ህዳር 14 ቀን በጥይት ተደብድበው በግፍ የተገድሉት 60 ዎቹ ባለስልጣናት እውነታዎች

0
0 0
Read Time:9 Minute, 39 Second

ሰለ 60 ዎቹ ባለስልጣናት እውነታዎች
ሺህ ዘጠኝ መቶ ስልሳ ሰባት……
ቀናት ቀናትን ወልደዋል፡፡ ሀገሪቱ ከጫፍ እስከ ጫፍ በአዲስ የለውጥ ማዕበል ውስጥ እየተናጠች ነው፡፡ ለዘመናት ስትተዳደርበት የቆየችውን ንጉሳዊ አስተዳደደር ፈንግሎ በሀገሪቱ ላይ ራሱን መንግስት ያደረገው የወታደራዊ ቡድን ስልጣኑን በህዝብ ለሚመረጠው አካል አስረክቦ ወደ ክፍሉ ከመመለስ ይልቅ ጡንቻውን አፈርጥሞ የምንጨርሰው ስራ አለና እሱን አጠናቀን ነው ወደ ክፍላችን የምንመለሰው በሚል በስውር እግሩን ማደላደል ቀጠለ፡፡
ህዳር 14 ቀን 1967 ደርግ ጽ/ቤት
በጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ወይም መንግሥት በጠቅላላ ጉባኤ እና በቋሚ ኮሚቴነት ንዑሳን ኮሚቴነት የተዋቀሩትና ሥልጣን በብቸኝነት ይዘው ያሉት ቡድኖች “ለፖለቲካ እስረኞች የፖለቲካ ውሣኔ ለመስጠት” በዚህቀን በደርግ ጽ/ቤት ጠቅላላ ስብሰባ ተቀምጠዋል፡፡ ሰው መግደልን አጀንዳ አድርገው ተወያይተው ለመግደልም ተስማምተው በእነርሱ ቁጥጥር ስር የነበሩ ሰዎችን ፊውዳል ፣ መኳንንትና መሣፍንት ስለሆኑ ደማቸውን የንፁህ ሰው ደም እንደፈሰሰ አንቆጥረውም ጨቋኞች ናቸው በማለት እንዲገደሉ በአንድነት ወስነውና ውሣኔውን እንዲያስፈፅሙ ፣ ለእስረኛ ኮሜቴና ለደርግ አባላት ትዕዛዝ ሰጥተው ከሕግ ውጭ በአዲስ አበባ ወህኒ ቤት ውስጥ 59 ሰዎች በጥይት ተደብድበው አንዲገደሉ አደረጉ፡፡
ድህረ ታሪክ
ምንም እንኳን በያሉበት ታድነተው እንዲያዙ ሐምሌ 11 ቀን 1966 በሻለቃ መንግሥቱ ኃይለማርያም የተፈረመ ተዕዛዝ ቢሰጥባቸውም ሃምሳ አምስቱ የንጉሱ ከፍተኛ ሚኒስትሮች፤ ጄኔራሎች፤ እና ከፍተኛ ሃላፊዎች በፈቃዳቸው እጃቸውን የሰጡ ነበሩ፡፡ከሟቾቹ አንዱ የሆኑት ሌተናል ጄኔራል በለጠ አበበ መስከረም 22 ቀን 1967 ለጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ የፃፉት ማመልከቻ የሚከተለው ነው፡፡
ሰኔ 28 ቀን 1966 ከደርጉ ዘንድ ትፈለጋለክ ተብዬ በተነገረው ቃል ከቤቴ ያለአንዳች ጥርጣሬና ማወላወል ወደዚህ ክፍለጦር ያአንዳች አጃቢ በራሴ ፈቃድ ብመጣ ወደእስር ቤት እንድገባ ታዝዤ ያለአንዳንች ጥፋት ሳልጠየቅ ሶስት ወር ሙሉ በእስር ቤት እገኛለሁ፡፡…..
የደርጉን ሥራ የምታካሂዱት ባለሥልጣኖች ሚስቶችና ልጆች አላችሁ ብዬ ስለማምን እነሱን በምታስቡበት መንፈስ የኔንም ቤተሰብ ችግር እድትመለከቱልኝ አሳስባለሁ፡፡
እንኳን እናንተ ወንድሞቻችን ይቅርና ባዕድ የሆነው ኢጣሊያን እንኳን ሀገራችንን በወረረ ጊዜ እጃቸውን ሰጥተው ያሠራቸውን ሰዎች ንብረት ሣይዝ፣ በሚስቶቻቸው እና በልጆቻቸው እጅ ቆይቶ እታሠሩበት ድረስ ስንቅ ያቀብሉ እንደነበር ቢጠየቅ ግልጽ የሆነ ታሪክ ያው ነው፡፡ ስለዚህ አጥፊ ወይም ንፁህ መሆኔ በዳኝነት ታይቶ እስኪታወቅ ድረስ የተያዘው የቤቶቼ ኪራይና ሌላውም ንብረቴ እንዲለቀቅ ደርጉ ትዕዛዝ እዲሰጥልኝ በቅን ልቦና እለምናለሁ፡፡
ይሁን እንጂ ዳኝነት አልተገኘም፡፡ ያለጥያቄ ሶት ወር ለመታሠራቸው ሲያመለክቱ ሕይወታቸውን ያለፍርድ ተነጠቁ፡፡
ሌተናል ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም የቀድሞ ንጉሥ ቀዳማዊ የኃይለስላሴን ባለሥልጣናት ሰብስቦ አራተኛ ክፍለ ጦር ከአጎረ በኋላ ጥቅምት 11 ቀን 1967 በሰጠው የንቅናቄ ትዕዛዝ ወደታላቁ ቤተመንግሥት አንዲዛወሩ አደረገ፡፡ በወሩ ህዳር 14 ቀን 1967 በራሱ ሰብሳቢነት በደርጉ ስብሰባ አዳራሽ ውስጥ ተቀምጦ ከስብሰባው አዳራሽ በታች ምድር ቤትና ሌላም ቦታ ታስረው በነበሩ 59 ሰዎች ላይ የሞት ውሳኔ ጣት በማውጣት ምልክት ሰጥቶና አሰጥቶ አዲስ አበባ ወህኒ ቤት ውስጥ በጥይት እሩምታ አስፈጅቶ እሬሣቸው ላይ ኖራ አስነስንሶ አፈር እዲለብሱ አደረገ፡፡
ሟቾች በሠላማዊ መንገድ እጃቸውን የሰጡ በፍርድ ያልተረጋገጠባቸው ንፁሃን ሰዎች ነበሩ፡፡የፈፀሙት ወንጀል ቢኖር በምርመራ ተጣርቶ በሕግ መሠረት እንዲመራ መርማሪ ኮሚሽን ተቋቁሞ ነበር፡፡ ከመርማሪ ኮሚሽኑ ሊቀመንበር ለሌተናል ኮለኔል ደገፋ ማሬ በልዩ ጦር ፍርድ ቤት የዐቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት ሹም አድራሻ ተደርጎ ህዳር 11 ቀን 1967 የተፃፈ ደብዳቤ እንደሚከተለው ይነበባል፡፡
ከኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ ስተዳደር ደርግ ህዳር 6 ቀን 1967 በቁጥር አ/ደ/ቸ/6/2325 የተጻፈልንን ደብዳቤ እናስታውሳለን፡፡ በ1966 የመርማሪ ኮሚሽን አዋጅ አንቀጽ10 እንደተመለከተው ኮሚሽኑ ስለወሎ ድርቅ፣ረሃብና እልቂት ባደረገው ምርመራ መሠረት ከዚህ ጋር በተያያዘው አባሪ ላይ በተመለከቱት የመንግሥት ባለሥልጣናት ላይ ተለይቶ የተመለከተው የወንጀል ክስ እንዲቀርብባቸው እናስታውቃለን፡፡
አባሪው ላይ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ሲባል በግፍ ያለፍርድ ከተገደለት ውስጥ፣ ፀሐፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ፣ አቶ አካለወርቅ ሀ/ወልድ፣ ጄኔራል ከበደ ገብሬ ፣ ልጅ እንዳልካቸው መኮንን፣ አቶ ሙላቱ ደበበ ፣ ዶክተር ተስፋዬ ገብረእግዚ ይገኙበታል፡፡
አቶ ሰይፉ ማህተመ ስላሴና ደጃዝማች ካሣ ወልደማርያም በሌላ ዙር ከተገደሉት ውስጥ ናቸው፡፡ አነዚህ ያፍርድ የተገደሉ ባለሥልጣኖች በመርማሪ ኮሚሽን የምርመራ ውጤት መሠረት ይጠየቁበታል የተባለው ወንጀል በ1949 ዓ.ም በወጣው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ቁጥ 412 የሥራ ግዴታን ተግባር መጣስ እና ቁጥር 509 ችግር ወይም ረሃብ እንዲመጣ ማድረግ የሚል ነበር፡፡ የመጀመሪያው በሦስት ወር፣ ሁለተኛው ከሦስት እሰከ አስር አመት በሚደርስ እሥራት የሚያስቀጣ ነበር፡፡
የኮሚሽኑ ምርመራ ውጤት የታሠሩትን ባለሥልጣናት በከባድ ወንጀል የማያስቀጣቸው መሆኑን የተረዳው ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ዝም ብሎ አልተቀመጠም፡፡ለልዩ ጦር ፍርድ ቤት ዐቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት ህዳር 10 ቀን 1967 በጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ሁለተኛ ምክትል ሊቀመንበር በሌ/ኮለኔል አጥናፉ አባተ ፊርማ በተላለፍ ትዕዛዝ መርማሪ ኮሚሽን በዘዘው መሠረት ክስ እንዳይቀጥል ትዕዛዝ ተሠጠ፡፡ በአራተኛው ቀን 59 ሚኒስትሮችና ጄኔራሎች ያለፍርድ ተገደሉ፡፡ ቢቻል በፍርድ ቢሞቱ ጥሩ ነበር፣ ሕግ ካልገደላቸው እኛ እንገድላቸዋለን ተባለ፣ ሆነ፡፡
በ59ኙ ከፍተኛ ባለስልጣናት ላይም ማን ይገደል በሚለው ላይ ድምፅ መስጠት ተጀመረ በስበሰባው ላይ ከጠቅላላ የደርግ አባሎች፣ ከምስራቅ ንዑስ ደርግ አባሎች፣ ከሰሜን ንዑስ ደርግ እና ከፖሊስ ንዑስ ደርግ በአጠቃላይ 93ሰዎች ተሰበስበዋል፡፡ በዚህም መሰረት የመጀመሪያው ተጠሪ የነበረው የፀሃፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ሃብተወልድ ስም ሆነ በ93 ድምፅ እንዲረሸኑ ተወሰነ፡፡ በመቀጠልም እነ ጄነራል ከበደ ገብሬ፤ ሌተናል ጄነራል ድረሴ ዱባለ፣ ልዑል አስራተ ካሳ ጄኔራል ሌተናል አበበ ገመዳ፤ሪር አድሚራል እስክንድር ደስታ፤ራስ መስፍን ስለሺ ስማቸው እየተጠራ በአብዛኞቹ ላይ 93 ድምፅ ተሰጠ በእለቱ በተደረገው ድምፅ አሰጣጥ በ37ቱ ላይ በ93ድምፅ በሌሎቹ ላይ ከ92 እስከ 51 ድምፅ በሆነ ውሳኔ እንዲረሸኑ ተወሰነ፡፡ቀደም ሲል የደርግ አባላት ቁጥር በተለያዩ ምክንያቶች ቀንሶ 93 ደርሶ ነበር፡፡ በዚህ ስብሰባ ላይ የተገኙ 93 ነበሩ፡፡ በድምጽ አሰጣጡ ዝርዝር ከፍተኛው ድምጽ በ93 መቆሙ ይታያል፡፡ የስብሰባው ቃለ ጉባኤ በወቅቱ የደርግ ዋና ፀሐፊ በነበረው በሟቹ በሻምበል ገብረየስ ወልደሃና መጻፉ በፖሊስ ላብራቶሪ ምርመራ ተረጋግጧል፡፡ ስብሰባው እንዴት እንደተጀመረ፣ እደተመራና እንደተፈፀመ፣ ከደርግ አባላት ውስጥ እነማን እንደተገኙ ምንና እዴት እንደወሰኑ ምስክሮች ለፍርድ ቤት አስረድተዋል፡፡ በደርጉ የስብሰባ ቃለ ጉባኤ 2ኛ መዝገብ የሠፈረው የአፈፃፀም ቅደም ተከተል በአይን ምስክሮችም ተደግፏል፡፡
በውሳኔው መሰረትም አዲስ አበባ ወህኒ ቤት ተገኝተው ሞት የተወሰነባቸው ሰዎች ቅጣቱን በትክክል ማየታቸውን እነዲያረጋግጡ ዘጠኝ የደርግ አባላት ሲመረጡ የደርጉ የእስረኛ አስተዳደር ፣ የመከላከያ፣ የደህነነትና የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ እዲያስተባብሩ በደርጉ ጠቅላላ ጉባኤ ተወስኖ እርምጃው ተወሰደ፡፡
ህዳር 14 ማታ ቅልጥ ባለና የደርግን ወገን ባልለየ ተኩስ 59 ጄኔራሎችና ሚኒስትሮች ተገደሉ፡፡ ለመግደል ከተሠማሩት ወታደሮች ውስጥ ስድስት ቆሰሉ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን የደርግ አባላት ኮለኔል መንግሥቱ ኃይለማርያምን ጨምሮ ታላቁ ቤተመንግስት ውስጥ ስብሰባው ሣይበተን ቁጭ ብለው የግድያውን መፈፀም ሪፖርት ይጠብቁ ነበር፡፡
ጉዞ ወደ መረሸኛ
በእስር ቤቱ ውስጥ ታስረው የነበሩና ያንን እለት የሚያስታውሱት የልዩ አቃቤ ህግ ሁለተኛ ምስክር በዕለቱ የተፈጠረውን እንዲህ አስረድተዋል፡፡
“ ….. 12 ሰዓት በሚሆንበት ጊዜ በእስር ቤቱ ግቢ ውስጥ ከሌላው ቀን በተለየ ባውዛዎች ይበሩ ጀመር፡፡ ከምሽቱ አንድ ሰዓት አካባቢ ተጨማሪ የታጠቁ ወታደሮችና የእስር ቤት መኪናዎች መጡ እና አስር ቤቱ ግቢ ገብተው ቆሙ፡፡ በእለቱ የእስር ቤቱ በር በጊዜ ተዘግቶ ነበር፡፡ ክፍት በነበረው ቦታ ብርድልብስ ሸፈኑበት እና ወደ አንድ ቁጥር እስር ቤት ሔደው የእስረኞች ስም መጥራት ጀመሩ፡፡ ከአንድ ቁጥር እስር ቤትሃያ ሰዎችን ጠርተው አስወጧቸው እና እኔ ወደነበርኩበት ቁጥር 2 እስር ቤት መጥተው በሩን ከፈቱ፡፡ በዚህ ጊዜ ሻለቃ ጌታቸው ሺበሺ እና አብሮት የነበረ ስሙ የማላውቀው ወታደር ወረቀት ይዘው ከዚህ ውስጥ ሰዎች ስንጠራ ቶሎ ብላችሁ ውጡ አሉ እና መጥራት ጀመሩ፡፡ እነሱ ስም ሲጠሩ የእስረኞች ኃላፊ ዶ/ር ምናሴ ኃይሌና እኔ ምክትል ስለነበርን በር ላይ ቆመን ወደ ክፍሉ እያስተጋባን እስረኞችን መጥራት ቀጠልን፡፡ በእኛ ክፍል አብረን ታስረን ከነበርነው ውስጥ ሃያ ሰባት ሰዎች ተጠርተው ወጡና ከአንድ ቁጥር ከወጡ እስረኞች ጋር አደባለቁአቸው፡፡ወዲያው በሰንሰለት እያቆራኙ ያስሩአቸው ነበር፡፡ እስረኞች ሲወጡ ከእስረኞች ውስጥ ኮ/ል አለምዘውድ ተሰማን “መልካም እድል” ስላቸው “እባክህ እናውቀዋለን አሉኝ፡፡” ሌ/ጄ ደበበ ኃ/ማርያም ተጠርተው በር ላይ ደርሰው ወደ ውስጥ ተመልሰው ከእኛ ጋር ታስረው የነበሩ ከአክሱም የመጡ ንቡረእድ ገ/ስላሴ ፀሐይን “ይፍቱኝ” ብለው መስቀል ተሳልመው ወጡ፡፡ ልጅ እንዳልካቸው ታሞ ተኝቶ ስለነበር ስጠራው “ደሞ ምን ይሆን?” ብሎ ወጣ፡፡ አብዛኛው እስረኛ በቢጃማ ነበር የወጣው፡፡ ከነዚህ ውስጥ ልዑል አስራተ ካሳታመው እግራቸው እያነከሰ በቢጃማ ነበር የወጡት፡፡ ልብስ ይቀይሩ መድሃኒት ይያዙ ሲባል አሁን ይመለሳሉ ቶሎ ብለው ይውጡ በማለት አስወጡአቸው፡፡ እስረኞቹ ከወጡ በኋላ የኛ በር ተዘጋ፡፡ ወዲያው መኪኖቹ ተንቀሳቀሱና ሔዱ፡፡ እኛ ከታሰርንበት ውጪ ሌሎች አራተኛ ክፍለ ጦር ከነበሩ እስረኞች ውስጥ በእዛን እለት ኮለኔልይገዙ ይመኔን አይቻለሁ፡፡ እንዲሁም ስማቸውን ለመጥራት ብቸገርም እኛ ከታሰርንበት ውጭ ታስረው የነበሩ እስረኞችን አይቻለሁ፡፡ ሰዎቹ ይመለሳሉ ብሉን ስንጠብቅ ሳይመለሱ ቀሩ፡፡ በማግስቱ ጠዋት አንድ ቁጥር እስር ቤት ውስጥ ታስረው የነበሩ ወታደሮች BBC ሬዲዩ ጣቢያ ሲያዳምጡ ሰማን ከእስር ቤት የተወሰዱ ሰዎች ተገድለዋል በማለት ሲናገሩ ነበር፡፡ እንዲሁም ጠባቂ ወታደሮችም እርስ በእርሳቸው ስለሰዎቹ መገደል ሲያወሩ ሰማን የሚሉ እስረኞች ነበሩ።
ህዳር 16 ቀን 1967 ሰኞ እለት ጠዋት 3 ሰዓት አካባቢ የቁጥር 1 እና ቁጥር 2 እስር ቤት ተጠሪዎች ደጃዝማች ካሳ ወ/ማርያም እና ዶ/ር ምናሴ ኃይሌን የማናውቃቸው ወታደሮች ትፈለጋላችሁ ብለው ወሰዷቸውና ከግማሽ ሰዓት በኋላ ተመልሰው መጡና በየክፍላችን ሰበሰቡን። ህዳር 14 ቀን 1967 የተወሰዱት እስረኞ አብዮታዊ እርምጃ ተወስዶባቸዋል ማለትም ተገድለዋል። በተረፋችሁት ላይ ምንም ተመሳሳይ እርምጃ አይወሰድም በአጭር ጊዜ ውስጥ ቃላችሁን እየሰጣችሁ ትፈታላችሁ ብለን እንድንነግር ታዘናል በማለት የእኛ ሰብሳቢ ነገረን። ቁጥር 1 እስር ቤትም ይኸው ተገልጾላቸዋል። በማግስቱ ህዳር 17 ቀን 1967 ሻለቃ ጌታቸው ሺበሺ፤መቶ አለቃ ጴጥሮስ ገብሬ እና የማላስታውሳቸው ወታደሮች እስር ቤት መጠተው እስረኛውን ሰብስበው ትላንት ለእስረኛ ተጠሪዎች የገለጽነውን ከእኛ አፍ እንድትሰሙ ነው። በቀራችሁት ላይ ምንም ነገር አይወሰድም ጥፋት ቢገኝባችሁም በፍ/ቤት ቀርባችሁ በእስራትና በገንዘብ ትቀጣላችሁ። ጥያቄውም በትንሽ ቀናት ውስጥ ተጀምሮ ትለቀቃላችሁ። ይህንንም በእግዚአብሔር ስም አረጋግጥላችኋለሁ ብሎ ማለልን። ዝርዝሩን ከዚህ ላይ ተረዱት በማለት ለየክፍሎቹ አንዳንድ ጋዜጣ ዋናውን ሰጠን። ጋዜጣው ላይም ሰዎቹ ስለመገደላቸው ይገልፃል።
እስረኞቹን ሲወስዱ ከሻለቃ ሺበሺ ጋር ሻለቃ ካሳዬ አራጋው ‘መቶ አለቃ ጴጥሮስ ገብሬ’ ፍስሐ አንደቶ የተባሉት አብረው ነበሩ። የቀሩትን ወታደሮች አላውቃቸውም። እኛ ከታሰርንበት ቁጥር አንድ እና ቁጥር ሁለት እስር ቤት ዉስጥ በጠቅላላዉ የተወሰዱት አርባ ሶስት ሲሆኑ ጋዜጣዉ ላይ የተገለፁት ሰዎች ሃምሳ ዘጠኝ ናቸዉ። ከእኛ እስር ቤት ዉጪ ሌላ ቦታ ታስረዉ ከነበሩት እስረኞች ዉስጥ ጨምረዉ መገደላቸዉን ጋዜጣ ላይ በማንበባችን አዉቀናል።”
የ60 ሰዎች አስክሬን ደረሰኝ
ምሽቱን በትዕዛዙ መሰረት ሰዎቹ ተገደሉ። የወህኒ ቤቱ አባል ሻምበል ነጋሽ ማሞ የ60 ሰዎችን አስክሬን ተረክቦ ደረሰኝ ሰጠ። 60ኛው በዛው ዕለት ከደርጉ ጋር ተዋግተው እራሳቸውን የገደሉት የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ የመጀመሪያው ሊቀመንበር የነበሩት የሌ/ጄኔራል አማን ሚካኤል አንዶም አስክሬን ነበር።በግድያው ወቅት በተባራሪ ጥይት የቆሰሉ የደርግ ወገኖች ማንነት ተረጋግጦ በደርጉ የሕክምና መኮንን በመ/አለቃ እዳለ ገላን በኩል ሕክምና ተደረገላቸው።
ባለስልጣናቱ ላይ እነማን ተኮሱ?
ለደርጉ ሃላፊዎች አዲስ አበባ ወህኒ ቤት ግቢ ውስጥ በአካል ተገኝተው የአፄ ኃይለስላሴን ጄኔራሎችና ሚኒስትሮች ተኩሰው የገደሉ የደርግ አባላት ስም ዝርዝርና የተኮሱት ጥይት መጠን በሻለቃ ጌታቸው ሺበሺ ሪፖርት ተደረገ። በዚሁ መሠረት፣
ሻለቃ ጌታቸው ሺበሺ- 43 ጥይት
ሻምበል ተፈራ- 32 ጥይት
ሻምበል ኃይሌ መለስ- 25 ጥይት
ባሻ ተፈራ ጅፋር- 60 ጥይት
፶/አለቃ በቀለ ደጉ- 32 ጥይት
ፒ/ኦ ሚካኤል- 25 ጥይት
፶/አ ዳምጤ- 16 ጥይት
ወታደር ደጀኔ አ/አገኘሁ- 40 ጥይት
ወታደር ገ/ጊ ብርሃኑ- 50 ጥይት
ሻለቃ ባሻ ለማ ኩምሳ- 7 ጥይት
ም/፲/አ ግርማ አየለ-3 ጥይት
(በፌ.ከ.ፍ.ቤት ወነጀል መዝገብ ቁጥር 1/87(401/85) ውስጥ የ ልዩ አቃቤ ህግ ማስረጃ ድ.1.9.3)
በግድያው ላይ በጠቅላላው 393 ጥይቶች መተኮሳቸው ተረጋገጠ። ይህ ቁጥር በደርግ አባላቱ ብቻ የተተኮሰውን የሚያካትት እንጂ በሌሎች ወታደሮች የተተኮሰውን አይጨምርም።
የመጨረሻዋ ሰዓት ምን ትመስል ነበር?
ግድያው ሲፈፀም የነበረው የዓይን እማኝ ይናገራል
‹‹ ስራ ጨርሼ ከቀኑ አስር ሰዓት ስወጣ በር ላይ ትዝ እንደሚለኝ አስር አለቃ ገረመው እንዳትወጡ ተብለናል አለኝና ቆየሁ። አስራ አንድ ሰዓት ተኩል በሚሆንበት ጊዜ አስር አለቃው ከመሣሪያ ግምጃ ቤት ካቴና አውጡ አለንና አወጣን። ከዚህ በኋላ ሻምበል ባሻ ደጀኔ የሚያሽከረክረው እስረኛ ማጓጓዢያ ከባድ መኪና ውስጥ ግቡ ተባልንና ከገረመው ጋር ገባን። ሌሎች እነ እከሌ የማልላቸው ሁለት ወይም ሶስት የጦር ሰራዊት አባላት ጭምር ያሉባቸዉ መኪናዎች እየመሩን በግምት ከ12፡30 እስከ አንድ ሰዓት መካከል አራት ኪሎ ቤተመንግስት ገባን እንደገባን ቤተመንግስት ግቢ ዉስጥ ፎቅና ምድር ቤት ያለዉ ህንፃ ፊት ለፊት አዙሩና አቁሙ አሉን። መኪናዉ ቆመ ወረድን። አካባቢዉን ስናይ ባዉዛ ይበራል ፣ ፀሀይ ሆኗል። ዙሪያዉ በታንክ ተከቧል። ሚሊታሪ ፖሊስ በብዛት አለ። እኛ ከጠሪዎች ሶስት እርምጃ እርቀን እስረኞቹ ከምድር ቤቱ በየተራ በየስማቸዉ እየተጠሩ ወጥተዉ እኛ ዘንድ ሲደርሱ በተሰጠን ትዕዛዝ መሰረት የአንዱን እስረኛ ግራ እጅና የሌላኛውን እስረኛ ቀኝ እጅ አንድ ላይ በማድረግ በካቴና እናቆራኛቸዋለን። ከዚያ በኋላ መኪና ላይ ሚሊታሪ ፖሊሶች ያሳፍራሉ። በዚህ አይት በግምት ከሀምሳ በላይ ሰዎች ተቆራኝተዉ መኪና ላይ ተጫኑ፣ መኪና ዉስጥ ገባንና ጉዞ ተጀመረ።”
የሟቾቹ ሚኒስትሮች እና ጄኔራሎች የመጨረሻ ቃል ምን ነበር?
“በጉዞ ላይ እስረኞቹ የትነዉ የሚወስዱን ወቴ ሲሉኝ እኔም አላወኩም አልኳቸው። ሜክሲኮ አደባባይ ደርሰን ወደ ወህኒ ቤት መስመር መኪናዉ ሲጠመዘዝ ደስታ ተሰማቸዉና ወህኒ ቤት ከገባን ጥሩ ነዉ ቤተሰቦቻችንም ይጠይቁናል ብለዉ ተወያዩ።ጉዞ ቀጠለና የአዲስ አበባ ወህኒ ቤት ግቢ በር ተከፍቶ መኪናው እስረኞቹን እንደያዘ ሲገባ በመኪናው መብራት ሳንጃ ያለው መሳሪያ ይዘው የተደረደሩትን ወታደሮች እስረኞቹ ሲያዩ በመደናገጥ ተንጫጩ። ራስ መስፍን ስለሺ ‹ይህ ባርያ ሊፈጀን ነው› ‹ለፍርድ ሳንቀርብ፣ፈርድ ይታይልን› እያሉ ጮኹ። ሌሎቹም ተንጫጩ ፤ አስተጋቡ ። መኪናው ወደፊት ሄደና አዙሮ ቆመ። እስረኞች ወርደው በሰልፍ መደዳ የህንፃው ግንብ ከኋላቸው ሆኖ ቆሙ። የመኪና መብራት ይበራባቸዋል። ፊሽካ ድምፅ ተሰማ፡፤ ማን እንደነፋው አላውቅም። ሁለት ጊዜ እንደተነፋ ተኩስ ተከፈተ። ተኩስ የተከፈተው በተደረደሩት እስረኞች ላይ ነው። በርቀት ግቢ ውስጥ ምንም መሣሪያ ሣንይዝ በማናውቀው ሁኔታ በተፈጠረው ተኩስ ተደናግጠን እያለን በጥይት ጭንቅላቴን ተመታሁ። ሆስፒታል ገባሁ ከዚህ በኋላ የሆነውን አላውቅም።”
“መጀመሪያ እኔን ግደሉኝ”
-ኮሎኔል ያለም ዘውድ ተሰማ
ስለ ግድያው አፈፃፀም ኮሎኔል ተስፋዬ ወ/ስላሴ ሰብሳቢው አጠገብ ሆኖ ሂደቱን በመገናኝ ሬዲዮ ይከታተል ነበር። በስተመጨረሻም የግድያው ዋና አስፈፃሚ ሻለቃ ጌታቸው ሺበሺ ከተገዳዮቹ መካከል ኮሎኔል ያለም ዘውድ ተሰማ እየፎከሩ “መጀመሪያ እኔን ግደሉኝ” እንዳሉ ጄኔራል አሰፋ አየነ “እጠቅማችኋለሁ አትግደሉኝ” እንዳሉ ከርሸናው በሁዋላም ቀብራቸው መፈፀሙን ሪፖርቱን ለጉባኤውአቀረበ። ታሪክም እያንዳንዷን መዝግቦ እንዲህ አኖረ።

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *