብት ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡

እንደዚህ ዓይነት ነገር ተደርጎ አያውቅም እንዲያውም በተለያዩ ጊዜያት ጦርነት በነበረበት ወቅትና ሥጋት ሲኖር አገሪቱን አደጋ ላይ ይጥላሉ የሚባሉ አካላት ወደ መሀል ከተማ እንዳይገቡ ፍተሻ ይደረግ ነበር፡፡ ነገር ግን አሁን እንደሚደረገውና መታወቂያ እያዩ የመመለስ ተግባር እንዳልነበር አስረድተዋል፡፡

የፌዴራል መንግሥቱ የአገሪቷን ሕዝቦች የሚያገናኙ ዋና ዋና መስመሮች የመቆጣጠር ሥልጣን ያለው በመሆኑ እነዚህ ቦታዎች ላይ የፌዴራል አካላት እንጂ እያንዳንዱ ክልል በየፈሠሩ ኬላ እየሠራ እከሌ ያልፋል እከሌ አያልፍም የሚል ከሆነ የአገሪቱን ደኅንነት አደጋ ላይ እንደሚጥል አሳስበዋል፡፡



በመሆኑም ክልሎች እንዲህ ዓይነት ከልክ ያለፈ የመቆጣጠር ሥልጣን ሊሰጣቸው አይገባም ያሉት አቶ ያሬድ ይህ አካሄድ የፌዴራል መንግሥቱን ሥልጣን ጭምር የሚጋፋ በመሆኑ እንደዚህ ዓይነቱ አካሄድ ሕገ መንግሥቱን አለፍ ሲልም ሰብዓዊ መብትን የሚጥስ አሠራር በአጭሩ መቆም ካልቻለ ነገም ሌላው ክልል ተነስቶ በዚሁ ተግባር ሊሰማራ እንደሚችልና አላስፈላጊ ግጭት የፈጸሙትን የክልል አካላት በሕግ ተጠያቂ መደረግ አለባቸው፡፡

ዜጎችን መፈተሹ አግባብ ቢሆንም በተደጋጋሚ ቅሬታ እየተፈጠረ ሲታይ የእነዚህ ተሳፋሪዎችን ማንነት ማጣራት ካስፈለገ ከመነሻው ጀምሮ በመለየት እንዳያልፉ ማድረግ ሲገባ ገና ለገና በዚህ አቅጣጫ ሕወሓት ሊመጣ ይችላል በሚል ሥጋት ሰዎችን ማባሪያ ለሌለው እንግልት ማጋለጥ ትክክል አይደለም ብለዋል፡፡

ደኅንነት የማጣራት ሥራውን መሥራት ተገቢ ቢሆንም የሰዎችን በመንግሥትና የመንግሥት ተቋማት ላይ ያላቸውን እምነት ሊሸረሽር የሚችል ችግር በመሆኑ ጉዳዩ የፖለቲካ መፍትሔ እንደሚስፈልገው አብራርተዋል፡፡

ነገር ግን በዚህ ሁሉ መሀል ሰርገው የገቡ ካሉና ለሥጋት የዳረጉ አካላት ተገኝተው ከሆነ እንደ ማስረጃ መቅረብ አለበት እንጂ በደፈናው በዚህ አቅጣጫ ይመጣሉ በሚል ሥጋት ብቻ ሕዝብን ማንገላታት ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

የመብት ተሟጓጋቹና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ኅብረት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሱድ ገበየሁ በበኩላቸው የአዲስ አበባን ወይም ሌላውን አካባቢ ሰላም ለማረጋገጥ የሚደረገው ሥራ ምንም ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ባይሆንም ዜጎች ማንነታቸውን የሚገልጽ መታወቂያ ይዘውና ከየት ተነስተው የት እንደሚያርፉ የሚታወቁ ከሆነ ማንገላታት ከሕግ ውጪ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም በተጠቀሰው መስመር ወደ አዲስ አበባ የሚመጡት ዜጎች ለሕክምና፣ ለትምህርት ወይም የተለያዩ ዓላማዎች ከመሆኑም በላይ አንድ አገር ውስጥ እየተኖረ በዚህ ደረጃ ከአንዱ ክልል ወደ ሌላው ክልል እንዳይንቀሳቀስና ዜጎችን በማንነት ላይ የምትከታተል ከሆነ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል ብለዋል፡፡

ለችግሩ በአስቸኳይ መፍትሔ መሰጠት እንዳለበት ያሳሰቡት አቶ መሱድ ችግሩ ካልተፈታ በክልሎች መካከል ያለውን የወንድማማችነት ስሜት በጣም የሚያደበዝዝ ሰለመሆኑም አስረድተዋል፡፡

በመሆኑም ሰላማዊ ተሳፋሪን ወደ መጣበት እንዲመለስ ማድረግ ትክክለኛ የመንግሥት ሥራ ያልሆነና ኢሕገ መንግሥታዊ ተግባር ስለመሆኑም ተናግረዋል፡:

source:https://www.ethiopianreporter.com/

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *