ንፁህ ህዝብ ለምን ይለቅ? እናት አገር ለምን ትሙት?
በቀለ ገሠሠ (ዶ/ር) June 2026
በመጀመሪያ በአርሲ ቤተክርስቲያንና ምእመናን ላይ ሰሞኑን ስለደረሰው እጅግ አሳፋሪ አረመኔያዊ ጭፍጨፋ የተሰማኝን ትልቅ አዘኔታ እገልፃለው፣ እግዚአብሔር አምላካችን የሞቱትን ነብስ ይማርልን፣ በነፍሰገዳዮቹና ቤተክርስቲያን አውዳሚዎች ላይ ፍርዱን ይስጥልን።
፩ኛ/ ኢትዮጵያ ማን ናት? ምንስ አበረከተች?
ኢትዮጵያ እግዚአብሔር አምላካችን ሁሉን አሟልቶ ፈጥሮ ለብዙ ሺ ዓመታት የኖረች ቅድስት አገር ናት።
ኦርቶዶክስና ሙስሊም ተከታዮች ተከባብረው ተፋቅረው የኖሩባት ልዩ አገር ናት። የተለያዩ ጎሣና ነገዶች ተጋብተው ተባብረው በሰላም የኖሩባት አገር ነበረች።
እንግዳ ተቀባይ ናት።
የውጪ ወረራም ሲመጣባት በእግዚአብሔር ኃይል በጋራ መክታ ነፃነቷን አስከብራ የኖረች አገር ናት። አፍሪቃን ከባርነትና ከቅኝ አገዛዝ ለማውጣት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገች የተከበረች አገር ናት። ከአፍሪቃ የሊግ ኦፍ ኔሽን ብቸኛ አባል ነበረች። የዓለም መንግሥታት መሥራች አባል ናት።
በአፍሪቃ አንድነት ምሥረታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጋለች።
በነዚህም ምክንያቶች የአፍሪቃ ህብረትና የተለያዩ ዓለማቀፋዊ ቅርንጫፍ ድርጅቶች መቀመጫ ሆነች።
፪ኛ/ ጠላቶችዋ ለምን በዙ?
ሀ) የውጪ ታሪካዊ ጠላቶች ቂም ይዘውብናል።
ዐፄ ቴዎድሮስ በመቅደላ ላይ ለእንግሊዝ ወራሪ ኃይሎች እጅ አልሰጡም።
በአድዋ ላይ ጣሊያንን አቸንፈን ታሪክ ሠራን።
በማይጨው ዳግመኛ ወረራ ወቅት መርዝ ጪሶችንና ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎችን ተቓቁመን ከአምስት ዓመት መራራ ትግል በኋላ ነፃነታችንን አስከበርን።
እላይ እንደተጠቀሰው የአፍሪቃ አገሮች ከባርነትና ከቅኝ አገዛዝ ነፃ እንዲወጡ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጋለች።
ለዚህ ደግሞ የአማራው ህዝብና ኦርቶዶክስ ሃይማኖት ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረጋቸው ምክንያት እነርሱን አጥፍተው ኢትዮጵያን በትነው አፍሪቃን ወደባርነት ሊመልሱ ይፈልጋሉ።
ለ) የውስጥ ጨፍጫፊና ተገንጣይ ኃይሎች ሚና
ጣሊያኖች ከዐድዋ ሽንፈት በኋላ ተጠራርገው ይወጣሉ የሚል ግምት ነበረ።
እነርሱ ግን ወደባህረ ነጋሢ ሸሽተው ተቀመጡ። ስሟንም ወደኤርትራ ቀይረው ተቆጣጠሯት።
በመጨረሻም በፌደረሽን ከእናት አገሯ ጋር ተመልሳ ተቀላቀለች። ፌደረሽኑም ሲፈርስ ያንን ለማስመለስ ጀብኃ ተቋቁሞ ተነሣ። ቀጥሎም ሸዓቢያ ተፈጠረ። በውጪ ድጋፎችና በውስጥ ድክመቶች ምክንያት ጥያቄው ከፌደረሽን ወደግንጠላ ተሸጋገረ። ወታደራዊው ደርግም ለአስራ ሰባት ዓመታት ብዙ መሪዎችን፣ ጄነራሎችና ምሁራንን ጨፍጭፎ ሲዳከም ሥልጣኑን ለሸዓቢያና ወያኔ ኃይሎች አስረክቦ ወደውጪ ፈረጠጠ። ወያኔ ሥልጣን ስትረከብ የኤርትራን ግንጠላ ቶሎ አመቻቸች። ዘረኛ ህገመንግሥት አወጡ። በውሸት ትርክቶች በተለይ አማራውን የህዝብ ጠላት አስመሰሉ ።
ወያኔም ከሃያ ሰባት የብዝበዛ ዓመታት በኋላ ተዳክማ ሥልጣኑን ለኦሮሞ ኃይሎች አስረክባ ወደመቀሌ አፈገፈገች።
፫ኛ/ የሚካሄደው ጭፍጨፋና አገር የማፍረስ ዘመቻ፣
በተለይ የዐቢይ ኦሮሙማ አስተዳደር ከተመሰረተ ወዲሁ ሁኔታዎች በመባባስ ላይ ይገኛሉ።
የሚከተሉ ግልጽ ወንጀሎች በመካሄድ ላይ ይገኛሉ፣
የአማራ ህዝብ ጭፍጨፋ፣
የኦርቶዶክስ ተከታዮች ጭፍጨፋ፣
አብያተ ክርስቲያናት ጥቃት፣
ትምህርት ቤቶችን መዝጋት፣
የህክምና እድሎችን መንፈግ፣
ህዝብ ማፈናቀል፣
ቅርሶች ማውደምና ንብረቶች መዝረፍ፣
እርጋታ ማሳጣት፣
ኢኮኖሚ ማውደም፣
በአፍሪቃም ሆነ በዓለም ፊት እንድትናቅ ማድረግ፣
አገር መበተን፣
ወዘተ።
ለምን ለምን ለምን?
፬ኛ/ መደምደሚያ
እላይ የተጠቀሱትን እጅግ አስከፊ አደጋዎች እኩል እንረዳለን ወይ? ከሆነስ ለምን ታላቅ ህብረት ፈጥረን ለሁሉም የሚበጅ ለውጥ ቶሎ ማምጣት አቃተን? ከዚህ በላይ ምን እየተጠበቀ ይገኛል???
ወያኔ የአማራን ለም መሬት በመንጠቅ የትግሬ አገር የመመስረቱ ህልም እብደት ነው።
የኦሮሙማ ኃይሎች ደግሞ አማራን፣ ኦርቶዶክስንና ሌሎችንም በመጨፍጨፍ የኦሮሞ አገር የመገንባት ህልም እንደዚሁ እብደት ነው።
በተለይ የትግሬና ኦሮሞ ህዝብ ቶሎ ነቅቶ ለአንድነት፣ ለሰላምና ዘለቄታ ለሚኖረው እድገት ከሌሎች ጋር አብሮ ቢሰለፍ ይሻላል።
ሌሎችም ነግ በእኔ ብለው በመነሳት ለህልውናው በመዋደቅ ላይ ከሚገኘው ፋኖ ጎን መሰለፍ ይጠበቅባቸዋል።
የውጪ ኃይሎችም ኢትዮጵያን በመበተን ጥቅም እናገኛለን ብለው ከገመቱ ተሳስተዋልና ካለፉት ስህተቶቻቸው ተምረው ከሰይጣናዊ እርምጃዎቻቸው ቢቆጠቡ ይሻላቸዋል።
እግዚአብሔር አምላካችን በንፁሃን ምስኪን ዜጎቻችን ጎን በመሆን የጨፍጫፊና አውዳሚ ኃይሎችን ክንድ ይስበርልን
ሰላሙን ያውርድልን፣ አሜን።
