ከኢዜማ የለቀቁ አመራሮችና አባላት በአዲስ የፖለቲካ አስተሳሰብ ሊመጡ እንደሚችሉ ፍንጭ ሰጡ

0
0 0
Read Time:2 Minute, 27 Second

ሲሳይ ሳህሉ


ከሰሞኑ ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ፓርቲ ራሳቸውን ያገለሉ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች አባላት በአዲስ የፖለቲካ ፍልስፍና ሊመጡ እንደሚችል ፍንጭ ሰጡ፡፡

ሰባት የፓርቲው አባላት ግንቦት 17 ቀን 2015 ዓ.ም. ከኢዜማ ጋር መለያየታቸውን ያስታወቁት አቶ የሸዋስ አሰፋ፣ አቶ ሀብታሙ ኪታባ፣ አቶ ተክሌ በቀለ፣ አቶ ዳንኤል ሺበሺ፣ ወ/ሮ ናንሲ ውድነህ፣ አቶ የጁአልጋው ጀመረና አቶ ኑሪ ሙደሲር ናቸው፡፡ ከቅርብ ሳምንታት በፊት በተመሳሳይ አቶ አንዷለም አራጌ ከፓርቲው ራሳቸውን ማግለላቸው የሚታወስ ነው፡፡

አቶ ሀብታሙ ኪታባ ኢዜማ በ2014 ዓ.ም. ባደረገው የሥራ አስፈጻሚ ምርጫ ፉክከር ቀርበው ከነበሩት ከአቶ አንዷለም አራጌ ጋር ለፓርቲው መሪና ምክትል መሪ ለመሆን ተወዳድረው እንደነበር ይታወሳል፡፡

ሪፖርተር ከፓርቲው መልቀቃቸውን በተመለከተ ያነጋገራቸው አቶ ሀብታሙ እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ የባህል ለውጥ የሚስፈልገው መሆኑንና በቀጣይ ሦስት ወራት በፓርቲዎች ዕድገት ዙሪያ ላይ የሚያጠነጥን ሰፊ ውይይት በማድረግ፣ ‹‹የኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅቶች ምን ገጠማቸው?›› የሚለው ላይ ሰፋ ያለ ዳሰሳ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡

አገሪቱ የተሻለ የፖለቲካ አማራጭ ያስፈልጋታል የሚሉት አቶ ሀብታሙ፣ በቀጣይ የተሻለ አማራጭ የሚሆን የፖለቲካ ኃይል መምጣቱ እንደማይቀር ተናገረዋል፡፡

በመሆኑም በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ካለፉ አባቶችና እናቶች ጋር በመመካከር፣ ከአንድ ፓርቲ ወደ ሌላ ፓርቲ ከመሄድ ባለፈ ጠንካራ ፍተሻ በማድረግ በቀጣይ ጥቂት ወራት  ውስጥ በሚደረጉ ውይይቶች የሚወለዱ አዳዲስ ዕርምጃዎች እንደሚኖሩ ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጅ ከኢዜማ ከለቀቁት አባላት ውስጥ የትኞች አባላት በአንድ ላይ መጥተው ወደ ሌላ አማራጭ የፖለቲካ ኃይል ውስጥ እንደሚገቡ አልገለጹም፡፡

አቶ ሀብታሙ ለሪፖተር እንደገለጹት በኢዜማ ውስጥ የሚነሱ የፓርቲ ጥያቄዎችን በውስጥ የፓርቲ አሠራር ለመፍታት የፓርቲው መሪዎች ዝግጁ አለመሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

‹‹ብልፅግና መረን እየወጣ ባለበት በዚህ ጊዜ ኢዜማ የአጃቢነት ሚናው በተለይም በዚህ ዓመት ፍንትው ብሎ ወጥቷል፤›› የሚሉት አቶ ሀብታሙ፣ በጉራጌ ዞን የኢዜማው መሪ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) የብልፅግናን ዓላማ ለማስፈጸም ከብልፅግና ፓርቲ ፕሬዚዳንት ጋር ተጉዞው ሕዝቡን ለማሳመን ሲጥሩ ታይተዋል ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ የጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) የፖለቲካ መጽሐፍ የሆነውን መደመር፣ የኢዜማው መሪ መድረክ ላይ ወጥተው ለማብራራት የሚሞክሩ ነገር ግን ‹‹የተፎካካሪ ፓርቲ መሪ ነኝ›› የሚሉ አካል ስለመሆናቸው ተናግረዋል፡፡

 በመሆኑም እነዚህ ነገሮችን እያዩ መቀመጡ የፓርቲው መሪ የሚያደርጉትን ነገር ዕውቅና መስጠት ስለሆነ ዘግይቶም ቢሆንም ለመውጣት መወሰናቸውን ተናግረዋል፡፡ አቶ ሀብታሙ እንደሚሉት ከ70 እስከ 80 በመቶ በላይ የሚሆነው የኢዜማ አባል ፓቲውን ለቆ እንደወጣና ፓርቲው በመንጋ አስተሳሰብ ውስጥ ያሉ ሰዎች የሚንቀሳቀሱበት ሆኗል ብለዋል፡፡

ከፓርቲው የለቀቁት አባላት በጋራ ባወጡት መግለጫ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ አሁን የገጠመው መከራ በታሪኩ ገጥሞት የማያውቅ፣ እዚህ መከራ ውስጥ ከመግባቱ በፊት መንገዳችንን እንድናስተካክል በፓርቲው ውስጥም በብዙ በፓርቲው ጉባዔዎች ሁሉ ሳይቀር ስህተቶች ይታረሙ ይሆናል በማለት የትግሉን መድረክ ለማስፋት ቢሞከርም በተለያዩ ውስጣዊና ውጫዊ ምክንያቶች ማሳካት እንደልተቻለ ተናግረዋል፡፡ ኢዜማን ጠግኖ ለማዳን የተደረገው ትግልም ከንቱ ቀርቷል ብለዋል በመግለጫቸው፡፡

በግልጽ እየታየ እንደሚገኘው የኢዜማ ከፍተኛ አመራር አገርን ለመታደግ፣ ሕዝብንና ፓርቲዎችን አስተባብሮ ከማታገል ይልቅ አገዛዙ እየፈጸመ ላለው አገር አቀፍ ግፍ ድጋፍ እየሰጠ ስለመሆኑም በመግጫው ተብራርቷል፡፡

የጋራ መግለጫው የፓርቲው አመራር ኢዜማ ከቆመላቸው መሠረታዊ ዓላማዎች፣ መርሆዎችና እሴቶች በመውጣት የገዥውን ቡድን እሴቶችና ዓላማዎች እያራመደ እንደሆነ አስታውቋል፡፡

በተለያዩ ወቅቶችና ሁኔታዎች አባላት ለፓርቲው አመራር የሚቀርቡ ጥያቄዎችን ተቀብሎ ለጤናማ ውይይትና ለንግግር ዝግጁ ከመሆን ይልቅ፣ ንቁ አባላቶችን በተለያዩ ፍረጃዎች ከደንብና አሠራር ውጪ ለማሸማቀቅ ሲሞከር እንደነበርም መግለጫቸው ያብራራል፡፡

በዚህና በሌሎች በርካታ ምክንያቶች ፓርቲውን ማዳን በማይቻልበት ሁኔታ ላይ መደረሱን የሚያብራረው መግለጫው፣ በዚህ ሁኔታ አብሮ መቆየት ተጨማሪ ብዥታንና የሌለ ተስፋን እንዲጠበቅ የሚያደርግ በመሆኑ ለሕዝብ፣ ለአባላትና ለደጋፊዎች ግልጽ መሆን እንዳለበት በመግለጽ ከኢዜማ አባልነት ያገለሉ መሆኑን አንስቷል፡፡

source: www.ethiopianreporter.com

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *