img_6204
0 0
Read Time:10 Minute, 12 Second


የወያኔ ተስፈኞች ቁማር፦ ርዕዮተ-ዓለማዊ ገዳይን ለጊዜያዊ ጥቅም የመቸብቸብ አደጋ

«የጽምዶ ግብዝ መሪና ዕውር ተከታይ»

በዶክተር ሶስና ታደሰ — በፖለቲካ ሳይንስ እና በስትራቴጂያዊ ጥናት

«የጽምዶ ግብዝ መሪና ዕውር ተከታይ» — The Cynical Leader and Blind Follower of Tsimdo
«ዓይንህን ካልገለጥክ፣ ሌላ አካል የአንተን መንገድ ይወስነዋል!»

የዋና አዘጋጁ መቅድም

የኢትዮጵያ ትሪቡን አንባቢዎች፦ ወቅታዊውን የ«ጽምዶ» ጥምረት ውዝግብ አስመልክቶ አዘውትረው ምሁራዊ ድምጻቸውን ከሚያበረክቱልን መካከል አንዷ የሆኑት ዶክተር ሶስና ታደሰ፣ የተሻሻለና የተስተካከለ የአስተያየት ትንተና (Op-Ed) ልከውልናል። ጽሑፉ ከዚህ ቀደም በዶክተር ሲሳይ ሙሉ «ጊዜያዊ እፎይታ ለዘላቂ ኪሳራ? በፋኖ እና ህወሓት ጥምረት ዙሪያ ያለ ስትራቴጂካዊ ምልከታ» በሚል ርዕስ በ«ቦርከና» የአስተያየት መድረክ ላይ የቀረበውን መከራከሪያ በቀጥታ የሚመልስ ሆኖ፣ ጉዳዩን ከፖለቲካ ሳይንስ ማዕቀፍ አኳያ ይፈትሻል።

ጸሓፊዋ በዚህ ትንተናቸው፦ በዶክተር ሲሳይ መከራከሪያ ውስጥ ያሉ አራት አበይት የፅንሰ-ሐሳብ ድክመቶችን በምሁራዊ መንገድ ይመረምራሉ፤ የአንዳርጋቸው ጽጌን ቀደም ያለ የቃል ምስክርነትና የአሁኑን የትርክት መዋዠቅ ጎን ለጎን ያስቀምጣሉ፤ ርዕዮተ-ዓለማዊ ገዳይን ለጊዜያዊ ጥቅም አጋር የማድረግን አደጋ በ1927ቱ የሻንጋይ ጭፍጨፋና በ1804ቱ የሰርቢያውያን የሕልውና ተጋድሎ ታሪካዊ ማነጻጸሪያዎች ያስረዳሉ፤ ለአማራ ሕዝብና ለፋኖ አመራሮች «ዓይኑን የጨፈነ መሪና ተከታይ» የሚለውን ሥነ-ልቦናዊ ወጥመድ በመጠቆም ስልታዊ የመውጫ መንገዶችን ያመላክታሉ።

እንደተለመደው፣ በዚህ ጽሑፍ የሰፈሩት ሐሳቦችና ድምዳሜዎች የጸሓፊዋ የግል አመለካከቶች እንጂ የኢትዮጵያ ትሪቡንን የአርትዖት አቋም የግድ አይወክሉም። — የኢትዮጵያ ትሪቡን የአርትዖት ክፍል


በቅርቡ በ«ቦርከና» ነፃ አስተያየት መድረክ ላይ «ጊዜያዊ እፎይታ ለዘላቂ ኪሳራ? በፋኖ እና ህወሓት ጥምረት ዙሪያ ያለ ስትራቴጂካዊ ምልከታ» በሚል ርዕስ በዶክተር ሲሳይ ሙሉ የቀረበው ጽሑፍ፣ የ«ጽምዶ»ን አክሳሪነት በፖለቲካ ስሌት መዝኖ ለማሳየት የሞከረና ጥምረቱን የተቃወመ ቢሆንም፤ የችግሩን መዋቅራዊ፣ ርእዮተ-ዓለማዊና ሞራላዊ ጥልቀት ሙሉ በሙሉ ወደ ጎን የተወ፣ ጉዳዩን ከሰማዕታት ደምና ከአማራ ሕልውና አውርዶ እንደ ተራ «የንግድ ስሌት» ያቀለለ ትንተና ሆኖ አግቼዋለሁ።

ሕወሓት (ፋሽስት ወያኔ) የትናንት የደምና የእልቂት ታሪክ ብቻ አይደለም፤ የዛሬም፣ የነገም፣ የዘወትርም የሕልውና ጠላት ነው! ሕወሓት አማራን ማጥፋትንና የዐጽመ-ርስቱን መሬቶች መዋጥ የፖለቲካ እስትንፋሱና የሕልውናው መሠረት አድርጎ የተፈጠረ፣ በዚያው ዓላማ የኖረ፣ አሁንም በራያ፣ በጠለምት፣ ሁመራ/ሸረሪና እና በየግንባሩ ጦር እየሰበቀ ያለ መዋቅራዊና ዘላቂ ጠላት ነው።

ይህንን አሁናዊና ዘላቂ ጠላት የሆነ ኃይል፣ «የአማራ ትግል አጋር» አድርገው ለማቅረብ ለሚሞክሩ አድርባዮች ምሁራዊ ሽፋን መስጠትም ሆነ ጉዳዩን ወደ ተራ «የትርፍና ኪሳራ ሂሳብ» ማውረድ፣ በድፍን አማራ ሕዝብ፣ በሰማዕታት አጥንትና በታሪካዊ ክስተት ላይ የተፈጸመ ከባድ የፖለቲካ ወንጀል በመሆኑ በዝምታ የሚታለፍበት ጊዜ አክትሟል።

ሕወሓት የትናንት የደምና የእልቂት ታሪክ ብቻ አይደለም፤ የዛሬም፣ የነገም፣ የዘወትርም የሕልውና ጠላት ነው!

፩. የዶክተር ሲሳይ ጽሑፍ አራት መዋቅራዊ ክፍተቶች (Conceptual Flaws)

የዶክተር ሲሳይ ትንተና በውጤቱ ደረጃ የፋኖ እና ሕወሓት ጥምረትን አውዳሚነት ለመጠቆም ቢሞክርም፣ ከርእዮተ-ዓለምና ከሞራል አኳያ የሚከተሉት አራት አደገኛ ክፍተቶች ተስተውለውበታል፦

፩. ጉዳዩን ወደ ተራ «የትርፍና ኪሳራ የንግድ ስሌት» ማውረድ፦ ዶክተር ሲሳይ የጥምረትን ቅቡልነት ለመመዘን ያቀረበው መለኪያ “ዛሬስ እያንዳንዱ ወገን ከጥምረቱ ምን ያተርፋል? ምንስ አሳልፎ ይሰጣል?” የሚል የንግድ ድርድር የሚመስል ስሌት ነው። የአማራ ሕዝብ የሕልውና ተጋድሎ ግን የሞራል እና የመርህ ጉዳይ እንጂ፣ በሰማዕታት ደም ላይ የሚደረግ የትርፍና ኪሳራ የሂሳብ ማወራረጃ ቁማር አይደለም።

፪. የርእዮተ-ዓለም እና የስትራቴጂ መደራረብ (Confusing Ideology with Tactics)፦ በፖለቲካ ሳይንስ «ቋሚ ጠላት የለም» የሚለው መርህ ለታክቲክና ለስትራቴጂ እንጂ ለርእዮተ-ዓለም አይሰራም። የዐማራ ሕዝብ የሕልውና ትግል ርእዮተ-ዓለም (የዐማራ ብሔርተኝነት) ደግሞ የዐማራን ዘር ማጥፋት ከፈጸሙና የሐሰት ትርክት ከገነቡ ኃይሎች ጋር መቆምን በቀይ መስመር ደረጃ በፅኑ ይከለክላል። ጉዳዩን ሙሉ በሙሉ ወደ «ጊዜያዊ ጥቅም» ስሌት ብቻ ማውረድ የትግሉን ሞራላዊ የበላይነት ያሳጣዋል።

፫. «ነገ የኃይል ሚዛኑ ቢቀየር ጥምረት ይቻላል» የሚል አደገኛ ቀዳዳ ይከፍታል፦ የዶር ሲሳይ መከራከሪያ “የበፊቱን በደል የሚያካክስ ጥምረት ከተፈጠረ… ጥምረቶች እንደሁኔታው እየተፈተሹ ቅቡልናቸው ሊመዘን ይችላል” የሚል አደገኛ ቀዳዳ ይተዋል። ይህ ማለት «ነገ ሕወሓት የተሻለ የሎጂስቲክስ አቅርቦትና ዋስትና ቢሰጥ ጥምረቱ ትክክል ሊሆን ይችላል» ወደሚል የክህደት መንደርደሪያ ይመራል። እውነተኛ የአማራ የሕልውና ተጋድሎ ግን «ሕወሓት ወንጀሉን አምኖ ሳይቀበል፣ የሐሰት ትርክቱን ሳያፈርስና ወርሮ የያዛቸውን ርስቶች ሙሉ በሙሉ ሳያስረክብ ምንም ዓይነት ጥምረት በምድር ላይ ሊኖር አይችልም» በሚል ፅኑ መርህ ላይ ይቆማል።

፬. የታሪክ በደልን ማለስለስ (Softening Structural Genocide)፦ ጽሑፉ የዘር ማጥፋትና የወረራ ታሪክን “የታሪክ በደል እና ቅሬታ ብቻ ጥምረት ለመፍጠር ብቸኛ መስፈርት አይደለም” በማለት ያቃልላል። በሕወሓት የተፈጸመው ግማሽ ክፍለ-ዘመን የዘለቀ የዘር ማጥፋት፣ የወልቃይትና የራያ ወረራ እንዲሁም መዋቅራዊ ጭፍጨፋ እንደ ተራ «የቀደመ የታሪክ ቅሬታ ወይም ቁስል» ተደርጎ ሊወሰድ አይችልም።

በጥቅሉ ሕወሓት፣ በእርሱ ዘንድ “ቋሚ ወዳጅ፣ ቋሚ ጠላት የለም” የሚለው ዓለም አቀፋዊ የፖለቲካ መርህ አይሰራም። ዛሬም አማራን ቋሚ ጠላቱ አድርጎታል፤ በ1968ዓ.ም. በማንፌስቶው ላይ ያሰፈረውን ጠላትነት በቋሚነት ይዞት ዘልቋል። አቅምና እድል ባገኘበት ጊዜ ሁሉ አማራ ላይ የጥፋት ሰይፉን መዝዞ አጥቅቶታል።

ሕወሓት የሃምሳ ዓመት ደመኛ ጠላትነት የተከለ ኃይል ነው። ዛሬም ጊዜና ሁኔታዎችን አስልቶ በአማራ ሕዝብ ላይ የጭካኔ ሰይፉን እንደሚመዝ እየታወቀ፣ ከዚህ ኃይል ጋር ሊኖር የሚችልን ጥምረት በትርፍ እና ኪሳራ መልኩ የንግድ ችርቻሮ አስመስሎ ማቅረብ ኢ-ፍትሐዊነት ነው። ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት የአማራ ሕዝብ ሲዋደቅላቸው የኖረው ራያ አላማጣ፣ ራያ ኦፍላ፣ ኮረም፣ አበርገሌ፣ ወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ታሪካዊ ርስቶቻችን በሁኔታዎች የማይቀያየሩ፣ ቋሚና ዘላቂ የማንነት እና የክብር ጉዳይ ነው። እነዚህ ታሪካዊ የአማራ ርስቶች የግዛት ሁኔታ እና የአማራ ሕዝብ ሥነ-ልቦናዊ ስሪት የሚወሰኑ የዕጣ ፈንታው ወሳኝ ጉዳዮች በመሆናቸው ጥምረትን በትርፍ እና ኪሳራ መልኩ ለማስረዳት መሞከር በሕልውና ትግሉ ላይ የሞራል የበላይነትን የሚያሳጣ ጉዳይ ነው።

፪. የወያኔ ተስፈኞች፣ የትርክት ክህደት እና የአንዳርጋቸው ፅጌ የራስ-ተቃርኖ ምስክርነት

ዛሬ ልባቸውንና ጉንጫቸውን አሳብጠው ሚዲያ ላይ እየወጡ ፋሽስት ወያኔን እንደ አማራ «ትግል አጋር» እንድንቀበለው የክፍለ ሕዝብ ስራ የሚሰሩ፣ የዘመኑ ሴኮቱሬዎች፣ አብዛኞቹ የዛሬዋን “የጥፋት ኢትዮጵያ” የፈጠረውን የፋሽስት ወያኔ አገልጋይ የነበረው አቋም ያልለቀቃቸው፣ በአማራ ሕልውና ተጋድሎ ላይ ተጣብቀው የተቀመጡ የሥልጣን ተስፈኞች ናቸው። እነዚህ ተስፈኞች ከ50 ዓመታት በላይ በአማራ ሕዝብ ላይ በቀጥታ መዋቅራዊ እና የቡድን ጥቃቶች ሲፈጸሙ፤ አንድም በዝምታ ውስጥ ነበሩ፤ አንድም የጥፋት ታሪኩ ተጋሪ ናቸው። በዝምታም ሆነ በተሳትፎ ሲያስፈጽሙ የኖሩትን የዘር ማጥፋት፣ ወረራ፣ ማፈናቀልና መዋቅራዊ ጭፍጨፋ «የቀደመ የታሪክ ቅሬታ» አድርገው ማቀለላቸው ትልቅ የሞራልና የመርህ ውድቀት ነው።

የሚገርመው ግን፣ የዚሁ የ«ጽምዶ» አጀንዳ ዋና አራጋቢ የሆኑት እነ አንዳርጋቸው ፅጌ ራሳቸው፣ ገና ከአራት ዓመታት በፊት ሕወሓት (TPLF) ለአማራ ሕልውናም ሆነ ለሀገር ድርድር የማይበጅ ፍጹም ተላላኪና አረመኔ ቡድን መሆኑን በይፋ የመሰከሩት ምስክርነት ዛሬ ላይ ትልቅ የታሪክ ፍርጃ ሆኖባቸዋል።

አንዳርጋቸው በወቅቱ የሕወሓትን መዋቅራዊ የክህደት ባሕሪ ሲያጋልጥ በቁጭት እንዲህ ብሎ ነበር፦

«ወያኔዎች በታሪካቸው ከተመሠረቱበት ጊዜ ጀምሮ ከማንኛውም ድርጅት ጋራ በውይይት እና በድርድር የፈቱት ችግር የላቸውም… ስምምነት የገቡትን ሰዎች በተኙበት በማረድ ነው የጀመሩት… ሌሊት በተኙበት የሰሜኑን እዝ እንዳረዱት ማለት ነው። … እነሱ የማይቆጣጠሩት፣ የበላይነትን የማያገኙበት ምንም ነገር አይፈቅዱም።… ይህንን ከፍተኛ የበላይነት ተጠቅመው ከአማራ ክልል እንደ ወልቃይት ዓይነቱን እና ራያን የመሳሰሉ ቦታዎች በጉልበት የወሰዱ ሰዎች ናቸው። እነዚህ ሰዎች ከዚህ ከፍተኛ በጉልበት ያገኟቸውን የበላይነት ዝቅ ወደሚያደርግ ድርድር ለመግባት ፈቃደኛ አይደሉም።»

ይህ ራሱ አንዳርጋቸው በአንደበቱ የመሰከረው ሀቅ ፍጹም የማይታበል እውነት ነው። ሕወሓት ትናንትናም ሆነ ዛሬ ጦር የሚያዘጋጀውና የሚሰብቀው ለሁለት ዓላማዎች ብቻ ነው፦

  • አማራን በማንነቱ ማጥፋት፣ ማውደም እና የበላይነቱን መልሶ መጫን፤
  • የአማራ አጽመ-ርስት የሆኑትን ወልቃይትን፣ ጠገዴን፣ ጠለምትን፣ ሁመራን፣ ኮረምን፣ አላማጣን፣ ዋጃን፣ መሆኒንና መላውን የራያ ወረዳዎች በጉልበት ወርሮ «ታላቋን ትግራይ» መመሥረት።

ነገር ግን ዛሬ ላይ የገጠመን ትልቁ የትርክት ክህደትና የፖለቲካ ቁማር—የዚሁ ምስክርነት ባለቤት የነበሩት አንዳርጋቸው ፅጌ ራሳቸው፣ ዛሬ አቋማቸውን በ360 ዲግሪ ገልብጠው— ሕወሓት «ጥያቄዎቹን ከአብይ ተወግዶ ሰላምና መረጋጋት በሚፈጠርበት ሰአት ላይ በውይይት የሚፈታ አጀንዳ ነው የሚል አቋም ወስደዋል» በማለት የሕወሓትን የዳግም ወረራናና የርስት ፍላጎት በይፋ ሲቀበሉ እና የሰሜን እዝ የታረደበትን የክህደት ቢላዋ በፋኖ አንገት ላይ ለመድገም ሲጣደፉ መታየታቸው ነው።

አማራ በየግንባሩ የመሳደድ፣ የማፈናቀልና የመጨፍጨፍ የሕልውና አደጋ ተጋርጦበት ባለበት ተጋላጭ ወቅት፣ አጋጣሚውን ተጠቅመው የትናንት የክህደት ታሪኩን የዘነጉለትን የሕወሓትን የልብ ትርታ በመከተል የወልቃይትንና የራያን አጽመ-ርስት አሳልፎ ለመስጠት መጣደፍ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰማዕታት ደም የፈሰሰበትን ታሪካዊ ርስት እንደ «የሰሊጥ መሬት ፍላጎትና የኢኮኖሚ ጥቅም ሽኩቻ» አድርጎ ለማንኳሰስ መሞከር የለየለት የታሪክ ክህደት እና የወያኔ ተስፈኞች ተላላኪነት ማረጋገጫ ነው። ትናንት «ስምምነት አድርገው በተኙበት ያርዳሉ» ተብሎ የተመሰከረባቸውን ኃይሎች ዛሬ «የአማራ አጋር» አድርጎ ለማቅረብ መሞከር፣ የዐማራን ሕዝብ አውቆ ወደ ማረጃ ቤት የመንዳት ያህል ከባድ የፖለቲካ ወንጀል ነው! ከዚህ ላይ ገና ከጅምሩ ሕወሓትን ይቃወማሉ የተባሉ የፋኖ አመራርችና ተዋጊ ሀይሎች በተጠና መንገድ ተመርጠው መገደላቸውን እና ከትግሉ ሜዳ ገለል እንዲሉ መደረጋቸውን ሳንረሳ ማለት ነው።

፫. የርዕዮተ-ዓለም ቀውስ፦ የጥቅም ስሌት ከሞራልና ከመርህ በላይ ሊሆን አይችልም!

በታሪክ እንደታየው—የራሱ መዋቅራዊ የጥፋት አጀንዳ ያለውን ርእዮተ-ዓለማዊ ገዳይን ለጊዜያዊ የፖለቲካ ጥቅም «አጋር» ማድረግ መጨረሻው የከፋ ውድቀት እና የራስን አንገት ለሳንጃ ማመቻቸት ነው። የዛሬው የ«ጽምዶ» አራጋቢዎች የሚያቀርቡትን ዓይነት «የጋራ ጠላትን ለማጥፋት ጊዜያዊ ስልታዊ ጥምረት መፍጠር ያዋጣል» የሚለውን የሞኝ ስሌት በታሪክ ትልቅ ማረጋገጫ ያለው የሚከተለውን የዓለም አቀፍ የታሪክ ማስረጃ እንመልከት፦

የ1927ቱ የአንደኛው የቻይና ግንባር ማክተሚያ (The Shanghai Massacre)፦ በወቅቱ የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ በማዕከላዊ መንግሥት ላይ የነበሩትን አምባገነን የጦር አበጋዞችን (Warlords) ለመጣል ሲል፣ መዋቅራዊ ጠላቱ ከነበረውና ሥር ከሰደደው ብሔረተኛው ኩኦሚንታንግ (KMT) ፓርቲ ጋር «የመጀመሪያው የጋራ ግንባር» በሚል ስልታዊ ጥምረት ፈጥሮ ነበር። ነገር ግን የጋራ ጠላታቸው እንደተዳከመ እና ጥምረቱ ለብሔረተኞቹ አስፈላጊነቱ ሲያበቃ፣ በጥምረቱ ሰበብ የኮሙኒስቶቹን አደረጃጀት፣ የስምሪት ምሥጢር እና ድክመት በቅርበት በሚገባ ያጠናው የብሔረተኛው ጦር መሪ ቺያንግ ካይ-ሼክ፣ በ1927 በሻንጋይ ከተማ ውስጥ ትናንት አብረውት በጋራ የተሰለፉትን አጋሮቹን ላይ ድንገተኛ፣ የከሃዲነት እና አረመኔያዊ ጥቃት ሰነዘረ። በጥቂት ቀናት ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ የኮሙኒስት ታጋዮችን እና አመራሮችን በአሰቃቂ ሁኔታ ጨፈጨፋቸው። ይህም ለረጅም ዓመታት ለዘለቀው እና በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ዜጎች እልቂት ምክንያት ለሆነው የቻይና የእርስ በእርስ ጦርነት ቀጥተኛ መነሻ ሆነ።

ይህ የታሪክ ጥቁር ጠባሳ ዛሬ ላይ ለዐማራ ሕዝብ ሕልውና ተጋድሎ የሚያስተምረው አንድ ትልቅ መሠረታዊ ሀቅ አለ፦ ከመዋቅራዊ ጠላት ጋር የሚደረግ «ጽምዶ» መጨረሻው ጠላት ራሱን አደራጅቶ አንተን በምቾት እና ያለ ምንም ተከላካይ የሚጨፈጭፍበትን ወጥመድ በገዛ እጅህ ማዘጋጀት መሆኑን ብቻ ነው። አሁንም በየግንባሩ ጦር እየሰበቀ ያለውን፣ አማራን ማጥፋት እና መሬቱን መዋጥ መዋቅራዊ መታወቂያው ያደረገውን የዘወትር ገዳይ (ሕወሓትን) ለጊዜያዊ ጥቅም «አጋር» ማድረግ—ገዳዩን በራስ እጅ አጠናክሮ ራስን ለቀጣይ ይበልጥ ለከፋ እልቂት ማዘጋጀት ነው። ሕወሓት አሁናዊ የዘር ማጥፋት ወንጀሉን እና ፍላጎቱን በይፋ ሳይተው፣ የሐሰት ትርክቱን ሳያፈርስና ወርሮ የያዛቸውን ታሪካዊ ርስቶች (ራያን) በይፋ ሳይመልስ የሚደረግ ማንኛውም «ጽምዶ»—የርእዮተ-ዓለም ክህደት፣ የታሪክ መደለዝ እና የአማራ ሰማዕታት ደም ንግድ ነው!

፬. የመዋቅራዊ ትግል ባህሪ እና የታሪካዊ ማኅበረሰቦች ተሞክሮ፦ የአማራ ትግሕ የመውጫ መንገድ

ከሁሉም በላይ መታወቅ ያለበት መሠረታዊ እውነት ቢኖር፦ የአማራ ሕዝብ ስቃይና የዘር ማጽዳት አደጋ በደርግ ዘመን ጀምሮ የተቃኘ፣ በሕወሓት የእቅድና የትርክት መዋቅር የፀና እና በየስርዓቱ ተቋማዊ ድጋፍ ያለው እንጂ በአብይ አህመድ ዘመን ብቻ የጀመረ አይደለም፤ አብይ ከስልጣን ስለወረደም ብቻ አያበቃም!

ይህ ሀቅ የአማራ ሕዝብን የሕልውና ተጋድሎ የስልጣን ሽግግር ብቻ ከሚፈልጉ ሌሎች አምባገነንነትን ከሚቃወሙ ኃይሎች ይለየዋል። በመሆኑም የአብይ አገዛዝ ከስልጣን መወገድ የትግላችን አንዱ ጊዜያዊ ውጤት እንጂ የትግላችን ስትራቴጂካዊ ግብ ተደርጎ መወሰድ የለበትም። ስትራቴጂካዊ ግባችን ፀረ-አማራውን መዋቅር፣ የሐሰት ትርክትና የዘር ማጥፋት ስጋት ከመሰረቱ መደምሰስና አማራዊ የሕልውና ዋስትናን ማስከበር ነው።

ዛሬ በአብይ አህመድ የኦሮሙማ አገዛዝ፣ በኦነግ/OLA እና በሕወሓት የተደገሰለትን የተደራረበ የህልውና አደጋ ለመቀልበስ፣ የአማራ ሕዝብ መውሰድ ያለበት ታሪካዊ ምሳሌ የሰርቢያውያንን የመጀመሪያ ታሪካዊ ተጋድሎ (The First Serbian Uprising – 1804) ነው። ሰርቢያውያን እንደ አማራ ሁሉ የሀገሪቱ መሠረትና ግዙፍ ማኅበረሰብ ሆነው ሳለ፣ በየአካባቢው በተደራጁ የታጠቁ አምባገነን ኃይሎችና የክልል የጦር አበጋዞች መዋቅራዊ የዘር ማጥፋት፣ የማፈናቀልና የካርታ ወረራ አደጋ ተደግሶባቸው ነበር።

ሰርቢያውያን ከዚህ ታሪካዊ አደጋ የዳኑት ከከሃዲዎች ጋር «ጽምዶ» በመፍጠር ወይም በተኩስ ማቆም ስም ታሪካዊ ርስታቸውን አሳልፎ በመቸብቸብ አልነበረም። ይልቁኑ በታሪክ ካራጆርጄ (Karađorđe) በሚባለው ቆራጥ መሪ ዙሪያ በመሰብሰብ፣ በየአካባቢው ተበታትነው የነበሩትን ሃይዱክስ (Hajduks) የተባሉትን የሕዝብ የሲቪል መከላከያ ኃይሎች (ልክ እንደ ወቅቱ የፋኖ አደረጃጀቶች) ወደ አንድ ወጥ፣ በጥብቅ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ዲሲፕሊን የሚገዛ ማዕከላዊ ዕዝ በመቀየር ነው።

በአሁኑ ወቅት ለአማራ ሕዝብ የሚያስፈልገው ታሪካዊ መስመር ይህ ነው፦

  • አማራዊ ዓላማና ራዕይ ያለው፣ በጥብቅ ዲሲፕሊን የሚመራና በጠራ ድርጅታዊ መዋቅር የተገነባ የጋራ ማዕከላዊ ዕዝ፤
  • እንደ ካራጆርጄ ዓይነት ከራሱ በላይ ለሆነ ታሪካዊ ዓላማ የቆመ፣ ቆራጥና ጀግና አታጋይ መሪ መፍጠር ብቻ ነው።

፭. «ግብዝ መሪና ዕውር ተከታይ»፦ የጥምረት ስም (ጽምዶ) እና የቀጠናው ቁማር

የፖለቲካ ሳይንስ እና የስትራቴጂ ጥናት እንደሚያስተምሩት፣ በአንድ የነፃነት ትግል ውስጥ ሊከሰት የሚችል ትልቁ አውዳሚ አደጋ «ግብዝ መሪና ዕውር ተከተይ» (The Cynical Leader and Blind Follower) የሚፈጥሩት ጥምረት ነው። እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት መሠረታዊ እውነት ቢኖር፦ የዚህ «ጽምዶ» አጀንዳ አራጋቢ የሆኑት የፋኖ የበላይ መሪዎች ዕውር አይደሉም! በተቃራኒው፣ እነሱ የራሳቸውን ሥልጣንና የግል ጥቅም ብቻ አስልተው፣ የአማራን ሕዝብ ደምና ታሪካዊ ርስት ለቀጠናዊ ፖለቲካ ቁማር አሳልፈው የሸጡ፣ በሰማዕታት አጥንት ላይ የሚነግዱ አደገኛ ግብዞች ናቸው።

ትልቁ አደጋ የሚመጣው፣ ከታችኛው መዋቅር ያለውና በታማኝነት የሚዋጋው እውነተኛው ታጋይና ተከታይ፣ የመሪዎቹን ግብዝነትና ሴራ ሳይረዳ፣ «ለጋራ ጠላት መውደቅ ነው» በሚል ስሌት ብቻ በዕውር ድንብር (blindly) የሚከተልበት ሁኔታ ሲፈጠር ነው። ይህ ግብዝ መሪው የሕዝብን ትግል ለጠላት አሳልፎ የሚቸበችብበት፣ ተከተዩ ደግሞ የራሱን ዓይን ሸፍኖ የሚነዳበት ጉዞ፣ የመጨረሻ መዳረሻው ወደ አደገኛ ገደል ብቻ ነው!

ዓይንህን ካልገለጥክ፣ ሌላ አካል የአንተን መንገድ ይወስነዋል!
If you don’t open your eyes, someone else will decide your path

የአማራ ፋኖ የታችኛው መዋቅር ታጋይና የአማራ ወጣት ዓይኑን ገልጦ የነዚህን ግብዝ መሪዎች የጽምዶ ሴራ ካላወገዘና የራሱን መስመር ካልቀረጸ፣ ሕወሓትና የወያኔ ተስፈኞች የሕልውናውን ጥፋት፣ የሕዝቡን አጽመ-ርስትና እጣ-ፋንታ አሳልፈው ለመቸብቸብ የራሳቸውን ውሳኔ ይጭኑበታል።

ይህ የ«ግብዝ መሪና ዕውር ተከተይ» መዋቅር የጽምዶ አራጋቢዎችን አድርባይነትና የፖለቲካ ነጋዴነት በጥቂት አረፍተ ነገሮች የሚያጋልጥ እጅግ የሚመጥን ሳይንሳዊ ማሳያ ነው! አማራ ከራሱ አማራዊ የሕልውና መርህ እና ከታሪካዊ ርስቱ ውጭ፣ መዋቅራዊ ከሆኑና ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከተመሰረቱ ፀረ-አማራ ድርጅቶች ጋር የሚፈጥረው አንዳችም አጋርነት አያስፈልገውም። አማራ በራሱ ነፃ የእዝ ቁጥጥር እና በጥብቅ ድርጅታዊ ዲሲፕሊን ላይ ጸንቶ ሲቆም፣ የትኛውንም ጠላት ድል የማድረግ ሙሉ ታሪካዊ አቅም አለው!

ማጠቃለያ፦ ለቦርከና አንባቢዎችና ለፋኖ አመራሮች የቀረበ ጥሪ

  • «ጽምዶ» በሐሰት፣ በተቃርኖና በወያኔ ተስፈኞች የስልጣን ጥም የተሰራ የካርዶች ቤት (House of Cards) በመሆኑ በድፍን አማራ ሕዝብ ዘንድ ውድቅ ሆኗል!
  • የጽምዶ ደላሎችና የወያኔ ተስፈኞች በአማራ ሕዝብ ስም የመደራደርና የመነገድ አንዳችም የሞራልና የታሪክ ውክልና የላቸውም!
  • የፋኖ አመራሮችና ታጋዩ ወጣት ይህንን መርህ አልባ «ጽምዶ» በይፋ በማፍረስ፣ የትግሉን ስትራቴጂካዊና ርእዮተ-ዓለማዊ ነፃነት ማስከበር አለባቸው!
  • የአማራ ሕዝብ አሸናፊነት የሚረጋገጠው ከነባርና ከዛሬም ድረስ ገዳዮቹ የዘወትር ጠላቶቹ ጋር በ«ጽምዶ» ስም በመንበርከክ ሳይሆን፣ በራሱ አማራዊ መርህ፣ በጥብቅ ድርጅታዊ ዲሲፕሊንና በታሪካዊ ርስቱ ማስከበር ላይ ጸንቶ ሲቆም ብቻ ነው!

ዶክተር ሶስና ታደሰ

The Ethiopian Tribune — ነፃ የአስተያየት መድረክ

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *