ለተከበሩ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢኦ እና ለአምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ የተጻፈ ግልጽ ደብዳቤ
ግልጽ ደብዳቤ
ለተከበሩ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢኦ እና ለአምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ የተጻፈ ግልጽ ደብዳቤ
ስለ አማራ ህዝብ የህልውና ትግል መጠለፍ፣ ስለ “አፋብን/ፅምዶ/AFS” ህገ–ወጥነት እና በታጋይ እስክንድር ነጋ ህይወት ላይ የተደቀነው አጣዳፊ የግድያ ስጋት
ዶክተር ሶስና ታደሰ
ጥቅምት 20 ቀን 2019 ዓ.ም (30 October 2026)
ከ፦ ዶክተር ሶስና ታደሰ
ለ፦
- ለተከበሩ ማርኮ ሩቢኦ፣ የአሜሪካ መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር
- ለአምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ፣ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር
- ለአለም አቀፍ የዲፕሎማሲ አካላት፣ ለሰብአዊ መብት ተቋማት እና ለፖሊሲ አውጪዎች
ቀን፦ ጥቅምት 17 ቀን 2019 ዓ.ም (ኦክቶበር 27፣ 2026)
ጉዳዩ፦ ስለ አማራ ህዝብ የህልውና ትግል መጠለፍ፣ ስለ “አፋብን/ፅምዶ/AFS” ህገ-ወጥነት እና በታጋይ እስክንድር ነጋ ህይወት ላይ የተደቀነው አጣዳፊ የግድያ ስጋት
የተከበሩ ሚኒስትር ሩቢኦ፣ አምባሳደር ማሲንጋ እና የተከበራችሁ ዲፕሎማቶች፦
ይህንን ግልጽ ደብዳቤ የምፅፍላችሁ እንደአንድ የአማራ ተወላጅ፣ ምሁር እና የአማራ ህዝብ መብት ተቆርቋሪ ሲሆን፣ ዓላማውም በኢትዮጵያ ውስጥ የአማራ ህዝብ የህልውና የመከላከል ትግል በውስጥና በውጭ ኃይሎች መጠለፉን፣ “አፋብን/ፅምዶ/AFS” በሚል ስም የተዋቀረውን የውጭ ኃይሎች ተላላኪ ስብስብ ህገ-ወጥነት፣ እንዲሁም በታዋቂው የሰብአዊ መብት ተሙጋችና የፖለቲካ አመራር እስክንድር ነጋ ላይ የተደቀነውን አካላዊ አደጋ ማሳወቅ ነው።
ዓለም ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ለፍትህ፣ ለእኩልነትና ለዲሞክራሲ የታገለ ታላቅ ሰው መሆኑን አረጋግጧል፤ ስለሆነም የእሱን ጀግንነት በመግለጽ ጊዜ አላባክንም። በኢትዮጵያ የሕወሓት መራሹ የኢሕአዴግ መንግሥት የግፍ አገዛዝ ምክንያት ከ7 ዓመታት የእስርና የእንግልት ዘመን በኋላ እስክንድር ነጋን በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ሲያገኙት ሚኒስትር ማርኮ ሩቢኦ እስክንድርን ሲገልፁት እንዲህ ብለው ነበር፦
“After advocating on his behalf, I was honored to meet with Ethiopian journalist Eskinder Nega, who is finally free after being wrongly imprisoned for almost 7 years. His case is a reminder of why we must continue to advocate for #humanrights worldwide #ExpressionNOToppression.”
1. የአራት ዓመታት መስዋዕትነት እና የተጠለፉት ድርጅታዊ መዋቅሮች
የሰብአዊ መብት ተሟጋች ታጋይ እስክንድር ነጋ 3 አሥርት ዓመታትን ለሰላማዊ ዲሞክራሲያዊ ትግል የሰጠ ከመሆኑም በላይ እሳት በሚተፋ ብዕሩ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ብልሽት የሞገተ፣ የአማራን ሕዝብ የዘር ማጥፋት ወንጀል በጽሑፎቹ ያሳወቀ፣ ብሎም ላለፉት አራት ዓመታት የአማራን ህዝብ ከጅምላ ጭፍጨፋና ከዘር ማጥፋት (ጄኖሳይድ) ለመታደግ በጫካ ውስጥ በርካታ እንግልቶችን ያሳለፈ የዘመናችን ክስተት ነው።
የኦህዴድ ብልፅግና መንግሥት ከሕወሓት ጋር ባደረገው ስምምነት መሠረት የሕወሓት ታጣቂ ኃይሎች ትጥቅ ሳይፈቱ የአማራን ልዩ ኃይል አባላትና የአማራ ፋኖ ኃይልን ትጥቅ አስፈታለሁ ብሎ የግዳጅ ስምሪት ለማስፈፀም በተንቀሳቀሰበት ወቅት፣ የአማራ ልዩ ኃይልም ሆነ የአማራ ፋኖ “የዘር ማጥፋት ጦርነት ያደረገብን ፀረ–አማራው ሕወሓት ትጥቅ ሳይፈታ እኛ አንፈታም“ በማለት ከኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል ጋር ቀጥተኛ ውጊያ መጀመሩ ይታወቃል። በስርዓቱ ይደረጉ የነበሩ መድሏዊ አሰራሮችና የዘር ማጥፋት ወንጀሎች ለትግሉ መቀጣጠል ትልቅ አስተዋፅኦ አድርገዋል።
በዚህ ወቅት እስክንድር ነጋ ትግሉን በአንድ ጥላ ስር ለማሰባሰብ “አማራ ሕዝባዊ ግንባር (APF)”ን የመሰረተ ሲሆን፣ በመቀጠልም በታጋዮች ከፍተኛ ድምፅ ተመርጦ “አማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (AFPO/አፋሕድ)”ን ከ19 ወራት በላይ መርቷል። ሆኖም ግን ከብአዴንና ሕወሓት መዋቅር ጋር ግንኙነት ያላቸው የውስጥ ሴረኞች ድርጅቱን ለማፍረስ ተንቀሳቅሰዋል። በመጨረሻም አፋሕድ እንዲፈርስ በማድረግ፣ የውጭ ኃይሎችን የጂኦ-ፖለቲካ ቁማር የሚያገለግለውን “አፋብን (AFNM)” የተባለውን ድርጅት ፈጥረዋል።
2. የትግሉ መጠለፍ ማረጋገጫዎች፦ የእስክንድር ነጋ ይፋዊ መግለጫዎች
የአማራ ህዝብ የህልውና ትግል መጠለፉ በእስክንድር ነጋ ይፋዊ መግለጫዎችና ደብዳቤዎች በጥብቅ የተሰነደ እውነታ ነው፦
- ነሐሴ 18 ቀን 2018 ዓ.ም (ከዶቼ ቬለ / DW ጋር ባደረገው ይፋዊ ቃለ-መጠይቅ)፦
- መስከረም 12 ቀን 2019 ዓ.ም (ዘመነ ካሴ በትግራይ ቴሌቪዥን ከሰጠው መግለጫ በኋላ ባስተላለፈው መልእክት)፦
- ጥቅምት 17 ቀን 2019 ዓ.ም (ለአፋብን ፖሊት ቢሮ ባስገባው ይፋዊ የመልቀቂያ ደብዳቤ)፦
እስክንድር ነጋ ህዝባዊ ውክልና የሌላቸውን ጥምረቶች ውድቅ በማድረግ፦ “የመላው የፋኖ አባላት ሳያውቁ የሚደረግ ‘ፅምዶ‘ ተቀባይነት የለውም“ ሲል ተናግሯል።
አክሎም በህይወቱ ላይ የተደቀነውን አጣዳፊ አደጋ ሲገልፅ፦ “ከመንግሥት ወታደራዊ ኃይሎች እና ለጊዜው ስማቸውን መጥቀስ ከማይፈልጉ ታጣቂዎች ተደጋጋሚ የግድያ ሙከራ ይደረግብኛል“ በማለት አስበብቦ ነበር።
መስከረም 10 ቀን ዘመነ ካሴ በትግራይ ቴሌቪዥን ላይ ወጥቶ “ትብብር ለሕልውና” የሚል ድርጅት መመስረታቸውን መናገሩን ተከትሎ፣ እስክንድር እንደገለጸው፣ አፋብን ያለምንም አባላት እውቅና ከፀረ-አማራና ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች (በተለይም ሕወሓት፣ ኦነግ ሸኔ እና ጉምዝ ነፃ አውጭ) ጋር አብሮ ለመሰለፍ መስማማቱ ምንም ዓይነት ተቀባይነት እንደሌለው አጋልጧል።
እነዚህ ኃይሎች፦ “ባለፉት 8 ዓመታት ጭምር በቀጥታ በአማራ ህዝብ ላይ ማንነትን መሰረት ያደረገ የጅምላ ጭፍጨፋ የፈፀሙ የታጠቁ ኃይሎች መሆናቸው በገለልተኛ የሰብአዊ መብት ተቋማት የተረጋገጠባቸውና የህግና የሞራል ተጠያቂነት ያለባቸው ናቸው“ ሲል ገልጿል።
እስክንድር ለአፋብን ፖሊት ቢሮ ባስገባው ደብዳቤ የሕወሓትና ሕወሓት አፍቃሪ ብአዴኖች የ30 ዓመት መዋቅራዊ እቅድ ትግሉን እንዴት እንደጠለፈው እንደሚከተለው አብራርቷል፦
“ሕወሓት አፍቃሪው ብአዴን/ሕወሓት በአገዛዙ ውስጥ፣ በኢኮኖሚው ውስጥ፣ በሚዲያው እና በዲያስፖራው ከ30 ዓመታት በላይ የተገነባ ኔትወርክ ያለው ስብስብ ነው። ይህ ስብስብ ከሌሎች አካላት በተለየ መልኩ፣ ፋኖ መንቀሳቀስ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ራሱ በቀጥታ የሚቆጣጠረውን ፋኖ ለማደራጀት ሙከራ አድርጎ አልሳካለት ሲለው፣ በቀጣይነት፣ በመላው አማራ ክልል ብቅ ብቅ ያሉትን የፋኖ አደረጃጀቶችን ለመጥለፍ ለዓመታት የተንቀሳቀሰ ነው። ከብዙ ልፋት በኋላ ጠለፋው ተሳክቶለትም፣ ‘ጊዜ የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል‘ እንዲሉ፣ ለሦስት አሥርት ዓመታት በዘለቀው የሕወሓት አገዛዝ ዘመን ጥርስ አልባ ሆኖ የኖረ ቢሆንም፣ በአሁኑ ጊዜ በአፋብን ውስጥ ዋነኛው የፖለቲካ እና የሕዝብ ግንኙነት ሥራዎች መዘውር እና ድምፅ ሆኗል።“
3. አፋብን/ፅምዶ (AFS)፦ በፍፁም የህዝብ ውክልና የሌለው የውጭ ኃይሎች ተላላኪ (Proxy Platform) ነው!
የአማራን ህዝባዊ እንቅስቃሴ እወክላለሁ የሚለው ትብብር ለሕልውና/ፅምዶ (AFS) ከአማራ ህዝብ የተሰጠው ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ፣ ህጋዊ ወይም ሞራላዊ ስልጣን የለውም።
- የመሬቱን ነባራዊ ሁኔታ መካድ፦ አፋብን/AFS የአማራ ህዝብ ደሙን አፍሶ አጥንቱን ከስክሶ በታሪካዊ የመሬት ባለቤትነቱ ያስከበረውን መብትና ነባራዊ እውነታ ወደ ኋላ በመመለስ ማንነቱንና መሬቱን ለሕወሓት ዳግም ባርነት አሳልፎ ለመስጠት ይሞክራል። ለምሳሌ አምባሳደር ማሲንጋ በወልቃይት ባደረጉት ጉብኝት ወቅት ወልቃይት የአማራ ተወላጆች ርስት መሆኑንና የአካባቢውን ህዝብ ፍላጎት በአካል ተመልክተዋል።
- ከጭፍጨፋ አፈፃሚዎች ጋር የተደረገ ትብብር፦ ከብዙሃኑ የፋኖ ታጋዮች እውቅና ውጭ፣ የሰማዕታትን ደምና የፍትሕ ጥያቄ በመካድ በትብብር ስም ጥምረት በመፍጠር በአማራ ህዝብ ላይ የጅምላ ጭፍጨፋ ከፈፀሙ አካላት ጋር ስብጥር ፈጥሯል። እስክንድር ነጋ እንዳስቀመጠው፣ ይህ ሁኔታ “በሬ ከአራጁ ጋር እንደሚባለው“ ሆኖበታል። ምክንያቱም ፋሽስት ወያኔ ትናንትናም ሆነ ዛሬ ጦር የሚሰብቀውና የሰበቀው አማራን ለማጥፋት እና የአማራ ሕዝብ አጽመ ርስቱ የሆኑትን ወልቃይትን፣ ጠገዴን፣ ጠለምትን፣ ሁመራን፣ ኮረምን፣ አላማጣ፣ ዋጃ፣ መሆኒ እና በወረራ የያዛቸውን የራያ አካባቢዎች ለመውረር እና ታላቋን ትግራይ ለመመስረት ብቻ ነው። ፋሽስት ወያኔ ከዚህ ውጭ የሚዋጋበት ወይንም ከአማራ የሕልውና ትግል ጋር የሚተባበርበት አንዳችም ምክንያት የለውም!!
4. አክራሪነትን እና በሲቪል አቪዬሽን ላይ የተደቀነውን ዛቻ ማውገዝ
እውነተኛው የአማራ ህዝባዊ ትግል የሚንቀሳቀሰው በዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ህጎች (IHL) መሠረት ነው። ከፅምዶ/AFS ጋር ተያያዥነት ባላቸው አካላት በሲቪል አቪዬሽን (እንደ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ አውሮፕላን) ወይም መሰረተ-ልማቶች ላይ የሚሰነዘሩ የጥቃት ጥሪዎችን በጽኑ እናወግዛለን።
እነዚህ ድርጊቶች በ1971ዱ የሞንትሪያል ኮንቬንሽን መሠረት የዓለም አቀፍ አቪዬሽን ቴረሪዝም ወንጀሎች ናቸው። ሚኒስትር ማርኮ ሩቢኦ በትክክል እንደተረዱት፣ በዋና ከተማውና በመሰረተ-ልማቶች ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶች ‘የአሸባሪዎች’ እና ‘የተገንጣይ ኃይሎች’ ስራ እንጂ የጸና መርህ ያለውን ህዝባዊ የአማራን የመከላከል ትግል አይወክሉም።
5. በእስክንድር ነጋ ላይ የተደቀነው አጣዳፊ የህይወት አደጋ
በአሜሪካ ፖሊሲ አውጪዎች ዘንድ በደንብ የሚታወቀው እስክንድር ነጋ፣ የአማራን ህዝብ አሳልፎ ለመስጠት እምቢ በማለቱ ምክንያት በውስጥ ሴረኞች ታግቶ ይገኛል፤ እንዲሁም ከተቃዋሚ የታጠቁ ቡድኖች አጣዳፊ የህይወትና የግድያ አደጋ ተደቅኖበታል። እንደሚታወቀው ይህ የሕወሓት አፍቃሪ ቡድን እንደ አርበኛ ከፍያለው ደሴ እና ሌሎች በርካታ ስመ-ጥር የሆኑ ለአማራ ሕዝብ ትግል ታማኝ ታጋዮችን ከውስጥ በሴራ አስገድሏል። በመሆኑም ይህ ተመሳሳይ ድርጊት በእስክንድር ላይ ከመፈፀሙ በፊት አለምአቀፍ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ ትኩረት እንዲሰጠው ያስፈልጋል
ጥሪያችን፦
- የእስክንድር ነጋን ደህንነት ማረጋገጥ፦ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ እና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተቋማት (Amnesty International, Human Rights Watch) የእስክንድር ነጋን ደህንነት በአጣዳፊነት እንዲከታተሉና ከለላ እንዲደረግለት እንዲጠይቁ።
- የተጠለፉ ቡድኖችን ውድቅ ማድረግ፦ የአሜሪካ መንግሥት እንደ አፋብን/AFS ያሉ የተገንጣይ እና የሀገር አፍራሽ ሚና የሚጫወቱ የውጭ ኃይሎች መጠቀሚያዎች ፈፅሞ የአማራን ሕዝብ የማይወክሉ በመሆናቸው ከወዲሁ ውድቅ እንዲደረጉና ምንም ዓይነት ህጋዊ ተቀባይነት እንደሌላቸው ማሳወቅ።
- የህዝቡን ተቃውሞ ማወቅ፦ ይህ ስብስብ በአማራ ሕዝብ ዘንድ በይፋ መወገዙን ማወቅ፤ በተለይም አሁን በጎጃም እየተቀጣጠለ በመጣው ሰልፍ ላይ የፅምዶ ኃይሎች ተወግዘዋል፤ የነ ዘመነ ካሴ፣ የነ ደብረጽዮን ገብረሚካኤል እና ኩምሳ ድሪባ (ጃል ማሮ) ፎቶዎች ላይ በትልቁ የ ‘X’ ምልክት በማድረግ ህዝቡ ቁጣውን አሳይቷል። ይህም ስብስቡ የአማራን ሕዝብ የማይወክል መሆኑን ግልጽ ማሳያ በመሆኑ ዓለም አቀፉ ዲፕሎማሲያዊ ማህበረሰብ ይህንን ስብስብ ከአማራ ህዝብ ትግል ለይቶ እንዲመለከተው እንጠይቃለን።
- በመሬት ላይ ያሉ ነባራዊ ሁኔታዎችን ማከበር፦ በምስራቅ አፍሪካ የሚደረግ ማንኛውም የሰላም ጥረት የአማራን ህዝብ መስዋዕትነት ያከበረ፣ የአማራ ፋኖን ከፅምዶ ኃይሎች ለይቶ የሚያይ፣ የዘር ማጥፋት ወንጀል የፍትህ ጥያቄን ያከበረ እና በወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምት፣ ሁመራ፣ ኮረም፣ አላማጣ፣ ዋጃ፣ መሆኒ እና ራያ ያሉትን ታሪካዊ ነባራዊ ሁኔታዎች ያገናዘበ መሆን አለበት።
ከክብሮት ጋር፣
ዶክተር ሶስና ታደሰ
ለአማራ ሕዝብ የሕልውና ትግል ተቆርቋሪ
— The Ethiopian Tribune —
