መደምሰስ ወይስ መገንባት? ጥፋት ወይስ ልማት? ጭለማ ወይስ ብርሃን?

0
0 0
Read Time:2 Minute, 29 Second

በቀለ ገሠሠ (ዶ/ር)

1ኛ/ መንደርደሪያ፤

እናት አገር ታማለች። ልጆችዋ ዘራቸዉና ኃይማኖታቸዉ እየተመረጠ እየተጨፈጨፉና እንደቅጠል እየረገፉ ናቸዉ። አቢያተ ክርስቲያናትና ገዳማት እየተቃጠሉ ናቸዉ። ታሪካዊ ቅርሶች እየተቃጠሉና እየተዘረፉ ናቸዉ። ማሳዎችና ምርቶች እየተቃጠሉና እየተመረዙ ናቸዉ። ትምህርት ቤቶችና ኮሌጆች እየተቃጠሉ ናቸዉ። ሕፃናት ጭምር ለጦርነት እየተማገዱ ይገኛሉ። በሌላዉ በኩል ደግሞ በየዕለቱ ለጆሮ የሚሰቀጥጡ ከንቱ ፉከራዎችና ቀረርቶዎች መስማት ሰለቸን። በአንዳንድ ቦታዎች ጭፈራዎችም ይታያሉ። በዚህ ሁኔታ ሰላምና ዕድገት ከቶ ሊመጣ አይችልም። በመቶዎችና በሺዎች ዓመታት ወደኋላ ይመልሰናል። እግዚኦ ብለን ተነስተን ዉድ አገራችንን የምናድንበትና ደጋጉን ህዝባችንን የምንታደግበት ጊዜ እንጂ የግል ጥቅም የምናሳድድበት፤ የምንጨፍርበትና የምንቀልድበት ሰዓት አለመሆኑን ተገንዝበን የየግላችንን መልካም አስተዋጽኦ እንድናደርግ በትህትና አሳስባለሁ።

2ኛ/ የዘር ማጥፋትና መጠፋፋት ለምን አስፈለገ?

በተለይ አማራዉና የኦርቶዶክስ ተከታዮች በወያኔ/ኢህአዴግ አምባገነን አስተዳደር ላለፉት 30 ዓመታት ቁም ስቅላቸዉን እንዲያዩ ተፈረደባቸዉ። በቤኒሻንጉል/ጉሙዝ፤ በወለጋ፤ በሰሜን ሸዋ፤ ወዘተ በመካሄድ ላይ ያሉትን አረመኔያዊ ጭፍጭፋዎች መስማት ይዘገንናል። ጭቁን አማራ የሠራዉ ምንም ኃጢያት ሳይኖር ለዚህ እንግልት መዳረጉ ከባድ ወንጀል ነዉ። ይባስ ብሉ እነርሱን ለመታደግ የሚደርስላቸዉ አካል መጥፋቱ እጅግ በጣም አሳሳቢ ሆኖ ቆይቷል። አንዳንድ ጽንፈኞች አማራ ካልጠፋ ሥልጣን መያዝ የሚችሉ አይመስላቸዉም። አንዳንዶች ደግሞ በዉሸት ትርክቶች የተመረዙ ናቸዉ። ዕዉነተኛዉን ሃቅ የሚያስጨብጥ ኃይል ጠፋ። በተለይ በወለጋ፤ በቤኒሻንጉል፤ በሰሜን ሸዋ፤ ወዘተ እየተካሄዱ ያሉት ጭፍጨፋዎች ቶሎ መቆም ይገባቸዋል። በዚህ ረገድ መንግሥትና የአገር መከላከያ ኃይሎች የሚጠበቅባቸዉን ግዳጆች እንዲወጡ መገፋፋት ያስፈልጋል። ምን እንደሚጠበቅ ሊገባኝ አልቻለም።

አሁን ደግሞ በትግራይ ክልል ዉስጥና አካባቢዎች (በተለይ በአማራና በአፋር ክልሎች ጭምር) የሚታዩት እልቂቶችና ዉድመቶች እጅግ በጣም ያሳዝናሉ። ደጋግመን እንደምናነሳዉ የወያኔን አስተዳደርና የትግራይን ንፁሕ ዜጋ ነጥሎ ማየት ያስፈልጋል። በርግጥ የወያኔ/ኢህአዴግ አመባገነን አስተዳደር በመላዉ ህዝባችን ላይ ታላላቅ ጉዳቶች አድርሷል። ወንጀለኞችን ለፍርድ ለማቅረብ ተብሎ በተቀሰቀሰዉ ጦርነት ብዙ ጉዳቶች እንደደረሱ ይሰማል። አሁንም መፍትሔዉ ቀላል ነዉ። በወንጀል የሚጠረጠሩ መሪዎች ይወገዱ። በነርሱ ምትክ ከህዝቡ መካከል ገለልተኞች ተመርጠዉ ጊዜያዊ አስተዳደር ይረከቡ። ስንት ሰዉ እስከሚያልቅ ድረስ ነዉ የሚጠበቀዉ? ግብዞች አንሁን። ትግራይና አማራ በመጠፋፋታቸዉ ትርፍ ይገኛል ብለዉ የሚያስቡ ጽንፈኞች ካሉ ተሳስተዋል። አንዱ ወድሞ አንዱ አይተርፍም፤ ችግሮቹ ይቀጣጠላሉ፤ ተያይዞ መጥፋትን ያስከትላል። በጭቁን ትግሬ፤ አማራ፤ አፋር፤ ወዘተ ህዝብ መካከል እርቀ ሰላም ይዉረድ። ምስኪን ወጣቶችን ለጦርነት መማገድ ትልቅ ኃጢያት ነዉ። ሕይወት ማጥፋት፤ ንብረት ማዉደምና ቅርሳቅርሶችን ማቃጠልና መዝረፍ ያሳፍራል። በተለይ አማራዉና ትግሬዉ ለብዙ ሺ ዓመታት በኃይማኖት፤ በጋብቻ፤ በታሪክ፤ በጉርብትና፤ ወዘተ ተሳስሮ የኖረ ህዝብ መሆኑ ባይረሳ መልካም ነዉ። የጂቡቲ መስመር ተከፍቶ ሰብዓዊ እርዳታ በተገቢዉ መንገድ እንዲደርስ ማረጋገጥ ያስፈልጋል። እርስ በርስ ለመጠፋፋት የዉጪ ጠላቶችን መጋበዙ ይቁም። የዉጪ ኃይሎች የሚቆሙት ለራሳቸዉ ጥቅም እንጂ ለኛ ህዝብ አለመሆኑ መታወቅ አለበት። በኢራቅ፤ በሶሪያ፤ በሊብያ፤ በአፍጋኒስታንና በኛም አካባቢ በኤርትራ ላይ የደረሰዉን አዉዳሚ ጣልቃ ገብነቶች መገንዘብ ያስፈልጋል።

3ኛ/ ዕድገት ለማምጣት፤

ሰላምና መረጋጋቶች ሳይኖሩ ዘለቄታ ያለዉ ዕድገት ሊመጣ አይችልም። ህዝብ እተጨፈጨፈና እየተፈናቀለ፤ ማሳዎችና እህሎች እየተቃጠሉ፤ የቤት እንስሳት እየተገደሉና እየተዘረፉ ስለኢኮኖሚ ዕድገት ማሰብ አይቻልም።

ከዚህ በፊት እጅግ በጣም ሲያሳስቡን የነበሩ ጉዳዮች የአየር ንብረት መለወጥ፤ የአፈር መሸርሸርና ጠፍነት፤ የእህል ምርትና የከብት እርባታ መቀነስ፤ የማገዶ እጥረት፤ የሃይቆች መበከልና መድረቅ፤ የጎርፍ ማጥለቅለቅ፤ የአዉሎ ንፋስ አደጋዎች፤ የብዝሃ ሕይወት መቀነስ፤ ወዘተ፤ ነበሩ። ዛሬ ደግሞ የሰዉ ሕይወት እራሱ የባሰ አደጋ ላይ መዉደቅ ተጨመረበት።

ገበሬ በሰላም ወጥቶ ካላረሰ፤ ነጋዴዉ በነፃ እየተዘዋወረ ካልነገደ፤ ተማሪዉ በሰላም ትምህርት ቤት ገብቶ ካልተማረ የአገር ኢኮኖሚ ዕድገት አይታሰብም። የተለመደዉ መፈናቀልና ስደት እየባሰበት ይሄዳል። ሰላም ካለ ዉድ አገራችን መላዉን ህዝባችንን የመቀለብ እግዚአብሔር የሰጣት በቂ የተፈጥሮ ኃብት አላት። እነርሱን እየተንከባከብን በሰላም ብንኖር ይሻለናል።

በስብዕና፤ በፈሪሃ እግዚአብሔርና ባለንበት የ21ኛዉ ክፍለ ዘመን ሥልጣኔ ብንገዛ መልካም ነዉ።

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *