ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙ በርካታ ሰዎች ወደ ከተማዋ እንዳይገቡ በፖሊስ መከልከላቸውን ገለጹ

0
0 0
Read Time:4 Minute, 32 Second

‹የኦሮሚያ ክልል መፍትሔ እንዲሰጥበት አሳውቀናል›› 

የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ

‹‹ጉዳዩ ከሽብር ቡድን ሰርጎ ገቦች ጋር የተያያዘ ነው›› 

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት

ከአማራ ክልል በተለይም ከሰሜን ወሎና ደቡብ ወሎ በደብረ ብርሃን አቋርጠው ወደ አዲስ አበባ ለመግባት በአገር አቋራጭ ተሽከርካሪ የሚጓዙ ተሳፋሪዎች፣ ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡና ወደ መጡበት እንዲመለሱ መደረጋቸውን ተሳፋሪዎችና የአማራ ክልል መንግሥት አስታወቁ፡፡

ባለፈው ሳምንት ለተከታታይ ቀናት ሪፖርተር ያነጋገራቸውና የችግሩ ሰለባ እንደሆኑ የገለጹ አብዛኛዎቹ ተሳፋሪዎች፣ ከሰሜን ወሎና ደቡብ ወሎ የመጡ መሆናቸውን፣ የሰሜን ሸዋ ዋና ከተማ ደብረ ብርሃንን አልፈው ወደ አዲስ አበባ ለመግባት የኦሮሚያ ክልል ወሰን ውስጥ እንደገቡ ከፍተኛ የሆነ እንግልትና ውጣ ውረድ፣ እንደደረሰባቸውና ቢያንስ ስድስት ጊዜ በፖሊስ ፍተሻ እንደተደረገባቸው ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ ፍተሻውን አልፈው የአዲስ አበባ የመጨረሻዋ መዳረሻ የሆነችው ለገዳዲ ከተማ ሲደርሱ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መታወቂያ የላችሁም ተብለው ወደ መጡበት እንዲመለሱ መደረጋቸውን በርካታ ተሳፋሪዎች ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

የሕዝብ ተሽከርካሪዎች ላይ የሚደረገው ፍተሻ የተሳፋሪዎች ማንነት ላይ ያነጣጠረ መሆኑን፣ በተለይም የአማራ ክልል የሚል መታወቂያ የያዙ፣ የአዲስ አበባ ወይም የሌላ ያልያዙ ተሳፋሪዎች ወደ መጡበት እንዲመለሱ መደረጋቸውን ቅሬታቸውን ያቀረቡ ተሳፋሪዎች አስታውቀዋል፡፡

ሐምሌ 17 ቀን 2014 ዓ.ም. መነሻቸውን ከወልዲያ ከተማ አድርገው ወደ አዲስ አበባ ሲጓዙ የነበሩና የአማራ ክልልን አልፈው ኦሮሚያ ክልል እንደገቡ ተደጋጋሚ ፍተሻ ተደርጎባቸው፣ ለገዳዲ ከደረሱ በኋላ፣ ‹‹የአዲስ አበባ መታወቂያ የላችሁም›› በሚል ምክንያት ወደ ደብረ ብርሃን እንዲመለሱ መደረጋቸውን ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንዲት እናት ለሪፖርተር ሲናገሩ ‹‹ሁኔታው በጣም አሳዛኝ ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ከሸኖ ከተማ ጀምሮ እስከ ሰንዳፋ ድረስ የተደረገብን ፍተሻ በጣም አድካሚ ከመሆኑም በላይ፣ የአዲስ አበባ መታወቂያ የላችሁም በሚል ሲሳለቁብን ማየት እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ አሳፋሪ ተግባር ነው፤›› ያሉት እኚህ እናት፣ ‹‹ፖሊሶች ፍተሻ ካደረጉ በኋላ የአዲስ አበባ መታወቂያ የሌላቸውን እዚያው ክልላቸው ወስደህ አውርዳቸው፤›› በማለት ለሾፌሩ መናገሩን አስረድተዋል፡፡

በዚህም የተነሳ በግዴታ ለገዳዲ ከደረሱ በኋላ እንደገና ተመልሰው ደብረ ብርሃን ከተማ እንዳደሩ ገልጸው፣ በስተመጨረሻም በነጋታው የቤት መኪና ተከራይተው ለቅሶ እንደሚሄዱ በመናገር አዲስ አበባ መግባታቸውን ተናግረዋል፡፡

‹‹በመጀመሪያ ጉዟችን ከቀኑ 9 ሰዓት አካባቢ ወደ አዲስ አበባ ተቃርቦ የነበረው የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ታግቶ እስከ ምሽቱ ተስፋ ባለመቁረጥ ብንቆምም፣ መጨረሻ ላይ አማራጭ ስናጣ ወደ ደብረ ብርሃን ሄደን አድረናል፤›› ብለዋል፡፡

የተፈጠረውን ክስተት አስከፊነት አስመልክተው ሲያስረዱ በጊዜው ገንዘብ ስለነበራቸው ከፍለው እንደተመለሱ፣ ነገር ግን ገንዘብ የሌላቸው ሰዎች ከመኪና እንዲወርዱ ሲደረጉ ሕፃን ልጅ የያዙ እናቶች ጭምር ለመመለሻ የሚሆን ገንዘብ አጥተው ሜዳ ላይ ወድቀው እንደነበር ገልጸዋል፡፡

‹‹ይህን ያህል አማራ ምን አድርጎ ነው? ወስደህ አውርዳቸው እንዴት ይባላል? ኢትዮጵያዊ አይደለንም ወይ? ብዙ ግፍ ያለበት ክልል እኮ ነበር፣ በአማራ ላይ ይህ ሁሉ ሲደረግ ሕግ አለ ወይ ያስብላል ሲሉ፤›› ጠይቀዋል፡፡

አደራው ኃይሌ የተባሉ ተሳፋሪ ከደሴ ከተማ ሐምሌ 19 ቀን 2014 ዓ.ም. ወደ አዲስ አበባ እየተጓዙ በነበሩበት ወቅት 100 ኪሎ ሜትር በማይሞላ ርቀት ውስጥ ከጫጫ ከተማ እስከ ለገዳዲ ከተማ ቢያንስ ሰባት ጊዜ መፈተሻቸውን፣ የመጨረሻው የአዲስ አበባ መግቢያ ፍተሻ በነበረው ለገዳዲ ሲደርሱ ከጥቂት የአዲስ አበባ ከተማ መታወቂያ ከያዙ ሰዎች ውጪ ቀሪዎቹ ወደ መጡበት እንዲመለሱ መደረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

ድርጊቱ በጣም የሚያሳዝን መሆኑንና አቶ ከመኪና እንዲወርዱ ከተደረጉ በኋላ ስልካቸውን ከፍተው እንዲያሳዩና በውስጥ ያሉ ምሥሎችና ድምፆችን እንዲከፍቱ መደረጋቸውንም ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ መታወቂያ የያዙና ወደ ደሴ ለሥራ ተጉዘው ተመልሰው ወደ አዲስ አበባ የመጡ አንድ የግል ድርጅት ሠራተኛ ስማቸው ሳይጠቀስ ለሪፖርተር አስተያየት ሲሰጡ፣ ሁኔታው የሕግ ድጋፍ ያለው እንደማይመስልና አልፎ አልፎ ፖሊሶቹ በመሰላቸው አሠራር እንጂ እንዲህ ዓይነት ድርጊት የሚፈቅድ ምንም ዓይነት የሕግ መሠረት ማቅረብ አይቻልም ብለዋል፡፡

አክለውም ድርጊቱ አሳፈሪ በመሆኑ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ለጉዳዩ አፋጣኝ መልስ መስጠት ካልቻለ፣ እንደ አገር አብሮ ባኖረ ሕዝብ ላይ አሁን ያለው የፖለቲካ ግለት ተጨምሮበት የባሰ ቁርሾ፣ እርስ በርስ የመለያየትና ከፋፋይ የሆነ አጀንዳ እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡

ሪፖርተር ቅሬታውን አስመልክቶ ያነጋገራቸው የአማራ ክልል የኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ጉዳዩ ስለመከሰቱ መረጃ እንዳላቸው፣ ነገር ግን የሕወሓት ሠርጎ ገቦችን ለመያዝ በሚል ግልጽ ባልሆነ መንገድ ዜጎች እየተንገላቱ በመሆኑ ጉዳዩን ለኦሮሚያ ክልል መፍትሔ እንዲሰጥበት ማሳወቃቸውን ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ ሪፖርተር የመንገደኞቹን ቅሬታ በመያዝ ከኦሮሚያ ክልል መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ መረጃ ለማግኘት በተደጋጋሚ ቢደወልም፣ ክልሉ መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ ይሁን እንጂ የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር አቶ አራርሳ መርዳሳ፣ ሪፖርተር ያቀረበላቸውን ጥያቄ ከሰሙ በኋላ መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡

በሌላ በኩል የሰሜን ሸዋ ዞን የፀጥታና አስተዳደር መምሪያ ኃላፊ አቶ ዋሲሁን ብርሃኑ ጉዳዩ መከሰቱን መረጃ እንዳላቸው፣ ተሳፋሪዎች የዞኑ ዋና ከተማ የሆነችውን ደብረ ብርሃን ከተማ ካለፉ በኋላ እንዲህ ዓይነት ችግር መፈጠሩን ጠቁመው፣ ከኦሮሚያ ክልልና ከአዲስ አበባ ፖሊስ ደውላችሁ አጣሩ ብለዋል፡፡  

መንገደኞች የደብረ ብርሃን ከተማን በነፃነት ካለፉ በኋላ እንዲመለሱ በሚደረጉ ተሽከርካሪዎች ምክንያት ቱለፋ በምትባል ቦታ መጨናነቅ መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡

ሪፖርተር ወደ አዲስ አበባ ለመግባት የአዲስ አበባ መታወቂያ ተጠየቅን ያሉ ቅሬታ አቅራቢዎችን ጥያቄ ይዞ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፀጥታ ቢሮ የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊን የጠየቀ ሲሆን፣ የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊው ስለሚባለው ጉዳይ ምንም ዓይነት መረጃ የለንም ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ምክትል ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ፣ የተጠቀሰው ጉዳይ አይመለከተንም ብለዋል፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ሚኒስትር ደኤታ ወ/ሪት ሰላማዊት ካሳ ለሪፖርተር በሰጡት ምላሽ፣ ጉዳዩ የሕወሓት የሽብር ቡድን በወረራ ይዟቸው ከነበሩት የአማራ ክልል አካባቢዎች የተለያዩ የመታወቂያ ማኅተሞችና የአስተዳደር ሰነዶችን በመዝረፉና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እነዚህን ሐሰተኛ መታወቂያዎች ሰነዶችን የያዙ ሠርጎ ገቦች ወደ አዲስ አበባ ሊገቡ ሲሉ በመያዛቸው ምክንያት የሚደረግ የክትትል ሥራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም የጥፋት ተልዕኮ የያዙና ከአማራ ክልል ተዘርፈው በተወሰዱ ሰነዶች ተመሳስለው የተሰሩ መታወቂያዎችን የያዙ ግለሰቦች አሁንም ወደ አዲስ አበባ ለመግባት የሚያደርጉት ጥረት እንዳለ ለፀጥታ ኃይሎች መረጃው በመድረሱ፣ ይህንን ለመከላከል ጥብቅ ፍተሻዎችና ማጣራቶች እየተደረጉ ነው ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ  አዲስ አበባን የጥፋት ተልኳቸው መዳረሻ ለማድረግ እየሞከሩ ያሉትን አካላት ለመከላከል በሚወሰደው ዕርምጃ፣ በመንገደኞች ላይ ተፅዕኖ መፍጠሩንና ዜጎችም ለእንግልት እየተዳረጉ መሆኑን የተመለከቱ ቅሬታዎች እንደደረሳቸው፣  ይህም በደኅንነት ፍተሻና ማጣራት አፈጻጸም ላይ መሻሻል ያለበትን ሁኔታ ለይቶ የፀጥታ ኃይሉ የማስተካከያ ዕርምጃ እንዲወስድ ይደረጋል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልና የአብን ከፍተኛ አመራር አባል አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ ከአማራ ክልል የወሎ አካባቢዎች ተነስተው መዳረሻቸውን አዲስ አበባ ከተማ ያደረጉ ዜጎች ኦሮሚያ ክልል ሸኖ ከተማ ሲደርሱ መታወቂያቸው እየታየ ከተሳፈሩበት መኪና እንዲወርዱና ወደ መጡበት እንዲመለሱ መደረጉን ተጨባጭ መረጃዎች እንደደረሳቸው አስታውቀዋል፡፡ ‹‹የሚመለከታቸው የፌዴራልና የኦሮሚያ ክልል የሥራ ኃላፊዎች በዜጎች ላይ እየተፈጸመ ያለውን መጉላላትና አግላይ የነውር ተግባር ታስቆሙ ዘንድ ጥሪዬን አቀርባለሁ፤›› ሲሉ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው አሳስበዋል፡፡

Source:Reporter

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *