እንኳን ከዘመነ ማርቆስ ወደ ዘመነ ሉቃስ አሸጋገረን
የኢትዮጵያ ትሪቡን
እንቁጣጣሽ · ዘመነ ሉቃስ ፳፻፲፱
እንኳን ከዘመነ ማርቆስ ወደ ዘመነ ሉቃስ አሸጋገረን
የልዑል ኤርሚያስ ሣህለ ሥላሴ ኃይለ ሥላሴ የአዲስ ዓመት መልእክት · ፳፻፲፱ ዘመነ ሉቃስ ወንጌላዊ
የኢትዮጵያ ትሪቡን የልዑል ኤርሚያስ ሣህለ ሥላሴ ኃይለ ሥላሴን — የኢትዮጵያ ዘውድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት — የ፳፻፲፱ ዓ.ም. (ዘመነ ሉቃስ) የአዲስ ዓመት መልእክት ሙሉ በሙሉ ለንባብ አብቅቷል።
በዓለም ዙርያ ለምትገኙ ክቡራን እና ክቡራት የውድ ሀገራችን ኢትዮጵያ ልጆች በሙሉ እንኳን ከ፳፻፲፰ ዘመነ ማርቆስ ወደ ፳፻፲፱ ዘመነ ሉቃስ አሸጋገረን። እንደ አምናው በዘንድሮም ዘመን መለወጫን በምናከብርበት ጊዜ ኢትዮጵያ እና ወገኖቻችን ኢትዮጵያውያን የምንመኛቸው ብዙ ነገሮች አሉ። ዘመን በዘመን ሲተካ ወደሗላ ስንመለከት በአለፈው ዓመት በስኬት የፈጸምናቸው ድርጊቶች ሊያስደስቱንና ያልተሳኩልንንም ስናስብ ትምህርት እንዲሆኑን ይገባል። ያለፍናቸው የደስታ እና የሐዘን፥ የስራ እና የእረፍት፥ የምኞት እና የስኬት፥ ግዜዎችን እያስተዋልን ፈጣሪ አምላክን ማመስገን ይገባል። የእንቁጣጣሽ በዓል መሰረቱ ታላቋ ማክዳ ንግሥተ ሳባ ከእየሩሳሌም በተመለሰችበት ግዜ መሳፍንቶቿ “እንኳን በደህና ተመለሽ” ለማለት የእንቁ እና የከበሩ ጌጣጌጥ በስጦታ ስለ ሰጥዋት ነው። ይህ የዘመን መለወጫ በዓል እና የዓመታት፥ የወራት፥ የቀናት፥ የሰዓት፥ አቆጣጠራችን ከጥንት አባቶቻችን ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የሚያኮራ ልዩ ባሕላችን ነው። የኢትዮጵያዊነት ልዩ ኩራታችን ነው። ለዚህም ሁሉ የሚያኮራን እና ስማችንን ለሚያስጠራ ልዩ የሆነ የአገር ባሕል እና ሥርዓት አባቶቻችንና እናቶቻችንን ከሁሉም በላይ ፈጣሪን ማመስግን ተገቢ ነው።
ዘመን ሲለዋጥ ያለፈውን በማጤን እና አምላክን በማመስገን፥ የሚመጣውንም በተስፋ እና በጸሎት መቀበል የቆየ ልማዳችን ነው።
ዘመን ሲለዋጥ ያለፈውን በማጤን እና አምላክን በማመስገን፥ የሚመጣውንም በተስፋ እና በጸሎት መቀበል የቆየ ልማዳችን ነው። ከሁሉም በላይ በዚህ በአዲሱ ዓመት ለአገራችን እና ለሕዝባችን ሰላምን እንዲያወርድልን እግዚአብሔርን መለመን ተገቢ ነው። ጦርነት መከፋፈል እና ችግር እጅ ለ እጅ ተያይዘው በኢትዮጵያ ምድር ለበርካታ ዘመናት እምባ እንድናፈስ እና በስደት እንድንበተን አድርጎናል። ይህ እንዲቆም ሰላሙን ፍቅሩን አንድነቱን እና በረከቱን ፈጣሪ እንዲመልስልን መለመን ይገባናል። የዓለም ሰላም በደፈረሰበት እና የኑሮ ውድነት ባየለበት በዚህ አስቸጋሪ ግዜ ከኛ በባሰ ሁነታ ላይ ላሉ ሰዎች በቻሉት መጠን መርዳት ሀለዚያም በጸሎት እና በሐሳብ መደገፍ የሁላችንም ተግባር መሆን ይገባዋል።
ይህ አዲስ ዓመት ለአገራችን ለኢትዮጵያ እና ለልጆቿ እንዲሁም ለመላው ዓለም የሰላም የጤንነት የመታደስ ያድርግልን። ዘመነ ሉቃስ ፳፻፲፱ ዓመተ ምህረትን ልዑል እግዚአብሔር ይባርክልን ለዓመት ዓመት ያድርሰን።
— ልዑል ኤርሚያስ ሣህለ ሥላሴ ኃይለ ሥላሴ
የኢትዮጵያ ዘውድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት
በኢትዮጵያ ትሪቡን የታተመ · እንቁጣጣሽ ዘመነ ሉቃስ ፳፻፲፱
